ምዕራፍ ፭
አማልክቱ ሁሉንም ነገሮች ለመፍጠር እቅዳቸውን ጨረሱ—እንደ እቅዳቸውም ፍጥረታቸውን አከናወኑ—አዳም ሁሉንም ህያዋን ፍጡራንን ስም ሰጠ።
፩ እና እንደዚህ ሰማያትንና ምድርን እናም በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ እንደዚህ እንጨርሳለን።
፪ አማልክትም እርስ በራሳቸው እንዲህ ተባባሉ፥ በሰባተኛው ጊዜ የተማከርንባቸውን ስራችንን እንጨርሳለን፣ እና ከተማከርናቸው ስራዎችም በሰባተኛው ጊዜ እናርፋለን።
፫ እና አማልክት በሰባተኛው ጊዜ ከስራዎቻቸው በሙሉ እነርሱ (አማልክት) ለመስራት ከተመካከሩት ስለሚያርፉ በሰባተኛው ጊዜም ፈጸሙ፣ እና ይህን ቀደሱት። እንደዚህም ነበር ሰማያትንና ምድርን ለመፍጠር በመካከላቸው የተመካከሩበትን በዚያ ጊዜ የወሰኑበት።
፬ እና አማልክት ወርደው ምድርንና ሰማያትን በፈጠሩበት ጊዜ፣ እነዚህን የሰማያትና የምድር ትውልዶችን ፈጠሩ፣
፭ ከምድር ውስጥ ከመሆኑ በፊት ስለእያንዳንዱ የሜዳ አትክልት፣ እና ስለእያንዳንዱ የለምለም ተክል ከማደጉ በፊት በሚመለከት ባሉት ሁሉ መሰረት፤ እነዚህን ለማድረግ ሲማከሩበትም አማልክት በምድር ላይ እንዲዘንብ አላደረጉም፣ እና ሰውም መሬትን እንዲያርስ አልሰሩትምና።
፮ ነገር ግን ከምድር ጭጋግ ወደላይ ወጣ፣ እና ውሀ የምድርን ገጽ አረሰረሰ።
፯ እና አማልክት ሰውን ከአፈር አበጁት፣ እና መንፈሱን (ይህም ማለት የሰውን መንፈስ) ወሰዱና እርሱ ውስጥ ጨመሩት፤ በአፍንጫውም የህይወትን እስትንፋስ እፍ አሉበት፣ እና ሰውም ህያው ነፍስ ሆነ።
፰ አማልክትም በምስራቅ በዔድን ገነትን አዘጋጁ፣ እና በሰሩት ሰውነት ውስጥ መንፈሱን የጨመሩበትን ሰው በዚያም አስቀመጡት።
፱ እና ለአይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆኑ እያንዳንዱን ዛፍ አማልክቱ ከመሬት ውስጥ ፈጠሩ፣ ደግመውም በገነት መካከልም የህይወት ዛፍ፣ እና የመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ።
፲ የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስ ነበር፣ ከዚያም በአራት ተከፍሎአል እና አራት ራሶች ሆኗል።
፲፩ አማልክትም ሰውን ወሰዱ እና እንዲያለመልማትና እንዲጠብቃት በዔድን ገነት ውስጥ አስቀመጡት።
፲፪ አማልክትም ሰውን እንዲህ ብለው አዘዙት፥ በአትክልት ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ለመብላት ነጻ ነህ፣
፲፫ ነገር ግን ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥም ትሞታለህ። አሁን እኔ አብርሐም ጊዜው በቆሎብ መቆጠሪያ ጊዜ በሆነው በጌታ ጊዜ እንደሆነ አየሁ፤ እስከዚህም ጊዜ ድረስ አማልክቱ ለአዳም ጊዜ ማወቂያ አልሰጡትም ነበርና።
፲፬ እና አማልክቱም እንዲህ አሉ፥ ለሰው የሚመች ረዳት እንፍጠርለት፣ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለምና፣ ስለዚህ የሚመች ረዳት እንፍጠርለት።
፲፭ እና አማልክቱ በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣሉበት፤ አንቀላፋም፣ እና ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወሰዱና ስፍራውን በሥጋ ዘጉ፤
፲፮ አማልክቱም ከአዳም የወሰዱትን አጥንት ሴት አድርገው ሠሯት፣ ወደ አዳምም አመጧት።
፲፯ አዳምም እንዲህ አለ፥ ይህች አጥንት ከአጥንቴ፣ ስጋዋም ከስጋዬ ናት፤ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባላለች፤
፲፰ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ እና ከሚስቱም ይጣበቃል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
፲፱ ሰውና ሚስቱም፣ ሁለቱም ራቁታቸውን ነበሩ፣ አይተፋፈሩም ነበር።
፳ አማልክቱም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረጉ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያዩ ዘንድ ወደ አዳም አመጧቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ።
፳፩ አዳም ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣ፤ እናም ለአዳም የሚመች ረዳት ተገኘለት።