ኢየሱስ ክርስቶስ ሀብቱ ነው
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አተኩሩ። እርሱ አዳኛችን እና ቤዛችን፣ ልንመለከተው የሚገባን “[ትኩረታችን]” እና ታላቁ ሀብታችን ነው።
በ1907 (እ.አ.አ) ጆርጅ ኸርበርት የተባለ አንድ ሀብታም እንግሊዛዊ፣ የካርናርቨን አምስተኛው አርል 1 ወደ ግብፅ በመሄድ አርኪኦሎጂ ላይ ፍላጎት አሳየ። ወደ ታዋቂው የግብፅ ጥናት አድራጊ ሃዋርድ ካርተር ቀርቦ የሽርክና ሀሳብ አቀረበ። ካርተር የአርኪኦሎጂ ቁፋሮዎቻቸውን እንዲቆጣጠር፣ ካርናርቨን ደግሞ ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ ሊሸፍን ተስማሙ።
በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተሳካ ሁኔታ በአንድነት አሰሳ አደረጉ። ከዚያም የብዙ ፈርዖኖች መቃብር በተገኘበት በዘመናዊቷ ሉክሶር አቅራቢያ የሚገኘውን የነገስታት ሸለቆ ለመቆፈር ፈቃድ አገኙ። የንጉሥ ቱታንክሃሙንን መቃብር ለመፈለግ ወሰኑ። ቱታንክሃሙን ከ3 ሺህ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በግብፅ ዙፋን ላይ የነበረ ሲሆን ያልተጠበቀ ሞት ከመሞቱ በፊት ለ10 ዓመታት ያህል ነግሶ ነበር። 2 በነገሥታት ሸለቆ ውስጥ እንደተቀበረ ቢታወቅም 3 መቃብሩ ያለበት ቦታ ግን አይታወቅም ነበር።
ካርተር እና ካርናርቨን የቱታንክሃሙንን መቃብር በመፈለግ አምስት አመታትን ያለስኬት አሳለፉ። በመጨረሻም ካርናርቮን ፍሬ አልባውን ፍለጋ ማጠናቀቁን ለካርተር አሳወቀው። ካርተር አንድ ተጨማሪ ቁፋሮ እንዲያደርጉ ተማጸነ፣ ካርናርቨንም ፈቃደኛ ሆነ ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈንም ተስማማ።
ካርተር ከራሳቸው ካምፕ አካባቢ በስተቀር የነገስታት ሸለቆ ወለል በሙሉ በዘዴ ተቆፍሮ እንደነበር ተገነዘበ። እዚያ መቆፈር በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ መቃብሩ የሚወርዱ የመጀመሪያዎቹን ደረጃዎች አገኙ። 4
ካርተር በመጨረሻም ወደ ቱታንክሃሙን መቃብር መግቢያ ውስጥ አተኩሮ ሲመለከት በየቦታው ወርቅ አየ። ለሦስት ወራት የመግቢያውን ይዘት ከዘረዘሩ በኋላ፣ የታሸገውን የቀብር ሳጥን በየካቲት 1923 (እ.አ.አ)—ከ100 ዓመታት በፊት ከፈቱ። ይህ የሃያኛው ክፍለ ዘመን በጣም ታዋቂው የአርኪኦሎጂ ግኝት ነበር።
በእነዚያ ውጤታማ ባልነበሩ የፍለጋ ዓመታት ውስጥ ካርተር እና ካርናርቨን በእግራቸው ስር ያለውን ነገር ችላ ብለውት ነበር። ከአምስት መቶ አመታት በፊት፣ የመፅሐፈ ሞርሞን ነቢይ ያዕቆብ በአቅራቢያ ያለን ነገር እንደ ቀላል ነገር መውሰድን ወይም ዋጋውን ማቃለልን “ከሚገባው በላይ ማተኮር” ሲል ይጠራዋል። ያዕቆብ የኢየሩሳሌም ሰዎች ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ሲመጣ እንደማይቀበሉት አስቀድሞ ተመልክቶ ነበር። ያዕቆብ “ግልፁን ቃላት [የሚንቁ] … የማይረዱትን ብዙ ነገሮች [የሚመኙ] እንደሚሆኑ። ስለሆነም፣ በመታወራቸው ምክንያት፣ እውርነቱም የሚመጣው ከሚገባው በላይ በማተኮር እንደሆነ” ተንብዩአል።5 በሌላ አነጋገር እነሱ ይሰናከላሉ።
የያዕቆብ ትንቢት ትክክል ሆነ። በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት፣ ብዙዎች በእርሱ ላይ ከማተኮር ይልቅ አነስተኛ አስፈላጊነት ባላቸው ነገሮች ላይ ከሚገባው በላይ ያተኩሩ ነበር። ከዓለም አዳኙ አልፈው ይመለከቱ ነበር። የሰማይ አባትን እቅድ በመፈጸም ላይ ያለውን ሚና ከመቀበል ይልቅ፣ አወገዙት ከዚያም ሰቀሉት። ደህንነትን የሚያመጣላቸውን ሌላ ሰው ፈለጉ እንዲሁም ጠበቁ።
እንደ ኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲሁም እንደ ካርተር እና ካርናርቨን፣ እኛም ከሚገባው በላይ የምናተኩር ልንሆን እንችላለን። ከዚህ ዝንባሌ ልንጠበቅ ይገባናል አለበለዚያ ኢየሱስ ክርስቶስን ከህይወታችን እናጣዋለን እንዲሁም የሚሰጠንን ብዙ በረከቶች ሳንገነዘብ እንቀራለን ። እንፈልገዋለን። “ለማዳን ኃያል በሆነው …ሙሉ በሙሉ መተማመን” 6 እንዳለብን ተመክረናል።
አላማችን እርሱ ነው። እሱ ከሚያደርግልን በላይ የሆነ ነገር እንደሚያስፈልግ በተሳሳተ መንገድ ካሰብን በሕይወታችን ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን የተፅዕኖ ወሰን እና ኃይል እንክዳለን ወይም እንቀንሳለን። ምህረትን ጠይቋል፣ ይህንንም ምህረት ለኛ ዘርግቷል። 7 እርሱ ታላቁ “ለኃጢአታችን ስርየት [መመልከት ያለብን] ምንጭ” ነው። 8 እርሱ ከአብ ዘንድ ጠበቃችን ነው እናም እኛም በመንግስቱ ውስጥ ወራሾች ሆነን እንድንመለስ አብ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ በማድረግ ይደግፈናል። በአልማ ቃላት እኛ “በዐይናች[ን] ወደዚህና ወደዚያ [እን]መልከት፣ እናም የእግዚአብሔር ልጅ ህዝቡን ሊያድን እንደሚመጣና፣ ለህዝቡ ኃጢያት ክፍያ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት፣ እናም ሰዎች እንደስራቸው በመጨረሻውና በፍርዱ ቀን እንዲፈረድባቸው በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ትንሳኤን ያመጣ ዘንድ በድጋሚ ከሙታን እንደሚነሳ ማመን [እንጀምር]”። 9 ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እጅግ ውድ ነው።
አዳኙ የእለት ተእለት የንስሃ እድልን ጨምሮ ሆን ብለን በእርሱ ላይ እንድናተኩር ብዙ መንገዶችን ሰጥቶናል። አንዳንድ ጊዜ፣ ይህንን የተሰጠንን ታላቅ በረከት አሳንሰን እንመለከተዋለን ። የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ በአባቴ ተጠመቅሁ። በኋላ ላይ፣ የተጨናነቀ መንገድ ልናቋርጥ ስንል እጁን ያዝኩ። ትኩረት እየሰጠሁ ስላልነበረ ከመንገዱ ጠርዝ ልክ እንደወጣሁ አንድ ትልቅ የጭነት መኪና እያጓራ መጣ። አባቴ ከመንገዱ ላይ ጎትቶኝ ወደ ጠርዙ መለሰኝ። እሱ ያን ባያደርግ ኖሮ በጭነት መኪናው እገጭ ነበር። ሥርዓት አልበኛ ተፈጥሮዬን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ “ምናልባት ከተጠመቅኩ በኋላ አሁን እንዳለሁት በፍጹም ንጹህ መሆን ስለማልችል በጭነት መኪናው ተገጭቼ ሞቼ ብሆን ይሻለኝ ነበር” ብዬ አሰብኩ።
እንደ ስምንት ዓመት ልጅነቴ፣ የጥምቀት ውኃ ኃጢአትን እንደሚያስወግድ በስህተት ገምቼ ነበር። እንደዚያ አይደለም! ከተጠመቅኩኝ በኋላ በነበሩት አመታት፣ የጥምቀትን ቃል ኪዳን ስንፈፅም እና ስንጠብቅ ኃጢያት በኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ ሃይል እንደሚነጻ ተማርኩ።10 ከዚያም፣ በንስሐ ስጦታ፣ ንጹሕ ሆነን መቆየት እንችላለን። እንዲሁም ቅዱስ ቁርባን በህይወታችን ውስጥ የኃጢአታችንን ስርየት እንድናቆይ የሚያስችለንን ኃይለኛ የምግባር ዑደት እንደሚያመጣ ተምሬአለሁ።11
ልክ በካርተር እና በካርናርቨን እግር ስር እንደነበረው ውድ ሀብት፣ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ በተሳተፍን ቁጥር ውድ የሆኑ የቅዱስ ቁርባን በረከቶችን እናገኛለን። አዲስ ወደ እምነታችን የተለወጠ ሰው ወደ ጥምቀት እና ማረጋገጫ እንደሚቀርብበት መንገድ፣ በተሰበረ ልብ እና የተዋረደ መንፈስ፣ የጥምቀት ቃል ኪዳናችንን ለመጠበቅ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ከወሰንን መንፈስ ቅዱስ የዘወትር አጋራችን እንደሚሆን ቃል ተገብቶልናል። የኃጢያታችንን ስርየት ከሳምንት እስከ ከሳምንት እንድናገኝ መንፈስ ቅዱስ በመቀደስ ሃይሉ ይባርከናል። 12
መንፈሳዊ መሠረታችን የሚጠናከረው በንስሐ እና በትጋት ቅዱስ ቁርባንን ለመካፈል በመዘጋጀት ነው። በህይወታችን የሚገጥሙንን ምሳሌያዊ ዝናብ፣ ንፋስ እና ጎርፍ ማስተናገድ የምንችለው በጠንካራ መንፈሳዊ መሰረት ብቻ ነው። 13 በተቃራኒው፣ የቅዱስ ቁርባን ስብሰባን ላለመካፈል ስንመርጥ ወይም በቅዱስ ቁርባን ጊዜ በአዳኙ ላይ ሳናተኩር ስንቀር መንፈሳዊ መሰረታችን ይዳከማል። ሳናስበው “[እራሳችንን ከጌታ መንፈስ አርቀን፣ እንድንባረክ፣ እንድንበለጽግ እናም እንድንጠበቅ ዘንድ በጥበብ ጎዳና እንዲመራን በእኛ ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው እራሳችንን እናወጣለን]”። 14
መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ሲሆን በቤተ መቅደሶች ውስጥ እንደምንገባቸው ያሉ ሌሎች ቃል ኪዳኖችን እንድንገባ እና እንድንጠብቅ እንመራለን። እንዲህ ማድረጋችን ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ያጠናክርልናል። 15 በቅርብ ዓመታት ውስጥ የብዙ አዳዲስ ቤተመቅደሶች ትውውቅ በመደረጉ ቤተመቅደሶች ለአባላት ይበልጥ እያቀረቡ እንደሆነ አስተውላችሁ ይሆናል።16 በሚቃረን መልኩ ቤተመቅደሶች ይበልጥ ተደራሽ ሲሆኑ፣ ቤተመቅደስ ውስጥ መገኘት ይበልጥ ተራ ነገር አድርጎ ማየቱ ቀላል ይሆንብናል። ቤተመቅደሶች እሩቅ ሲሆኑ፣ ወደ ቤተመቅደስ ለመጓዝ እና ለማምለክ ጊዜያችንን እና ሃብታችንን ለመጠቀም እናቅዳለን። ለእነዚህ ጉዞዎች ቅድሚያ እንሰጣለን።
ቤተ መቅደስ ቅርብ ከሆነ፣ ለራሳችን፣ “እሺ፣ ሌላ ጊዜ እሄዳለሁ” በማለት ትንንሽ ነገሮች እንቅፋት እንዲሆኑብን ማድረግ ቀላል ሊሆን ይችላል። በቤተመቅደስ አቅራቢያ መኖር የቤተመቅደስ የጊዜ መርሐግብር ተለዋዋጭ መሆን ምቹ ነው ነገር ግን ያው ተለዋዋጭ መሆኑ ቤተ መቅደስን እንዳናደንቅ ሊያደርግ ይችላል። ይህን ስናደርግ፣ ወደ አዳኙ ቅዱስ ቤት ለመቅረብ ያለውን እድል በማቃለል “እይታችንን እንስታለን”። ቤተመቅደስ በአቅራቢያችን በሚሆንበት ጊዜ ለመገኘት ያለን ቁርጠኝነት ሩቅ ሆኖ እንዳለ ጠንካራ መሆን አለበት።
ካርተር እና ካርናርቨን የቱታንክሃሙንን መቃብር ለመፈለግ በነገስታት ሸለቆ ውስጥ ሌላ ቦታ ከቆፈሩ በኋላ እንዳላስተዋሉ ተረዱ። ሀብታችንን ለማግኘት ለጊዜው እንዳደረጉት ያለ ስኬት መልፋት አይጠበቅብንም። እንዲሁም ለምንጩ አዲስነት ዋጋ በመስጠት እና እንደዚህ አይነት ምክር ከትሑት የእግዚአብሔር ነቢይ ከምንቀበለው የተሻለ ይሆናል ብለን በማሰብ ከልዩ ምንጮች ምክር መፈለግ አያስፈልገንም።
በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው ንዕማን ለሥጋ ደዌው መድኃኒት ሲፈልግ፣ ራሱን በአንድ በቅርብ በሚገኝ ተራ ወንዝ ውስጥ ሰባት ጊዜ እንዲያጠልቅ በመጠየቁ ተቆጥቶ ነበር። ነገር ግን ተአምራቱ እንዴት መምጣት እንዳለበት በራሱ አስተሳሰብ ከመታመን ይልቅ የነቢዩ ኤልሳዕን ምክር እንዲከተል አሳመኑት። በዚህም ምክንያት ንዕማን ተፈወሰ። 17 ዛሬ በምድር ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን ነቢይ ካመንን እና ምክሩን በተግባር ላይ ካዋልን ደስታ እናገኛለን፣ እኛም መፈወስ እንችላለን። ሌላ የትም ቦታ መመልከት የለብንም።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድታስታውሱና በእርሱ ላይ እንድታተኩሩ አበረታታችኋለሁ። እርሱ አዳኛችን እና ቤዛችን፣ ልንመለከተው የሚገባን “[ትኩረታችን]” እና ታላቁ ሀብታችን ነው። ወደ እሱ ስትመጡ፣ የህይወት ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ብርታት፣ ትክክል የሆነውን ነገር ለመስራት ድፍረት እና ምድራዊ ተልእኳችንን ለመወጣት በሚያስችል ብርታት ትሸለማላችሁ። የንስሐ እድልን፣ ቅዱስ ቁርባንን የመካፈል እድልን፣ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች የመግባት እና የመጠበቅ በረከትን፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የማምለክ ደስታን፣ እና ህያው ነቢይን የማግኘት ደስታን እንደ ውድ ሀብት አድርጉ።
የዘለአለም አባት እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ እና እርሱም ህያው እንደሆነ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ፤ እርሱም የእኛ ደግ፣ የሰማይ ጓደኛችን እንደሆነ፣18 እናም ይህን የእርሱ ዳግም የተመለሰች ቤተክርስቲያን እንደሆነች ጥብቅ ምስክሬን እሰጣችኋለሁ። ስለ እምነታችሁ እና ስለ ታማኝነታችሁ እናመሰግናለን። እንድትባረኩ፣ እንድትበለጽጉ እና እንድትጠበቁ እጸልያለሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።