የደስታ ምልክቶች
በኢየሱስ ክርስቶስ መሠረት ላይ መገንባት ለደስታችን አስፈላጊ ነው።
ከበርካታ ዓመታት በፊት ለስራ ጉዳይ በአውሮፕላን በራራ ላይ ሳለሁ ከኔዘርላንድ የመጣ ሰው አጠገብ ተቀምጬ ነበር። በቤልጂየም እና በኔዘርላንድ ወጣት ሚስዮናዊ ሆኜ ስላገለገልኩ እሱን ላነጋግረው ጓጉቼ ነበር።
እንደተዋወቅን “የደስታ ፕሮፌሰር” የሚል ልዩ የሥራ ማዕረግ ያለው የቢዝነስ ካርዱን ሰጠኝ። ስለ ድንቅ ሙያው አስተያየት ሰጥቼ፣ አንድ የደስታ ፕሮፌሰር ምን እንደሚሠራ ጠየቅኩት። ትርጉም ያለው ግንኙነት እና ግቦችን በመፍጠር ሰዎች ደስተኛ ህይወት እንዲኖራቸው እንደሚያስተምር ነገረኝ። እኔም ፣ “ያ በጣም ጥሩ ነው፣ ነገር ግን እነዚያ ግንኙነቶች ከመቃብር በላይ እንዴት ይቀጥላሉ እንዲሁም የህይወት ዓላማ ምንድን ነው፣ ድክመቶቻችንን እንዴት ማሸነፍ እንችላለን፣ ከሞትን በኋላ የት እንሄዳለን? የሚሉ ሌሎች ከውስጥ የሚወጡ የህይወትን ትርጉም የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ብትችልስ?” በማለት መለስኩኝ። ለእነዚያ አይነት ጥያቄዎች መልስ ቢኖረን ኖሮ በጣም አስደናቂ ይሆን ነበር አለ፣ ከዚያም እኛ መልሶቹ እንዳለን ስላካፈልኩት ተደሰትኩኝ።
ዛሬ፣ ብዙ ነገሮች አስደሳች ነገር ግን ጥቂቶች በእውነት አስፈላጊ በሆኑበት በዚህ ግራ በሚያጋባ ዓለም ውስጥ ብዙዎች የማይኖሯቸው ለእውነተኛ ደስታ አስፈላጊ የሆኑ ጥቂት መርሆችን መከለስ እፈልጋለሁ።
አልማ የእርሱን ዘመን ህዝቦች፣ “እነሆም፣ ብዙ ነገር ይመጣል እላችኋለሁ፤ እናም እነሆ፣ ከሁሉም የበለጠ አንድ ነገር አለ—እነሆም አዳኙ የሚመጣበትና ከህዝቡ ጋር የሚኖርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም”ሲል አስተምሯቸዋል።1
የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ስንጠብቅ እና ስንዘጋጅ ይህ መግለጫ ዛሬም ለእኛ አስፈላጊ ነው!
ስለዚህ፣ የመጀመሪያ ምልከታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ መሠረት ላይ መገንባት ለደስታችን አስፈላጊ መሆኑ ነው። ይህ “እርግጠኛ መሰረት በሆነው ሰዎች ከገነቡበት ሊወድቁበት [የማይችሉበት] አስተማማኝ መሠረት ነው።”2 ይህን ማድረግም የመጣው ቢመጣ ለህይወት ፈተናዎች እንድንዘጋጅ ያደርገናል።
ከብዙ አመታት በፊት ከልጃችን ጀስቲን ጋር በአንድ የበጋ የወጣት ወንዶች ካምፕ ለመሳተፍ ሄድኩ። አክቲቪቲው እየተካሄደ እያለ፣ እሱና ጓደኞቹ የቀስት ውርወራ አርማ ለማግኘት እንደሚፈልጉ በጉጉት አስታወቀ። ይህን ለማድረግ ወንዶቹ አጭር የጽሁፍ ፈተና ማለፍ እና የቀስቶችን ዒላማ መምታት ያስፈልጋቸው ነበር።
በጣም አዘንኩኝ። በወቅቱ ጀስቲን ከውልደቱ ጀምሮ ሲታገለው በነበረው በሳይስቲክ ፋይብሮሲስ (የሳምባ በሽታ) ምክንያት በጣም አቅመ ቢስ ነበር። ፍላጻውን ወደ ዒላማው ለመተኮስ ቀስቱን በደንብ ወደ ኋላ መጎተት ይችል ይሆን ስል ተጨነኩኝ።
እሱና ጓደኞቹ ወደ ቀስት የትምህርት ክፍል ሲሄዱ፣ በተሞክሮው እንዳይዋረድ በጸጥታ ጸለይኩ። ከሁለት አስጨናቂ ሰዓታት በኋላ፣ በታላቅ ፈገግታ ወደ እኔ አቅጣጫ ሲመጣ አየሁት። “አባ!” ብሎ ጮኸ። “የብቃት አርማውን አግኝቻለሁ! የመሀከለኛውን ዒላማ መታሁ፤ ኢላማው ከእኔ ኢላማ አጠገብ ነበር፣ ግን የመሀከለኛውን ዒላማ መታሁ!” የፍላጻውን አቅጣጫ መቆጣጠር ሳይችል ቀስቱን በሙሉ ኃይሉ ወደ ኋላ ጎትቶ ፍላጻውን ለቀቀው። “ይቅርታ፣ የተሳሳተ ኢላማ!” ላላለው ለዚያ ሩህሩህ የቀስት አስተማሪ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ። ከዚህ ይልቅ የጀስቲንን የአቅም ግልጽ የሆነ ገደብ እና ልባዊ ጥረት በመመልከት፣ በደግነት “ጥሩ ሥራ!” ሲል መለሰ።
የአቅም ገደብ ቢኖርብንም ክርስቶስንና ነቢያትን ለመከተል የምንችለውን ሁሉ ካደረግን፣ ለእኛም እንዲሁ ይሆናል። ቃል ኪዳኖቻችንን በማክበር እና ለኃጢአታችን ንስሐ በመግባት ወደ እርሱ ከመጣን፣ “መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ፣”3 የሚለውን የአዳኛችንን ምስጋና በደስታ እንሰማለን።
ስለዓለም አዳኝ አምላክነት እና ወደ እርሱ ለመቅረብ በትጋት በምንጥርበት ጊዜ ስለምናገኘው ቤዛዊ ፍቅሩ እንዲሁም የማዳን፣ የማጠንከር፣ የመርዳት እና የመባረክ ሃይሉ ምስክርነቴን እሰጣችኋለሁ። በተቃራኒም፣ በዙሪያችን ያሉ ብዙ ሰዎች የሚያምኑትን ለመከተል እየመረጥን እና እያደረግን ኢየሱስን ለመከተል የመንመርጥበት ምንም መንገድ የለም። አዳኙ ሞትን፣ በሽታን፣ እና ኃጢአትን አሸንፏል እናም እርሱን በሙሉ ልባችን የምንከተል ከሆንን፣ ለመጨረሻው ፍጽምናችን መንገድ አዘጋጅቶልናል።4
ሁለተኛው ምልከታዬ እኛ የአፍቃሪው የሰማይ አባት ወንድ እና ሴት ልጆች መሆናችንን ማስታወስ ለደስታችን ወሳኝ እንደሆነ ነው። ይህንን እውነታ ማወቅ እና ማመን በሕይወታችን ውስጥ ሁሉንም ነገር ይለውጣል።
ከበርካታ አመታት በፊት፣ ከቤተክርስቲያን ምድብ ወደ ቤት በአውሮፕላን ስንመለስ፣ እህት ሳቢን እና እኔ በመላጣ ጭንቅላቱ ጀርባ ላይ የተናደደ ሰው ፊት እና 439 ቁጥር የተነቀሰ በጣም ትልቅ ሰው ጀርባ ተቀምጠን ነበር።
አውሮፕላኑ ሲያርፍ፣ እንዲህ አልኩት፣ “ይቅርታ ጌታዬ። በጭንቅላትህ ጀርባ ላይ የተነቀስከውን ቁጥር ትርጉም ብጠይቅህ ቅር ይልሃል?” ስለ ቁጡ ፊት ለመጠየቅ አልደፈርኩም።
እሱም እንዲህ አለ “እኔ ነኝ። ያ ነኝ እንግዲህ እኔ። የዚያ ግዛት ባለቤት ነኝ፦ 219!”
በጭንቅላቱ ላይ ያለው ትክክለኛ ቁጥር አራት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ነበር፣ ስለዚህ ለእሱ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር በመሳሳቱ ተገረምኩ።
የዚህ ሰው ማንነት እና ለራሱ ያለው ግምት ከወሮበሎች ክልል ጋር በተገናኘ ቁጥር ላይ የተመሰረተ መሆኑ ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ አሰብኩ። ለራሴ አሰብኩ፣ ይህ ጠንከር ያለ ሰው በአንድ ወቅት ዋጋ ሊሰጠው እና በአባልነት መካተት የሚያስፈልገው የአንድ ሰው ትንሽ ልጅ ነበር። በርግጥ እሱ ማን እንደሆነ እና የማን እንደሆነ ቢያውቅ ኖሮ፣ ምክንያቱም ሁላችንም “በዋጋ ተገዝተናልና”።5
የግብፅ ልዑል ከተሰኘው ፊልም ላይ በሚገኝ መዝሙር ውስጥ “ህይወታችሁን በእግዚአብሄር አይን እዩ” የሚል ጥበብ ያዘለ ስንኝ አለ።6 የመለኮታዊ የዘር ሐረጋችንን እና የዘለአለም እምቅ ችሎታችንን እውቀት በጥልቅ ስንገነዘበው፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን “በመስታወት፣ በድንግዝግዝ እንደምናይ”7 ህይወትን አላማ እንዳለው፣ ለመማር እና ለማደግ አስደሳች እንደሆነ ያልተለመደ ተግባር አድርገን ማየት እንችላለን።
ሦስተኛው የደስታ ምልክት የነፍስን ዋጋ ሁል ጊዜ ማስታወስ ነው። ይህንንም ከሁሉ በተሻለ መንገድ የምናደርገው፣“እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ”8 የሚለውን የአዳኙን ምክር በመከተል ነው።
በተጨማሪም፣ “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል” ሲል አስተምሯል።9
መፅሐፈ ምሳሌ “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፥ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” ሲል በጥበብ ምክር ይሰጣል።10
በጣም ደግ በመሆናችን አንቆጭም። በእግዚአብሔር አመለካከት ደግነት ከትልቅነት ጋር ተመሳሳይ ነው። የደግነት አንዱ ክፍል ይቅር ባይ መሆን እና አለመፍረድ ነው።
ከብዙ አመታት በፊት፣ ወጣት ቤተሰባችን እንደየቤተሰብ የቤት ምሽት አካል ፊልም ለማየት ሄድን። ከአንደኛው ልጃችን እና ከባለቤቴ ቫለሪ በስተቀር ሁላችንም በመኪናው ውስጥ ነበርን። ውጪው ጨልሞ ነበር፣ እና ልጃችን በሩን ብርግድ አድርጎ ወደ መኪናው ሲሮጥ፣ በረንዳው ላይ ድመታችን እንደሆነች የገመተውን ሳያስበው ረገጠ። ከኋላው ለነበሩት ለልጃችን እና ባለቤቴ አለመታደል ሆኖባቸው፣ ድመታችን ሳይሆን ዋጋቸውን የሰጣቸው በጣም ደስተኛ ያልሆነ የሚገማ ሽንት የሚረጭ አውሬ ነበር! ሁላችንም ወደ ቤት ተመለስን፣ ሁለቱም ገላቸውን ታጠቡ እናም ፀጉራቸውን በቲማቲም ጭማቂ ታጠቡ፣ ይህም የአውሬውን ሽታ ያስወግዳል ተብሎ ይታሰባልና። ከታጠቡ እና ልብሳቸውን ከቀይሩ በኋላ፣ ሁላችንም ምንም አይነት ሽታ ስላልሸተተን ወደ ፊልም ለመሄድ የምንችል መሆናችንን ወሰንን።
በቴአትር ቤቱ የኋላ ወንበሮች እንደተቀመጥን ፣ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በድንገት አንድ አንድ እያሉ ፈንዲሻ ለመግዛት ወስነው ወጡ። ሲመለሱ ግን ማንም ወደ መጀመሪያው ቦታው አልተመለሰም።
ያንን ገጠመኝ ስናስታውስ ስቀን ነበር፣ ነገር ግን ሁሉም ኃጢያቶቻችን ሽታ ቢኖራቸውስ? ሐቀኝነትን፣ ፍትወትን፣ ምቀኝነትን ወይም ኩራትን ማሽተት የምንችል ብንሆንስ ኖሮ? የራሳችን ድክመቶች ስለሚገለጡ፣ለሌሎች ትንሽ አሳቢ እና ጠንቃቆች እንሆናለን እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ በህይወታችን ውስጥ አስፈላጊ ለውጦችን ስናደርግ፣ እነሱም ለእኛ፣ እንደዚያው እንደሚያደርጉ ተስፋ እናደርጋለን። በቤተክርስቲያን ውስጥ የትምባሆ ሽታ ቢሸተኝ እወዳለሁ፣ ምክንያቱም አንድ ሰው ለመለወጥ እየሞከረ እንደሆነ በእርግጥም ያመለክታል። እነርሱም ጥሩ አቀባበል የሚያደርጉላቸው የሚያቅፏቸው እጆች ያስፈልጋቸዋል።
ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን በጥበብ እንዳሉት፣ “የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታይን ለመለየት ከሚቻልባቸው እጅግ ቀላል መንገዶች አንዱ ያ ሰው ለሌሎች ሰዎች ያለው ርህራሄ ነው።”11
ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች እንዲህ ሲል ፅፏል፣ “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።”12
እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት፣ በሰማይ አባታችን እና በአዳኛችን እንድንታመን እንጂ እነርሱን ለመተካት እንዳንሞክር ተጠይቀናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ሰው ፍጹም አለመሆኑን በሚገባ ያውቃል እናም ፍጹም በሆነ መልኩ ይፈርዳል።
አራተኛው የደስታ ምልክት ዘለአለማዊ እይታን መያዝ ነው። የአባታችን እቅድ እስከ ዘለአለም ይዘልቃል፤ እዚህ እና አሁን ላይ ማተኮር እንዲሁም ከዚህ በኋላ የሚመጣውን መርሳት ቀላል ነው።
ይህን ትምህርት ከበርካታ አመታት በፊት በወቅቱ የ16 አመት ልጅ በነበረችው ሴት ልጃችን ጄኒፈር በኩል በጠንካራ ሁኔታ ተምሬያለው ። የሁለት ሳንባ ንቅለ ተከላ ሊደረግላት ነበር፤ አምስቱ የታመሙት የሳምባዋ አንጓዎች ሙሉ በሙሉ ተወግደው በሁለት ጤነኛ ትንንሽ አንጓዎች ይተካሉ፤ ይህም በሁለት አስደናቂ የክርስቶስ አይነት ጓደኞች የተሰጡ ነበሩ። በጣም አደገኛ የሆነ ሂደት ነበር፣ ሆኖም ከቀዶ ጥገናዋ በፊት በነበረው ምሽት 90 ፓውንድ (41 ኪሎ ግራም) ብቻ የምትመዘነው ጄኒፈር ልትሰብከኝ እንዲህ አለች፣ “አትጨነቅ፣ አባ! ነገ በአዲስ ሳንባ እነቃለሁ ወይም በተሻለ ቦታ እነቃለሁ። ሁለቱም አማራጮች መልካም ይሆናሉ።” ይህ እምነት ነው፤ ይህ ዘለአለማዊ እይታ ነው! ህይወትን ከዘለአለማዊ እይታ አንፃር ማየት ግልጽነት፣ ማጽናኛ፣ ድፍረት እና ተስፋ ይሰጣል።
ከቀዶ ጥገናው በኋላ የመተንፈሻ ቱቦው ወጥቶ ጄኒፈር እንድትተነፍስ ይረዳት የነበረውን ማሺን ለማጥፋት በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው ቀን ሲደርስ፣ የእርሷ ትንንሽ ሁለት የሳንባ አንጓዎች እንደሚሰሩ ለማየት በጭንቀት ጠበቅን። የመጀመሪያውን ትንፋሿን ስታወጣ፣ ወዲያው ማልቀስ ጀመረች። ስጋታችንን አይታ፣ ፈጥና “መተንፈስ በጣም ጥሩ ነው” ብላ ጮኸች።
ከዚያን ቀን ጀምሮ፣ ስለመተንፈስ ችሎታዬ የሰማይ አባትን ጠዋት እና ማታ አመሰግነዋለሁ። ካላስተዋልን እንደተራ ልንመለከታቸው በምንችላቸው ስፍር ቁጥር በሌላቸው በረከቶች ተከበናል። በተቃራኒው፣ ምንም ነገር በማይጠበቅበት እና ሁሉም ነገር በአድናቆት በሚታይበት ጊዜ፣ ህይወት አስደናቂ ይሆናል።
ፕሬዘደንት ኔልሰን እንዳሉት፦ “እያንዳንዱ አዲስ ጥዋት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። የምንተነፍሰውን አየር እንኳን የሰጠን በፍቅር ነው። ከቀን ወደ ቀን ይጠብቀናል እናም ከአንዱ አፍታ ወደ ሌላው ይደግፈናል። ስለዚህ የማለዳው የመጀመሪያ ተግባራችን ትሁት የሆነ የምስጋና ጸሎት ማቅረብ መሆን አለበት።”12
ያም ወደ አምስተኛው እና የመጨረሻው ምልከታዬ ያመጣኛል፣ ያም ማለት እናንተ ከምታመሰግኑት በላይ ደስተኛ መሆን አትችሉም።
ጌታም ፣ “እናም ሁሉንም ነገሮች በምስጋና የሚቀበል እርሱ የከበረ ይሆናል።” ሲል ተናግሯል።14 ምናልባት ይህ የሚሆነው ምስጋና ሌሎች በርካታ በጎ ነገሮችን ስለሚያመጣ ነው።
በየማለዳው ከእንቅልፋችን የምንነቃው በቀደመው ምሽት ምስጋና ባቀረብንባቸው በረከቶች ብቻ ቢሆን ግንዛቤያችን እንዴት ይለወጥ ነበር። በረከቶቻችንን አለማድነቅ እርካታ እንዳይኖረን ሊያደርግ ይችላል፣ ይህም ምስጋና የሚያስገኝልንን ደስታና ሀሴት ሊሰርቅብን ይችላል። በታላቁ እና ሰፊው ህንፃ ውስጥ ያሉት ከሚገባው በላይ እንድናተኩር፣ በዚህም ጠቃሚ የሆነውን ነገር ሙሉ በሙሉ እንድንስት ያባብሉናል።
በእውነቱ፣ ትልቁ ደስታ እና ምድራዊ በረከት ከእርሱ ጋር ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን ስንገባ እና ስንጠብቅ በእግዚአብሔር ጸጋ አማካኝነት በምንሆነው ውስጥ ይገኛል ። አዳኛችን በኃጢያት ክፍያ መስዋዕቱ ያጸዳናል እንዲሁም ያጠራናል እናም እሱን በፈቃዳቸው ስለሚከተሉት ሲናገርም፣ “እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ” ብሏል።15
ህይወታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ መሠረት ላይ ከገነባን፤ እንደ እግዚአብሔር ወንድ እና ሴቶች ልጆች እውነተኛ ማንነታችንን ዋጋ ከሰጠን፤ የነፍስን ዋጋ ካስታወስን፤ ዘለአለማዊ አመለካከትን ከያዝን፤ እና ብዙ በረከቶቻችንን፣ በተለይም ወደ እሱ እንድንመጣ ክርስቶስ የሚሰጠንን ግብዣ በአመስጋኝነት ከተቀበልን፣ በዚህ ምድራዊ ህይወት ወቅት የምንፈልገውን እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንደምንችል ቃል እገባላችኋለሁ። ህይወት አሁንም ፈተናዎች ይኖሯታል፣ ነገር ግን በምንረዳቸው እና በምንኖርባቸው ዘለአለማዊ እውነቶች የተነሳ እያንዳንዱን በዓላማ እና በሰላም ስሜት በተሻለ ሁኔታ ለመጋፈጥ እንችላለን።
የዘለአለም አባታችንን የእግዚአብሔርን እና የተወደደ ልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን እውነታ ምስክርነቴን በደስታ እሠጣለሁ። ስለህያው ነቢያት፣ ባለራዕያት፣ እና ገላጮችም እመሰክራለሁ። በእነርሱ በኩል የሰማይን ምክር መቀበል ምን አይነት በረከት ነው። አዳኙ በግልፅ እንደተናገረው፣ “በእኔም ድምፅ ሆነ ወይም በአገልጋዮቼ ድምፅ፣ አንድ ነው።”16 በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።