ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፳፭


ምዕራፍ ፳፭

በዛራሔምላ የሙሌቅ ወገኖች ኔፋውያን ሆኑ—ስለአልማና ስለዜኒፍ ህዝብ ተማሩ—አልማ ሊምሂንና ህዝቡን ሁሉ አጠመቀ—ሞዛያ አልማ የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን እንዲያቋቁም ስልጣን ሰጠው። በ፻፳ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን ንጉስ ሞዛያ ህዝቡ ሁሉ በአንድነት እንዲሰበሰብ አደረገ።

እንግዲህ የሙሌቅ ትውልድ እንደነበረው ዛራሔምላ እናም ከእነርሱ ጋር ወደ ምድረበዳው እንደመጡት ህዝብ ብዛት፣ የኔፊ ልጆች የነበሩ፣ ወይንም የኔፊ ወገን የሆኑት ብዙ አልነበሩም።

እናም የኔፊም ሆኑ የዛራሔምላ ህዝብ ብዛት እንደላማናውያን አልነበረም፤ አዎን፣ ብዛታቸው እንደእነርሱ ግማሹ እንኳን አልነበረም።

እናም አሁን የኔፊ ህዝብ በሙሉ፣ ደግሞም የዛራሔምላም ህዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፣ እናም በሁለት ወገን ሆነው በአንድነት ተሰበሰቡ።

እናም እንዲህ ሆነ ሞዛያ የዜኒፍን ታሪክ ለህዝቡ አነበበ፤ እንዲነበብም አደረገ፤ አዎን፤ የዛራሔምላን ምድር ለቀው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በድጋሚ እስከተመለሱበት ድረስ የዜኒፍን ህዝብ ታሪክ አነበበ።

እናም ደግሞ የአልማንና ወንድሞቹን ታሪክ፣ የዛራሔምላን ምድር ለቀው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ፣ እንደገናም እስከተመለሱበት ድረስ ያለውን ስቃያቸውን ሁሉ አነበበ።

እናም አሁን፣ ሞዛያ ታሪኩን አንብቦ እንደጨረሰ፣ በምድሪቱ የቀሩት ህዝቦቹ በመገረምና በአድናቆት ተሞሉ።

ምን ማሰብ እንዳለባቸው አላወቁም ነበርና፤ ከባርነት የተለቀቁትን በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ታላቅ በሆነ ደስታ ተሞልተው ነበርና።

እናም በድጋሚ፣ በላማናውያን የተገደሉትን ወንድሞቻቸውን ባሰቡ ጊዜ በሃዘን ተሞሉ እናም ብዙ የሐዘን እንባም አፈሰሱ።

እናም እንደገና፣ ፈጣን የእግዚአብሔርን ቸርነት እናም አልማንና ወንድሞቹን ከላማናውያን እጅና ከባርነት ማውጣቱን ባሰቡ ጊዜ፣ ድምፃቸውን ከፍ አደረጉና ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ።

፲፩ እናም በድጋሚ፣ ወንድሞቻቸው ስለሆኑት ስለላማናውያን ኃጢያትና ስለመበከላቸው ባሰቡ ጊዜ ስለነፍሳቸው ደህንነት በህመምና በጭንቀት ተሞልተው ነበር።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያንን ሴቶች ለሚስትነት የወሰዱት የአሙሎንና የወንድሞቹ ልጆች፣ በአባቶቻቸው ባህርይ ተከፉ፣ እናም ከእንግዲህ በአባቶቻቸው ስም መጠራት አልፈለጉም፣ ስለዚህ የኔፋውያን ልጆች ተብለው ይጠሩ ዘንድና ኔፋውያን ተብለው ከሚጠሩት ጋር ይቆጠሩ ዘንድ የኔፊን ስም በራሳቸው ላይ ወሰዱ።

፲፫ እናም እንግዲህ የዛራሔምላ ህዝብ ሁሉ ከኔፋውያን ጋር ተቆጠሩ፣ እናም ይህ የሆነበት ምክንያት የኔፊ ዘር ከሆኑት በስተቀር መንግስቱ ለሌላ ባለመሰጠቱ ነበር።

፲፬ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ሞዛያ ለህዝቡ ንግግሩንና ንባቡን እንደጨረሰ አልማም ደግሞ ለህዝቡ እንዲናገር ፈለገ።

፲፭ እናም አልማ ተናገራቸው፣ በብዛትም በአንድ ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ፣ እናም ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌለኛው በጌታ ንስሃና እምነትን እየሰበከላቸው ሔደ።

፲፮ እናም የሊምሂን ህዝብና ወንድሞቹን ከባርነት የተለቀቁትን ሁሉንም ጌታ ከባርነት እንዳስለቀቃቸው እንዲያስታውሱ በጥብቅ መከራቸው።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ አልማ ህዝቡን ብዙ ነገሮችን ካስተማረና ንግግሩንም ከጨረሰ በኋላ፣ ንጉስ ሊምሂ መጠመቅን ፈለገ፤ እናም ህዝቡም በሙሉ ደግሞ ይጠመቁ ዘንድ ፈለጉ።

፲፰ ስለዚህ፣ አልማ ወደ ውኃው ገባ፣ እናም አጠመቃቸው፤ አዎን፣ ወንድሞቹን በሞርሞን ውሃ እንዳጠመቃቸው አይነት እነርሱንም አጠመቃቸው፤ አዎን፣ ያጠመቃቸው በሙሉ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባላት ሆኑ፤ እናም ይህ የሆነው በአልማ ቃል በማመናቸው የተነሳ ነው።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ሞዛያ በዛራሔምላ ምድር ላይ ሁሉ ቤተክርስቲያንን እንዲያቋቁም ለአልማ ፈቀደለት፣ እናም በሁሉም ቤተክርስቲያን ላይ ካህናትንና መምህራንን እንዲሾም ስልጣንን ሰጠው።

አሁን ይህ ሁሉ የተደረገበት ምክንያት ብዙውን ህዝብ በአንድ አስተማሪ ለመምራት ስለማይቻል፣ እነርሱም ሁሉ በአንድ ጉባኤ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ስለማይችሉ ነበር፤

፳፩ ስለዚህ ራሳቸውን ቤተክርስቲያናት ተብለው በሚጠሩ በተለያዩ ክፍሎች ሰበሰቡ፤ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን የራሱ ካህናትና መምህራን አለው፣ እናም እያንዳንዱ ካህን ቃሉን ከአልማ አንደበት በተቀበለው መሠረት ይሰብክ ነበር።

፳፪ እናም ስለዚህ ብዙ ቤተክርስቲያኖች ቢኖሩም ሁሉም አንድ ቤተክርስቲያን ነበሩ፣ አዎን፣ ይኸውም የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን፤ ከንስሃና በእግዚአብሔር እምነት በቀር በሁሉም በቤተክርስቲያናት ምንም አይሰበክም ነበር።

፳፫ እናም አሁን በዛራሔምላ ምድር ሰባት ቤተክርስቲያናት ነበሩ። እናም እንዲህ ሆነ ማንኛውም የክርስቶስን ወይም የእግዚአብሔርን ስም በእራሱ ለመውሰድ የፈለገ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያናት አባል ይሆናል፤

፳፬ እናም እነርሱ የእግዚአብሔር ሰዎች ተብለው ተጠርተዋል። እናም ጌታ መንፈሱን በእነርሱ ላይ አፍስሷል፣ እነርሱም ተባርከዋል፣ በምድሪቱም ላይ በለፅገዋል።