ምዕራፍ ፲፭
ኢየሱስ የሙሴ ህግ በእርሱ እንደተፈፀም ተናገረ—ኔፋውያን በኢየሩሳሌም የተናገረላቸው ሌሎቹ በጎች ናቸው—በክፋታቸው የተነሳ፣ በኢየሩሳሌም ያሉ የጌታ ሰዎች ስለተበተኑት የእስራኤል በጎች አያውቁም። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ዐይኑን በዙሪያው ባሉ ሰዎች ላይ አሳረፈ፣ እናም እንዲህ አላቸው፥ እነሆ ወደ አባቴ ከማረጌ በፊት ያስተማርኩትን ነገሮች ሰምታችኋል፤ ስለዚህ፣ ይህንን ንግግሬን የሚያስታውስ እናም የሚፈፅም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ የሙሴን ህግ በተመለከተ ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግባቸው የሚገረሙና፣ የሚደነቁ ጥቂቶች እንዳሉ አስተዋለ፤ አሮጌዎቹ ነገሮች እንዳለፉ እናም ሁሉም ነገሮች አዲስ እንደሆኑ የተነገሩትን አልተረዱምና።
፫ እናም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ አሮጌዎቹ ነገሮች አልፈዋል፣ እናም ሁሉም ነገር አዲስ ሆነዋል ስላልኳችሁ አትገረሙ።
፬ እነሆ፣ ለሙሴ የተሰጠው ህግ ተፈፅሟል እላችኋለሁ።
፭ እነሆ፣ ህጉን የሰጠሁት እኔ ነኝ፤ ከእስራኤል ህዝቦቼ ጋር ቃል ኪዳን የገባሁትም እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ህጉን ልፈጽም ስለመጣሁ ህጉ በእኔ ተፈፅሟል፤ ስለዚህ ይህም መጨረሻ አለው።
፮ እነሆ፣ ነቢያትን አልሽርም፣ ምክንያቱም ብዙዎች በእኔ አልተፈፀሙምና፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ይፈፀማሉ።
፯ እናም አሮጌዎቹ ነገሮች ያልፋሉ ስላልኳችሁ፣ ስለሚመጡት ነገሮች ተነግረው የነበሩትን አልሽርም።
፰ እነሆም፣ ከህዝቤ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን በሙሉ አልተፈጸመም፤ ነገር ግን ለሙሴ የተሰጠው ህግ በእኔ መጨረሻ አለው።
፱ እነሆ፣ እኔ ህግ እንዲሁም ብርሃን ነኝ። ወደ እኔ ተመልከቱ፣ እናም እስከመጨረሻው የጸናችሁ ሁኑ፣ እናም ህያው ትሆናላችሁ፤ እስከመጨረሻው ለሚፀናም የዘላለምን ህይወት እሰጠዋለሁና።
፲ እነሆ፣ ትዕዛዝን ሰጥቻችኋለሁ፤ ስለዚህ ትዕዛዜን ጠብቁ። እናም ህጉና ነቢያትም ይህ ነው፣ ስለእኔ በእውነት ይመሰክራሉና።
፲፩ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረበት ጊዜ፣ ለእነዚያ ለመረጣቸው አስራ ሁለቱ እንዲህ አላቸው፥
፲፪ እናንተ የእኔ ደቀመዛሙርት ናችሁ፤ እናም ለዮሴፍ ቤት ቅሪት ለሆኑትም ለእነዚህ ሰዎች ብርሃን ናችሁ።
፲፫ እናም እነሆ፣ ይህች ምድር የርስታችሁ ስፍራ ናት፣ እናም አብም ለእናንተ ይህን ሰጥቷችኋል።
፲፬ እናም በኢየሩሳሌም ለሚገኙት ወንድሞቻችሁ በማንኛውም ጊዜ ይህን እንድናገር አብ ትዕዛዝ አልሰጠኝም ነበር።
፲፭ አብ ከምድሪቱ እንዲወጡ ስለመራቸው የእስራኤል ቤት ስለሆኑት ሌሎች ነገዶች በየትኛውም ጊዜ በኢየሩሳሌም ላሉት ወንድሞቻችሁ እንድናገር ትዕዛዝ አልሰጠኝም።
፲፮ አብም እስከዚህ ድረስ ለእነርሱ እንድናገራቸው አዞኛል፥
፲፯ ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፣ ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ፣ እረኛውም አንድ ይሆናል።
፲፰ እናም እንግዲህ፣ አንገተ ደንዳና በመሆናቸውና፣ ባለማመናቸው ቃሌን ሊረዱ አልቻሉም፤ ስለዚህ ይህን ነገር በተመለከተ ከዚህ የበለጠ እንዳልናገር በአብ ታዝዤ ነበር።
፲፱ ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በክፋታቸው የተነሳ እናንተ ከእነርሱ ተለይታችኋል ብዬ እነግራችሁ ዘንድ አብ አዞኛል፤ ስለዚህ በክፋታቸውም የተነሳ ነው ስለእናንተ የማያውቁት።
፳ እናም እንደገና እውነት እላችኋለሁ፣ ሌሎች ነገዶችን አብ ከእነርሱ ለይቷል፤ እናም በክፋታቸው የተነሳ ነው ስለእነርሱ የማያውቁት።
፳፩ እናም እውነት እላችኋለሁ፤ ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፤ እነርሱም ድምጼን ይሰማሉ፤ እናም አንድ መንጋና፣ እረኛውም አንድ ይሆናል፣ በማለት የተናገርኩአችሁ እናንተ ናችሁ።
፳፪ እናም ሌሎቹ በጎች አህዛብ ናቸው ብለው ስለገመቱ እኔን አልተረዱኝም፤ ምክንያቱም አህዛብ በእነርሱ ስብከት እንደሚለወጡ አልተረዱምና።
፳፫ እናም ድምፄን ያዳምጣሉ ማለቴንም አልተረዱም፤ እናም በማንኛውም ጊዜ አህዛብ ድምፄን መስማት እንደማይችሉ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ካልሆነም በቀር ራሴን እንደማልገልፅላቸውም አልተረዱኝም።
፳፬ ነገር ግን እነሆ፣ ድምፄን ሰምታችኋልም፣ አይታችሁኛልም፤ እናንተም የእኔ በጎች ናችሁ፤ እናም አብ ለእኔ ከሰጣቸው መካከልም የተቆጠራችሁ ናችሁ።