አጠቃላይ ጉባኤ
በቃላት እና በተግባር ስለኢየሱስ ክርስቶስ መመስከር
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


9:45

በቃላት እና በስራ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መመስከር

ህይወታችንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ጋር በማስማማት ለመኖር ስንጥር፣ ምግባራችን ለቤዛችን ህያው ምስክር ይሆናል።

በጥምቀት ከምንገባቸው ቃል ኪዳኖች አንዱ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳችን ላይ ለመውሰድ ፈቃደኞች መሆናችንን ነው። የዛሬ አላማዬ በቻልነው መጠን በቃልም ሆነ በተግባር ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ በመመስከር የልጁን ስም በራሳችን ላይ እንደምንወስድ እግዚአብሔርን ማሳየት እንደምንችል እንድናስታውስ ለማድረግ ነው።

ከትንሳኤው በኋላ በአሜሪካ ላሉ ሰዎች ሲያገለግል እና ሲያስተምር አዳኝ እንዲህ አውጇል፦

“ስሜ የሆነውን፣ የክርስቶስን ስም በእራሳቸው ላይ መውሰድ እንዳለባቸው ቅዱሳን መጻሕፍትን አላነበቡምን? በዚህ ስም በመጨረሻው ዘመን ትጠሩበታላችሁና፤

“እናም ስሜን በራሱ ላይ የወሰደና፣ እስከመጨረሻው በዚህ የፀና በመጨረሻው ዘመን እርሱ ይድናል።”1

ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “የአዳኝን ስም መውሰድንም—በስራዎቻችን እና በቃላቶቻችን—ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ለሌሎች ማወጅን እና መመስከርን ያካትታል።”2

እንደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት፣ በያለንበት ሁሉ የጌታ እና የስሙ ምስክሮች በመሆን የመቆም በረከት እና እድል አለን።3 ህይወታችንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ጋር በማስማማት ለመኖር ስንጥር፣ ምግባራችን ለቤዛችን እና ለስሙ ህያው ምስክር ይሆናል። በተጨማሪም፣ ስለ ክርስቶስ የምናምነውን፣ የሚሰማንን ወይም የምናውቀውን ለሌሎች በማካፈል ስለ ክርስቶስ በቃል እንመሰክራለን።

በቃላችን እና በተግባራችን የጌታን ምስክርነታችንን በትህትና ስናካፍል፣ መንፈስ ቅዱስ4 እውነተኛ ልብ፣ ክፍት ልቦች እና ፈቃደኛ አእምሮዎች ላላቸው ኢየሱስ በእውነት ክርስቶስ መሆኑን ያረጋግጣል።5

ስለ እርሱ በመናገር እና በቤተክርስቲያን ስብሰባዎች የጌታ ንፁህ ምስክር በመሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳቸው ላይ እንደሚወስዱ እግዚአብሔርን የሚያሳዩ ሁለት የቅርብ ጊዜ እና የሚያነሳሱ ምሳሌዎችን ላካፍላችሁ እወዳለሁ።

የመጀመሪያው ምሳሌ፦ እኔና ባለቤቴ እሌን በ2022 (እ.አ.አ) ወደ ስፔን ሄደን በነበረበት ጊዜ፣ በዚያ በነበረች አንዲት ትንሽ የቤተክርስቲያኗ ክፍል ውስጥ የእሁድ ስብሰባዎችን እንሳተፍ ነበር። እኔ በንግግር መድረክ አጠገብ፣ ባላቤቴም ከተሳታፊዎች ጋር ተቀምጣ ሳለች፣ ከአንዲት አረጋዊት ሴት አጠገብ እንደተቀመጠች አስተዋልኩ። የቅዱስ ቁርባን ስብሰባው ሲያልቅ፣ ወደ እሌን አመራሁና ከአዲሷ ጓደኛዋ ጋር እንድታስተዋውቀኝ ጠየቅኋት። እሷም እንዲህ አደረገች፣ ይህች የቤተክርስቲያኗ አባል ያልሆነች ሴት ቤተክርስቲያኗን ለሁለት አመታት ያህል እየጎበኘች እንደነበረች አመለከተች። ይህን በሰማሁ ጊዜ፣ ይህችን አምላክ የምትፈራ ሴት ተመልሳ ረዘም ላለ ጊዜ እንድትመጣና በስብሰባዎቻችን ላይ እንድትገኝ ያደረጋት ምን እንደሆነ ጠየቅኳት። ሴትየዋ በፍቅር እንዲህ መለሰች፦ “ወደዚህ መምጣት የምወደው በስብሰባችሁ ላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለምትናገሩ ነው።”

የዚያች የቤተክርስቲያን ክፍል አባላት በስብሰባዎቻቸው ላይ ስለክርስቶስ በግልፅ ይናገሩ፣ ያስተምሩ፣ እና ይመሰክሩ ነበር።

ሁለተኛ ምሳሌ፦ በብራዚል አካባቢ ካገለገልኩኝ በኋላ፣ በቤተክርስቲያኗ ዋና መሥሪያ ቤት ለማገልገል አዲስ ጥሪን ተቀበልኩ። በዚህ አመት በሐምሌ መጨረሻ ላይ ወደ ሶልት ሌክ ሲቲ ስንዛወር፣ የእሁድ ስብሰባዎቻችንን በአዲሱ እና በአስደናቂው አጥቢያችን ውስጥ ተሳተፍን። ከእነዚህ ስብሰባዎች አንዱ የጾም እና የምሥክርነት ስብሰባ ነበር። ቅዱስ ቁርባንን በጥልቅ አክብሮት ከተካፈሉ በኋላ፣ አባላት ተነሥተው ስለ አዳኙ ከልብ የመነጨ ምስክርነቶችን አንድ በአንድ ይሰጡ ነበር። ስብሰባው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮረ ነበር፣ እናም መንፈሱም በጥልቅ ይሰማን ነበር። ታነጽን እንዲሁም እምነታችንም ጠነከረ። እውነትን በቅንነት የሚፈልጉ የቤተክርስቲያኗ ጓደኞች በዚያ ስብሰባ ላይ ቢኖሩ ኖሮ፣ ይህች የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንደሆነች ያወቁ ነበር።

የቤተክርስቲያናችን ስብሰባዎች ስለ ክርስቶስ የምንመሰክርበት እና የልጁን ስም በራሳችን ላይ በመውሰድ ደስተኞች መሆናችንን ለእግዚአብሔር ምልክት የምንሰጥበት የምርጫ እድሎች መሆናቸውን ማየት እንዴት ያለ በረከት ነው።

አሁን፣ በድርጊት ስለ እርሱ በመመስከር የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳችን ላይ ስለመውሰድ አንድ ኃይለኛ ምሳሌ ልጥቀስ።

ባለፈው ነሀሴ፣ በዩባ ከተማ ወደሚገኘው የፌዘር ሪቨር የካሊፎርኒያ ቤተመቅደስ የማሳያ ጉብኝት ላይ ለመሳተፍ ከሽማግሌ ጆናታን ኤስ ሽሚት ጋር አብሬ ሄጄ ነበር። እዚያ፣ በቤተመቅደሱ ጉብኝት ላይ ቡድኖችን በመምራት ተባርኬ ነበር። ከእነዚህ ቡድኖች አንዱ የቤተክርስቲያኗ አባል የሆነውን ቨርጂል አትኪንሰንን እና ሰባት ከሌላ እምነት የመጡ ጓደኞቹን ያካትት ነበር። በጉብኝቱ ማብቂያ ላይ፣ በቤተመቅደስ እትመት ክፍል ውስጥ፣ ወንድም አትኪንሰን በእለቱ ወደ ቤተመቅደስ ለመጡ ጓደኞቹ ያለውን ፍቅር ሲገልጽ ስሜታዊ ነበር። ይህን ካደረገ በኋላ ወዲያውኑ በቡድኑ ውስጥ ያለች አንዲት ሴት ተነስታ እንዲህ አለች፣ “ሁላችንም ቨርጂልን እንወደዋለን። እምነቱን በእኛ ላይ ጭኖብን አያውቅም። ሆኖም በዚህ ጉዳይ አያፍርም ነበር። የሚያምንበትን ነገር ይኖርበታል።”

ባለፉት ዓመታት፣ የወንድም አትኪንሰን የክርስቶስ አይነት ህይወት ለጓደኞቹ ጠንካራ ምስክር ሆኖ አገልግሏል። የእሱ ምሳሌ የክርስቶስን ስም በራሱ ላይ እንደወሰደ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።

በመጨረሻም፣ የክርስቶስን ስም በእኛ ላይ እንዴት እንደምንወስድ እና ትክክለኛውን የቤተክርስቲያኗን ስም በመጠቀም ስለ እርሱ ስለመመስከር የተማርኩትን ትምህርት ላካፍላችሁ።

በህይወት ያሉ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆኑት ፕሬዘደንት ኔልሰን በ2018 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ ላይ “የቤተክርስቲያኗ ትክክለኛ ስም” የሚል ርእስ ባለው ንግግር ላይ እንዲህ ብለዋል፦ ማስተካከያ ነው ። ይህ የጌታ ትእዛዝ ነው። ጆሴፍ ስሚዝ በእርሱ በኩል በዳግም የተመለሰችውን ቤተክርስቲያን ስም አልሰጠም፤ ሞርሞንም አላደረገውም። ‘በመጨረሻዎቹ ቀናትም ቤተክርስቲያኔ የምትጠራው በዚህ፣ እንዲሁም የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ ስም ነው’ (Doctrine and Covenants 115፥4) ያለው አዳኝ ራሱ ነበር።””6

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁላችንም ነቢዩን ለመከተል እና የተገለጠውን የቤተክርስቲያኗን ስም ለመጠቀም ቆርጠን ወስነን ከአጠቃላይ ጉባኤው ወጣን። ትክክለኛውን የቤተክርስቲያኗ ስም ለመጠቀም ጥንቃቄ አደረኩኝ። ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ጊዜያት በጣም ንቁ መሆን ነበረብኝ እንዲሁም ወደ ድሮው ልምዴ አለመመለሴን ማረጋገጥ ነበረብኝ። ከመጀመሪያዎቹ ሙከራዎች በኋላ፣ የተገለጠውን የቤተክርስቲያኗን ስም ለመጠቀም የበለጠ ምቾት ተሰማኝ። ብዙ ጊዜ፣ የቤተክርስቲያኗን ስም በፍጥነት እንደምናገር አምናለሁ። ሰዎች ለቤተክርስቲያኗ ሙሉ ስም ትኩረት አይሰጡም እንዲሁም ትንሽ ረዘም ያለ ነው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተሰማኝ።

ነገር ግን፣ ከጊዜ በኋላ የቤተክርስቲያኗን ሙሉ ስም ሆን ብሎ መናገሩ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ለመናገር እና በእውነቱ ስሙን በቤተክርስቲያኗ ስም በማወጅ ስለ አዳኝ ለመመስከር ጠቃሚ እድሎችን እንደሰጠኝ ተገነዘብኩ። እንዲሁም ትክክለኛውን የቤተክርስቲያኗን ስም ለሌሎች ስናገር፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ይበልጥ በተደጋጋሚ እንደማስታውስ እና በህይወቴ ውስጥ የእሱ ተጽእኖ እንደሚሰማኝ አስተውያለሁ።

ነቢዩን በመከተል፣ ሁላችንም ትክክለኛውን የቤተክርስቲያኗን ስም በመጠቀም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በተጨማሪ ለመመስከር መማር እንችላለን፣ በዚህም በሙላት የጌታን ስም በራሳችን ላይ እንወስዳለን።

በዚህ ሰንበት ጥዋት፣ ፕሬዘደንት ኔልሰን የእግዚአብሔር በህይወት ያሉ ነቢይ መሆናቸውን እና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ዳግም የተመለሰች ቤተክርስቲያን እንደሆነች በደስታ እመሰክራለሁ። ስለ እግዚአብሔር ልጅ እና አምላክነቱ በትህትና እመሰክራለሁ። እርሱ የእግዚአብሔር በኩር እና አንድያ ልጅ፣ አዳኛችን እና ቤዛችን፣ አማኑኤል ነው።7 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።