ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፳፬


ምዕራፍ ፳፬

አሙሎን አልማንና ህዝቡን አሳደደ—የሚፀልዩ ከሆነ ይገደላሉ—ጌታ ሸክማቸውን ቀሊል እንዲመስል አደረገው—ከባርነት አዳናቸው፣ እናም ወደ ዛራሔምላ ተመለሱ። ከ፻፵፭–፻፳ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ አሙሎን በላማናውያን ንጉስ ፊት ሞገስን አገኘ፤ ስለዚህ፣ የላማናውያን ንጉስ ለእርሱና ለወንድሞቹ በህዝቡ ላይ፣ አዎን፣ በሻምሎን ምድርም ባሉት ህዝቦች ላይ ጭምር፣ እናም እንዲሁም በሼምሎን ምድርና በአሙሎን ምድር ላይ መምህር ሆነው እንዲሾሙ አደረጋቸው።

ላማናውያን እነዚህን ምድር ሁሉ ወስደዋልና፤ ስለዚህ፣ የላማናውያን ንጉስ በእነዚህ ምድር ላይ ሁሉ ነገሥታትን ሾሟል።

እናም አሁን የላማናውያን ንጉስ ስሙ ላማን ይባል ነበር፣ እርሱም በአባቱ ስም ይጠራ ነበር፤ ስለዚህ ንጉስ ላማን ተብሎ ይጠራም ነበር። እናም በብዙ ህዝብ ላይ ንጉስ ነበር።

እናም በህዝቡ በተያዘው ምድር ላይ ሁሉ የአሙሎንን ወንድሞች መምህር አድርጎ ሾማቸው፤ እናም የኔፊን ቋንቋ በላማናውያን ሁሉ መካከል ማስተማር ጀመሩ።

እናም አንዱ ከሌለኛው ወዳጅ የሆኑ ህዝቦች ነበሩ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን አያውቁትም ነበር፤ የአሙሎንም ወንድሞች ጌታ አምላካቸውንም ሆነ የሙሴን ህግ በተመለከተ ምንም አላስተማሩአቸውም ነበር፤ የአቢናዲንም ቃላት አላስተማሩአቸውም ነበር፤

ነገር ግን ታሪካቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውና እርስ በርስ እንዲፅፉ አስተማሩአቸው።

እናም ላማናውያን ሀብታም መሆን ጀመሩ፣ እናም እርስ በርስ የንግድ ልውውጥ በማድረግ በጣም አደጉ፣ እንዲሁም የዓለምን ጥበብ በተመለከተ ብልጥና ብልህ ህዝብ መሆን ጀመሩ፤ አዎን፣ እጅግ ብልጥ የሆኑት ሠዎች ከራሳቸው ወንድሞች በስተቀር ሁሉንም አይነት ኃጢያትና ዝርፊያ በማድረግ ይደስቱ ነበር።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ አሙሎን በአልማና በወንድሞቹ ላይ ስልጣኑን ማሳየት ጀመረ፤ እናም እርሱን ማሳደድና፣ ልጆቹ ልጆቻቸውን እንዲያሳድዱ አደረገ።

አልማ ከንጉሱ ካህን አንዱ መሆኑን፣ እናም የአቢናዲን ቃል ያመነውና፣ ከንጉሱም ፊት እንዲወጣ የተደረገው እርሱ እንደነበር አሙሎን ያውቅ ነበር፤ እናም ስለዚህ በእርሱ ተቆጥቶ ነበር፤ እርሱ በንጉስ ላማን አገዛዝ ስር ነበር፣ ቢሆንም በእነርሱ ላይ ስልጣኑን ተጠቅሞ ነበር፣ እናም ኃላፊነቱን በእነርሱ ላይ አደረገ፣ አስገባሪዎችንም በእነርሱ ላይ አደረገ።

እናም እንዲህ ሆነ ስቃያቸው ታላቅ ስለነበር ወደ እግዚአብሔርም በኃይል መጮህ ጀመሩ።

፲፩ እናም አሙሎን ጩኸታቸውን ማቆም እንዳለባቸው አዘዘ፣ እናም እንዲጠብቁአቸው ጠባቂዎችን በእነርሱ ላይ አደረገ፣ ይኸውም እግዚአብሔርን የሚጠራ ማንም ሰው እንዲገደል ነበር።

፲፪ እናም አልማና ህዝቡ ወደ ጌታ አምላካቸው ድምፃቸውን ከፍ አላደረጉም፣ ነገር ግን ልባቸውን ወደ እርሱ አፈሰሱ፤ እናም እርሱ የልባቸውን ሐሳብ ያውቅ ነበር።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ የጌታ ድምፅ በስቃያቸው እንዲህ በማለት መጣ፥ ራሳችሁን አቅኑም መልካም መፅናኛ ይኑራችሁም፤ ከእኔ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን አውቀዋለሁና፤ ከህዝቤም ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ እናም ከባርነት አስለቅቃቸዋለሁ።

፲፬ እናም ደግሞ በባርነት በነበራችሁ ጊዜም ቢሆን፣ በጀርባችሁም እንኳን ሊሰማችሁ እንዳይቻላችሁ፣ በትከሻችሁ ላይ ያለውን ሸክም አቃልልላችኋለሁ፤ እናም ይህንን የማደርገው ከዚህ በኋላ ለእኔ በምስክርነት እንድትቆሙ ነው፤ እናም እኔ ጌታ እግዚአብሔር በእውነት በመከራቸው ጊዜ ህዝቤን እንደምጎበኝ ታውቁ ዘንድ ነው።

፲፭ እናም አሁን እንዲህ ሆነ በአልማና በወንድሞቹ ላይ የሆነው ሸክም ቀለለላቸው፣ አዎን፣ ሸክማቸውን ማቅለል እንዲችሉ እናም በደስታና በትዕግስት ለጌታ ፈቃድ ተቀባይ እንዲሆኑ ጌታ ብርታትን ሰጥቷቸዋል።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ እምነታቸውና ትዕግስታቸው ታላቅ በመሆኑ፣ የጌታ ድምፅ በድጋሚ እንዲህ በማለት ወደ እነርሱ መጣ፥ መፅናናትም ይብዛላችሁ፣ ነገ ከባርነት አስለቅቃችኋለሁና።

፲፯ እናም ለአልማ እንዲህ አለው፥ ከዚህ ህዝብ ፊት ትሄዳለህ፣ እናም እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፣ ይህንንም ህዝብ ከባርነት አስለቅቃለሁ።

፲፰ አሁን እንዲህ ሆነ አልማና ህዝቡ መንጋዎቻቸውን እናም ደግሞ እህላቸውን በአንድነት በምሽት ሰበሰቡ፤ አዎን፣ እንዲያውም ምሽቱን ሁሉ መንጋዎቻቸውን በአንድነት ይሰበስቡ ነበር።

፲፱ እናም ጠዋት ጌታ በላማናውያን ላይ ከባድ እንቅልፍን ጣለባቸው፤ አዎን፣ እናም አስገባሪዎቻቸው ሁሉ በከባድ እንቅልፍ ላይ ነበሩ።

እናም አልማና ህዝቡ ወደ ምድረበዳው ተጓዙ፤ እናም ቀኑን በሙሉ ከተጓዙ በኋላ ድንኳናቸውን በሸለቆ ተከሉ፣ እናም በምድረበዳው ውስጥም መንገዱን አልማ ስለመራቸው ሸለቆውን አልማ ብለው ጠሩት።

፳፩ አዎን፣ እናም በአልማ ሸለቆ ምስጋናቸውን ለእግዚአብሔር አበረከቱ፣ ምክንያቱም ለእነርሱ መሀሪ ነበርና፣ እናም ሸክማቸውን አቅልሎላቸዋልና ከባርነትም አስለቅቆአቸዋልና፤ በባርነት ስር ነበሩ እናም ጌታ አምላካቸው ካልሆነ በቀር ማንም ሊያስለቅቃቸው አይቻለውምና።

፳፪ እናም ለእግዚአብሔር ምስጋናን አቀረቡ፣ አዎን፣ ወንዶቻቸውና፣ ሴቶቻቸው ሁሉ፣ እናም መናገር የሚችሉት ልጆቻቸው ሁሉ እግዚአብሔርን በማወደስ ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ።

፳፫ እናም አሁን ጌታ ለአልማ እንዲህ አለው፥ ላማናውያን ነቅተዋል እናም ያሳድዷቸዋልና ፍጠን፣ አንተንና ይህንን ህዝብ ከዚህ ምድር አውጣ፤ ስለዚህ ከዚህ ምድር ውጡ፣ እናም ላማናውያኖች ይህንን ህዝብ ለማሳደድ ከዚህ አልፈው እንዳይመጡ በዚህ ሸለቆ ውስጥ አቆማቸዋለሁ።

፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ከሸለቆው ወጥተው ሄዱና፣ ጉዞአቸውን ወደ ምድረበዳው አደረጉ።

፳፭ እናም ለአስራ ሁለት ቀናት በምድረበዳው ከቆዩ በኋላ በዛራሔምላ ምድር ደረሱ፤ እናም ንጉስ ሞዛያ ደግሞ በደስታ ተቀበላቸው።