ምዕራፍ ፲፮
ኃጢአተኞች እውነትን ለመቀበል አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል—የሌሂ ወንዶች ልጆች የእስማኤልን ሴቶች ልጆች አገቡ—ሊያሆናው በምድረበዳ ውስጥ መንገዳቸውን መራቸው—ከጌታ የመጡ መልዕክቶች በተለያዩ ጊዜዎች በሊያሆናው ላይ ይፃፉ ነበር—እስማኤል ሞተ፣ ቤተሰቦቹም በስቃዮች ምክንያት አጉረመረሙ። ከ፮፻–፭፻፺፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ፣ ወንድሞቼን ማነጋገር ከጨረስኩኝ በኋላ፣ እነሆ እነርሱ አንተ እኛ ልንጸናው ከምንችለው የበለጠ አስቸጋሪ ነገሮችን ነገርከን አሉኝ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ እውነትን በተመለከተ ለኃጢአተኞች የተናገርኳቸው ነገሮች አስቸጋሪ እንደሆኑ አውቃለሁ አልኩ፤ እናም ፃድቃን ከጥፋት ነፃ መሆናቸውን ተናገርኩ፣ በመጨረሻውም ቀን ከእግዚአብሔር ጋር ከፍ እንደሚደረጉም መሰከርኩ፤ ስለዚህ ጥፋተኞች እውነትን ከባድም አድርገው ይወስዱታል፣ ከመሀከላቸው ይለያቸዋልና።
፫ እናም ወንድሞቼ፣ አሁን እናንተ ፃድቃን እንዲሁም እውነትን ለማዳመጥ ፈቃደኞች ብትሆኑ ኖሮ፣ በእግዚአብሔርም ፊት በቅንነት ትራመዱ ዘንድ በጥብቅ ከተከተላችሁት፣ በእውነት ምክንያት አታጉረመርሙም፣ ከባድ ነገሮችን በእኛ ላይ ትናገራለህ አትሉም።
፬ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ ወንድሞቼ የጌታን ትዕዛዛት እንዲጠብቁ በሙሉ ትጋት አበረታታኋቸው።
፭ እናም እንዲህ ሆነ፤ እነርሱ በፅድቅ ጎዳና ይራመዱ ዘንድ ደስታና ታላቅ ተስፋ እስኪኖረኝ ድረስ በጌታ ፊት እራሳቸውን ዝቅ አደረጉ።
፮ አሁን እነዚህ ነገሮች ሁሉ የተባሉትና የተደረጉት አባቴ ልሙኤል ብሎ በጠራው ሸለቆ በድንኳን በነበረበት ጊዜ ነው።
፯ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ ከእስማኤል ሴቶች ልጆች አንዷን ለማግባት ወሰድኳት፤ እናም ደግሞ ወንድሞቼ የእስማኤልን ሴቶች ልጆች ለማግባት ወሰዱ፤ ደግሞም ዞራም የእስማኤልን ትልቋን ሴት ልጅ ለማግባት ወሰደ።
፰ አባቴም የተሰጡትን የጌታን ትዕዛዛት በሙሉ ፈፀመ። እናም ደግሞ እኔ፣ ኔፊ፣ በጌታ እጅግ ተባረክሁ።
፱ እናም እንዲህ ሆነ የጌታ ድምፅ አባቴን በምሽት ተናገረው፣ እናም በማግስቱ ወደ ምድረበዳው መጓዝ እንዳለበት አዘዘው።
፲ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ በጠዋት ተነሳ፣ እናም ወደ ድንኳኑ በር ሄደ፣ በመሬቱ ላይ በጥበብ የተሰራውን ክብ ኳስ በአድናቆት ተመለከተ፤ ይህም የተሰራው ከንፁህ ነሐስ ነበር። በኳሱም ላይ ሁለት እንዝርቶች ነበሩ፤ እናም አንደኛው በምድረበዳ ውስጥ መሄድ ያለብንን አቅጣጫ ይጠቁማል።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ምድረበዳ መሸከም የሚያስፈልገንና ማንኛውንም ነገሮች፣ እናም ጌታ የሰጠንን ቀሪ ቀለብ ሁሉ በአንድ ላይ ሰበሰብን፤ እንዲሁም ከሁሉም ዓይነት ዘሮች ወደ ምድረበዳው መሸከም የምንችለውን ወሰድን።
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ድንኳናችንን ይዘን የላማንን ወንዝ በማቋረጥ ወደ ምድረበዳው ሄድን።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ለአራት ቀን በስተደቡብ በደቡብ-ምስራቅ አቅጣጫ ተጓዝን፣ እናም እንደገና ድንኳናችንን ተከልን፤ ቦታውንም ሻዘር ብለን ጠራነው።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ለቤተሰቦቻችን ምግብ የዱር እንስሳቶችን ለማደን ቀስቶቻችንንና ደጋኖቻችንን ወስደን ወደ ምድረበዳ ተጓዝን፤ ለቤተሰቦቻችንም ምግብ ካደንን በኋላ በምድረበዳ ውስጥ በድጋሚ ወደቤተሰቦቻችን ሻዘር ወደሚባለው ቦታ ተመለስን። እናም በድጋሚ በምድረበዳ ውስጥ ያንኑ አቅጣጫ በመከተል በምድረበዳው ይበልጥ ለም በሆነው በቀይ ባህር ዳርቻ አጠገብ ተጓዝን።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ለብዙ ቀናት ለምግብ የዱር አውሬዎችን በቀስቶቻችንና፣ በደጋኖቻችንና፣ በድንጋይ እንዲሁም በወንጭፋችን በመግደል ተጓዝን።
፲፮ እናም የኳሱን አቅጣጫ ተከተልን፣ እርሱም በምድረበዳ ይበልጥ ለም ወደሆነው ስፍራዎች የሚመራን ነበር።
፲፯ እናም ለብዙ ቀናት ከተጓዝን በኋላ፣ እራሳችንን ለማሳረፍና ለቤተሰቦቻችንም ምግብ ማግኘት እንድንችል ለጊዜው ድንኳኖቻችንን ተከልን።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ ምግብ ለማደን ስሄድ፤ እነሆ፣ ከንፁህ ብረት የተሰራውን ደጋኔን ሰበርኩ፤ እናም ደጋኔን ከሰበርኩ በኋላ፣ ምግብ ስላላገኘን እነሆ ደጋኔን በመስበሬ ወንድሞቼ በእኔ ተናድደው ነበር።
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ፣ ያለምንም ምግብ ወደቤተሰቦቻችን ተመለስን፣ እናም በጉዞአቸው ምክንያት በጣም ደክሟቸው፣ በምግብ ፍላጎት ምክንያት የበለጠም ተሰቃዩ።
፳ እናም እንዲህ ሆነ፣ ላማንና ልሙኤል እንዲሁም የእስማኤል ወንዶች ልጆች በምድረበዳ ውስጥ በስቃያቸውና በመከራቸው ምክንያት እጅግ ማጉረምረም ጀመሩ፤ እናም ደግሞ አባቴ በጌታ አምላኩ ላይ ማጉረምረም ጀመረ፤ አዎን ሁሉም እጅግ አዝነው ነበር፤ በጌታም ላይ እንኳን አጉረምርመው ነበር።
፳፩ አሁን እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ፣ ቀስቴን በማጣቴ ከወንድሞቼ ጋር ተሰቃየሁ፣ እናም ቀስታዎቻቸውም መለጠጥ ባለመቻላቸው እጅግ አስቸጋሪ፣ አዎን ምግብ ማግኘት እስከማይቻለን ድረስም ሆነ።
፳፪ እናም እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ፣ እነርሱ በጌታ አምላካቸው ላይ በማጉረምረም እንኳን ልባቸውን እንደገና በማጠጠራቸው ምክንያት፣ ወንድሞቼን ብዙ ተናገርኳቸው።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ፣ ከእንጨት ቀስት እናም ቀጥ ካለ ዱላ ደጋንን ሰራሁ፣ ስለዚህ በቀስትና ደጋን፣ በወንጭፍና በድንጋይ ታጠቅሁ። አባቴንም ምግብ ለማግኘት ወዴት ልሂድ? አልኩት።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ፣ በእኔ ቃላት ምክንያት እራሳቸውን ትሁት በማድረግ፣ ጌታን ጠየቀ፤ እኔም ብዙ ነገሮችን በነፍሴ ኃይል ሁሉ ተናገሬአቸው ነበርና።
፳፭ እናም እንዲህ ሆነ፣ የጌታ ድምፅ ወደአባቴ መጣ፤ እናም እርሱ በጌታ ላይ በማጉረምረሙ በእውነት ተገሰፀ፣ ስለዚህም እጅግ ሀዘን ተሰማው።
፳፮ እናም እንዲህ ሆነ፣ የጌታ ድምፅ፣ ወደኳሱ ተመልከት፣ እናም የተፃፉትን ነገሮች አስተውል አለው።
፳፯ እናም እንዲህ ሆነ፣ አባቴ በኳሱ ላይ የተፃፉትን ነገሮች ሲያስተውል እርሱ፣ እናም ደግሞ ወንድሞቼና የእስማኤል ወንዶች ልጆች እንዲሁም ሚስቶቻችን፣ እጅግ ፈሩና ተንቀጠቀጡ።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ በኳሱ ላይ ያሉት አመልካቾች የሚሰሩት፣ ለእነርሱ በምንሰጣቸው እምነት፣ እናም ትጋትና፣ ትኩረት እንደሆነ ተመለከትኩ።
፳፱ እናም ደግሞ በእነርሱ ላይ ለማንበብ ግልፅ የነበሩ፤ የጌታን መንገድ በተመለከተም ግንዛቤን የሚሰጡ አዲስ ፅሁፎች ተፅፎ ነበር፣ ለእርሱም በምንሰጠው እምነትና ትጋት መሰረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጻፋልም ይለወጣልም። በዚህም እኛ በቀላል ዘዴ ጌታ ትላልቅ ነገሮችን ለማምጣት እንደሚችል እናያለን።
፴ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ በኳሱ ላይ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት፣ ወደተራራው ጫፍ ሄድኩ።
፴፩ እናም እንዲህ ሆነ የዱር እንስሳትን በመግደል ለቤተሰቦቻችን ምግብ አገኘሁ።
፴፪ እናም እንዲህ ሆነ፣ ወደ ድንኳናችን የገደልኳቸውን እንስሳት ተሸክሜ ተመለስኩ፤ እናም አሁን እነርሱ ምግብ ማግኘቴን በተመለከቱ ጊዜ ደስታቸው ምን ያህል ነበር! እናም እንዲህ ሆነ፣ እነርሱ በጌታ ፊት እራሳቸውን ዝቅ አደረጉና ምስጋናን ለእርሱ አቀረቡ።
፴፫ እናም እንዲህ ሆነ፣ እንደገና ተጓዝን፣ በመጀመሪያ እንደተጓዝነው በዚያው አቅጣጫ አቅራቢያ ተጓዝን፤ እናም ለአጭር ጊዜ ቆይታ እናደርግ ዘንድ ለብዙ ቀናት ከተጓዝን በኋላ እንደገና ድንኳናችንን ተከልን።
፴፬ እናም እንዲህ ሆነ እስማኤል ሞተ፤ እናም ናሆም ተብሎ በሚጠራም ቦታ ተቀበረ።
፴፭ እናም እንዲህ ሆነ፣ የእስማኤል ሴት ልጆች አባታቸውን በማጣታቸውና በምድረበዳ ውስጥ በመሰቃየታቸው የተነሳ እጅግ አዘኑ፤ እናም ከኢየሩሳሌም እንዲወጡ ስላደረገ በአባቴ ላይ አጉረመረሙ፣ እንዲህም አሉ—አባታችን ሞቷል፤ አዎን፣ በምድረበዳ ውስጥ ብዙ ተንከራተትን፣ እንዲሁም በብዙ መከራ፣ ረሃብ፣ ጥማትና ድካም ተሰቃየን፤ ከእነዚህ ሁሉ ስቃዮች በኋላም በረሃብ የተነሳ በምድረበዳ ውስጥ እንጠፋለን።
፴፮ እናም እነርሱ በአባቴ ላይና ደግሞ በእኔ ላይ አጉረመረሙ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እንደገና ለመመለስም ፈለጉ።
፴፯ እናም ላማን ለልሙኤል ደግሞም ለእስማኤል ወንዶች ልጆች እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ እነሆ አባታችንን፣ እናም ደግሞ እራሱን በእኛ በታላላቅ ወንድሞቹ ላይ ገዢ እንዲሁም አስተማሪ ያደረገውን ወንድማችን ኔፊን እንግደላቸው።
፴፰ አሁን ኔፊ ጌታ ከእርሱ ጋር መነጋገሩን እናም ደግሞ መላዕክቶች እንደጎበኙትና እንዳስተማሩት ተናግሯል። ነገር ግን እነሆ እርሱ እንደዋሸን እናውቃለን፤ እነዚህንም ነገሮች የሚነገረንና፣ በብልህ ዘዴዎቹ ብዙ ነገሮችን ያደረገው፣ እኛንም እንዲያሞኘን ዘንድ፣ ምናልባትም እኛን እንግዳ ወደ ሆነው ምድረበዳ ሊመራን እንዲችል በማሰብ ነው፤ እናም በእኛ ላይ ማንኛውንም በፍላጎቱና በሚያስደስተው መሰረት ያደርግ ዘንድ እኛን ከወሰደ በኋላ በእኛ ላይ እራሱን ንጉስና ገዢ ለማድረግ አስቦአል። በዚህም መንገድ ወንድሜ ላማን በእነርሱ ልብ ቁጣን አነሳሳ።
፴፱ እናም እንዲህ ሆነ፣ ጌታ ከእኛ ጋር ነበር፤ አዎን የጌታ ድምፅ መጣ፣ ብዙ ቃላትም ተናገራቸው፣ እናም በብርቱ ገሰፃቸው፤ በጌታም ድምፅ ከተገሰፁ በኋላ ቁጣቸውን አቆሙና፣ ለኃጢአታቸው ንስሀ ገቡ፣ በዚህም ጌታ እንደገና ምግብ ማግኘት እንድንችል ባረከን፣ ስለዚህ አልጠፋንም።