የመጀመሪያው የኔፊ መጽሐፍ
ንግስ እና አገልግሎቱ
የሌሂና የሚስቱ የሳርያ፣ እንዲሁም የእርሱ አራት ልጆች (ከበኩር ጀምሮ) ላማን፣ ልሙኤል፣ ሳምና፣ ኔፊ ተብለው የሚጠሩት መዝገብ። ጌታ ሌሂን ከኢየሩሳሌም ምድር እንዲወጣ አስጠነቀቀው፣ ምክንያቱም እርሱ የህዝቡን ክፋት በተመለከተ ስለተነበየ እነርሱ ህይወቱን ሊያጠፉ ፈለጉ። ከቤተሰቡም ጋር የሶስት ቀን ጉዞ ወደ ምድረበዳ አደረገ። ኔፊ የአይሁዶችን መዝገብ ለመውሰድ ወንድሞቹን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ምድር ተመለሰ። ስለስቃያቸው ታሪክ። እነርሱም የእስማኤልን ሴት ልጆች አገቡ። ቤተሰቦቻቸውንም ይዘው ወደ ምድረበዳ ሄዱ። በምድረበዳ ውስጥ የነበራቸው ስቃያቸውና መከራቸው። የጉዞአቸውም አቅጣጫ። ወደ ትልቁ ውሃ መጡ። የኔፊ ወንድሞች በእርሱ ላይ አመፁ። እርሱም እነርሱን ዝም አሰኛቸው፣ እና መርከብን ሰራ። የቦታውንም ስም ለጋስ ብለው ጠሩት። ታላቁን ውሃ ተሻግረው ወደ ቃል ኪዳን ምድር ቀጠሉ። ይህ በኔፊ አመዘጋገብ መሰረት ነው፣ ወይም በሌላ አነጋገር እኔ፣ ኔፊ፣ ይህን ታሪክ ፃፍኩ።
ምዕራፍ ፩
ኔፊ የእርሱን ሕዝብ የሕይወት ታሪክ መመዝገብ ጀመረ—ሌሂ የእሳት አምድ በራዕይ አየ እናም ከትንቢት መጽሐፍም አነበበ—እግዚአብሔርንም አወደሰ፣ የመሲህን መምጣት አስቀድሞ ተናገረ፣ እንዲሁም የኢየሩሳሌምን ጥፋት ተነበየ፣ በአይሁዶች ስደት ደረሰበት። ፮፻ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እኔ ኔፊ፣ ከመልካም ወላጆች የተወለድኩ በመሆኔ አባቴ ከሚያውቃቸው በመጠኑ ተማርኩ፤ እናም በዘመኔም ብዙ መከራን ብመለከትም፣ በጊዜዬ ሁሉ ከጌታ ድጋፍን በማግኘቴ፣ አዎን የእግዚአብሔርን ቸርነትና ሚስጥሮች ታላቅ ዕውቀት በማግኘቴ፣ በጊዜዬ የተፈፀሙ ድርጊቶቼን እመዘግባለሁ።
፪ አዎን፣ የአይሁዶችን ትምህርት እና የግብፃውያንን ቋንቋ በያዘው በአባቴ ቋንቋ እጽፋለሁ።
፫ የምፅፈው ታሪክ እውነት እንደሆነ አውቃለሁ፣ በገዛ እጄም እፅፈዋለሁ፣ እናም እንደዕውቀቴም እፅፈዋለሁ።
፬ እናም እንዲህ ሆነ በይሁዳ ንጉስ ሴዴቅያስ በአንደኛ የንግስ ዓመት መጀመሪያ (አባቴ ሌሂ በህይወቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ውስጥ ኖሯል)፤ እና በዚያም አመት ህዝቡ ንስሀ መግባት እንዳለባቸው አለበለዚያ ታላቋ ከተማ ኢየሩሳሌም መጥፋት እንዳለባት የሚተነብዩ ብዙ ነቢያት ተነሱ።
፭ ስለዚህ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ሌሂ በወጣ ጊዜ፣ አዎን በሙሉ ልቡ በእርግጥ ስለህዝቡ ወደጌታ ይፀልይ ነበር።
፮ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ጌታ ሲፀልይ የእሳት አምድ ወረደና በፊቱ በአለት ላይ አረፈ፣ ብዙ አየ፣ ሰማም፤ እናም ባያቸውና በሰማቸው ነገሮች ምክንያት እጅግ ፈራና ተንቀጠቀጠ።
፯ እናም እንዲህ ሆነ በኢየሩሳሌም ወደ ሚገኘው ቤቱ ተመለሰ፤ እናም በመንፈስና ባያቸው ነገሮች ተዳክሞ እራሱን በአልጋው ላይ ወረወረ።
፰ እና በመንፈስ እንዲህ ተዳክሞ፣ በራዕይ ተወሰደ፣ እንዲሁም ሰማያት ተከፍተው አየ፤ እግዚአብሔርንም በዙፋኑ ተቀምጦ አምላካቸውን ሲያሞግሱና ሲዘምሩ በሚታዩት ስፍር ቁጥር በሌላቸው መላእክት ተከብቦ ማየቱን ተገነዘበ።
፱ እናም እንዲህ ሆነ እርሱ ከሰማይ መካከል አንድ ሰው ሲወርድ አየ፣ ድምቀቱም ከቀትር ፀሐይ ይበልጥ እንደነበር ተመለከተ።
፲ እናም ሌሎች አስራ ሁለት እሱን ሲከተሉት አየ፣ ብርሃናቸውም ከጠፈር ውስጥ ከዋክብት የሚልቅ ነበር።
፲፩ እነርሱም ወረዱና ወደ ምድር ገፅ መጡ፤ አንደኛውም መጣና በአባቴ ፊት ቆሞ፣ መፅሐፍ ሰጠውና ማንበብ እንዳለበት ነገረው።
፲፪ እንዲህ ሆነ እያነበበ ሳለ በጌታ መንፈስ ተሞልቶ ነበር።
፲፫ እናም እርሱ እንዲህ ብሎ አነበበ፥ ወዮ፣ ወዮ፣ ለኢየሩሳሌም፣ ያንቺን ርኩሰት አይቻለሁና፣ አዎን እናም አባቴም ኢየሩሳሌም መጥፋት እንዳለባት ብዙ ነገሮችን አንብቧል—ነዋሪዎችዋ ብዙዎቹ በሰይፍ ይጠፋሉ እንዲሁም አብዛኞቹ ወደ ባቢሎን በምርኮ ይወሰዳሉ።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ብዙ ታላቅና አስደናቂ ነገሮችን ባነበበና ባየ ጊዜ ለጌታ ብዙ ነገሮችን በመገረም ተናገረ፣ እነኚህም አቤቱ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ስራዎችህ ታላቅና አስደናቂ ናቸው! ዙፋንህ ከፍ ብሎ በሰማይ ነው። እንዲሁም ኃይልህ፣ ቸርነትህና ምህረትህ በምድር ባሉ ፍጡራን ሁሉ ላይ ነው፤ ምክንያቱም አንተ መሀሪ በመሆንህ ወደ አንተ የሚመጡት እንዲጠፉ አትፈቅድምና! የመሳሰሉትን ነበር።
፲፭ እናም አምላኩን ያመሰግን የነበረበት የአባቴ አነጋገር እንዲህም ነበር፤ ባያቸው ነገሮች፣ አዎን፣ ጌታ ለእርሱ ባሳየውም፣ ነፍሱ ተደስታለች፣ ልቡም በሙሉ በመንፈስ ተሞልታለች።
፲፮ እናም አሁን እኔ ኔፊ አባቴ የፃፋቸውን ነገሮች በሙሉ አልመዘግብም፣ በራዕይና በህልም ያያቸውን ብዙ ነገሮች ፅፏልና፤ እና ይኸውም እኔ አጠቃልዬ የማልመዘግባቸውን የተነበያቸውንና ለልጆቹ የተናገራቸውን ብዙ ነገሮች ደግሞ ፅፏል።
፲፯ ነገር ግን እኔ በዘመኔ የፈፀምኳቸውን እመዘግባለሁ። እነሆም የአባቴን ታሪክ በእጄ በሰራኋቸው ሰሌዳዎች ላይ አሳጥሬ ፅፌአለሁ፤ ስለዚህ የአባቴን ታሪክ ካሳጠርኩ በኋላ የራሴን የሕይወት ታሪክ እፅፋለሁ።
፲፰ ስለዚህ ጌታ ብዙ ድንቅ ነገሮችን፣ አዎን፣ ስለኢየሩሳሌም መጥፋትን ስለሚመለከት፣ ለአባቴ ሌሂ ካሳየው በኋላ፣ እነሆ በህዝቡ መካከል ሄደ እናም ስላየውና ስለሰማቸው ነገሮች ለእነርሱ መተንበይና ማወጅ እንደጀመረ እናንተ እንድታውቁት እፈልጋለሁ።
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ በእነርሱ ላይ በመሰከራቸው ነገሮች ምክንያት አይሁዶች ተሳለቁበት፣ ምክንያቱም እርሱ በእውነት ስለክፋታቸውና ስለእርኩሰታቸው መስክሯል፤ እንዲሁም ያያቸውና የሰማቸው ነገሮች፣ ደግሞም በመፅሐፉ ውስጥ ያነበባቸው ነገሮች በግልጽ ስለመሲሕ መምጣትና ደግሞም ስለአለም ቤዛነት እንደሚገልጹ መሰከረ።
፳ እና አይሁዶች ይህንን በሰሙ ጊዜ በእርሱ ተቆጡ፤ አዎን እንዲሁም ልክ እንዳሳደዱአቸውና እንደወገሩአቸው፣ እንደገደሉዋቸውም የጥንት ጊዜ ነቢያት፤ ይገድሉትም ዘንድ የእርሱንም ሕይወት ደግሞ ሊወስዱ ፈለጉ። ነገር ግን እነሆ፣ እኔ ኔፊ የጌታ ምህረቶች ርህራሄ በእምነታቸው ምክንያት ለመዳን ሀይል እስኪኖራቸው ድረስ ሀያል እንዲሆኑ በመረጣቸው ላይ ሁሉ እንደሆነ አሳያችኋለሁ።