እንዲያዩ ዘንድ
ሌሎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወስደውን መንገድ እንዲያዩ ብርሃናችሁ እንዲበራ ለማድረግ እድሎችን ፈልጉ እናም ጸልዩ።
ወንድሞች እና እህቶች፣ በዚህ ስብሰባ በተሰማን መንፈስ ልባችን ተባርኳል እናም ታድሷል፡፡
ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የብርሃን አምድ በአንድ ወጣት ላይ በጫካ ውስጥ አረፈ፡፡ በዚያ ብርሃን ውስጥ፣ ዮሴፍ ስሚዝ እግዚአብሔር አብን እና ልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ተመለከተ። ብርሃናቸውም ምድርን ከሸፈነው መንፈሳዊ ጨለማ ገፎ ለዮሴፍ ስሚዝ እና ለሁላችንም ወደፊት የሚያሳየውን መንገድ አመለከተ። በዚያን ቀን በተገለጠው ብርሃን ምክንያት በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል የሚገኘውን የሙሉነት በረከቶችን መቀበል እንችላለን።
በወንጌሉ ዳግም የመመለስ ጸጋ፣ በአዳኛችን ብርሃን ልንሞላ እንችላለን። ሆኖም፣ ያ ብርሃን ለእናንተ እና ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡ “መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ እንዱሁም በሰዎች ፊት ብርሃናችሁ እንዲያበራ” ኢየሱስ ክርስቶስ ጠርቶናል፡፡1 “እንዲያዩ ዘንድ ” የሚለውን ሐረግ እወደዋለሁ፡፡ ሌሎች መንገዱን እንዲመለከቱ እና ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ ለመርዳት ከጌታ ዘንድ የመጣ የልባዊ ፍላጎት ጥሪ ነው።
የ10 ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ በትውልድ ከተማዬ በነበራቸው ሃላፊነት ምክንያት ቤተሰባቸን የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ጉባዬ አባል የነበሩት ሽማግሌ ኤል. ቶም ፔሪን የማስተናገድ ክብር ነበረን።
በቀኑ መገባደጃ ላይ ቤተሰባችን እና ከፔሪ ቤተሰብ ጋር የእናቴን ጣፋጭ የፖም ኬክ ለመብላት በሳሎን ውስጥ ተቀመጥን፣ ሽማግሌ ፔሪም በዓለም ዙሪያ ስለሚገኙት ቅዱሳን ታሪኮች ነገሩን፡፡ በጣም ተደስቼ ነበር፡፡
እናቴ ወደ ኩሽና ጠርታኝ “ቦኒ ፣ ዶሮዎቹን መገብሽ?” ብላ ቀላል ጥያቄ ስትጠይቀኝ እየመሸ ነበር።
ልቤ ወደቀ፤ አልመገብኳቸውም፡፡ የጌታን ሐዋርያ ትቼ መሄድ ስላልፈለኩኝ ዶሮዎቹ እስከ ጠዋት ድረስ ሊጾሙ እንደሚችሉ ሀሳብ አቀረብኩኝ፡፡
እናቴ “አይሆንም” ብላ በእርግጠኝነት መለሰችልኝ፡፡ በዚህን ጊዜ፣ ሽማግሌ ፔሪ ወደ ኩሽና ገቡና በጓጓ ድምጻቸው “አንድ ሰው ዶሮዎቹን መመገብ እንዳለበት ሰማሁ?” ብለው ጠየቁ። “እኔና ልጄ አብረን መቀላቀል እንችላለን?”
ኦህ፣ አሁን ዶሮዎቹን መመገብ እንዴት ያለ ፍጹም ደስታ ሆነ! ትልቁን ቢጫ ባትሪ መብራት ለማምጣት ሮጥኩ፡፡ በደስታ ሙላት፣ ያረጀውን ወደ ዶሮ ቤት የሚወስደውን መንገድ በመዝለል መራሁ። የባትሪ መብራቱን በእጄ በማወዝወዝ የበቆሎ ማሳውን ተሻግረን በስንዴ ማሳው ውስጥ አለፍን፡፡
መንገዱን አቋርጦ የሚያልፈውን አነስተኛ የመስኖ ጉድጓድ ስደርስ፣ ከዚህ በፊት ብዙ ምሽቶች እንዳደረኩት በደመ ነፍስ ዘለልኩት። ሽማግሌ ፔሪ በጨለማ ባልታወቀ መንገድ ላይ ለመከተል ያደረጉትን ጥረት አልተገነዘብኩም። የሚደንሰው የእጄ መብራት ጉድጓዱን እንዲያዩት አልረዳቸውም። ለማየት ቀጥተኛ ብርሃን ባለመኖሩ በቀጥታ ውሃው ውስጥ ገቡና ከፍ ያለ የማቃሰት ድምጽ አሰሙ፡፡ በድንጋጤ፣ አዲሱ ጓደኛዬ እርጥብ እግራቸውን ከጉድጓዱ አውጥተው ውሃውን ከሚከብደው ከቆዳ ጫማቸው ሲያርገፈግፉ አየሁ፡፡
በውሃ በራሰው እና በሚያሟልጨው ጫማቸው፣ ሽማግሌ ፔሪ ዶሮዎቹን ለመመገብ ረድተውኛል። በጨረስን ጊዜ በፍቅር በተሞላ ንግግር፣ “ቦኒ፣ መንገዱን ማየት አለብኝ። በምራመድበት ቦታ ላይ እንዲያበራ መብራቱን እፈልጋለሁ፡፡”
መብራቴን እያበራሁ ነበር ነገር ግን ሽማግሌ ፔሪን በሚረዳ መንገድ አልነበረም። አሁን መንገዱን በደህና ለማየት ብርሃኔ እንደሚያስፈልጋቸው በማወቅ፣ ከእግራቸው ፊት ለፊት ብርሃኑ እንዲያበራ አተኩሬ ነበር እናም በልበ ሙሉነት ወደ ቤት መመለስ ችለናል፡፡
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ለበርካታ ዓመታት ከሽማግሌ ፔሪ የተማርኩትን መሰረታዊ መርህ አሰላሰልኲኝ። በዘፈቀደ የብርሃን ጨረሮችን በመወዝወዝ ዓለምን በአጠቃላይ ብሩህ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ጌታ ብርሃናችንን እንድናበራ ይጋብዘናል፡፡ ሌሎች ወደ ክርስቶስ የሚወስደውን መንገድ እንዲያዩ ያንን ብርሃናችንን ስለማተኮር ነው። እስራኤልን በመጋረጃው በዚህ ጎን መሰብሰብ ነው—ሌሎች ቅዱስ-ቃል-ኪዳኖችን ከእግዚአብሄር ጋር በመግባት እና በመጠበቅ ረገድ ቀጣዩን ደረጃ እንዲመለከቱ መርዳት ነው።2
አዳኝም እንደመሰከረው፣ “እነሆ እኔ ብርሃን ነኝ፤ ምሳሌም ትቼላችኋለሁ።”3 ከሱ ምሳሌዎች ውስጥ አንዱን እንመልከት፡፡
በጉድጓዱ አቅራቢያ የነበረችው ሴት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላወቀች እና በራሷ ማህበረሰብ ውስጥ በብዙዎች የተጣለች ሳምራዊ ሴት ነበረች። ኢየሱስ አገኛት እና ንግግር ጀመረ፡፡ ስለ ውሃ አናገራት፡፡ እርሱ እራሱ “የሕይወት ውሃ” መሆኑን ሲገልፅ ወደ የበለጠ ብርሃን መራት።4
ክርስቶስ ስለእርሷ እና ስለፍላጎቷ በርህራሄ ያውቅ ነበር። ሴትየዋ ባለችበት ተገናኛት እናም ስለምታውቀው እና ስለተለመደ ነገር ያነጋግራት ጀመረ። እሱ በዚያ ቢያቆም ኖሮ መልካም አጋጣሚ ነበር። ነገር ግን ወደ ከተማዋ በመሄድ “መታችሁ እዩ … ይህስ ክርስቶስ አይደለምን?” ብላ ለማወጅ ውጤት አታመጣም ነበር፡፡5 ቀስ በቀስ በውይይቱ ውስጥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን አገኘች፣ እናም ያለፈ ታሪኳ ምንም ቢሆን፣ ሌሎች መንገዱን እንዲያዩ የሚያበራ የብርሃን መሳሪያ ሆነች።6
አሁን ብርሃንን በማጋራት የአዳኝን ምሳሌን የተከተሉትን ሁለት ሰዎችን እንመልከት፡፡ በቅርብ ጊዜ ጓደኛዬ ኬቭን ለእራት ከአንድ የንግድ ሥራ አስፈፃሚ ጎን ተቀምጦ ነበር፡፡ ለሁለት ሰዓታት ያህል ምን ማውራት እንዳለበት ተጨነቀ፡፡ ኬቪን ምሪትን ተከትሎ እንዲህ ብሎ ጠየቀ “ስለ ቤተሰብህ ንገረኝ፡፡ የመጡት ከየት ነው? ”
ሰውየው ስለ ሃረጉ ብዙም አያውቅም፣ ኬቭን ስልኩን አውጥቶ እንዲህ አለ፣ “ሰዎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያገናኝ አፕሊኬሽን አለኝ፡፡ ማግኘት የምንችለውን እንመልከት፡፡”
ከረጅም ውይይት በኋላ፣ የኬቭን አዲሱ ጓደኛ፣ “ቤተሰብ ለቤተ-ክርስቲያንህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?” ብሎ ጠየቀ።
ኬቭን በቀላሉ መለሰ፣ “ከሞትን በኋላ በሕይወት መኖራችንን እንደምንቀጥል እናምናለን፡፡ ቅድመ አያቶቻችንን ለይተን ካወቅን እና ስማቸውን ወደ ቤተመቅደስ ተብሎ ወደሚጠራው ቅዱስ ስፍራ የምንወስድ ከሆነ፣ ከሞቱ በኋላ እንኳን ቤተሰባችንን አንድ የሚያደርጋቸውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ማከናወን እንችላለን።”7
ኬቭን የጀመረው እሱ እና አዲሱ ጓደኛው በጋራ ስላላቸው ነገር ነበር፡፡ ከዛ የአዳኙን ብርሀን እና ፍቅር የሚመሠክርበትን መንገድ አገኘ።
ሁለተኛው ታሪክ፣ የኮሌጅ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ስለሆነችው ኤላ ነው፡፡ የእሷ ምሳሌ የጀመረው የሚስዮን ጥሪዋን በትምህርት ቤት ሳለች የተቀበለች ጊዜ ነው፡፡ የአገልግሎት ጥሪዋን በቡድንዋ ፊት ለመክፈት መረጠች፡፡ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ምንም አያውቁም እናም ኤላ ለማገልገል ስላላት ፍላጎት አልገባቸውም። የቡድን አባሎችዋ መንፈስን በሚሰማቸው መልኩ እንዴት የአገልግሎት ጥሪዋን ለነሱ መግለጽ እንዳለባት ለማወቅ ደጋግማ ጸለየች፡፡ መልሷስ?
“ፓወር ፖይንት አዘጋጀሁ፣ ምክንያቱም ያን ያህል ጎበዝ ነኝ።” አለች ኤላ። ከ 400 በላይ ከሚሆኑ ተልእኮዎች በአንዱ ውስጥ ስለማገልገል እና ምናልባትም ቋንቋን ስለ መማር እድል ነገረቻቸው፡፡ እርሷም እያገለገሉ ያሉትን በሺዎች ስለሚቆጠሩ ሚስዮናውያን ጎላ አድርጋ ገለጸች፡፡ ኤላ በአዳኝ ምስል እና በዚህ አጭር ምስክርነት አበቃች፤ “ቅርጫት ኳስ በሕይወቴ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮችች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አገሪቷን አቋርጬ ለዚህ አሰልጣኝ እና ከዚህ ቡድን ጋር ለመጫወት ቤተሰቦቼን ተውኩ፡፡ ከቅርጫት ኳስ የበለጠ ለእኔ አስፈላጊ የሆኑት ሁለት ነገሮች እምነቴ እና ቤተሰቤ ናቸው፡፡ ”8
አሁን፣ “እነዚህ ታላላቅ የ 1000 ዋት ምሳሌዎች ናቸው፣ ግን እኔ ባለ 20 ዋት አምፖል ነኝ፣” ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ አዳኙ እንዲህ ሲል እንደመሰከረ አስታውሱ፣ “እናንተ የምትይዙት ብርሃን ነኝ”9 ሌሎችን ወደ እርሱ የምንጠቁም ከሆነ እሱ ብርሃንን እንደሚያመጣ ያስታውሰናል፡፡
እኔ እና እናንተ አሁኑኑየምናጋራው በቂ ብርሃን አለን። አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲቀርብ የሚረዳውን ቀጣይ እርምጃ ማብራት እንችላለን፣ እና ከዚያ ቀጣዩን እርምጃ እናም ቀጣዩን።
እራሳችሁን ጠይቁ፣ “እነሱ የሚፈልጉትን መንገድ ለማግኘት እናንተ ያላችሁን ብርሃን የሚሹ ማን ናቸው?”
ውድ ጓደኞቼ፣ ብርሃናችን ማንጸባረቅ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ጌታም እንዲህ ሲል ነግሮናል፣ “እና የት እንደሚያገኙትም ባለማወቃቸው ምክንያት እውነትን እንዳያገኙ የተደረጉ ብዙዎችም በምድር ላይ አሉ፡፡”10 ማገዝ እንችላለን። ሌሎች እንዲያዩት ሆን ብለን ብርሃናችንን ማብራት እንችላለን። ግብዣ መስጠት እንችላለን።11 ምንም ያህል የሚገታ ቢሆንም፣ ወደ አዳኝ ለመሄድ አንድ ደረጃን ከሚወስዱ ሰዎች ጋር መጓዝ እንችላለን። እስራኤልን መሰብሰብ እንችላለን፡፡
ጌታ እያንዳንዱን ትንሽ ጥረት እንደሚያጎላ እመሰክራለሁ። መንፈስ ቅዱስ ምን ማለት እና ማድረግ እንዳለብን እንድናውቅ ያደርገናል። እንደዚህ ያሉት ሙከራዎች ከምቾት ቦታችን እንድንወጣ ይጠይቅን ይሆናል፣ ግን ጌታ ብርሃናችን እንዲበራ እንደሚረዳን እርግጠኛ መሆን እንችላለን፡፡
ይህን ቤተክርስቲያን በራዕይ መምራት ለሚቀጥለው የአዳኝ ብርሃን ምን ያህል አመስጋኝ ነኝ።
ሁላችንም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እንድንከተል እና በዙሪያችን ያሉትን በርህራሄ እንድንገነዘብ እጋብዛለሁ። ሌሎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን መንገድ እንዲያዩ ብርሃናችሁ እንዲበራ ለማድረግ እድሎችን ፈልጉ እናም ጸልዩ። ቃል ኪዳኑም ታላቅ ነው “የሚከተለኝ በጨለማ አይመላለስም የሕይወትን ብርሃን ያገኛል እንጂ፡፡”12 አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአለም መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት፣ ብርሃን እና ፍቅር መሆኑን እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።