ምዕራፍ ፯
ሼረም ክርስቶስን ካደ፣ ከያዕቆብ ጋር ተጣላ፣ ምልክትን በግድ ፈለገ፣ እናም በእግዚአብሔር ተቀሰፈ—ሁሉም ነቢያት ስለክርስቶስና ስለኃጢያት ክፍያው ተናግረዋል—ኔፋውያን በዘመናቸው እንደሚንከራተቱ፣ በመከራ እንደተወለዱና፣ በላማናውያን እንደተጠሉ ኖሩ። ከ፭፻፵፬–፬፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ጥቂት አመታት ካለፉ በኋላ፣ ከኔፋውያን መካከል ስሙም ሼረም የተባለ አንድ ሰው መጣ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ እርሱ በህዝቡ መካከል መስበክና፣ ክርስቶስ የሚባል እንደሌለም ለእነርሱ ማወጅ ጀመረ። እናም ለህዝቡ ብዙ የሽንገላን ነገሮች ሰበከ፤ ይህንንም ያደረገው የክርስቶስን ትምህርት ለመጣል ነበር።
፫ እናም የህዝቡንም ልብ ያስት ዘንድ በትጋት በመስራት የብዙዎችን ልብ አሳተ፤ እናም እኔ ያዕቆብ በሚመጣው ክርስቶስ እምነት እንዳለኝ ስለሚያውቅ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ብዙ አጋጣሚዎችን ፈለገ።
፬ እናም የተማረ ነበር፣ ስለዚህ የህዝቡን ቋንቋ በፍጹም እውቀት ያውቅ ነበር፣ ስለሆነም፣ በዲያብሎስ ኃይል መሰረት ብዙ ሽንገላንና፣ ብዙ የንግግር ኃይል መጠቀም ችሏል።
፭ እናም እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ብዙ ራዕይና ብዙ ነገሮችን ያየሁ ቢሆንም፣ እርሱ እኔን ከእምነቴ ለማናወጥ ተስፋ ነበረው፤ እኔ በእውነት መላዕክቶችን አይቻለሁ፣ እነርሱም እኔን አስተምረውኛልና። እናም ደግሞ ከጊዜ ወደጊዜ የጌታ ድምፅ በቃሉ ሲናገረኝ ሰምቻለሁ፤ ስለሆነም፣ ልናወጥ አልችልም።
፮ እናም እንዲህ ሆነ እርሱ ወደ እኔ መጣና፣ በዚህ ሁኔታ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፥ ወንድም ያዕቆብ፣ አንተን እናገር ዘንድ ብዙ አጋጣሚዎችን ፈለግሁ፤ ወንጌል ወይም የክርስቶስን ትምህርት ብለህ የምትጠራውን ለመስበክ እንደተጓዝክ ሰምቻለሁ እናም ደግሞ አውቄአለሁ።
፯ እናም ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ጎዳና እንዲስቱና፣ ትክክለኛ የሆነውን የሙሴን ህግ እንዳይጠብቁት ከዚህ ህዝብ አብዛኛውን አስተሀል፤ እናም ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ይመጣል ወደምትለው ፍጡር አምልኮ የሙሴን ህግ ለውጠሀል። እናም አሁን እነሆ፣ እኔ ሼረም ይህ ስድብ እንደሆነ አውጅልሀለሁ፤ ማንም ሰው የሚመጡ ነገሮችን መናገር ስለማይችል፣ እንደነዚህ አይነት ነገሮችን አያውቅምና። እናም እንደዚህ ነበር ሼረም ከእኔ ጋር የተጣላው።
፰ ነገር ግን እነሆ፣ ጌታ እግዚአብሔር በቃሉ እስከማሳፍረው ድረስ ለነፍሴ መንፈሱን አፈሰሰልኝ።
፱ እናም ለእርሱ እንዲህ አልሁ፥ የሚመጣውን ክርስቶስ ትክዳለህን? እና እርሱም አለ፥ክርስቶስ ከአለ አልክደውም፤ ነገር ግን ክርስቶስ እንደሌለ፣ እንዳልነበረ፣ እንደማይኖርም አውቃለሁ።
፲ እናም እንዲህ አልኩት፥ በቅዱስ መጽሐፍት ታምናለህ? እርሱም አዎን አለ።
፲፩ እናም እኔም አልኩት፥ አንተ እነርሱን አትረዳቸውም፤ ምክንያቱም እነርሱ በእውነት ስለክርስቶስ ይመሰክራሉና። እነሆ፣ የትኛውም ነቢይ ክርስቶስን በተመለከተ ከመናገር በስተቀር የፃፈ ወይም የተነበየ የለም እልሀለሁ።
፲፪ እናም ይህ ብቻም አይደለም—ይህ ለእኔ ተገልፆልኛል፣ ሰምቻለሁም ተመልክቻለሁምና፤ እናም ይህ ደግሞ ለእኔ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጾልኛል፤ ስለሆነም፣ ምንም አይነት የኃጢያት ክፍያ ባይኖር ኖሮ የሰው ዘር በሙሉ መጥፋት እንደሚኖርበት አውቃለሁ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ እርሱም አለኝ፥ አንተ በዚህ ብዙ በምታውቀው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ምልክትን አሳየኝ።
፲፬ እናም አልኩት፥ እውነት መሆኑን ለምታውቀው ለአንተ ምልክት ለማሳየት እግዚአብሔርን የምፈትነው እኔ ማን ነኝ? ነገር ግን የዲያብሎስ በመሆንህ ትክደዋለህ። ይሁን እንጂ፣ የእኔ ፈቃድ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አንተን የሚቀጣ ከሆነ ይህ በሰማይም በምድርም ኃይል እንዳለው፤ እናም ደግሞ ክርስቶስ እንደሚመጣ ምልክት ይሆንሃል። እናም አቤቱ ጌታ የእኔ ፈቃድ ሳይሆን ያንተ ይሆናል።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ስናገር፣ የእግዚአብሔር ኃይል ወረደበት፣ በዚህም ምክንያት መሬት ወደቀ። እናም እንዲህ ሆነ ለብዙ ቀናት እንክብካቤን አገኘ።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ ለህዝቡም ተናገረ፥ ልሞት ስለሆነ ነገ በአንድ ላይ ተሰብሰቡ፤ ስለሆነም፣ ከመሞቴ በፊት ለህዝቡ መናገር እፈልጋለሁ።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ በማግስቱ ብዙዎች በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፤ እናም ለእነርሱ በግልፅ ተናገረ፣ ያስተማራቸውንም ነገሮች ካደ፣ እናም ስለክርስቶስ እንዲሁም ስለመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲሁም ስለመላዕክቶች አገልግሎት መሰከረ።
፲፰ እናም በዲያብሎስ ኃይል ተታሎ እንደነበር በግልፅ ተናገራቸው። እናም ስለሲዖልና ዘለዓለማዊነት እንዲሁም ዘለዓለማዊ ቅጣት ተናገረ።
፲፱ እናም አለ፥ ይቅርታ የሌለው ኃጢያት በመፈፀሜ ፈርቻለሁ፣ ምክንያቱም ለእግዚአብሔር ዋሽቻለሁና፤ ክርስቶስን ክጃለሁና፣ ቅዱስ መጽሐፍንም አምኛለሁ ብያለሁና፤ እነርሱም በእውነት ስለእርሱ መስክረዋል። እናም ለእግዚአብሔር በመዋሸቴ ሁኔታዬ መጥፎ ይሆናል ብዬ እጅግ እፈራለሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ።
፳ እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ቃላት ሲናገር ሌላ ምንም ማለት አልቻለም፣ እናም ሞተ።
፳፩ እናም ወደሞት ሲቀርብ እነዚህን ነገሮች መናገሩን ህዝቡ በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ተደነቁ፤ እናም እንዲህም ሆኖ በመሸነፍ ወደ መሬት እስከሚወድቁ ድረስ የእግዚአብሔር ኃይል በእነርሱ ላይ ወረደ።
፳፪ አሁን ይህ ነገር እኔን ያዕቆብን አስደስቶኛል፣ ምክንያቱም በሰማይ ያለውን አባቴን ይህን ጠይቄአለሁና፤ እርሱም ጩኸቴን ሰምቷል፣ እናም ፀሎቴን መልሷል።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ እንደገና ሰላምና የእግዚአብሔር ፍቅር በህዝቡ መካከል ዳግሞ ተመለሰ፤ እናም ቅዱሳን መጻሕፍትን መረመሩና፣ የዚህን የኃጢአተኛውን ሰው ቃል ከእንግዲህ አላዳመጡም።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያንን ወደ እውነተኛ እውቀት ለመመለስ ብዙ ዘዴዎች ተቀይሰው ነበር፤ ነገር ግን በጦርነትና ደም መፋሰስ ስለሚደሰቱና፣ ከእኛ ከወንድሞቻቸው ዘለዓለማዊ የሆነ ጥላቻ ስለነበራቸው ሁሉም በከንቱ ነበሩ። እናም በጦር መሳሪያዎቻቸው ኃይል ሁልጊዜም ሊያጠፉን ፈለጉ።
፳፭ ስለሆነም፣ የኔፊ ህዝብ በእነርሱ ላይ ከነመሳሪያዎቻቸው፣ እናም በሙሉ ኃይላቸው፣ የደህንነታቸው አለት በሆነው በእግዚአብሔር በማመን መሸጉ፤ ስለሆነም ጠላቶቻቸውን በማሸነፍ ቀጠሉ።
፳፮ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ያዕቆብ መሸምገል ጀመርኩ፤ እናም የዚህ ህዝብ ታሪክ በሌላኛው የኔፊ ሰሌዳዎች በመቀመጡ፣ ስለሆነም፣ ባለኝ እውቀት መፃፌን በመናገር፣ ጊዜው ከእኛ ጋር አልፏል፣ እናም ደግሞ ህይወታችን ልክ እንደህልም አልፏል፤ ከኢየሩሳሌም ተጥለን ወጥተን ስደተኞች በመሆናችን፣ በምድረበዳ ውስጥ በመከራ ስለተወለድን፣ እናም በራሳችን ወንድሞች ስለተጠላን፣ ይህም ጦርነትና ፀብን ስላስነሳ፣ ብቸኛና ጭምት ሰዎች ነበርን በማለትይህንን ታሪክ አጠቃልላለሁ፤ ስለሆነም፣ በዘመናችን ሁሉ አለቀስን።
፳፯ እናም እኔ ያዕቆብ፣ በቅርቡ ወደ መቃብሬ መሄድ እንዳለብኝ ተመለከትኩ፣ ስለሆነም፣ ለልጄ ኢኖስ አልኩት፥ እነዚህን ሰሌዳዎች ውሰድ። እናም ወንድሜ ኔፊ ያዘዘኝን ነገሮች ነገርኩትና እርሱም ለትዕዛዛቱ ታዛዥ ለመሆኑ ቃል ገባ። እናም በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ ጥቃቅን የሆኑትን ጽሁፎችን መፃፌን ጨረስኩ፤ አብዛኞቹ ወንድሞቼ ቃሌን እንደሚያነቡ በማመን ለአንባቢያን ደህና ሁኑ እላለሁ። ወንድሞች ደህና ሁኑ።