ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፳፪


ምዕራፍ ፳፪

በመጨረሻው ቀን ፅዮንና ካስሚያዎችዋ ይቋቋማሉ፣ እናም እስራኤል በምህረትና በደግነት ይሰበሰባሉ—እነርሱም አሸናፊ ይሆናሉ—ኢሳይያስ ፶፬ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም የተፃፈውም እንዲህ ይፈፀማል፥ አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ እልል በይ፤ እናም በዝማሬ ጩኺ፣ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነችው ልጆች በዝተዋልና ይላል ጌታ።

የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፤ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቆጥቢ፣ ገመድሽን አስረዝሚና ካስሞችሽንም አፅኚ፤

በቀኝና በግራም ትስፋፊያለሽ፣ እናም ዘሮችሽም አህዛብን ይወርሳሉና የፈረሱትን ከተሞች መኖሪያ ያደርጋሉ።

አታፍሪምና አትፍሪ፤ እንድታፍሪ ስለማይደረግ ዝም አትበይ፤ የልጅነትሽን እፍረት ትረሺዋለሽ፣ የልጅነትሽን ብሉሽነትሽን ውቅት ከእንግዲህ አታስታውሺም፣ የመበለትነትሽንም ወቅት ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢውም።

ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፤ ስሙም የሰራዊት ጌታ ነው፤ እናም የእስራኤል ቅዱስ የሆነውም አዳኝሽ ነው—የምድር ሁሉ አምላክ ተብሎም ይጠራል።

ጌታ እንደተተወችና እንደተበሳጨች መንፈስ፣ እናም በልጅነት እንደጣሉአት ሚስት ጠርቶሻል ይላል አምላክሽ።

ለጥቂት ጊዜ ጣልኩሽ፣ ነገር ግን በታላቅ ምህረት እሰበስብሻለሁ።

በጥቂት ቁጣ ለቅፅበት ፊቴን ከአንቺ ሰወርኩ፣ ነገር ግን በዘለዓለም ቸርነት እምርሻለሁ ይላል ጌታ አዳኝሽ።

ይህ ለእኔ እንደ ኖህ ውኃ ነው፤ የኖህ ውሃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደማልሁ እንዲሁ አንቺን እንዳልቆጣ እንዳልዘልፍሽም ምያለሁ።

ተራሮች ይፈርሳሉ፤ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፣ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አያልፍም፣ የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም ይላል መሃሪሽ የሆነ ጌታ።

፲፩ አንቺ የተቸገርሽ ሆይ፣ በአውሎ ነፋስም የተናወጥሽ፣ ያልተፅናናሽም! እነሆ፣ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፤ በሰንፔርም ጌጥ እመሰርትሻለሁ።

፲፪ የግንብሽንም ጉልላት በቀይ ዕንቁ፤ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሰራለሁ።

፲፫ እናም ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ እናም የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል።

፲፬ በፅድቅ ትታነፂያለሽ፤ ከግፍ አድራጊ አትፈሪምና ድንጋጤም ወደ አንቺ አይቀርብም።

፲፭ እነሆ፣ በእርግጥም ባንቺ ላይ ይሰበሰባሉ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሳ ይወድቃሉ።

፲፮ እነሆ፣ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለስራውም መሳሪያ የሚያወጣ ብር ሰሪን እኔ ፈጥሬአለሁ።

፲፯ በአንቺ ላይ የተሰራ መሳሪያ ሁሉ አይከናወንም፣ በፍርድም በሚነሳብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የጌታ ባሪያዎች ቅርስ ይህ ነው፤ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው ይላል ጌታ።