ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፱


ምዕራፍ ፱

በጭለማው ውስጥ፣ የክርስቶስ ድምጽ በክፋታቸው የተነሳ የብዙ ሰዎችን እንዲሁም የከተሞቹን ጥፋት አወጀ—መለኮታዊነቱንም ደግሞ አወጀ፣ የሙሴ ህግም እንደተሟላም አስታወቀ፣ እናም ሰዎችም ወደ እርሱ እንዲመጡ፣ እናም እንዲድኑ ጋበዛቸው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ገጽ ሁሉ ላይ ባሉ ነዋሪዎቹ መካከል አንድ ድምፅ መጥቶ እንዲህ ሲል መጮኹ ተሰማ፥

ለዚህ ህዝብ ወዮ፣ ወዮ ወዮለት፣ ንሰሃ ካልገቡ በስተቀርም ለምድር ነዋሪዎች በሙሉ ወዮላቸው፤ መልካም የሆኑት የህዝቦቼ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በመገደላቸው ዲያብሎስ ይስቃል፣ እናም መላዕክቶቹም ይደሰታሉና፤ እናም በክፋታቸውና በእርኩሰታቸው የተነሳ ነው የወደቁት!

እነሆ፣ ታላቋን የዛራሄምላን ከተማ እናም ነዋሪዎችዋን በእሳት አቃጥያቸዋለሁ።

እናም እነሆ፣ ታላቋን የሞሮኒን ከተማና በዚያም የሚገኙትን ነዋሪዎች በባህሩ ጥልቅ እንዲሰጥሙም አድርጌአለሁ።

እናም እነሆ፣ ክፋታቸውንና ርኩሰታቸውን ከፊቴ ለመሸሸግ፣ የነቢያቱ እናም የቅዱሳን ደም ከእንግዲህ በኔ ላይ እንዳይመጣ ታላቋን የሞሮኒሀን ከተማና ነዋሪዎችዋን በመሬት ውስጥ ሸፍኜአቸዋለሁ።

እናም እነሆ፣ የጌልገላ ከተማ እንድትሰጥም እናም በዚያን ስፍራ የሚገኙት ነዋሪዎችም በምድሪቱ ውስጥ እንዲቀበሩ አድርጌአለሁ፤

አዎን፤ እናም የኦኒሀ ከተማና ነዋሪዎችዋ፤ እናም የሞኩም ከተማና ነዋሪዎችዋ፤ እናም የኢየሩሳሌም ከተማና ነዋሪዎችዋ፤ ከእንግዲህ ወዲያ የነቢያቱና የቅዱሳን ደም በእነርሱ ላይ ወደ እኔ እንዳይመጣ ክፋታቸውን እናም ርኩሰታቸውን ከፊቴ ለመሸሸግ በስፍራቸው ውሃ እንዲመጣባቸው አደረግሁ።

እናም እነሆ፣ የጋድያንዲን ከተማና፣ የጋድዮምናን ከተማ፣ እናም የያዕቆብን ከተማና፣ የጊምጊምኖን ከተማ፣ በሙሉ እንዲሰምጡ አደረኳቸው፣ እናም በስፍራው ኮረብታዎችንና ሸለቆዎችን ሰራሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የነቢያቱና፣ የቅዱሳን ደም በእነርሱም ላይ ወደ እኔ እንዳይመጣ ክፋታቸውን፣ እናም ርኩሰታቸውን ከፊቴ ለመሸሸግ በስፍራው የነበሩትን ነዋሪዎች በመሬት ውስጥ ቀበርኳቸው።

እናም እነሆ፣ ከምድር ኃጢአቶች ሁሉ በላይ በነበረው ኃጢአቶቻቸውና ክፋቶች፤ በሚስጥራዊው ግድያቸው፣ እንዲሁም በህብረታቸው የተነሳ ታላቋ ከተማ የንጉስ ያዕቆብ ህዝብ የሰፈረባት ያዕቆቡጋትን በእሳት እንድትቃጠል አደረግሁ፤ ምክንያቱም እነርሱ ነበሩ የህዝቤን ሠላም እናም የምድሪቱን አገዛዝ ያጠፉት፤ ስለዚህ ከእንግዲህም ወዲያ የነቢያቱምና የቅዱሳን ደም በእነርሱም ላይ ወደ እኔ እንዳይመጣ ከፊቴም ለማጥፋት እንዲቃጠሉ አደረግሁ።

እናም እነሆ፣ ስለ ኃጢአታቸውና ርኩሰታቸው እንዲናገሩ የላኳቸውን ነቢያት በማስወጣት በሰሩት ክፋትና፣ በድንጋይ ስለወገሩአቸው፣ የላማን ከተማና፣ የኢዮሽ ከተማ፣ እናም የጋድ ከተማና፣ የቂሽቁመንን ከተማ፣ እንዲሁም ነዋሪዎቻቸው በእሳት እንዲቃጠሉ አደረግሁ፤

፲፩ እናም ሁሉንም አስወጥተው ስለወረወሩአቸው፣ በመካከላቸውም ምንም ፃድቅ የሆነ ባለመኖሩ በመካከላቸውም የላኳቸው ነቢያትና፣ ፃድቃኖች ደም ከመሬት ወደ እኔ እንዳይጮህ ክፋቶቻቸው፣ እናም ርኩሰታቸው ከፊቴም ይደበቁ ዘንድ እሳት ላኩባቸውና፣ አጠፋቸው።

፲፪ እናም በክፋቶቻቸውና በርኩሰታቸው የተነሳም በዚህች ምድር፣ እናም በዚህ ህዝብ ላይ ብዙ ታላቅ ጥፋቶች እንዲሆኑ አደረግሁ።

፲፫ አቤቱ ከእነርሱ የበለጠ ፃድቅ በመሆናችሁ እናንተ የተረፋችሁትን ሁሉ እፈውሳችሁ ዘንድ ለኃጥያታችሁ ንስሃ ገብታችሁ እናም ተለውጣችሁ አሁን ወደ እኔ አትመለሱምን?

፲፬ አዎን በእውነት እላችኋለሁ፣ ወደ እኔ ከመጣችሁ ዘለዓለማዊ ህይወትን ታገኛላችሁ። እነሆ የምህረት ክንዴ ወደ እናንተ ተዘርግታለች፣ እናም ማንም ቢመጣ እቀበለዋለሁ፣ እናም ወደ እኔ የሚመጡ የተባረኩ ናቸው።

፲፭ እነሆ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ የሆንኩኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ። ሰማያትንና ምድርን፣ እናም በውስጧ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ፈጥሬአለሁ። ከመጀመሪያው ጀምሮ ከአብ ጋር ነበርኩኝ። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ አለ፤ በእኔም የአብ ስሙን አስከብሯል።

፲፮ የእኔ ወደሆኑት መጣሁና፣ የራሴ የሆኑትም አልተቀበሉኝም። እናም የእኔን መምጣት በተመለከተ ቅዱሳን መጻሕፍት ተፈጽመዋል።

፲፯ እናም ለተቀበሉኝ ሁሉ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠኋቸው፣ እናም በስሜ ለሚያምኑትም ሁሉ እንዲህም አደርጋለሁ፣ እነሆም በእኔም ቤዛነት ይመጣልና በእኔም የሙሴ ህግ ተፈፀሟል።

፲፰ እኔ የአለም ብርሃንና ህይወት ነኝ። አልፋና ኦሜጋ፤ የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ነኝ።

፲፱ እናም ከእንግዲህ ደምን በማፍሰስ አታበረክቱልኝም፤ አዎን፣ መስዋእቶቻችሁና የሚቃጠሉት መስዋእቶች ማንኛውንም ስለማልቀበል መስዋእቶቻችሁ እናም የሚቃጠሉት መስዋእቶቻችሁ ይቆማሉ።

እናም ለእኔም መስዋእት የተሰበረ ልብና የተዋረደ መንፈስ ታቀርባላችሁ። እናም ወደ እኔም በተሰበረ ልብና በተዋረደ መንፈስ የሚመጣ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ አጠምቀዋለሁ፤ ላማናውያንን እንኳን ቢሆን በመለወጣቸው ወቅት በእኔ በነበራቸው እምነት የተነሳ በእሳት እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠመቁት፣ እናም ይህንንም አያውቁም ነበር።

፳፩ እነሆ ዓለምን ከኃጢያት ለማዳን ለዓለም ቤዛነትን ለማምጣት ወደ ዓለም መጥቻለሁ።

፳፪ ስለዚህ ንሰሃ የሚገባን እናም እንደህፃን ልጅ ወደ እኔ የሚመጣንም እቀበለዋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግስትም እንደነዚህ ላሉት ናትና። እነሆ፣ እንደነዚህ ላሉትም ህይወቴን ሰጥቻለሁና፣ እናም በድጋሚም አንስቼዋለሁ፤ ስለዚህ የምድር ዳርቻ ሁሉ ንሰሃ ግቡ፣ ወደ እኔም ኑና፣ ዳኑ።