የዋህ እና በልብ ትሁት
የዋህነት የቤዛው ወሳኝ ባሕርይ ሲሆን የሚለየውም የጽድቅ መልስን በመስጠት፣ በፈቃደኝነት በመታዘዝ እና በጥንካሬ ራስን በመቆጣጠር ነው።
የቤተክርስቲያኗ መሪዎችን ለመደገፍ ስለነበረው ቅዱስ አጋጣሚ ደስ ብሎኛል፣ እንዲሁም ሽማግሌ ጎንግን እና ሽማግሌ ሶሬስን ወደ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን እንኳን ደህና መጣችሁ እላለሁ። የእነዚህ ታማኝ ሰዎች አገልግሎቶች በአለም ዙሪያ የሚገኙ ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን ይባርካሉ እናም አብሬያቸው ለማገልገል እና ከእነሱም ለመማር ጓጉቻለሁ።
ሁላችንም ለማንጸባረቅ መጣር ስላለብን ስለአዳኙ አምላካዊ ባህርይ1 ወሳኝ ገጽታ ስንማር መንፈስ ቅዱስ እንዲያስተምረን እና እንዲያበራልን እጸልያለሁ።
በኋላ በመልእክቴ ውስጥ የተወሰነውን ባህርይ ለይቼ ከማውጣቴ በፊት ይህንን የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን አቀርባለሁ። እባካችሁ እያንዳንዱን ምሳሌ በጥንቃቄ አድምጡና ለማነሳው ጥያቄ ሊሆኑ የሚችሉ መልሶችን ከእኔ ጋር አስቡ።
ምሳሌ #1። ወጣቱ ባለጠጋ እና አሙሌቅ
በአዲስ ኪዳን ውስጥ “ቸር መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ህይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ”2ብሎ ስለጠየቀ ወጣት ባለጠጋ እንማራለን። አዳኙ በመጀመሪያ ትእዛዛትን እንዲጠብቅ ምክር ሰጠው። በመቀጠልም መምህሩ በተለይ ለእሱ ፍላጎቶች እና ሁኔታዎች የሚሆን ተጨማሪ መስፈርት ሰጠው።
“ኢየሱስም ፍጹም ልትሆን ብትወድ፣ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፣ መዝገብም በሰማያት ታገኘኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ አለው።
“ጎበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ።”3
የወጣቱን ባለጸጋ ምላሽ በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ከሰፈረው የአሙሌቅ ተሞክሮ ጋር አነጻጽሩ። አሙሌቅ ብዙ ዘመዶች እና ጓደኞች4የነበሩት ታታሪ ሰራተኛ እና የበለፀገ ሰው ነበር። እራሱን ብዙ ጊዜ የተጠራ ሆኖም የሚሰማ ሰው እንዳልነበረ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ነገሮች የሚያውቅ ሆኖም አላውቅም የሚል እንደነበር ገልጿል።5 በመሰረቱ መልካም የሆነው ሰው አሙሌቅ ልክ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደተገለጸው ባለጠጋ ወጣት በአለም ጉዳዮች ትኩረቱ ተወስዶበት ነበር።
ምንም እንኳን ቀድሞ ልቡን አደንድኖ የነበረ ቢሆንም አሙሌቅ የመልዓኩን ድምጽ ታዘዘ፣ ነቢዩ አልማን በቤቱ ተቀበለ እንዲሁም ምግብ አቀረበለት። በአልማ ጉብኝት ወቅት በመንፈሳዊ እንዲነቃ ተደረገ እንዲሁም ወንጌልን እንዲሰብክ ተጠራ። ከዚያም አሙሌቅ “ሁሉንም ወርቅ፣ ብርና የከበሩ ነገሮችን ለእግዚአብሔር ቃል በመተው፣ በአንድ ወቅት ጓደኞቹ በነበሩት እናም በአባቱና በነገዱ ተወግዞ [ነበር]።”6
በባለጠጋው ወጣት እና በአሙሌቅ ምላሾች መካከል ያለው ልዩነት ምን ይገልጻል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ምሳሌ #2። ፓሆራን
በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ በተገለጸው አደገኛ ጦርነት ወቅት የኔፋውያን ሰራዊት ሻምበል በነበረው በሞሮኒ እና በምድሪቱ ዋና ዳኛ እና አስተዳዳሪ በነበረው በፓሆራን መካከል የመልእክቶች ልውውጥ ተደርጎ ነበር። ከመንግስት በቂ ድጋፍ ባለማግኘቱ ምክንያት ሰራዊቱ እየተሰቃየበት የነበረው ሞሮኒ “በወቀሳ መልክ“7 ከእርሱ ጋር ስለነበሩት መሪዎች ሃሳብ የለሽነት፣ ስንፍና፣ ችላ ባይነት አልፎ ተርፎም ክህደት በመክሰስ ለፓሆራን ጻፈለት።8
ፓሆራን በቀላሉ በሞሮኒ እና ትክክለኛ ባልሆነ ውንጀላው ተቀይሞ ሊሆን ይችል ነበር፣ ነገር ግን አላደረገውም። በርህራሄ እንዲሁም ሞሮኒ ያላወቀው የነበረውን በመንግስት ላይ የተነሳ አመፅ በመግለጽ ምላሽ ሰጠው። ከዚያም ፓሆራን እንዲህ አለ፦
“እነሆ፣ ሞሮኒ እልሀለሁኝ፣ በታላቁ ስቃይህ አልደሰትም፤ አዎን፣ ይህ ነፍሴን ያሳዝናታል።…
“እናም እንግዲህ በደብዳቤህ ላይ ወቅሰኸኛል፣ ነገር ግን ይህ ምንም አይደለም፣ እኔም አልተቆጣሁም ነገር ግን ከልብህ ታላቅነት ተደስቻለሁ።”9
ፓሆራን ለሞሮኒ ክሶች የሰጠው ጥንቃቄ የተሞላበት እና የታሰበበት ምላሽ ምን የሚገልጽ ይመስላችኋል?
ምሳሌ #3። ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እና ፕሬዘደንት ሔንሪ ቢ. አይሪንግ
ከስድስት ወራት በፊት በተካሄደው አጠቃላይ ጉባኤ፣ ፕሬዘዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ያሉትን እውነቶች እንዲያጠኑ፣ እንዲያሰላስሉ እና በተግባር እንዲያውሉ ከፕሬዚዳንት ቶማስ ኤስ.ሞንሰን ለቀረበላቸው ግብዣ የሰጡትን ምላሽ ገልጸዋል። እንዲህ ብለዋል “ምክሩን ለመከተል ጥረት አድርጊያለሁ። ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ፣ መፅሐፈ ሞርሞን ምን እንደ ሆነ፣ ምን እንደሚያረጋግጥ፣ ምንን ውድቅ እንደሚያደርግ፣ ምን እንደሚያሟላ፣ ምን እንደሚያብራራ እና ምን እንደሚገልጽዝርዝሮችን አውጥቻለሁ። መፅሐፈ ሞርሞንን በእነዚህ ማጉያ መነጽሮች አማካኝነት መመልከት ትክክለኛ እና ጥልቅ ግንዛቤን የሚሰጥ እንዲሁም አነቃቂ ተሞክሮ ነበር! እርሱን ለእያንዳንዳችሁ እመክራለሁ።”10
ፕሬዚዳንት ሄንሪ ቢ. አይሪንግም እንዲሁ የፕሬዚዳንት ሞንሰን ጥያቄ በህይወታቸው ውስጥ ስላለው አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህንን አስተውለዋል፦
“መጽሐፈ ሞርሞንን በየቀኑ ለ50 ዓመታት አንብቤአለሁ። ስለዚህ ምናልባት የፕሬዘዳንት ሞንሰን ቃላት ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ለሌሎች ሰዎች ናቸው ብዬ ላስብ እችል ነበር። ነገር ግን እንደ አብዛኞቻችሁ የነቢዩ ማበረታቻ እና ቃል-ኪዳን የበለጠ ጥረትን እንዳደርግ ሲጋብዘኝ ተሰምቶኛል። …
“ለእኔ እና ለብዙዎቻችሁ አስደሳቹ ውጤት ነቢዩ የገባው ቃል ኪዳን ነው።”11
እነዚህ ሁለት የጌታ ቤተክርስቲያን መሪዎች ለፕሬዚዳንት ሞንሰን ግብዣ የሰጡት ፈጣን እና ልባዊ ምላሾች ምን ይገልጻል ብላችሁ ታስባላችሁ?
በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑት የአሙሌቅ፣ የፓሆራን፣ የፕሬዚዳንት ኔልሰን እና የፕሬዚዳንት አይሪግ ምላሾች በአንድ የክርስቶስ ዓይነት ባህርይ ብቻ ተብራርተዋል የሚል ሀሳብ እያቀረብኩኝ አይደለም። በእርግጠኝነት ብዙ ተያያዥ ባህሪዎች እና ተሞክሮዎች በእነዚህ አራት ታማኝ አገልጋዮች ሕይወት ውስጥ ወደታየው መንፈሳዊ ብስለት መርተዋል። ሆኖም አዳኙ እና ነቢያቱ ሁላችንም የበለጠ በተሟላ ሁኔታ ልንረዳው እና በሕይወታችን ውስጥ ልናካትተው ጥረት ማድረግ ስለሚገባን አንድ አስፈላጊ ባህርይ አጉልተው አሳይተዋል።
የዋህነት
እባካችሁ በሚከተለው የቅዱሳን መጻህፍት ጥቅስ ውስጥ ጌታ ራሱን ለመግለጽ የተጠቀመበትን ባሕርይ አስተውሉ፦ “ቀንበሬንም በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ፦ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።”12
በሚያስተምር መልኩ አዳኙ ሊመርጣቸው ከሚችላቸው ባሕርያት እና በጎነቶች መካከል በየዋህነት ላይ አጽንኦት መስጠትን መርጧል።
ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በ1829 በተቀበለው ራእይ ውስጥም ተመሳሳይ ነገር በግልጽ ይታያል። ጌታ እንዲህ ብሏል፣ “ከእኔ ተማር፣ እናም ቃላቴን አድምጥ፤ በመንፈሴ በትህትና ተጓዝ፣ እናም በእኔ ሰላምን ታገኛለህ።”13
የዋህነት የቤዛው ወሳኝ ባሕርይ ሲሆን የሚለየውም የጽድቅ መልስን በመስጠት፣ በፈቃደኝነት በመታዘዝ እና በጥንካሬ ራስን በመቆጣጠር ነው። ይህ ባህርይ የአሙሌቅን፣ የፓሆራንን፣ የፕሬዚዳንት ኔልሰንን እና የፕሬዚዳንት አይሪንግን ምላሾች ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ለመገንዘብ ይረዳናል።
ለምሳሌ ፕሬዚዳንት ኔልሰን እና ፕሬዚዳንት አይሪንግ መፅሐፈ ሞርሞንን እንዲያነቡ እና እንዲያጠኑ ከፕሬዚዳንት ሞንሰን ለተሰጣቸው ማበረታቻ በጽድቅ እና በፍጥነት ምላሽ ሰጡ። ምንም እንኳን ሁለቱም ሰዎች አስፈላጊ በሆነ እና በሚታይ የቤተክርስቲያን የስራ መደቦች ላይ እያገለገሉ እና ለአስርተ ዓመታት ቅዱሳን መጻሕፍትን በስፋት እያጠኑ ያሉ ቢሆኑም፣ በምላሾቻቸው ምንም የማመንታት ወይም ሁሉን የማውቀው እኔ ነኝ የሚል ስሜት አላሳዩም።
አሙሌቅ በፈቃደኝነት ለእግዚአብሄር ፈቃድ ተገዝቷል፣ ወንጌልን ለመስበክ የቀረበውን ጥሪ ተቀብሏል እንዲሁም የተደላደለ ኑሮውን እና የታወቁ ዝምድናዎቹን ትቷል። እናም ፓሆራን በመንግስት ላይ በተነሳው አመፅ ስለተከሰቱት ተግዳሮቶች ለሞሮኒ ባብራራ ጊዜ በቁጣ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ በአመለካከት እና በጠንካራ ራስን መቆጣጠር ተባርኳል።
በወቅቱ የእኛ ዓለም ውስጥ ስለክርስቶስ ዓይነት የየዋህነት ባህርይ ያለው ግንዛቤ ብዙ ጊዜ የተሳሳተ ነው። የዋህነት ጥንካሬ እንጂ ድክመት አይደለም፣ ንቁ እንጂ ምላሽ የማይሰጥ አይደለም፣ ደፋር እንጂ ዓይናፋር አይደለም፣ ቁጥብ እንጂ ከመጠን በላይ የሚሄድ አይደለም፣ ልከኛ እንጂ ራስን ከፍ የሚያደርግ አይደለም፣ እንዲሁም ደግ እንጂ ከእኔ በላይ ላሳር የሚል አይደለም። የዋህ ሰው በቀላሉ አይበሳጭም፣ አያስመስልም፣ ወይም እብሪተኛ አይሆንም እንዲሁም የሌሎችን ስኬት በቀላሉ ይቀበላል።
ግን ትህትና ደግሞ በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍን እና ያለማቋረጥ የእርሱን መመሪያ እና ድጋፍ መፈለግን ሲያመለክት፣ የየዋህነት መለያ ባህርዩ ከመንፈስ ቅዱስም ሆነ አነስ ያለ ብቃት፣ ተሞክሮ ወይም ትምህርት ያላቸው ከሚመስሉ፣ አስፈላጊ ስራ ያልያዙ ሊሆኑ ከሚችሉ ወይም ምንም አስተዋጽዖ ማድረግ የሚችሉ ከማይመስሉ ሰዎች ለመማር ያለ የተለየ መንፈሳዊ ተቀባይነት ነው። በሶርያ የንጉስ ወታደሮች አለቃ የሆነው ንዕማን እንዴት ኩራቱን አሸንፎ በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ እንዲታጠብ በነቢዩ ኤልሳዕ የታዘዘውን እንዲያደርግ አገልጋዮቹ የሰጡትን ምክር በትህትና እንደተቀበለ አስታውሱ።14 የዋህነት ብዙውን ጊዜ ከታዋቂነት፣ ከኃላፊነት፣ ከስልጣን፣ ከሀብት እና ከመደነቅ ከሚመጣ የኩራት መታወር ዋነኛ መከላከያ ነው።
የዋህነት—የኢየሱስ አይነት ባህርይ እና መንፈሳዊ ስጦታ
የዋህነት በፍላጎት፣ የግብረገብ ምርጫን በጻድቅነት በመጠቀም፣ እንዲሁም የኃጢያታችንን ስርየት ለማግኘት ዘወትር በመትጋት የሚዳብር ባህርይ ነው።15 በትክክል ልንፈልገው የምንችለው መንፈሳዊ ስጦታም ነው።16 ሆኖም እንደዚህ አይነት በረከት የተሰጠበትን ዓላማዎች ማስታወስ አለብን፣ ይህም የእግዚአብሔርን ልጆች ለመጥቀም እና ለማገልገል ነው።
ወደ አዳኙ ስንመጣ እና ስንከተለው በሚያድግ ሁኔታ እና ደረጃ በደረጃ ይበልጥ እንደ እርሱ ለመሆን ንቁ እንሆናለን። በተስተካከለ የራስ ቁጥጥር እንዲሁም በታረቀ እና በረጋ ባህርይ በኩል መንፈሱ ኃይል ሰጥቶናል። ስለዚህ የዋህ ማለት እንደ የመምህሩ ደቀመዛሙርትነታችን የምንሆነው ነገር እንጂ እንዲሁ የምናደርገው ነገር ብቻ አይደለም።
“ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ።”18 ሆኖም “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።”19 እውቀቱ እና ብቃቱ ኩራተኛ ሊያደርገው ይችል ነበር። ከዚያ ይልቅ ተባርኮበት የነበረው የየዋህነት ባህርይ እና መንፈሳዊ ስጦታ በሕይወቱ ውስጥ እብሪትን አዳከመ እንዲሁም የእግዚአብሔርን አላማዎች ለመፈጸም ሙሴን መሳሪያ አድርጎ አጎላው።
መምህሩ እንደ የየዋህነት ምሳሌ
ታላላቅ እና ትርጉም ያላቸው የየዋህነት ምሳሌዎች በራሱ በአዳኙ ሕይወት ውስጥ ይገኛሉ።
“ከሁሉም ነገሮች በታች የወረደው”20 እና የተሰቃየው፣ የደማው እና “ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን” የሞተው21 በትህትና የደቀመዛሙርቱን በአቧራ የተሸፈነ እግር አጥቧል ።22 እንዲህ ዓይነቱ የዋህነት የጌታ የአገልጋይነት እና የመሪነት የመለያ ባሕርይ ነው።
ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ከፍተኛ ሥቃይ በደረሰበት ጊዜ የመጨረሻውን የጽድቅ ምላሽ እና በፈቃደኝነት የመገዛት ምሳሌ ሰጠ።
“ወደ ስፍራውም ደርሶ [ደቀመዛሙርቱን] እንዲህ አላቸው፣ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ።
“ተንበርክኮም …
“አባት ሆይ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር፡፡”23
በዚህ ለዘላለም አስፈላጊ በሆነው እና በአሰቃቂው ተሞክሮ፣ የአዳኙ የዋህነት የእግዚአብሔርን ጥበብ ከራሳችን ጥበብ በላይ የማስቀመጥን አስፈላጊነት ለእያንዳንዳችን ያሳያል።
የጌታ በፈቃደኝነት የመገዛት እና ጠንካራ ራስን የመቆጣጠር ወጥነት ለሁላችንም አድናቆትን የሚያጭርም አስተማሪም ነው። የታጠቁ የቤተመቅደስ ጠባቂዎች እና የሮማ ወታደሮች ኢየሱስን ለመያዝ እና ለማሰር ጌቴሴማኒ ሲደርሱ ጴጥሮስ ጎራዴውን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ቀኝ ጆሮ ቆረጠው።24 ከዚያም አዳኙ የአገልጋዩን ጆሮ ዳሰሰ እና ፈወሳው።25 እባካችሁ ከመያዝ እና ከመሰቀል ሊያድነው ይችል የነበረውን ያንኑ ሰማያዊ ሃይል ተጠቅሞ እጁን ዘርግቶ ሊይዘው የሚችለውን እንደባረከው ልብ በሉ።
እንዲሁም ይሰቀል ዘንድ መምህሩ እንዴት በጲላጦስ ፊት እንደተከሰሰ እና እንደተፈረደበት አስቡ።26 ኢየሱስ ተላልፎ በተሰጠበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?”27 ሆኖም “ለህያዋን እና ለሙታን ዘላለማዊ ዳኛ”28 የሆነው በተገላቢጦሽ በጊዜያዊ የፖለቲካ ተሿሚ ፊት ተፈረደበት። “ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ [ኢየሱስ] አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።”29 የአዳኙ የዋህነት በስነምግባር በተሞላ ምላሹ፣ በጠንካራ ራስን መቆጣጠሩ እና ማለቂያ የሌለውን ኃይሉን ለግል ጥቅም ለማሳየት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ታይቷል።
የተስፋ ቃል እና ምስክርነት
የዋህነት ሁሉም መንፈሳዊ አቅሞች እና ስጦታዎች የሚመነጩበት መሠረት እንደሆነ ሞርሞን ለይቶ አስቀምጧል።
“ስለሆነም፣ አንድ ሰው እምነት ካለው ተስፋ ሊኖረው ይገባል፤ ያለ እምነት ምንም ዓይነት ተስፋ ሊኖር አይችልምና።
“እናም በድጋሚ፣ እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ የዋህ እና በልቡ የሚራራ ካልሆነ በስተቀር እምነት እና ተስፋ ሊኖረው አይችልም።
“ከሆነ ግን እምነቱ እና ተስፋው ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም በልቡ የሚራራ እናም የዋህ ካልሆነ በጌታ ፊት ተቀባይነት አይኖረውምና፤ እናም ሰው የዋህ እናም በልቡ የሚራራ፣ እናም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ከሆነ እርሱ ልግስና ሊኖረው ይገባዋል፤ ልግስና ግን ከሌለው እርሱ ከንቱ ነውና፤ ስለሆነም ልግስና ሊኖረው ይገባል።”30
አዳኙ “የዋሆች ብፁአን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና።”ሲል ተናግሯል።31 የዋህነት የመለኮታዊ ባህርይ አስፈላጊ ገጽታ ነው እናም በአዳኝ የኃጢያት ክፍያ ምክንያት እና በእርሱም አማካኝነት በሕይወታችን ውስጥ ሊከሰት እና ሊዳብር ይችላል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የተነሳ እና ህያው ቤዛችን እንደሆነ እመሰክራለሁ። እንዲሁም በየዋህ መንፈስ ስንሄድ እንደሚመራን፣ እንደሚጠብቀን እና እንደሚያጠነክረን ቃል እገባለሁ። የእነዚህን የተረጋገጡ እውነቶች እና ተስፋዎች ምስክርነቶቼን የምናገረው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው አሜን።