ምርጥ ቤቶች
አዳኙ የተዋጣለት ኢንጂነር፣ ገንቢ እና የውስጣዊ ንድፍ ባለሙያ ነው። የእርሱ ፕሮጀክት የነፍሳችን ፍጹምነትና እና ዘላለማዊ ደስታ ነው።
በቅርቡ በሶልት ሌክ ከተማ አንድ የማስታወቂያ ሰሌዳ ቀልቤን ሳበው። የቤት እቃ እና የውስጥ ዲዛይን ድርጅትን ያስተዋውቃል። በቀላሉ እንዲህ ይላል “በሶልት ሌክ ከተማ ውስጥ ያሉ ምርጥ ቤቶችን ማገልገል።”
መልእክቱ ቀልብ የሚስብ ነበር—“ምርጥ ቤት“ ምንድን ነው? ራሴን ስለዚያ ጥያቄ እያሰብኩኝ አገኘሁት፣ በተለይ ባለቤቴ ካቲ እና እኔ ያሳደግናቸውን ልጆች አና ዛሬ እነሱ እያሳደጓቸው ያሉትን ልጆች በተመለከተ። እንደማንኛውም ወላጆች፣ ስለ ቤተሰባችን እንጨነቃለን እናም እንጸልያለን። አሁንም እንደዚያ እናደርጋለን። ለእነሱ በጣም የተሻለውን ከልብ እንፈልጋለን። እነሱ እና ልጆቻቸው እንዴት ነው በምርጥ ቤቶች ውስጥ መኖር የሚችሉት? እኔ እና ካቲ የመጎብኘት እድል ስላለን የቤተክርስቲያኗ አባላት ቤቶች ላይ አሰላስያለሁ። በኮሪያ እና በኬንያ፣ በፊሊፒንስ እና በፔሩ፣ በላኦስ እና በላቲቪያ ውስጥ ወዳሉ ቤቶች ተጋብዘናል። ስለ ጥሩ ቤቶች አራት ምልከታዎችን ላጋራ።
በመጀመሪያ፣ ከጌታ እይታ አንጻር፣ ምርጥ ቤቶችን መመስረት በዚያ ከሚኖሩት ሰዎች የግል ባህርያት ጋር ቀጥተኛ ዝምድና አለው። እነዚህ ቤቶች በእቃዎቻቸው ወይም በንብረቶቹ ባለቤቶች ሃብት ወይም ማህበራዊ ደረጃ በጠቃሚ ወይም በዘላቂ በሆነ መንገድ ጥሩ የተደረጉ አይደሉም። የማንኛውም ምርጥ ቤት ባሕርይ በቤቱ ነዋሪዎች ውስጥ የሚንፀባረቀው የክርስቶስ አምሳል ነው። ይበልጥ ትርጉም ያለው የነዋሪዎቹ ነፍሶች ውስጣዊ ንድፍ እንጂ መዋቅሩ አይደለም።
እነዚህ የክርስቶስ ባህርያት የሚገኙት “በጊዜ ሂደት”1 በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ በሚደረግ የታሰበበት እድገት ነው። የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት በጥሩነት ለመኖር የሚጥሩ ሰዎችን ሕይወት ያጌጣሉ። ወለሉ የጭቃም ሆነ የእምነበረድ፣ ቤቶችን በወንጌል ብርሃን ይሞላሉ። ምንም እንኳን በቤተሰባችሁ ውስጥ “እነዚህን ነገሮች ለመሻት“2 መመሪያውን የምትከተሉት እናንተ ብቻ ብትሆኑም፣ ለቤተሰባችሁ ቤት መንፈሳዊ ማሳመሪያዎች አስተዋፅ ማበርከት ይችላሉ።
የቤት ግንባታችን ሳይሆን መንፈሳዊ ህይወታችንን በማደራጀት፣ በማዘጋጀት እና በመመስረት “[እራሳችንን] ለማደራጀት አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ ለማዘጋጀት፤ አንዲሁም ቤትን ለመመስረት” የጌታን ምክር እንከተላለን። የአዳኙን የቃል ኪዳን መንገድ በትእግስት ስንከተል፣ ቤታችን “የክብር ቤት፣ የስርዓት ቤት፣ [እናም] የእግዚአብሔር ቤት“ ይሆናል።3
ሁለተኛ፣ በምርጥ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ቅዱሳን መጻህፍትን እና የህያው ነቢያትን ቃላት ለማጥናት ጊዜ ይሰጣሉ። ፕሬዘዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን ቤታቸንን በወንጌል ጥናት “እንድንለውጥ“ እና “እንደገና እንድናስተካክል”4ጋብዘውናል። ግብዣቸው ጥሩ ቤቶች ደግነት፣ የግል እድገት ወሳኝ ሥራ፣ እና ድክመቶቻችንን የሚያስተካክሉ ነገሮች የሚገኙበት እንደሆኑ ይገነዘባል። የዘወትር ንስሃ የበለጠ ደግ፣ አፍቃሪ እና የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረን የሚያስችለን የለውጥ መሳሪያ ነው። ቅዱሳን መጻህፍትን ማጥናት ልግስናው እና ፀጋው እድገታችንን ወደሚደግፈው ወደ አዳኛችን ያቀርበናል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ መፅሐፈ ሞርሞን እና የታላቁ ዋጋ እንቁ ስለ ቤተሰቦች ታሪኮች ይናገራሉ፣ ስለዚህ እነዚያ መለኮታዊ መጽሃፍት እጅግ በጣም ጥሩ ቤቶችን ለመገንባት አቻ የሌላቸው መመሪያ መጻህፍት መሆናቸው አያስደንቅም። የወላጆችን ጭንቀት፣ የፈተና አደጋን፣ የጽድቅ ድል አድራጊነትን፣ የረሃብ እና የመትረፍረፍ ፈተናዎችን፣ እና የጦርነትን አሰቃቂ አስፈሪነት እና የሰላምን ሽልማቶችን ይዘግባሉ። ቅዱሳን መጻሕፍት ቤተሰቦች በጽድቅ አኗኗር እንዴት እንደሚሳካላቸው እና ሌሎች መንገዶችን በመከተል እንዴት እንደሚወድቁ ደጋግመው ያሳዩናል።
ሶስተኛ ፣ጥሩ ቤቶች ጌታ ለምርጥ ቤቶች የሰጠውን ንድፍ ይከተላሉ። ቤተመቅደስን መገንባት በመሰረታዊ ደረጃዎች ይጀምራል—ማለትም የቀለም ብሩሽን በማጽዳት እና መሬቱን በማስተካከል። መሬቱን ለማዘጋጀት የሚደረጉት የመጀመሪያ ጥረቶች መሠረታዊ ትዕዛዞችን ከመጠበቅ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ታእዛዛቶቹ ደቀመዝሙርነት የተገነባባቸው መሰረቶች ናችው። ልክ እንደ ቤተመቅደስ የብረት መዋቅር፣ ጥብቅ ደቀመዝሙርነት ጠንካራ፣ ጽኑ፣ እና የማንነቃነቅ፣5 እንድንሆን ያደርገናል። ይህ የማይነቃነቅ መዋቅር ጌታ መንፈሱን እንዲልክ አና ልባችንን እንዲቀይር ይፈቅዳል።6 ታላቅ የልብ ለውጥ መለማመድ ለቤተመቅደስ የውስጥ ክፍል የሚያማምሩ ገጽታዎችን እንደመጨመር ነው።
በእምነታችን ስንቀጥል ጌታ ቀስ በቀስ ይለውጠናል። የእሱን አምሳል በገጽታችን እንቀበላለን እናም የባህሪውን ፍቅር እና ውበት ማንጸባረቅ እንጀምራለን።7 እንደ እርሱ ስንሆን፣ የእርሱ ቤት እንደ ቤታችን ይሰማናል፣ እንዲሁም የእኛ ቤት እንደ ቤቱ ይሰማዋል።
ቤታችን ከሱ ቤት ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ለቤተመቅደስ ፈቃድ ብቁ በመሆን እና ሁኔታችን እንደሚፈቅደው ቶሎቶሎ በመጠቀም ልንጠብቅ እንችላለን። ይህንን ስናደርግ የጌታ ቤት ቅድስና በእኛም ቤት ላይ ያርፋል።
ታላቁ የሶልት ሌክ ቤተመቅደስ በአቅራቢያ ቆሟል። ቤተመቅደሱ በተራ መሳሪያዎች፣ በአካባቢው ጥሬ እቃዎች፣ እና በማያቋርጥ ብርቱ ስራ በፈር ቀዳጆች ከ1853 እስከ 1893 (እ.አ.አ) ተገነባ። የጥንት የቤተክርስቲያን አባላት የሰጡት ምርጥ የምህንድስና፣ የሥነ ሕንጻ፣ አና የውስጣዊ ንድፍ በሚሊዮኖች የሚታወቅ ልዩ የጥበብ ስራ ፈጠረ።
ቤተመቅደሱ ከተመረቀ 130 የሚሆኑ አመታት አለፉት። ትላንትና ሽማግሌ ጌሪ ኢ.ስቲቨንሰን እንደገለጹት፣ ቤተመቅደሱን ለማነጽ ጥቅም ላይ የዋሉት የህንድስና መርሆዎች በአዲስ እና ደህንነታችው በተጠበቁ ደረጃዎች ተተክተዋል። የቤትመቅደስ ምህንድስናን እና መዋቅራዊ ድክመቶቹን አለማጠናከር፣ የሚችሉትን ሁሉ አድርገው የቤተመቅደሱን እንክብካቤ ለመጪው ትውልድ የተዉትን የፈር ቀዳጆቹን በራስ መተማመን መክዳት ነው።
የቤተመቅደሱን መዋቅር እና የመሬት መንቀጥቀጥ ጥንካሬ ለማሻሻል ቤተክርስቲያኗ የአራት አመት የእድሳት ፕሮጀክት ጀምራለች።8 መሰረቱ፣ ወለሎቹ፣ እና ግድግዳዎቹ ይጠናከራሉ። በዛሬው ጊዜ ያሉት ምርጥ የምህንድስና እውቀቶች ቤተመቅደሱን ወደ ዘመናዊ ደረጃዎች ያመጡታል። የመዋቅር ለውጦቹን ለማየት አንችልም፣ ነገር ግን የሚያስከትሉት ውጤቶች እውን እና አስፈላጊ ይሆናሉ። በዚህ ስራ ሁሉ የቤተመቅደሱ ማራኪ ውስጣዊ ንድፍ ገጽታዎች ተጠብቀው ይቆያሉ።
በሶልት ሌክ ሲቲ ቤተመቅደስ እድሳት እየተሰጠን ያለውን ምሳሌ መከተል እና እንዳንዳችን የራሳችንን መንፈሳዊ ምህንድስና ወቅታዊ ስለመሆኑ ለመፈተሽ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። በየወቅቱ እራስን መመርመር፣ እግዚአብሔርን “ደግሞስ የሚጎድለኝ ምንድን ነው“9 ብሎ ከመጠየቅ ጋር ተጣምሮ ምርጥ ቤት ለመገንባት አስተዋጽኦ ለማድረግ እያንዳንዳቸንን ሊረዳን ይችላል።
አራተኛ፣ ምርጥ ቤቶች ከህይወት ማአበሎች መሸሸጊያዎች ናቸው። የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁ “በምድሪቱ ላይ እንደሚበለፅጉ“ ቃል ገብቷል።10 የእግዚአብሔር ብልጽግና በህይወት ችግሮች ቢኖሩም ወደፊት የመግፋት ሃይል ነው።
በ2012 (እ.አ.አ) ስለችግሮች አንድ ጠቃሚ ትምህርት ተማርኩኝ። በፓራጓይ አሱንሲዮን እያለሁኝ ከከተማው የካስማ ፕሬዘዳንት ጋር ተገናኘሁኝ። በዚያን ወቅት ፓራጓይ አስፈሪ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ነበረች፣ እናም ብዙ የቤተክርስቲያን አባላት እየተሰቃዩ ነበር እንዲሁም ፍላጎታቸውን ለማሳካት አልቻሉም ነበር። በሚስዮን እስከመጣሁበት ጊዜ ድረስ ደቡብ አሜሪካ ጎብኝቼ አላውቅም ነበር እናም በፓራጓይ ተገኝቼ አላውቅም ነበር። የዚህ ቦታ እንደ ክልል አመራር ገና ለጥቂት ሳምንታት በማገልገል ላይ ነበርኩኝ። ለእነዚያ የካስማ ፕሬዘዳንቶች መመሪያ ለመስጠት ስላለመቻሌ በመፍራት፣ በየካስማዎቻቸው ምን መልካም ነገሮች እንዳሉ ብቻ እንዲነግሩኝ ጠየቅኳቸው። የመጀመሪያው የካስማ ፕሬዘዳንት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ ስላሉ ነገሮች ነገረኝ። ቀጣዩ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ ስላሉ ነገሮች እና ስላሉ ጥቂት ችግሮች ነገረኝ። ወደመጭረሻው የካስማ ፕሬዘዳንት ስንደርስ ተከታታይ የሚያበሳጩ ችግሮችን ብቻ ጠቀሰ። የካስማ ፕሬዘዳንቶቹ የሁኔታውን ጥልቀት ሲያብራሩ፣ ይበልጥ ሃሳብ እየገባኝ ሄደ፣ እንደውም ስለምናገረው ነገር ተስፋ ወደመቁረጥ ሄድኩኝ።
የመጨረሻው የካስማ ፕሬዝዳንት አስተያየቱን በመጨረስ ላይ ሳለ፣ አንድ ሀሳብ ወደ አዕምሮዬ መጣ፤ “ሽማግሌ ክሌይተን፣ ይህንን ጥያቄ ጠየቃቸው፥ ‘ፕሬዘዳንቶች በካስማችሁ ካሉት አባላት ሙሉ አስራት የሚከፍሉት፣ ለጋስ የጾም በኩራት የሚከፍሉት፣ በቤተክርስቲያን ጥሪያቸውን የሚያጎሉት፣ በየወሩ ቤተሰቦቻቸውን እንደ የቤት ለቤት አስተማሪ ወይም እንደ የሴቶች የቤት ለቤት ጉብኝት አስተማሪ የሚጎበኙ፣11 የቤተሰብ የቤት ምሽት የሚያከናውኑት፣ ቅዱሳት ጽሁፎችን የሚያጠኑት፣ እና በየቀኑ የቤተሰብ ጸሎት የሚያደርጉት እነማን ናቸው፣ ስንቶቻችው ናቸው ያለቤተክርስቲያን ጣልቃ መግባት ችግሮቻቸውን በራሳችው መፍታት የማይችሉት?’”
ለተቀበልኩት መነሳሳት ምላሽ የካስማ ፕሬዘዳንቶቹን እነዚያን ጥያቄዎች ጠየኳቸው።
በመደነቅ ተመለከቱኝና እንዲህ አሉኝ፣ “ፑኤስ፣ ኒንጉኖ፣“ ትርጓሜውም “ማንም የለም” ማለት ነው። ከዚያም አንዳቸውም የተጠቀሱትን ነገሮች ሁሉ የሚያደርጉ አባላት በራሳቸው ሊያቃልሏቸው ያልቻሏቸው ችግሮች እንዳልነበሩ ነገሩኝ። ለምን? ምክንያቱም እነርሱ በምርጥ ቤቶች ውስጥ ነው የኖሩት። ታማኝ አኗኗራቸው በአኮኖሚ ቀውሱ ውስጥ ጥንካሬ፣ ራእይ፣ እና የሚያስፈልጋቸው ሰማያዊ እርዳታ ሰጥቷቸዋል።
ይህ ማለት ጻድቃን አይታመሙም፣ አደጋ አይደርስባቸውም፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አያጋጥማችውም፣ ወይም በህይወት ወስጥ ብዙ ሌሎች አስቸጋሪ ነገሮች አይጋፈጡም ማለት አይደለም። ምድራዊ ህይወት ሁልጊዜ ፈታኝ ነገሮችን ያመጣል፣ ነገር ግን ከጊዜ ወደጊዜ ትእዛዛትን ለማክበር የሚጥሩት በሰላም አና በተስፋ ወደፊት በሚሄዱበት መንገድ ሲባረኩ አይቻለሁኝ። እነዚያ በረከቶች ለማንኛውም ሰው ይገኛሉ።12
ዳዊት “ጌታ ቤትን ካልሰራ ሰራተኞቹ በከንቱ ይደክማል“ ሲል አውጇል።13 በየትኛውም ቦታ ብትኖሩ፣ ቤታችሁ ምንም ቢመስል፣ እናም ቤተሰባችሁ ከምንም የተውጣጣ ቢሆን፣ ለቤተሰባችሁ ምርጥ ቤቶችን ለመገንባት ማገዝ ትችላላችሁ። በዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ለዚያ እቅዶችን ይሰጣል። አዳኙ የተዋጣለት ኢንጂነር፣ ገንቢ እና የውስጣዊ ንድፍ ባለሙያ ነው። የእርሱ ፕሮጀክት የነፍሳችን ፍጹምነት እና ዘላለማዊ ደስታ ነወ። በእርሱ አፍቃሪ እርዳታ፣ ነፍሳችሁ እርሱ እንደሚፈልጋት ትሆናለች እናም ራሳችሁም ልትሆኑ የምትችሉትን እጅግ ምርጥ ስሪት፣ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ቤት ውስጥ ለመመስረት እና ለመኖር የተዘጋጃችሁ ልትሆኑ ትችላላችሁ።
በአመስጋኝነት ጋር የሁላችንም አባት እግዚአብሔር ህያው እንደሆነ እመሰክራለሁ። ልጁ፣ ጌታ ኢየሱስ ከርስቶስ፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ እና ቤዛ ነው። በፍጹም ፍቅር ይወዱናል። የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በምድር የጌታ መንግስት ናት። ህያው ነቢያት እና ሐዋርያት ይመሯታል። መጽሐፈ ሞርሞን እውነት ነው። ተመልሶ የተቋቋመው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እጅግ በጣም ጥሩ ቤቶችን ለመመስረት ፍጹም ንድፍ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።