ምዕራፍ ፲፭
አልማና አሙሌቅ ወደ ሲዶም ሄዱ እናም ቤተክርስቲያንን አቋቋሙ—አልማ በቤተክርስቲያኗ አባል የሆነውን ዚኤዝሮምን ፈወሰው—ብዙዎች ተጠመቁ፣ እናም ቤተክርስቲያኗ በለፀገች—አልማና አሙሌቅ ወደ ዛራሔምላ ሄዱ። በ፹፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ አልማና አሙሌቅ ከከተማው እንዲወጡ ታዘው ነበር፤ እናም ወጥተው ሄዱና፣ ወደ ሲዶም ምድር ወጡ፤ እናም እነሆ፣ በአልማ ቃል በማመናቸው ከአሞኒያህ ምድር የተባረሩትንና በድንጋይ የተመቱትን ሰዎች ሁሉ አገኙአቸው።
፪ እናም በሚስቶቻቸውና በልጆቻቸው ላይ የደረሱትን ሁሉና፣ ደግሞ እነርሱን በተመለከተ እናም ስለመዳናቸው ኃይል ተረኩላቸው።
፫ እናም ደግሞ ዚኤዝሮም በክፋቱ የአዕምሮ ጭንቀት የተነሳ፣ አልማና አሙሌቅ ከእንግዲህም አይኖሩም በማለት በመገመቱ በሀይለኛ ንዳድ ታሞ በሲዶም ውስጥ ተኛ፤ እናም በክፋቱም ምክንያት ተገድለዋል ብሎ ገምቶ ነበር። እናም ይህም ታላቅ ኃጢያትና ሌሎች ኃጢአቶቹ፣ መዳኛ ሳያገኝ፣ እስከሚቆስል ራሱን አሰቃዩት፤ ስለዚህ በሚያቃጥል እሳት መንገብገብ ጀመረ።
፬ እንግዲህ፣ አልማና አሙሌቅ በሲዶም ምድር ውስጥ መሆናቸውን ሲሰማ፣ ልቡ መደፋፈር ጀመረ፤ እናም ወደ እርሱ እንዲመጡ ፈልጎ፣ በፍጥነት መልዕክት ላከባቸው።
፭ እናም እንዲህ ሆነ የላከውን መልዕክቱን ተቀብለው በፍጥነት ወደ እርሱ ሄዱ፤ ወደ ዚኤዝሮም ቤት ገቡም፤ እናም ታሞ በአልጋው ላይ አገኙት፣ በንዳዱም ተዳክሞ ነበር፤ አዕምሮውም በክፋቱ ምክንያት እጅግ ቆስሎ ነበር፤ እናም ሲመለከታቸው እጁን ዘረጋ፣ እንዲፈውሱትም ለመናቸው።
፮ እናም እንዲህ ሆነ አልማ በእጁ በመያዝ እንዲህ ሲል ተናገረው፥ ለማዳን የሆነውን የክርስቶስን ኃይል ታምናለህን?
፯ እናም እንዲህ በማለት መለሰለት፥ አዎን፣ አንተ ያስተማርካቸውን ቃላት በሙሉ አምናለሁ።
፰ እናም አልማ እንዲህ አለ፥ በክርስቶስ ቤዛነት ካመንህ መፈወስ ትችላለህ።
፱ እናም እርሱ እንዲህ አለ፥ አዎን፣ እንደቃልህ አምናለሁ።
፲ እናም አልማ እንዲህ ሲል ወደ ጌታ ጮኸ፥ አቤቱ ጌታ አምላካችን፣ በዚህ ሰው ላይ ምህረትን አድርግና በክርስቶስ ባለው እምነቱ ፈውሰው።
፲፩ እናም አልማ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ ዚኤዝሮም በእግሮቹ ዘለለና፣ መራመድ ጀመረ፤ ይህም የተደረገው በህዝቡ ሁሉ ታላቅ መገረም ነበር፣ እናም የዚህ እውቀትም በሲዶም ምድር ሁሉ ተሰራጨ።
፲፪ እናም አልማ በጌታ ዚኤዝሮምን አጠመቀው፤ ከእዚያም ጊዜ ጀምሮ ለህዝቡ መስበክ ጀመረ።
፲፫ እናም አልማ በሲዶም ምድር ቤተክርስቲያንን አቋቋመ፣ እናም ለመጠመቅ የፈለጉትን ሁሉ በጌታ ለማጥመቅ ካህናትንና መምህራንን ቀባ።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ ብዙ ነበሩ፤ በሲዶም ዙሪያ ካሉት ከሁሉም አካባቢ መጡና ተጠመቁ።
፲፭ ነገር ግን በአሞኒሀ ምድር ያሉትን ሰዎች በተመለከተ፣ ልባቸው የጠጠረና አንገታቸው የደነደነ ሆኖ ቀጠለ፤ እናም የአልማንና የአሙሌቅን ኃይል በሙሉ የመጣው ከዲያብሎስ ነው እያሉ ለኃጢአታቸው ንስሃ አልገቡም፤ ምክንያቱም ኃይማኖታቸው የኔሆር ነበርና፣ እናም ለኃጢያት ንስሃ መግባትንም አያምኑም ነበር።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ አልማና አሙሌቅ፤ አሙሌቅ በአሞኒያህ ምድር የነበሩትን ሁሉንም ወርቅ፣ ብርና የከበሩ ነገሮችን ለእግዚአብሔር ቃል በመተው፣ በአንድ ወቅት ጓደኞቹ በነበሩት እናም በአባቱና በነገዱ ተወግዞ ነበር፤
፲፯ ስለሆነም፣ አልማ በሲዶም ቤተክርስቲያንን ካቋቋመ በኋላ፣ መገታቱን ተመለከተ፣ አዎን፣ ሰዎች ከልባቸው ኩራት እንደተገቱ፣ እናም ከሰይጣን፣ ከሞትና ከጥፋት እንዲድኑ በእግዚአብሔር ፊት እራሳቸውን ትሁት ሲያደርጉ እናም በቅዱስ ስፍራቸው በመሰዊያ ፊት እግዚአብሔርን ለማምለክ ያለማቋረጥ ለመጠበቅና ለመፀለይ እራሳቸውን በአንድ ላይ መሰብሰብ እንደጀመሩ ተመለከተ፤
፲፰ አሁን አስቀድሜ እንደተናገርኩ እንዲሁም አልማ እነዚህን ነገሮች ከተመለከተ በኋላ፣ አሙሌቅን ወሰደና ወደ ዛራሔምላ ምድር ይዞት ሄደ፣ ወደ ቤቱም ወሰደው፣ በመከራውም አገለገለውና በጌታ እንዲበረታ አደረገው።
፲፱ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የነገሱበት አስረኛው የመሣፍንቱ የንግስ ዘመን እንደዚህ ተፈፀመ።