2010–2019 (እ.አ.አ)
የፀጋ ስጦታ
ኤፕረል 2015


19:13

የፀጋ ስጦታ

ዛሬና ለዘላለም የእግዚአብሔር ፀጋ ልባቸው ለተሰበረው እና መንፈሳቸው ለተዋረደው ሁሉ ይገኛል።

በፋሲካ እሁድ በአለም ታሪክ ውስጥ በጣም ሲጠበቅ የነበረውንና ክብራዊ የሆነውን ክስተት እናከብራለን።

ሁሉንም የቀየረ ቀን ነው።

በዛን ቀን ሕይወቴ ተቀየረ።

ሕይወታችሁም ተቀየረ።

የሁሉም የእግዚአብሔር ልጆቸ እጣ ፈንታ ተቀየረ።

በዛን በተቀደሰ ቀን፣ የሆነው ምርኮኛ አድርጎን የነበረውን የሃጢያትንና የሞትን ቀንበር በራሱ ላይ የወሰደው የሰው ዘር ሁሉ አዳኝ፣ እነዛን ቀንበሮች ሰባብሮ ነፃ አወጣን።

በተወደደው ቤዛችን መስዋዕትነት ምክንያት፣ ሞት መውጊያ የለውም፣ ሲኦል ድል መንሻ የለውም።1ሰይጣን ዘላቂ ኃይል የለውም እናም እኛ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ ሕያው ተስፋ… የወለደን” ነን።2

በእውነትም፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በራሳች[ን] በዚህ ቃል [ለመጽናናት]” እንችላለን ያለው ትክክል ነበር።3

የእግዚአብሔር ፀጋ

ብዙውን ጊዜ ስለ አዳኝ የሃጢያት ክፍያ እንናገራለን እናም ይህን ማድረግ ትክክል ነው።

የያዕቆብ ቃላት እንደሚሉት“የእርሱን ፍጹም እውቀት ለማወቅና፣ የትንሳኤንና የሚመጣው ዓለም እውቀትን ለማግኘት የክርስቶስን የኃጥያት ክፍያ ለምን አትናገሩም?”4 ነገር ግን በሁሉመ አጋጣሚ “ስለክርስቶስ ስንናገር፣…በክርስቶስ ስንደሰት፣…ስለክርስቶስ ስንሰብክ እና ስለክርስቶስ ትንቢት ስንናገር”5፣ ለእግዚአብሔር ልጅ ዘላለማዊ መስዋዕትነት የክብር እና የምስጋና ስሜታችንን በፍፁም ማጣት የለብንም።

የአዳኝ የሃጢያት ክፍያ በትምህርታችን፣ በንግግራችን ወይም በልባችን ውስጥ ተራ መሆን አይችልም። ቅዱስ ነው፣ በዚህ “ታላቅ እና የመጨረሻ መስዋዕትነት” ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ “በስሙ ለሚያምኑ ደህንነትን” ያመጣው።6

እኛ ፍፁም ያልሆንን፣ ያልነፃን፣ ስህተት የምንሰራ እና በብዛት የማናመሰግን ብንሆንም የእግዚአብሔር ልጅ እኛን ለማዳን እራሱን ዝቅ ማድረጉን ሳስብ እደነቃለሁ። ውስን በሆነው አስተሳሰቤ የአዳኝን የሃጢያት ክፍያ ለመረዳት ሞክሬያለሁ እናም ያገኘሁት ብቸኛ መግለጫ እግዚአብሔር በጥልቅ፣ በፍፁም እና በዘለአለማዊ መንገድ እንደሚወደን ነው።“የክርስቶስን ፍቅር ሰፋቱና፣ ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቀቱም” ምን ያህል እንደሆነ ለመገመት እራሱ አልጀምርም።7

የዛ ፍቅር ኃይለኛ መገለጫ መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት የእግዚአብሔር ፀጋ ብለው የሚጠሩት፣አሁን ከሚሳሳትና ውስን ከሆነው ማንነታችን “በእውነት እና ሁሉንም ነገሮች በማወቅ [እስከምንከበር] ድረስ፣ [የእውነት እና የብርሀንን]” ክብር ሰዎች ወደምንሆንበት የምናድግበት መለኮታዊ እርዳታና የጥንካሬ ስጦታ ነው።8

ይህ የእግዚአብሔር ፀጋ በጣም ግሩም ነው። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በሰዎች በትክክል አልተረዳም።9 ይሁን እንጂ፣ በእርሱ ዘላለማዊ ቤተ-መንግስት ያዘጋጀልንን መውረስ ከፈለግን፣ ስለ እግዚአብሔር ፀጋ ማወቅ አለብን።

ስለሆነም ስለ ፀጋ መናገር እወዳለው። በተለይ በመጀመሪያ ፀጋ የሰማይን ደጃፎችእንዴት እንደሚከፍት እና በመቀጠል የሰማይን መስኮቶች እንዴት እንደሚከፍት።

አንደኛ፥ ፀጋ የሰማይን ደጃፎች ይከፍታል

ምክንያቱም ሁላችንም “ሃጢያትን ሰርተናልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎናል፣”10 እናም ምክንያቱም “ንፁ ያልሆነ ማንኛውም ነገር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ ስለማይችል”11 ወደ እግዚአብሔር መገኛለመመለስ ሁላችንም ብቁ አይደለንም።

ምንም እንኳን እግዚአብሔርን በሙሉ ነፍሳችን ብናገለግለውም፣ በቂ አይደለም፤ምክንያቱም “የማንጠቅም ባሪያዎች”12 ስለምንሆን። ወደ ሰማይ መሄጃ መንገድን ማግኘት አንችልም፤ በራሳችን የማሸነፍ ኃይሉ የሌለን የፍትህ ጥያቄ እንደ እንቅፋት ከፊታችን ይቆማል።

ነገር ግን ሁሉም አልጠፋም።

የእግዚአብሔር ፀጋ የእኛ ታላቅ እና ዘላለማዊ ተስፋ ነው።

በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት አማካኝነት የምህረት ዕቅድ የፍትህን ጥያቄ አሟልቷል፣13 “እንዲሁም ለሰዎች በንስሃ እምነት ይኖራቸው ዘንድ መፍትሄ [አምጥቷል]።”14

ሃጢያቶቻችን እንደ ደምም ቢቀሉ፣ እንደ ባዘቶ ይጠራሉ።15 ምክንያቱም አዳኛችን “ራሱን ለሁሉም ቤዛ ስለሰጠ፣”16 ወደ ዘላለማዊው መንግስቱ መግቢያ ለሁላችንም ተሰጥቶናል።17

ደጃፉ ተከፍቷል!

ነገር ግን የእግዚአብሔር ፀጋ ወደ ከዚ ቀደማችን ንፅህና ቦታችን አይመልሰንም። ደህንነት ስህተቶቻችንን እና ሃጢያቶቻችንን ማጥፋት ብቻ ማለት ከሆነ፣ ደህንነት ኃያል እንደመሆኑ በራሱ የአባትን ለእኛ ያለውን መሰረታዊ ግብ አያሳካም። አላማው ከፍተኛ ነው፥ ወንድና ሴት ልጆቹ እንደ እርሱ እንዲሆኑ ይፈልጋል።

ከእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ጋር የደቀመዝሙርነት መንገድ ወደ ላይ እንጂ ወደ ኋላ አይመራም።

መረዳት ወደማንችለው ከፍታ ይመራናል! በምንወዳቸው ሰዎች ተከብበን፣ “የእርሱን ሙላት እና ክብር”18 ወደምንቀበልበት ወደ ሰማይ አባታችን የሰለስቲያል መንግስት ክብር ይመራናል። ሁሉም ነገሮች የእኛ ይሆናሉ፣ እኛም የክርስቶስ እንሆናለን።19 በእርግጥም፣ አብ ያለው በሙሉ ለእኛ ይሰጠናል።20

ይህን ክብር ለመውረስ፣ ከተከፈተ ደጃፍ የበለጠ ያስፈልገናል፤ በዚህ ደጃፍ መግባት ያለብን በተቀየረ ልብ፣ እንዲሁም ቅያሬው አስገራሚ ሆኖ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ“በድጋሚ መወለድ፤ አዎን ከእግዚአብሔር በመወለድ፣ ከስጋዊና ከወደቅንበት ሁኔታ፣ ወደ ፃድቁ መንገድ በእግዚአብሔር በመፈወስ፣ የእርሱም ወንድና ሴት ልጆች የመሆን”21እንደሆነ በሚገልጹበት አይነት መቀየር ነው።21

ሁለተኛ፥ ፀጋ የሰማይን መስኮቶች ይከፍታል

የእግዚአብሔር ፀጋ ሌላኛው መሰረታዊ ነገር፣ እግዚአብሔር የኃይልና ጥንካሬ በረከቶችን የሚያፈስበት፣ የማንደርስባቸውን ነገሮች እንድናሳካ የሚረዳበት የሰማይ መስኮቶች መከፈት ነው። በእግዚአብሔር አስደናቂ ፀጋ ነው ልጆቹ የአታላዩን አደገኛና የተሰወሩ ፈተናዎችን ማሸነፍ የሚችሉት፣ ከሃጢያት በላይ የሚነሱት እና በክርስቶስ ፍፁም የሚሆኑት።22

ሁላችንም ድክመቶች ቢኖሩንም፣ ማሸነፍ እንችላለን። በእርግጥ፣ እራሳችንን ትሁት ካደረግን እና እምነት ካለን፣ ደካማ ነገሮቻችን ጠንካራ የሚሆኑልን በእግዚአብሔር ፀጋ ነው።23

በሕይወታችን ሙሉ የእግዚአብሔር ፀጋ ችሎታዎቻችንን የሚያጎላ እና ሕይወታችንን የሚባርክ ጊዜያዊ በረከቶችን እና መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይሰጠናል። ፀጋው ያጠራናል። ፀጋው የተሻለ እራሳችንን እንድንሆን ይረዳናል።

ማን ብቁ መሆን ይችላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የክርስቶስን ወደ ፈሪሳዊውስምኦንቤት ጉብኝት እናነባለን።

በውጪ ገፅታው፣ ስምኦን መልካም እና ፃደቅ ሰው ይመስላል። በተደጋጋሚ የኃይማኖት ግዴታውን ያከናውናል። ማለትም ህግን ጠብቋል፣ አስራቱነ ከፍሏለ፣ ሰንበትን ቀድሷል፣ ሁሌም ፀልይዋል እናም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዷል።

ነገር ግን ኢየሱስ ከስምኦን ጋር በነበረበት ጊዜ፣ አንዲት ሴት ቀረበች፣ የአዳኙን እግር በእንባዋ አጠበችው እናም እግሮቹን በመልካም ዘይት ቀባችው።

ይህቺ ሴት ሃጢያተኛ እንደሆነች ስለሚያውቅ ስምኦን በዚህ አይነት የአምልኮ ትዕይንት አልተደሰተም ነበር። ስምኦን ይህንን ኢየሱስ ካላወቀ ነብይ አይደለም፣ ባይሆን ኖሮ ሴቷ እንድትዳስሰው አይፈቅድላትም ነበር ብሎ አሰበ።

ሃሳቡን በመገንዘብ፣ ኢየሱስ ወደ ስምኦን ዞሮ ጥያቄ ጠየቀው። “አንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት”አለው። “በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ።

“የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማነኛው ነው?”

ስምኦን ብዙ የተተወለተ ሰው ነው ብሎ መለሰ።

ከዛ ኢየሱስ ኃይለኛ ትምህርት አስተማረ፤ “ይህችን ሴት ታያለህን… እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢያትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።”24

ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ብዙውን ጊዜ የትኛው ነን?

እንደ ስምኦን ነን? በራሳችን ፃድቅነት ተማምነን በመልካም ስራችን ደፋርና የተመቸን ነን? የእኛን ደረጃዎች ከማይጠብቁት ጋር ምናልባት ትንሽ ትዕግስተኛ አይደለንምን? ተግባራችን በልማድ እንዲመራ የምንፈቅድ፣ አንድን ነገር ሳናስብ የምናደርግ፣ ስብሰባዎቻችንን የምንካፈል፣ በወንጌል ትምህርት ክፍል የምናዛጋ እና በቅዱስ ቁርባን አገልግሎት ወቅት ስልካችንን የምንነካካ ነን?

ወይም በሃጢያት ምክንያት ሙሉ በሙሉ እና ተስፋ በማጣት መጥፋቷን እንዳሰበችው እንደዚህች አይነት ሴት ነን?

እጅግ እንወዳለን?

ለሰማይ አባታችን ያለንን እዳ እንረዳዋለን እናም በሙሉ ነፍሳችን ለእግዚአብሔር ፀጋ እንማፀናለን?

ለመፀለይ ስንንበረከክ፣ የሰራናቸውን የፅድቅ ስራዎች ለማስታወስ ወይም ስህተቶቻችንን ለመናዘዝ፣ የእግዚአብሔርን ምህረት ለመለመን እና ለድንቁ የቤዛነት ዕቅድ የምስጋና እንባ ለማፍሰስ ነውን?25

ደህንነት በታዛዥነት አማካኝነት ሊመጣ አይችልም፤ በእግዚአብሔር ልጅ ደም ነው የተገዛው።26 መልካም ስራችንን በደህንነት መለወጥ እንደምንችል ማሰቡ ልክ የአውሮፕላን ቲኬት ገዝተን አውሮፕላኑን የራሳችን እንዳደረግነው ማሰብ ማለት ነው። ወይም ለቤታችን የቤት ክራይ ከከፈልን በኋላ መላ የመሬትን ፕላኔት የራሳችን ማድረግ እንዳደረግን ማሰብ ማለት ነው።

ታዲያ ለምንድን ነው የምንታዘዘው?

ፀጋ የእግዚአብሔር ስጦታ ከሆነ፣ ታዲያ ለምንድን ነው ለእግዚአብሔር ትዕዛዛት መታዘዘ ጠቃሚ የሚሆነው? ከእግዚአብሔር ትዕዛዛት ጋር ለምን እንጨነቃለን-ወይም ያንን አስበን ለምንድን ነው ንስሃ የምንገባው? ታዲያ ለምንድን ነው ሃጢያተኞች እንደሆንን ተቀብለን እግዚአብሔር እንዲያድነን የማናደርገው?

ወይም ጥያቄውን በጳውሎስ ቃሎች ለማስቀመጥ፣ “ፀጋ እንዲበዛ በኃጢያት ፀንተን እንኑር?” የጳውሎስ መልስ ቀላል ነበር፥ “አይደለም።”27

ወንድሞች እና እህቶች ለእርሱ ባለን ፍቅር የተነሳ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንታዘዛለን!

በሙሉ ልባችንና አስተሳሰባችን የእግዚአብሔርን የፀጋ ስጦታ ለመረዳት መጣር የሰማይ አባታችንን በየዋህነትና በምስጋና እንድንወደውና እንድንታዘዘው የበለጠ ምክንያት ይሰጠናል። የደቀመዛሙርትነትን መንገድ ስንጓዝ፣ ያጠራናል፣ ያሻሽለናል፣ የበለጠ እንደ እርሱ እንድንሆን ይረዳናል እና ወደ እርሱ መገኛ ይመራናል።“የጌታ [የእግዚአብሔራችን] መንፈስ” የዚህን አይነት ለውጥ ያመጣል። “ታላቅ ለውጥ በልባችን….ከእንግዲህ ኃጢያት ለመፈፀም ምንም ፍላጎት የለንም፣ ነገር ግን ያለማቋረጥ መልካምን መስራት እንጂ።”28

ስለሆነም፣ ለእግዚአብሔር ትዕዛዛት የእኛ መታዘዝ፣ለእግዚአብሔር መልካምነትበማያልቀው የፍቅርና የምስጋና የተፈጥሮ ውጤት አማካኝነት ይመጣል። የዚህ አይነቱ እውነተኛ ፍቅርና ምስጋና ታዕምራት ባለው መልኩ ስራችንን ከእግዚአብሔር ፀጋ ጋር ያዋህደዋል። መልካምነት ያለማቋረጥ ሁሌም በሃሳባችን ውስጥ ይኖራል እናም ድፍረታችን በእግዚአብሔር ፊት ይጠነክራል።29

ውድ ወንድሞችና እህቶች፣ ወንጌልን በታማኝነት መኖር ቀንበር አይደለም። አስደሳች ተግባር--የዘላለምን ታላቅ ክብር የመውረስ ዝግጅት ነው። የሰማይ አባታችንን ለመታዘዝ እንሻለን ምክንያቱም መንፈሶቻችን ለመንፈሳዊ ነገሮች የበለጠ ምላሽ የሚሰጡ ይሆናሉና። ከዚህ በፊት የማናስባቸውን ነገሮች እንረዳለን። የአባትን ፈቃድ ስናደርግ ብሩህነት እና መረዳት ወደ እኛ ይመጣል።30

ፀጋ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እናም ለእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ትዕዛዞች የመታዘዝ ፍላጎታችን ይህን ቅዱስ ስጦታ እንደምንቀበል ለሰማይ አባታችን የምናሳውቅበት መንገድ ነው።

ማድረግ የምንችለው ሁሉ

ነብዩ ኔፊ የሚከተለውን ሲያውጅ ስለእግዚአብሔርን ፀጋ እንድንረዳው ጠቃሚ አስተዋፅኦ አበረከተ፥ “ልጆቻችንን እናም ደግሞ ወንድሞቻችንን ለማሳመን በትጋት እንፅፋለን፣ በክርስቶስ እንዲያምኑና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ የምንችለውን ካደረግን በኋላ፤ በፀጋው እንደዳንን አወቀናልና።31

ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ ጊዜ “የምንችለውን ካደረግን በኋላ” የሚለውን ሐረግ በተሳሳተ መንገድ እተረጉመው ይሆን ብዬ አስባለው። “በኋላ” የሚለው ቃል “ምክንያቱም” ከሚለው ጋር አንድ አይነት የትርጉም ፍቺ እንደሌለው መረዳት አለብን።

ማድረግ በምንችላቸው ነገሮች ሁሉ “ምክንያት” አንድንም። ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች በሙሉ ማንኛችንም አድርገናልን? ሁሉንም ሙከራዎች እስከምናሟጥጥ ድረስ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ በሚያድን ፀጋው ጣልቃ ለመግባት ይጠብቀናልን?

ብዙ ሰዎች በተደጋጋሚ ከእነሱ የሚጠበቀውን ማድረግ ባለመቻላቸው ምክንያት ተስፋ መቁረጥ ይሰማቸዋል። ከልምዳቸው “መንፈስ ተዘጋጅታለች ስጋ ግን ደካማ ነው”32 “ነፍሴም በክፋቴ ተነሳ ታዝናለች” በማለት ከኔፊ ጋር ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ያውጃሉ።33

የአዳኙ ፀጋ ሃጢያትን እንድናሸንፍ እንደሚፈቅድልንናእንደሚያስችለን ኔፊ እንዳወቀ እርግጠኛ ነኝ።34 ለዚህ ነው ኔፊ ልጆቹንና ወንድሞቹን “በክርስቶስ እንዲያምኑና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ” ለማሳመን ጠንክሮ የሰራው።35

መጨረሻ ላይ ያንን ነው ማድረግ የምንችለው! እናም በሟች ሕይወታችን ውስጥ ያ ነው ስራችን!

ፀጋ ለሁሉም ይገኛል

እስከዚያ የፋሲካ ጠዋት ድረስ አዳኙ ለእኛ ያደረገውን ነገር ሳስብ፣ ድምፄን ከፍ አድርጌ ለታላቁ ለእግዚአብሔር እና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ የምስጋና ጩኸቴን ማሰማት እፈልጋለው!

የሰማይ መዝጊያዎች ክፍት ናቸው!

የሰማይ መስኮቶች ክፍት ናቸው!

ዛሬና ለዘላለም የእግዚአብሔር ፀጋ ልባቸው ለተሰበረው እና መንፈሳቸው ለተዋረደው ሁሉ ይገኛል።36 ኢየሱስ ክርስቶስ ሟች ለሆነ አዕምሮዎች ለመረዳት ወደሚያዳግት ከፍታ ቦታዎች እንድንወጣ መንገዱን ንፁ አድርጎልናል።37

በአዲስ አይኖች እና ልብ የአዳኝን የሃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት ዘላለማዊ አስፈላጊነትን እንድናይ እፀልያለሁ። ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር እና ለእግዚአብሔር ዘላለማዊ የፀጋ ስጦት ትዕዛዛቱን በመጠበቅ እና በደስታ “በአዲስ ሕይወት በመመላለስ”38 ምስጋናችንን እንድናሳይ እፀልያለሁ ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በመምህራችን እና በቤዛችን ቅዱስ ስም፣ አሜን።