አጠቃላይ ጉባኤ
ከሕይወት ማዕበሎች መሸሸጊያ መፈለግ
የሚያዝያ 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ።


2:3

ከሕይወት ማዕበሎች መሸሸጊያ መፈለግ

ህይወታችንን የሚያጠቁ ማዕበሎች ቢኖሩም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እና የኃጢያት ክፍያው ሁላችንም የምንፈልገው መጠጊያ ናቸው።

በዘጠናዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ፣ በኮሌጅ በነበርኩበት ወቅት፣ በቺሊ ውስጥ የሳንቲያጎ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል አራተኛ ኩባንያ አባል ነበርኩ። እዚያ እያገለገልኩ እንደ የሌሊት ጠባቂ አካል በመሆን በእሳት ጣቢያው ውስጥ እኖር ነበር፡፡ ወደ ዓመቱ መገባደጃ ላይ፣ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የእሳት ጣቢያው ውስጥ መገኘት እንዳለብኝ ተነግሮኝ ነበር ምክንያቱም በዚያ ቀን ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ድንገተኛ አደጋ ይከሰት ነበር፡፡ በመደነቅ፣ “በእውነት?” ብዬ መለስኩ

እንግዲህ፣ እኩለ ሌሊት ላይ ርችቶች ሳንቲያጎ ከተማ ውስጥ መተኮስ ሲጀምሩ አብረውኝ ካሉ ጓደኞቼ ጋር እንደጠበቅኩ አስታውሳለሁ፡፡ ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞቶችን በመለዋወጥ እርስ በእርስ መተቃቀፍ ጀመርን። በድንገት በእሳት አደጋ ጣቢያው ውስጥ ደውሎች መጮህ ጀመሩ፣ ይህም ድንገተኛ አደጋ እንዳለ ያሳያል፡፡ መሳሪያችንን ይዘን እሳት ማጥፊያ መኪናው ላይ ወጣን፡፡ ወደ ድንገተኛ አደጋ ቦታ ስንሄድ፣ አዲሱን ዓመት የሚያከበሩ ብዙ ሰዎችን ስናልፍ፣ እነሱ ያልተጨነቁ እና ግድ ያልነበራቸው መሆናቸውን አስተዋልኩ፡፡ እነሱ ዘና በማለት በሞቃታማው የበጋ ምሽት ይደሰቱ ነበር። ሆኖም፣ በአቅራቢያው ባለ ስፍራ በችግር ውስጥ ያሉትን ለመርዳት የምንሄድላቸው ሰዎች በአስከፊ ችግር ውስጥ ነበሩ።

ምንም እንኳን ህይወታችን አንዳንድ ጊዜ በአንፃራዊነት የረጋ ሊሆን ቢችልም፣ ችግሮችን የመቋቋም አቅማችንን የሚገፉ ያልተጠበቁ ፈተናዎች እና ማዕበሎች የሚያጋጥሙን ጊዜ በእያንዳንዳችን ላይ እንደሚመጣ ይህ ተሞክሮ እንድገነዘብ ረዳኝ። አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ቤተሰብ እና የሥራ ፈታኝ ሁኔታዎች ፣የተፈጥሮ አደጋዎች እና ሌሎች የህይወት ወይም የሞት ጉዳዮች በዚህ ህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ማእበሎች ምሳሌዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

እነዚህ ማእበሎች ሲያጋጥሙን ብዙውን ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ወይም ፍርሃት ይሰማናል። ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳሉት፣ “እምነት የፍርሀት መድሃኒት ነው”—በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት (“እምነታችሁ ያሳይ፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2014(እ.ኤ.አ፣ 29) የሰዎችን ሕይወት የሚነኩትን ማእበሎች ስመለከት፣ የትኛውም ዓይነት ማዕበል እኛን ቢመታንም፣ መፍትሄ ቢኖረውም ይሁን መጨረሻው በእይታ ውስጥ ቢሆን፣ አንድ መጠለያ ብቻ እንዳለ እና ይህም ለሁሉም ማዕበሎች ተመሳሳይ እንደሆነ መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ። በሰማያዊ አባታችን የተሰጠው ይህ ብቸኛ መጠጊያችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና የኃጢያት ክፍያው ነው።

ማናችንም ብንሆን እነዚህን ማዕበሎች ከመጋፈጥ ነፃ አይደለንም። የመጽሃፈ ሞርሞን ነቢይ ሔለማን እንደዚህ አስተማረ፣ “አስታውሱ፣ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በክርስቶስ፣ አዳኝ በሆነው በአለቱ መሰረታችሁን መገንባት እንዳለባችሁ፤ ዲያብሎስ ኃይሉን፣ ንፋሱን፣ አዎን፣ በአውሎ ነፋስ እንደሚወረወረው ዘንጉን በላከ ጊዜ፤ አዎን ትክክለኛ መሰረት በሆነው ሰዎች ከገነቡበት ሊወድቁበት በማይችሉበት አለት ላይ ስለገነባችሁ በረዶው፣ እናም ኃይለኛው ውሽንፍር በሚመታችሁ ጊዜ እናንተን ወደ ስቃይና መጨረሻ ወደሌለው ባህረ ሰላጤ ጎትቶ ለመጣል ኃይል አይኖረውም” (ሔለማን 5፥12)።

መከራን በመቋቋም የራሳቸው ተሞክሮ የነበራቸው ሽማግሌ ሮበርት ዲ. ሄልስ እንዳሉት፣ “መከራ ዓለም አቀፋዊ ነው፤ እንዴት ለመከራ ምላሽ እንደምንሰጥ ግን ግላዊ ነው። መከራ ከሁለቱ መንገዶች በአንዱ ሊወስደን ይችላል፡፡ ከእምነት ጋር ከተጣመረ ማጠናከሪያ እና የመንፃት ተሞክሮ ሊሆን ይችላል፣ ወይም በጌታ የኃጢያት ክፍያ እምነት የሌለን ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ አጥፊ ኃይል ሊሆን ይችላል (“ሀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል፣” ኤንዛይን፣ ህዳር 1983(እ.ኤ.አ)፣ 66)።

ኢየሱስ ክርስቶስ እና የኃጢያት ክፍያው የሚሰጡትን መሸሸጊያ ለመጠቀም እንድንችል፣ ውስን እና በምድራዊ እይታ ውስጥ ያሉትን ህመሞች እንድናሸንፍ የሚያስችለንን እምነት በእርሱ ሊኖረን ይገባል። በምንሠራው ሁሉ ወደ እርሱ የምንመጣ ከሆነ ሸክማችንን ቀላል እንደሚያደርግልን ቃል ገብቷል፡፡

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” አለ።

ቀንበሬንም በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።

“ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴዎስ 11፥28–30፣ ይህንንም ተመልከቱ ሞዛያ 24፥14–15)።

እንደተባለው “እምነት ላለው ሰው፣ ምንም ማብራሪያ አያስፈልግም፡፡ እምነት ለሌለው ሰው ግን ምንም ማብራሪያ አይሰራም።” (ይህ መግለጫ በቶማስ አኳይናስ ላይ የተመሠረተ ነው፣ ግን እሱ ካስተማራቸው በቀላል አገላለጽ የተጨመቀ ነው፡፡) ሆኖም፣ እዚህ ምድር ላይ ስለሚከሰቱት ነገሮች ውስን ግንዛቤ አለን፣ እናም ብዙውን ጊዜ ለምንስለሚለው ጥያቄ መልስ የለንም። ይህ ለምን ተከሰተ? ይህ ለምን እኔላይ ተከሰተ? ምን መማር አለብኝ? መልሶች ሲሸሹን፣ በዚያን ጊዜ ነው አዳኛችን ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ የተናገራቸው ቃላት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚሆኑበት፤

“ልጄ፣ ለነፍስህ ሰላም ይኑርህ፤ ጭንቀትህ እና ስቃይህ ለጥቂት ጊዜ ቢሆን ነው፤

“ከዚያም፣ በመልካም ይህን ከጸናህ፣ እግዚአብሔርም ወደ ላይ ከፍ ያደርግሀል” (ት. እና ቃ. 121፥7–8)።

ምንም እንኳን ብዙ ሰዎች በእውነት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ቢሆንም፣ ዋናው ጥያቄ እሱን እናምናለን እንዲሁም የሚያስተምረንን እና እንድናደርግ የሚጠይቀንን እናምናለን ። ምናልባት አንድ ሰው ይህንን ሊጠይቅ ይችላል፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ በእኔ ላይ ስለሚደርሰው ነገር ምን ያውቃል? ደስተኛ እንድሆን የሚያስፈልገኝን ነገር እንዴት ያውቃል?” በእውነት ቤዛችን እና አማላጃችን ነው፣ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት የተናገረለት፤

በሰዎች የተናቀና የተጠላ ነው፤ ሀዘንን እና ህማምን የሚያውቅ ሰው ነው። …

በእውነት ስቃያችንን ተቀበለ፤ እናም ሀዘናችንን ተሸከመ። …

“ነገር ግን ስለመተላለፋችን እርሱ ቆሰለ፤ ስለበደላችንም ደቀቀ፤ የሰላማችን ተግሳፅ በእርሱ ላይ ነበር፤ እናም በቁስሉ ተፈወስን” (ኢሳያስ 53፥3–5)።

ሐዋሪያው ጴጥሮስም ስለ አዳኙ እንዲህ በማለት አስተምሮናል፣ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፣ በገዛ በስጋው ሃጢያታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፣ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ።”(1 ጴጥሮስ 2፥24)።

የጴጥሮስ የሞቱ ቀናት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ቃላቶቹ በፍርሃትና በአሉታዊ ስሜት አልተሞሉም፣ ይልቁንም ቅዱሳንን “በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆኑም” “እንዲደሰቱ” አስተምሯቸዋል፡፡ “የእምነታችን ፈተና፣ በእሳት ቢፈተንም” “ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ“ ለምስጋና እና ለክብር እና ለውዳሴ” እና “ለነፍሳችን ደህንነት መዳን” እንድናስብ ጴጥሮስ መክሮናል። ”(1 ጴጥሮስ 1፥6–7፣ 9)።

ጴጥሮስም ቀጠለ፤

“ወዳጆች ሆይ፣ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ፤

“ነገር ግን የክርስቶስን መከራዎች ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ፤ በብዙ ክብርም በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ በታላቅ ደስታ ትደሰታላችሁ” (1 ጴትሮስ 4፥12–13)።

ፕሬዘደንት ራስል ኤም ኔልሰን እንዳስተማሩት “ቅዱሳን በማንኛውም ሁኔታ መደሰት ይችላሉ።… የህይወታችን ትኩረት በእግዚያብሄር የደህንነት እቅድ …እና በኢየሱስ ክርስቶስና በወንጌሉ ላይ ሲሆን፣ በህይወታችን ከተከሰተውም ወይም—ካልተከሰተውም—ሁኔታ ባሻገር ደስታ ሊሰማን ይችላል። ደስታ ከሱና በሱ ምክንያት ይመጣል። የደስታ ሁሉ ምንጭ እሱ ነው” (“ደስታ እና መንፈሳዊ መዳን፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 82)።

በእርግጥ በማእበሉ ውስጥ ሳንሆን እነዚህን ነገሮች መናገር ይቀላል፣ በማዕበል ውስጥ ሆነን ከመኖር እና ከመተግበር ይልቅ። ነገር ግን ወንድማችሁ እንደመሆኔ፣ ህይወታችንን የሚታገሉት ማዕበሎች ምንም ይሁኑ ምን ኢየሱስ ክርስቶስ እና የኃጢያት ክፍያው ሁላችንም የምንፈልገው መሸሸጊያ መሆናቸውን ማወቁ ምን ያህል ዋጋ ያለው እንደሆነ ላጋራችሁ በቅንነት መፈለጌን እንደሚሰማችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን፣ እሱ እንደሚወደን እና ብቻችንን እንዳልሆንን አውቃለሁ። ሸክማችሁን ለማቃለል እና የምትፈልጉትን መሸሸጊያ ሊሆን እንደሚችል እንድትመጡ እና እንድትመለከቱ እጋብዛችኋለሁ። ሌሎች የሚፈልጉትን መሸሸጊያ ያገኙ ዘንድ ለመርዳት ኑ፡፡ የህይወት ማዕበል ለመቋቋም በሚረዳችሁ በዚህ መሸሸጊያ ውስጥ ኑ እና አብራችሁን ኑሩ፡፡ ከመጣችሁ፣ እንደምታዩ፣ እንደምትረዱ እንዲሁም እንደምትኖሩ በልቤ ውስጥ ምንም ጥርጥር የለም፡፡

ነብዩ አልማ የሚከተሉትን ለልጁ ለሄለማን መሰከረ፤ “እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ ሁሉ፣ በፈተናቸው፣ እናም በችግራቸው፣ እናም በስቃያቸው እንደሚደገፉ፣ እናም በመጨረሻው ቀን ከፍ እንደሚደረጉ አውቃለሁ።” (አልማ 36:3)።

አዳኙ እራሱ እንዲህ አለ፥

“ልባችሁ ይፅናኑ … ፤ ሁሉም ስጋዎች በእጆቼ ውስጥ ናቸውና፤ ዕረፉ እና እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ።. …፤

“ስለዚህ፣ እስከሞትም አትፍሩ፤ በዚህ አለም ደስታችሁ ሙሉ አይደለምና፣ ነገር ግን በእኔ ደስታችሁ ሙላት አለው። (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 101፥16፣ 36)።

በብዙ አጋጣሚዎች ልቤን የነካው “ነፍሴ ሆይ፣ እርጊ፣” የሚለው ዝማሬ ለነፍሳችን የመጽናናት መልእክት አለው፡፡ ግጥሞቹም እንደሚከተለው ያነባሉ፤

ነፍሴ ሆይ እርጊ፣ ሰዓቱ እየቀረበ ነው

ከጌታ ጋር ለዘላለም የምንሆንበት ጊዜ፣

ብስጭት፣ ሐዘንና ፍርሃት ሲጠፉ፣

ሐዘን ተረስቶ፣ የፍቅር ንፁህ ደስታ ሲመለስ፡፡

ነፍሴ ሆይ እርጊ፣ ለውጥ እና እንባ ሲያለፉ፣

በደህንነት እና በበረከት በመጨረሻ እንገናኛለን። (መዝሙር፣ ቁጥር 124)

የሕይወትን ማዕበሎች ሲያጋጥሙን፣ የተቻለንን ካደረግን እና በኢየሱስ ክርስቶስ እና በእርሱ የኃጢያት ክፍያ ላይ እንደ መሸሸጊያ የምንታመን ከሆነ፣ በእፎይታ፣ በመጽናናት፣ በጥንካሬ፣ በርህራሄ እና በምንፈልገው ሰላም የተባረክን እንደምንሆን አውቃለሁ። በዚህ ምድር ጊዜያችን ማብቂያ ላይ “መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” የሚለውን የጌታን ቃል በልበ ሙሉነት እንሰማለን(ማቲዮስ 25፥21)። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።