ምዕራፍ ፲፬
ሳሙኤል በምሽት ብርሃን እንደሚሆን እናም አዲስ ኮከብ በክርስቶስ መወለድ እንደሚሆን ተነበየ—ክርስቶስ ሰዎችን ከጊዜያዊው እንዲሁም ከመንፈሳዊው ሞት ያድናቸዋል—የሞቱም ምልክቶች የሶስት ቀን ጨለማ፣ የአለቶች መፈረካከስ፣ እናም ታላቅ የሆነ የምድር መናወጥን ያጠቃልላል። በ፮ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ላማናዊው ሳሙኤል ሊፃፉ የማይችሉ ከዚህ የበለጡ ታላቅ ነገሮችን ተንብዮአል።
፪ እናም እነሆ እንዲህም አላቸው፥ እነሆ፣ ምልክትን እሰጣችኋለሁ፤ ከዚህ ወዲያ አምስት ዓመት ይመጣል፣ እናም እነሆ፣ ከዚያም በስሙ የሚያምኑትን ሁሉ ሊያድናቸው የእግዚአብሔር ልጅ ይመጣል።
፫ እናም እነሆ ይህንን የምሰጣችሁ በመምጫው ጊዜ ለምልክት እንዲሆናችሁ ነው፤ እነሆም ከመምጣቱ አንድ ቀን በፊት ባለው ምሽትም ምንም ዓይነት ጨለማ እስከማይሆን ድረስ በሰማይ ታላቅ ብርሃን ይሆናል፤ ለሰዎችም እንደ ቀን ሆኖ ይታያቸዋል።
፬ ስለዚህ፣ ልክ አንድ ቀን እንደሆነና፣ ምሽት እንደሌለ፣ አንድ ቀንና አንድ ሌሊት እናም አንድ ቀን ይሆናሉ፤ ይህም ለምልክት ይሆናችኋል፤ ምክንያቱም የፀሐይ መውጫዋንና መጥለቂያዋን ታውቃላችሁና፤ ስለዚህ ሁለት ቀንና አንድ ምሽት እንደሚሆን በእርግጥ ታውቃላችሁ፣ ይሁን እንጂ ምሽቱ ጨለማ አይሆንም፤ እናም ይህ እርሱም ከመወለዱ በፊት የሚሆነው ምሽት ይሆናል።
፭ እናም እነሆ ተመልክታችኋት የማታውቋት አዲስ ኮከብም ትወጣለች፤ እናም ይህ ለምልክት ይሆናችኋል።
፮ እናም እነሆ፣ ይህ ብቻም አይደለም፤ በሰማይ ብዙ ምልክቶች እንዲሁም አስደናቂ ነገሮች ይሆናሉ።
፯ እናም እንዲህ ይሆናል፥ ሁላችሁም በመሬት ላይ እስከምትወድቁ ትደነቃላችሁ፣ እንዲሁም ትገረማላችሁ።
፰ እናም እንዲህ ይሆናል፥ በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ዘለዓለማዊ ህይወት ይኖረዋል።
፱ እናም እነሆ፣ ስለነዚህም ነገሮች መጥቼ ለእናንተ እንድናገር ጌታ በመላዕክቱ አዞኛል፤ አዎን እነዚህን ነገሮች ለእናንተ እንድተነብይ አዞኛል፤ አዎን፣ እንዲህም ብሎኛል፥ ንስሃ ግቡ እናም የጌታንም መንገድ አቅኑ ብለህ ለዚህ ህዝብ ጩህ።
፲ እናም እንግዲህ፣ ላማናዊ በመሆኔና ጌታ ያዘዘኝን ቃላት ለእናንተ በመናገሬ፣ እናም ለእናንተ ቃሉም አስቸጋሪ በመሆኑ፣ በእኔ ተቆጣችሁ፣ እናም እኔን ለማጥፋት ፈለጋችሁ፤ ከመካከላችሁም አውጥታችሁ ጥላችሁኛል።
፲፩ እናም ቃላቴን ትሰማላችሁ፤ ምክንያቱም ለዚህ ስል ነው ወደ ከተማዋ ግንብ የመጣሁት፣ ስለዚህ በክፋታችሁም የተነሳ የሚጠብቃችሁን የእግዚአብሔርን ቅጣት ትሰሙት እንዲሁም ታውቁት ዘንድ፤ እናም ደግሞ የንስሃን ሁኔታ እንድታውቁት ዘንድ የመጣሁት፤
፲፪ እናም ደግሞ የእግዚአብሔርን ልጅ፣ የሰማይና የምድር አባት የሆነውን፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ የሆነውን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት ታውቁ ዘንድ፤ እናም በስሙም እንድታምኑ ባለኝ አላማ፣ የመምጣቱን ምልክቶች እንድታውቋቸው መጣሁ።
፲፫ እናም በስሙ ካመናችሁ፣ በመልካምነቱ ለእነዚህ ስርየትን ታገኙ ዘንድ ለኃጢአታችሁ ሁሉ ንስሃን ትገባላችሁ።
፲፬ እናም እነሆ፣ በድጋሚ ሌላ ምልክት እሰጣችኋለሁ፤ አዎን፣ የሞቱን ምልክት።
፲፭ እነሆም፣ ደህንነት እንዲመጣ በእርግጥ መሞት ይገባዋል፤ አዎን፣ ሞቱ ሰዎች በጌታ ፊት እንዲቀርቡ የሙታን ትንሳኤን እንዲያመጣ ጠቃሚ እንዲሁም አስፈላጊ ይሆናል።
፲፮ አዎን፣ እነሆ፣ ይህ ሞት ትንሳኤን ያመጣል፣ እናም የሰው ዘር የሆኑትን በሙሉ ከፊተኛው ሞት ያድናል—መንፈሳዊ ከሆነው ሞት፣ የሰው ዘር በሙሉ በአዳም መውደቅ ከጌታ ፊት ተለይተዋል፣ በጊዜያዊም በመንፈሳዊም ሞት እንደሞቱ ናቸው።
፲፯ ነገር ግን እነሆ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ዘርን፣ አዎን፣ የሰው ዘርን በሙሉ ያድናል፣ እናም ወደ ጌታ ፊትም ያቀርባቸዋል።
፲፰ አዎን፣ እናም የንስሃንም አካሄድ ያመጣል፤ ንስሃ የሚገባ ቢኖር አይቆረጥምና ወደ እሳቱም አይወረወርም፤ ነገር ግን ንስሃ የማይገባ ይቆረጣል፣ እናም ወደ እሳቱ ይወረወራል፤ በድጋሚም መንፈሳዊ ሞት፣ አዎን፣ ሁለተኛ ሞት በእነርሱ ላይ ይመጣል፤ ለፅድቅ ከሆኑትም ነገሮችም በሚመለከት በድጋሚ ይቆረጣሉና።
፲፱ ስለዚህ ንስሃ ግቡ፤ ንስሃ ግቡ፣ እነዚህን ነገሮች በማወቃችሁ፣ እናም ባለማድረጋችሁ ራሳችሁን በእርግማን ስር በማድረግ ታሰቃያላችሁና፤ እናም ወደዚህ ሁለተኛ ሞትም ራሳችሁን ትጎትቱታላችሁ።
፳ ነገር ግን እነሆ፣ ስለሌላው ምልክት፣ የሞቱን ምልክት፣ በሚመለከት እንደነገርኳችሁ፤ እነሆ በሚሞትበት በዚያ ቀን፣ ፀሐይ ትጨልማለች፣ እናም ለእናንተ ብርሃን አትሰጥም፤ ደግሞ ጨረቃና ከዋክብትም ይጨልማሉ፤ እናም ከሞተበት ጊዜም እንኳን ጀምሮ ለሶስት ቀናት፣ ከሞት እስከሚነሳበት ጊዜ ድረስ፣ በዚህ በምድር ላይ ምንም ብርሃን አይኖርም።
፳፩ አዎን፣ ነፍሱን አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ ለብዙ ሰዓታት ነጎድጓድ እንዲሁም መብረቅ ይሆናል፣ እናም ምድር ትንቀጠቀጣለችና ትናወጣለች፤ እናም በምድር ላይ ያሉ ዓለቶች፣ በዚህ ጊዜ ጠጣር እንደነበሩ የምታውቋቸው ወይም አብዛኛው ክፍል አንድ ጠጣር የነበሩት፣ ከምድር በላይ የነበሩትና ከሥር ያሉትም ሁሉ ይሰባበራሉ፤
፳፪ አዎን ሁለት ቦታ ይከፈላሉ፤ እናም ከዚህም በኋላ ተጨማደውና ተሰነጣጥቀው፣ እናም በምድር ላይ የተሰባበሩ ቁርጥራጮች ሆነው፣ አዎን ከመሬት በላይና በታች ይገኛሉ።
፳፫ እናም እነሆ፣ ኃይለኛ ነፋስ ይኖራል፣ እናም ከፍታቸው ትልቅ የሆኑ ተራሮች እንደሸለቆ ዝቅ ይላሉ፣ አሁን ሸለቆ ተብለው የሚጠሩትም በከፍታቸውም ትልቅ የሆኑ ተራሮች ይሆናሉ።
፳፬ እናም ብዙ አውራ ጎዳናዎች ይሰባበራሉም፣ ብዙ ከተሞችም የወደሙ ይሆናሉ።
፳፭ እናም ብዙ መቃብሮችም ይከፈታሉና ሙታኖቻቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፣ ለብዙ ሰዎችም ብዙ የሆኑ ቅዱሳን ይታዩአቸዋል።
፳፮ እናም እነሆ፣ እንደዚህ መልአኩ ተናግሮኛል፤ ለብዙ ሰዓታትም ነጎድጓድ እንዲሁም መብረቅ እንደሚሆንም ተናግሮኛል።
፳፯ እናም እንዲህ አለኝ፥ ነጎድጓዱና መብረቁ እንዲሁም አይሎ ነፋስ እያለ እነዚህ ነገሮች ይሆናሉ፤ እናም ለሶስት ቀናትም ምድር በጨለማ ትከበባለች።
፳፰ እናም መልአኩ እንዲህ አለኝ፥ እነዚህ ምልክቶች እና እነዚህ ድንቅ የሆኑት በምድር ገፅ ላይ ሁሉ እንደሚሆኑ ያምኑ ዘንድ፣ በሰው ልጆች መካከል የማያምኑበት ምንም ምክንያት እንዳይኖር ከዚህ የበለጡ ታላቅ ነገሮችን ለብዙዎቹ ይታያሉ—
፳፱ እናም ይህም የሚያምን ሁሉ እንዲድን ነው፣ የማያምነውም ጻድቃዊ ፍርድ በእርሱ ላይ እንዲመጣ ነው፤ እናም ደግሞ ከተኮነኑ በራሳቸው ላይ የራሳቸውን ፍርድ ያመጣሉ።
፴ እናም አስታውሱ ወንድሞቼ የሚጠፋ ቢኖር የሚጠፋው ለራሱ እንደሆነና፣ ክፋትን የሚሰራም ለራሱ የሚሰራ እንደሆነ ከእንግዲህ አስታውሱ፤ እነሆም፣ እናንተ ነፃ ናችሁ፤ ለራሳችሁ እንድትሰሩ ተፈቅዶላችኋል፤ እነሆ እግዚአብሔርም እውቀትን ሰጥቷችኋል እናም እናንተን ነፃ አድርጓችኋል።
፴፩ እርሱም መልካምን ከመጥፎ ታውቁ ዘንድ እውቀትን ሰጥቷችኋል፤ እናም ህይወትን አለበለዚያም ሞትን ትመርጡም ዘንድ የነጻ ምርጫ ሰጥቷችኋል፤ እናም መልካምን መስራት ትችላላችሁ፣ መልካም ወደ ሆነውም ደግማችሁ ትመለሳላችሁ፣ ወይንም መልካም የሆነው ለእናንተ ይመለስላችኋል፤ ወይም ክፉ መስራት ትችላላችሁ፤ እናም ክፉ የሆነውም ደግሞ ይመለስላችኋል።