አጠቃላይ ጉባኤ
የእርሱ ልጆች ነን
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


9:42

የእርሱ ልጆች ነን

በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አንድ አይነት መለኮታዊ ምንጭ እና ገደብ የለሽ አቅም አለን።

እግዚአብሔር ነቢዩ ሳሙኤልን አዲሱን የእስራኤል ንጉሥ እንዲቀባ ወደ እሴይ ቤት በላከው ጊዜ ያጋጠመውን ታስታውሳላችሁን? ሳሙኤል የእሴይን የበኩር ልጅ ኤልያብን አየው። ኤልያብ ረጅም እንዲሁም የመሪ መልክ ነበረው። ሳሙኤል ይህን አየና አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሰ። ይህም የተሳሳተ መደምደሚያ ሆኖ ተገኘ፣ እናም ጌታ ሳሙኤልን እንዲህ ሲል አስተማረው፦ “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ … ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።”1

ሳኦልን እንዲባርከው ጌታ በላከው ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ሐናንያ ያጋጠመውን ታስታውሳላችሁን? የሳኦል ስም እና ድርጊት የሚታወቅ ነበር፣ ሐናንያ ስለ ሳኦል እና እርሱ ቅዱሳንን በጭካኔ ያለማቋረጥ ያሳድድ እንደነበረም ሰምቶ ነበር። ሐናንያ ሰማና ምናልባት ሳኦልን ማገልገል እንደሌለበት ደመደመ። ይህም የተሳሳተ መደምደሚያ ሆኖ ተገኘ፣ ጌታም ሐናንያን እንዲህ ሲል አስተማረው፦ “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው።”2

በእነዚህ ሁለት አጋጣሚዎች የሳሙኤልና የሐናንያ ችግር ምን ነበር? በአይናቸው አይተዋል፣በጆሮአቸውም ሰምተዋል፣ በዚህም ምክንያት በመልክና በወሬ ላይ ተመሥርተው በሌሎች ላይ ፍርድ ሰጥተዋል።

ጻፎችና ፈሪሳውያን ዝሙት ስትፈጽም የተያዘችውን ሴት ባዩ ጊዜ ምን ተመልከቱ? የተበላሸች ፣ ሞት የሚገባት ኃጢአተኛ ሴት። ኢየሱስ ባያት ጊዜ ምን ተመለከተ? ለጊዜው ለሥጋ ድካም የተሸነፈች ነገር ግን በንስሐ እና በኃጢያት ክፍያው መመለስ የምትችል ሴት። ሰዎች አገልጋዩ ሽባ ሆኖ የታመመውን የመቶ አለቃን ባዩ ጊዜ ምን ተመለከቱ? ምናልባት ሰርጎ ገብ፣ የውጭ ተወላጅ፣ የሚናቅ ሰው አይተው ይሆናል። ኢየሱስ ባየው ጊዜ ምን ተመለከተ? ለቤተሰቡ አባል ደህንነት የሚጨነቅ፣ በቅንነት እና በእምነት ጌታን የፈለገ ሰው። ሰዎች የደም መፍሰስ ችግር ያለባትን ሴት ሲያዩ ምን ተመለከቱ? ምናልባት ርኩስ የሆነች፣ መገለል ያለባት ሴት። ኢየሱስ ባያት ጊዜ ምን ተመለከተ? የታመመች፣ ብቸኛ እና ለመቆጣጠር በማትችለው ሁኔታ ምክንያት የተገለለች፣ ለመፈወስ እና እንደገና ከሰው ለመቀላቀል ተስፋ ያደረገች ሴት።

በእያንዳንዱም ሁኔታ፣ ጌታ እነዚህን ግለሰቦች ማን እንደሆኑ ተመለከተ እንዲሁም እያንዳንዱን በዚያ መሰረት አገለገለ። ኔፊ እና ወንድሙ ያዕቆብ እንደተናገሩት፦

“ሁሉም ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጋብዛል፤ … ፣ ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያውንና ነፃውን፤ ሴትና ወንድን አይክድም፤ እምነተቢሶችንም ያስታውሳል፤ … ሁሉም ለእግዚአብሔር አንድ ናቸው።”3

“አንዱ ፍጡር እንደሌላው በፊቱ የከበረ ነው።”4

እኛም እንዲሁ ዓይኖቻችንን፣ ጆሮዎቻችንን ወይም ፍርሃቶቻችንን እንዲያሳስቱን አንፍቀድ፣ ነገር ግን ልባችንን እና አእምሮአችንን ከፍተን እርሱ እንዳደረገው በዙሪያችን ያሉትን በነጻ እናገልግል።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ባለቤቴ ኢዛቤል ያልተለመደ የአገልግሎት ምድብ ተሰቷት ነበር። በአጥቢያችን ውስጥ ያሉ የጤና ችግር ያለባቸው እና ብቸኝነት በህይወታቸው ውስጥ ምሬት ያመጣባቸውን አንዲት አረጋዊ መበለት እንድትጎበኝ ተጠየቀች። መጋረጃቸው የተዘጋ ፣ መኖሪያቸው የተጨናነቀ ነበር፤ መጎብኘት አልፈለጉም እንዲሁም “ለማንም የማደርገው ምንም ነገር የለም” በማለት በግልጽ ተናገሩ። ኢዛቤል ተስፋ ሳትቆርጥ እንዲህ መለሰች፣ “አዎ፣ አለ!” መጥተን እንድንጠይቅዎት በመፍቀድ አንድ ነገር ሊያደርጉልን ይችላሉ።” እና ስለዚህ ኢዛቤል በታማኝነት ሄደጭ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ እኚህ መልካም እህት እግራቸው ላይ ቀዶ ጥገና ተደረገላቸው፤ ይህም ፋሻቸውን በየቀኑ መቀየር ይጠይቅ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እራሳቸው ማድረግ የማይችሉት ነገር ነበር። ለብዙ ቀናት ኢዛቤል ወደ ቤታቸው በመሄድ እግራቸውን አጥባ ፋሻቸውን ትቀይር ነበር። እሷ አስቀያሚነት አላየችም፤ መጥፎ ጠረንም አልሸተታትም። ፍቅር እና የርኅራኄ እንክብካቤ የምትፈልግ ቆንጆ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ነበር የተመለከተችው።

ባለፉት አመታት፣ ኢዛቤል ጌታ እንደሚያየው ለማየት ባላት ስጦታ እኔ እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎች ተባርከናል። የካስማ ፕሬዘደንትም ሆናችሁ ወይም የአጥቢያ ሰላምታ ሰጪ፣ የእንግሊዝ ንጉስ ብትሆኑ ወይም በዳስ ውስጥ የምትኖሩ፣ የእርሷን ቋንቋ ወይም የተለየ የምትናገሩ፣ ሁሉንም ትእዛዛት የምትጠብቁ ወይም አንዳንዶቹ የሚያስቸግሩህ ቢሆንም እንኳ፣ እርሷ ምርጥ የሆኑ ምግቦቿን በጣም ምርጥ በሆኑ ሳህኖቿ ላይ ታቀርብላችኋለች። የኢኮኖሚ ደረጃ፣ የቆዳ ቀለም፣ የባህል አይነት፣ ዜግነት፣ የጽድቅ ደረጃ፣ ማህበራዊ አቋም፣ ወይም ሌላ መጠቆሚያ ወይም መለያ፣ ለእርሷ ምንም አይነት ውጤት የላቸውም። በልቧ ታያለች፤ የእግዚአብሔር ልጅነትን በሁሉም ሰው ታያለች።

ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፥

“ጠላት፣ መለያዎች ስለሚከፋፍሉን እና ስለራሳችን እና አንዳችን ስለሌላችን የምናስብበትን መንገድ ስለሚገድቡ ይደሰታል። አንዳችን ሌላችንን ከምናከብረው በላይ መለያዎችን ስናከብር ምንኛ ያሳዝናል።

“መለያዎች ወደ ፍርድ እና ወደ ጠላትነት ያመራሉ። በብሔር፣ በዘር፣ በፆታዊ ማንነት፣ በጾታ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በባህል ወይም በሌሎች ጉልህ መለያዎች ምክንያት ሌላን የሚያጠቃ ወይም በጭፍን ጥላቻ የሚመለከት ፈጣሪያችንን የሚያስቆጣ ነው!”5

ፈረንሳይ የእኔ ማንነት አይደለም፤ የተወለድኩበት ቦታ ነው እንጂ። ነጭ የእኔ ማንነት አይደለም፤ የቆዳዬ ቀለም ወይም እጥረት ነው። ፕሮፌሰር የእኔ ማንነት አይደለም፤ ቤተሰቤን ለመደገፍ የምሰራው ስራ ነው እንጂ። የአጠቃላይ ባለስልጣን ሰባ የእኔ ማንነት አይደለም፤ በዚህ ጊዜ በመንግሥቱ ውስጥ የማገለግልበት ነው እንጂ።

ፕሬዘደንት ኔልሰን እንዳስታወሱን፣ “በመጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ፣ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ።”6 እናንተም እንዲሁ ናችሁ፤ እናም በአካባቢያችን ያሉም ሁሉም ሰዎች እንዲሁ ናቸው። ይህን አስደናቂ እውነት በይበልጥ በማድነቅ እንድናከብረው እጸልያለሁ። ይህም ሁሉንም ነገር ይለውጣል!

በተለያዩ ባህሎች ውስጥ ያደግን ልንሆን እንችላለን፤ ከተለያዩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ልንመጣ እንችላለን፤ ዜግነትን፣ የቆዳ ቀለምን፣ የምግብ ምርጫዎችን፣ የፖለቲካ ዝንባሌን፣ ወዘተ ጨምሮ ምድራዊ ቅርሶቻችን በጣም ሊለያዩ ይችላሉ። እኛ ግን፣ ሁላችንም፣ ማንም ሳይቀር፣ ልጆቹ ነን። በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አንድ አይነት መለኮታዊ ምንጭ እና ገደብ የለሽ አቅም አለን።

ሲ.ኤስ. ሉዊስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ለማናገር የማያስደስት በጣም ደብዛዛ ሰው አንድ ቀን አምላክ ሆኖ አሁን ብናየው፣ ለማምለክ በጣም የምንፈተንበት ፍጡር ሊሆን በሚችልበት ማህበረሰብ ውስጥ መኖር ከባድ ነገር ነው። … ተራ የሚባል ሰው የለም። ከተራ ሟች ጋር ተነጋግራችሁ አታውቁም። ብሔሮች፣ ባህሎች፣ ጥበቦች፣ ሥልጣኔ—እነዚህ ጠፊ ናቸው፣ ህይወታቸው ከእኛ ጋር ሲስተያይ እንደ ትንኝ ህይወት ነው። ነገር ግን የምንቃለዳቸው፣ አብረውን የሚሰሩት፣ የምንጋባቸው፣ የምንኮራባቸው እና የምንበዘብዛቸው የማይሞቱ ናቸው።”7

ቤተሰባችን በተለያዩ አገሮች እና ባህሎች ውስጥ የመኖር እድል አግኝቷል፤ ልጆቻችን ከተለያዩ ብሄረሰቦች ጋር ተጋብተው ተባርከዋል። ዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሁሉን እኩል አድራጊ መሆኑን ተረድቻለሁ። እኛ በእውነት ስንቀበለው፣ “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።”8 ይህ አስደናቂ እውነት ነፃ ያወጣናል፣ እንዲሁም እኛን እና እርስ በርስ ያለንን ግንኙነት ሊጎዱ የሚችሉ መለያዎች እና ልዩነቶች በቀላሉ “በክርስቶስ … [ይዋጣሉ]።”9 እኛ፣ እንዲሁም ሌሎች፣ “ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች [ነን] እንጂ እንግዶችና መጻተኞች”10 እንዳልሆንን ግልፅ ሆኗል።

አንድ የተለያየ ባህል እና ቋንቋ ክፍል ያለው ቅርንጫፍ ፕሬዘዳንት ይህንን፣ ሽማግሌ ገርሪት ደብሊው. ጎንግ እንዳደረጉት፣ የቃል ኪዳን መሆን እንደሆነ አድርገው ሲናገሩ ሰምቻለሁ።11 እንዴት ያለ ውብ ጽንሰ-ሀሳብ ነው! እኛ ሁላችንም አዳኙን እና ቃል ኪዳናቸውን በህይወታቸው ማእከል ላይ ለማድረግ እና ወንጌልን በደስታ ለመኖር የሚጥሩ ሰዎች ቡድን ነን። ስለዚህ፣ በተዛባ የሟችነት መነፅር እርስ በርሳችን ከመተያየት ይልቅ፣ ወንጌል እይታችንን ከፍ ያደርጋል እንዲሁም በማይለወጥ የቅዱስ ኪዳኖቻችን መነጽር እርስ በርሳችን እንድንተያይ ያስችለናል። ይህን በማድረግ፣ የራሳችንን ተፈጥሯዊ ጭፍን ጥላቻ እና ለሌሎች ያለንን አድሎአዊ አመለካከት ማስወገድ እንጀምራለን፣ ይህም በተራው በሚያስደንቅ በጎ ኡደት ለእኛ ያላቸውን ጭፍን ጥላቻ እና አድሎ እንዲቀንሱ ይረዳቸዋል።12 በእርግጥም፣ ውድ ነቢያችን እንደጋበዙን፦ “ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ አንዳችን ሌላችንን የምንንከባከብበት መንገድ በጣም አስፈላጊ ነው! በቤት ውስጥ፣ በቤተክርስቲያን፣ በስራ ቦታ እና በበይነመረብ ላይ ሌሎችን የምናነጋግርበት እና ስለእነርሱ የምናወራበት መንገድ በጣም አስፈላጊ ነው። ዛሬ፣ ከፍ ባለ እና ቅዱስ በሆነ መንገድ ከሌሎች ጋር እንድንገናኝ እጠይቃለሁ።”13

በዚህ ከሰአት በኋላ፣ በዚያ ግብዣ መንፈስ ፣ ቃል ኪዳኔን ለአስደናቂ የመጀመሪያ ደረጃ ልጆቻች ማከል እፈልጋለሁ፦

ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ካልተራመዳችሁ፣

አንዳንድ ሰዎች ከእናንተ ይርቃሉ፣

እኔ ግን አላደርገውም! አላደርገውም!

ብዙ ሰዎች እንደሚያወሩት የማትናገሩ ከሆነ፣

አንዳንድ ሰዎች ያወራሉ እንዲሁም ይስቁባችኋሃል፣

እኔ ግን አላደርገውም! አላደርገውም!

ከእናንተ ጋር እራመዳለሁ። ከእናንተ ጋር እነጋገራለሁ።

እንደዚህ ነው ለእናንተ ያለኝን ፍቅር የማሳየው።

ኢየሱስ ከማንም ሰው አልራቀም።

ፍቅሩን ለሁሉም ሰው ሰጥቷል።

እንደዚያውም አደርጋለሁ። አደርጋለሁ!14

የሰማይ አባታችን ብለን የምንጠራው፣ እርሱ በእርግጥ አባታችን እንደሆነ፣ እንደሚወደን፣ እያንዳንዱን ልጆቹን በቅርበት እንደሚያውቅ፣ ለእያንዳንዳቸው በጥልቅ እንደሚያስብ እና እኛ በእውነት ሁላችንም ከእርሱ ጋር በእርግጥም እንደምንመሳሰል እመሰክራለሁ። አንዳችን ሌላችንን የምንንከባከብበት መንገድ ለልጁ፣ ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው መስዋዕትነት እና የሃጢያት ክፍያ ያለን ግንዛቤ እና አድናቆት ቀጥተኛ ነጸብራቅ እንደሆነ እመሰክራለሁ። ልክ እንደ እርሱ፣ሌሎችን የምንወደው ትክክለኛው ነገር ስለሆነ እንጂ እነርሱ ትክክለኛውን ነገር እያደረጉ ስለሆነ ወይም “ትክክለኛውን” ነገር ስለሚገጥም እንዳልሆነ እጸልያለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።