ዘለአለማዊ እውነት
እውነትን የማወቅ ግዴታችን ከዚህ በላይ አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ለእግዚአብሔር አብ እና ለልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላደረጋችሁት ታማኝነት አመሰግናለው፣ እናም እርስ በርሳችሁ ለምታደርጉት ፍቅር እና አገልግሎት አመሰግናችኋለሁ። እናንተ በእውነትም አስደናቂ ናችሁ!
መግቢያ
ባለቤቴ አን እና እኔ በሙሉ ጊዜ ሚስዮን መሪነት እንድናገለግል ጥሪ ከተቀበልን በኋላ፣ ቤተሰባችን ወደ አገልግሎት ከመግባታችን በፊት የእያንዳንዱን ሚስዮናውያን ስም ለማወቅ ወሰንን። ፎቶዎችን አገኘን፣ የምናጠናባቸው ወረቀቶችን አዘጋጀን፣ እና ፊቶችን ማጥናት እና ስሞችን መገምገም ጀመርን።
በዚያ ከደረስን በኋላ፣ ከሚስዮናውያን ጋር የማስተዋወቂያ ስብሰባ አደረግን። እየተገናኘን እያለን፣ የዘጠኝ አመት ልጃችንን ይህን ሲል ሰማሁ፦
“ሳም፣ ስለተዋወቅን ደስ ብሎኛል!”
“ራሄል፣ ከየት ነሽ የመጣሽው?”
“ይገርማል ዳዊት፣ ረጅም ነህ!”
ደነገጥኩኝ፣ ወደ ልጃችን ሄጄ በሹክሹክታ፣ “ሚስዮናውያንን እንደ ሽማግሌ ወይም እህት መጥራታቸውን አናስታውስ” አልኩት።
ግራ የተጋባ እይታ ሰጠኝና፣ “አባዬ፣ ስማቸውን መገምገም ያለብን መስሎኝ ነበር” አለኝ። ልጃችን በመረዳቱ ላይ በመመሥረት ትክክል ነው ብሎ ያሰበውን አድርጓል።
ስለዚህ፣ በዛሬው ዓለም ውስጥ ስለ እውነት ያለን ግንዛቤ ምንድን ነው? ያለማቋረጥ በጠንካራ አስተያየቶች፣ በተዛባ ዘገባ እና ባልተሟሉ መረጃዎች እንጠቃለን። በተመሳሳይ፣ የዚህ መረጃ ምንጮች እና መጠን እያደጉ ናቸው። እውነትን የማወቅ ግዴታችን ከዚህ በላይ አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም።
ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነታችንን ለመመስረት እና ለማጠናከር፣ ሰላምን እና ደስታን ለማግኘት እንዲሁም መለኮታዊ አቅማችን ላይ ለመድረስ እውነት ወሳኝ ነው። ዛሬ፣ የሚቀጥሉትን ጥያቄዎች እናስብባቸው፦
-
እውነት ምንድን ነው እናም አስፈላጊ የሆነው ለምድነው?
-
እውነትን እንዴት እናገኛለን?
-
እውነትን ስናገኝ እንዴት ልናካፍል እንችላለን?
እውነት ዘለአለማዊ ነው
ጌታ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ “ነገሮች እንዳሉ፣ እንደነበሩ፣ እናም ወደፊት እንደሚሆኑ የሚታወቅበት እውነት ነው” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥24) በማለት አስተምሮናል። “የተፈጠረ ወይም የተሰራ አይደለም” ((ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥29) እናም “መጨረሻም የለውም” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥66)።1 እውነት ፍጹም፣ ቋሚ እና የማይለወጥ ነው። በሌላ አነጋገር እውነት ዘለአለማዊ ነው።2
እውነት መታለልን እንድንርቅ፣3 መልካሙን ከክፉ እንድንለይ፣4 ጥበቃን እንድንቀበል፣5 መጽናናትን እና ፈውስን እንድናገኝ ይረዳናል።6 እውነት ትግባራችንን ለመምራት፣7 ነጻ ሊያደርገን፣8 ሊቀድሰን፣9 እና ወደ ዘለአለም ህይወት ሊመራን10 ይችላል።
እግዚአብሔር ዘለአለማዊ እውነትን ይገልጣል
እግዚአብሔር ከራሱ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከመንፈስ ቅዱስ፣ ከነቢያት፣ እና ከእኛ ጋር በተያያዙ የመገለጥ የግንኙነቶች መረብ አማካኝነት ዘለአለማዊ እውነትን ይገልጥልናል። በዚህ ሂደት ውስጥ እያንዳንዱ ተሳታፊ ስላለው ለየት ያለ ግን እርስ በርስ የተቆራኘ ሚናዎችን እንወያይ።
በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር የዘለአለም እውነት ምንጩ ነው።11 እሱ እና ልጁ ኢየሱስ ክርቶስ12 ስለ እውነት ፍጹም ግንዛቤ አለው እናም ሁልጊዜ ከእውነት መርሆዎች እና ህጎች ጋር በሚስማማ መንገድ ይሰራል።13 ይህ ኃይል ዓለምን እንዲፈጥሩ እና እንዲያስተዳድሩ14 እንዲሁም እያንዳንዳችንን እንዲወዱን፣ እንዲመሩን እና እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል።15 እነርሱ የሚደሰቱባቸውን በረከቶች እንደሰትበት ዘንድ፣ እኛም እውነትን እንድንረዳ እናም እንድንጠቀም ይፈልጉናል።16 በአካል ወይም እንደ መንፈስ ቅዱስ፣ መላእክት፣ ወይም ህያዋን ነቢያት ባሉ መልእክተኞች በኩል እውነትን ሊነግር ይችላል።
ሁለተኛ፣ መንፈስ ቅዱስ ስለ እውነት ሁሉ ይመሰክራል።17 እውነትን ለእኛ በቀጥታ ይገልጻል እናም ሌሎች ስለሚያስተምሩት እውነቶችም ይመሰክራል። ከመንፈስ የሚመጡ ግንዛቤዎች እንደ ሀሳቦች ወደ አእምሯችን እና ወደ ልባችን እንደ ስሜቶች ይመጣሉ።18
አራተኛ፣ ነቢያት ከእግዚአብሔር እውነትን ተቀብለው ያንን እውነት ለእኛ ያካፍላሉ።19 በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከነበሩት ከድሮ ነቢያት20 እና በአጠቃላይ ጉባኤ ወቅት ከህያዋን ነቢያት እንዲሁም ከሌሎች በይፋ የመገናኛ መንገዶች እውነትን እንማራለን።
በመጨረሻም፣ እናንተ እና እኔ በዚህ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንጫወታለን። እግዚአብሔር እውነትን እንድንፈልግ፣ እንድናውቅ፣ እና እንድንሰራበት ይፈልገናል። እውነትን የመቀበል እና የመተግበር አቅማችን ከአብ እና ከወልድ ጋር ባለን ግንኙነት ጥንካሬ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ ባለን ምላሽ እና ከኋለኛው ቀን ነቢያት ጋር ባለን አሰላለፍ ላይ የተመሰረተ ነው።
ሰይጣን የሚሠራው ከእውነት እንድንርቅ መሆኑን ማስታወስ አለብን። ያለ እውነት የዘለአለም ህይወት ማግኘት እንደማንችል ያውቃል። እኛን ግራ ለማጋባት እና ከእግዚአብሔር ከተነገረው ነገር ለማዘናጋት የእውነትን ሰንሰለት ከዓለማዊ ፍልስፍናዎች ጋር ይሸምናል።21
ዘለአለማዊ እውነትን መፈለግ፣ ማወቅ እና መተግበር
ዘለአለማዊ እውነትን በምንፈልግበት ጊዜ፣22 የሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች ሃሳቡ ከእግዚአብሔር ወይም ከሌላ ምንጭ የመጣ እንደሆን ለማወቅ ይረዱናል።
-
ሐሳቡ ቅዱሳት መጻሕፍት ወይም ህያዋን ነቢያት ያለማቋረጥ የሚያስተምሩት ነውን?
-
ሃሳቡ በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት የተረጋገጠ ነውን?
እግዚአብሔር እውነትን በነቢያት በኩል ይገልጣል፣ እናም መንፈስ ቅዱስ እነዚያን እውነቶች ለእኛ ያረጋግጣል እናም እንድንጠቀምባቸው ይረዳናል።23 እነዚህን መንፈሳዊ መነሳሻዎች ለመፈለግ እና ሲመጡም ለመቀበል መዘጋጀት አለብን።24 ትሁት ስንሆን፣25 ከልባችን ስንጸልይና የእግዚአብሔርን ቃል ስናጠና፣26 እናም ትእዛዛቱን ስንጠብቅ27 የመንፈስን ምስክርነት እንቀበላለን።
መንፈስ ቅዱስ ልዩ እውነትን ካረጋገጠልን በኋላ፣ ያን መርህ በተግባር ስናውል በጥልቅ ለመረዳት እንችላለን። በጊዜ ሂደት፣ መርህን በተከታታይ ስንኖር፣ የዚያን እውነት እርግጠኛ እውቀት እናገኛለን።28
ለምሳሌ እኔ ስህተት ሰርቻለሁ እናም ለደካማ ምርጫዎች ተፀፅቻለሁ። ነገር ግን በጸሎት፣ በማጥናት እና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን፣ የንስሐን መርህ ምስክር ተቀብያለሁ።29 ንስሀ መግባት ስቀጥል፣ ስለ ንስሀ ያለኝ ግንዛቤ እየጠነከረ መጣ። ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ልጁ ይበልጥ እንደቀረብኩ ተሰማኝ። በየእለቱ የንስሐን በረከቶች ስለማገኝ፣ ኃጢአት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንደሚሰረይ አሁን አውቃለሁ።30
እውነት ገና ሳይገለጥ በእግዚአብሔር መታመን
ስለዚህ ገና ያልተገለጠን እውነት ከልባችን ስንፈልግ ምን ማድረግ አለብን? የማይመጡ የሚመስሉ መልሶችን ለማግኘት ለምንናፍቀው ታላቅ አዘኔታ አለኝ።
ጆሴፍ ስሚዝ ጌታ “ነገሩን በተመለከተ … እስካሳውቅ ድረስ ዝም በል” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥37) በማለት መክሮት ነበር።
እናም ለኤማ ስሚዝም “ስላላየሻቸው ነገሮች አታጉረምርሚ፣ ከአንቺ እና ከአለም ታግደዋል፣ ይህም ወደፊት በሚመጣው በእኔ ዘንድ ጥበብ ነው” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 25፥4) በማለት አብራርቷል።
እኔም በልብ ለሚሰሙ ያቄዎች መልሶች ፈልጌአለሁ። ብዙ መልሶች መጥተዋል፣ አንዳንዶች አልመጡም።31 የእግዚአብሔርን ጥበብ እና ፍቅር በማመን፣ ትእዛዛቱን በመጠበቅ እና በምናውቀው ላይ በመታመን ስንጠብቅ፣ የሁሉንም ነገር እውነት እስኪገልጥ ድረስ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል።32
ትምህርትን እና ፖሊሲዎችን መረዳት
እውነትን በምንፈልግበት ጊዜ፣ በወንጌላዊ ትምህርት እና በፖሊሲ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ይረዳል። ወንጌላዊ ትምህርት የሚያጠቁመው እንደ የአምላክ ተፈጥሮ፣ የመዳን እቅድ፣ እና የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት አይነት ዘለአለማዊ እውነቶችን ነው። ፖሊሲ በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ የወንጌላዊ ትምህርት አተገባበር ነው። ፖሊሲዎች እኛ ቤተክርስቲያንን በሥርዓት እንድናስተዳድር ያግዙናል።
ወንጌላዊ ትምህርት መቼም የማይለወጥ ሲሆን ፖሊሲ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይስተካከላል። ጌታ በነቢያቱ በኩል ወንጌላዊ ትምህርቱን ለመጠበቅ እና የቤተክርስቲያንን ፖሊሲዎች እንደ ልጆቹ ፍላጎት ለማሻሻል ይሰራል።
በሚያሳዝን ሁኔታ፣ አንዳንድ ጊዜ ፖሊሲን ከወንጌላዊ ትምህርት ጋር እንደባልቃለን። ልዩነቱን ካልተረዳን፣ ፖሊሲዎች ሲቀየሩ በተሳሳተ ሃሳብ የምንጓዝ ወደመሆን አድጋ ላይ ያደርሰናል፣ እናም አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔርን ጥበብ ወይም የነቢያትን የመገለጥ ሚና ለመጠራጠር እንዲጀምሩ ሊያደርግ ይችላል።33
ዘለአለማዊ እውነትን ማስተማር
እውነትን ከእግዚአብሔር ስናገኝ ያንን እውቀት ለሌሎች እንድናካፍል ያበረታታናል።34 ይህንን የምናደርገው በክፍል ውስጥ ስናስተምር፣ ልጅን ስንመራ ወይም ከጓደኛ ጋር ስለወንጌል እውነት ስንወያይ ነው።
አላማችን የመንፈስ ቅዱስን የመለወጥ ሀይል በሚጋብዝ መልኩ እውነትን ማስተማር ነው።35 ከጌታ እና ከነቢያቱ የተሰጡ ሊረዱ የሚችሉ አንዳንድ ቀላል ግብዣዎችን ላካፍላችሁ።36
-
የሰማይ አባት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እና መሠረታዊ ትምህርታቸውን ማእከላዊ አድርጉ።37
-
በቅዱሳት መጻህፍት እና በኋለኛው ቀን ነቢያት ትምህርቶች መሰረት ላይ ጽኑ።38
-
በብዙ ሥልጣናዊ ምስክሮች አማካይነት በተቋቋመው ትምህርት ላይ ተደገፉ።39
-
ግምቶችን፣ የግል አስተያየቶችን ወይም ዓለማዊ ሃሳቦችን አስወግዱ።40
-
ሚዛናዊ ግንዛቤን ለማጎልበት የትምህርት ነጥብን በተዛማጅ የወንጌል እውነቶች አውድ አስተምሩ።41
-
የመንፈስን ተጽዕኖ የሚጋብዙ የማስተማሪያ ዘዴዎችን ተጠቀሙ።42
-
አለመግባባትን ለማስወገድ ግልጽ በሆነ መንገድ ተነጋገሩ።43
እውነትን በፍቅር መናገር
እውነትን የምናስተምርበት መንገድ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ “እውነትን በፍቅር” እንድንናገር አበረታቶናል (ኤፌሶን 4፥14–15 ተመልከቱ)። ይህ ማለት እውነት ክርስቶስን በሚመስል ፍቅር ሲተላለፍ ሌላውን ለመባረክ ከሁሉ የተሻለ እድል አለው ማለት ነው።44
ያለ ፍቅር የተነገረ እውነት የመፍረድ፣ የተስፋ መቁረጥ እና የብቸኝነት ስሜትን ያስከትላል። ብዙውን ጊዜ ወደ ብስጭት እና መለያየት አልፎ ተርፎም ግጭት ያስከትላል። በሌላ በኩል እውነት የሌለው ፍቅር ባዶ ነው እንዲሁም የማደግ ተስፋ የለውም።
እውነትም ፍቅርም ለመንፈሳዊ እድገታችን ወሳኝ ናቸው።45 እውነት የዘለአለምን ህይወት ለማግኘት፣ አስፈላጊ የሆኑትን ትምህርቶች፣ መርሆች እና ህጎች የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ እውነትን በፍቅር መናገር እውነት የሆነውን ለመቀበል እና በተግባር ለማዋል የሚያስፈልገውን መነሳሳት ይፈጥራል።
በትዕግስት ዘለአለማዊ እውነትን በፍቅር ላስተማሩኝ ሰዎች ለዘለአለም አመስጋኝ ነኝ።
መደምደሚያ
ለማጠቃለል ያህል፣ ለነፍሴ መልህቅ የሆኑትን ዘለአለማዊ እውነቶችን ላካፍል። ዛሬ የተብራሩትን መሰረተ መርሆች በመከተል የእነዚህን እውነቶች እውቀት አግኝቻለሁ።
እግዚአብሔር አፍቃሪ የሰማይ አባታችን እንደሆነ አውቃለሁ።46 እርሱም ሁሉን የሚያውቅ፣47 ሁሉን ቻይ፣48 እና በፍጹም የሚያፈቅር ነው።49 እርሱ የዘለአለም ህይወትን ለማግኘት እና እርሱን እንድንመስል እቅድ ፈጥሯል።50
እንደዚያ እቅድ አካል ከኃጢአት እና ከሞት ያድነን ዘንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ልኳል።51 የአብን ፈቃድ እንድንፈጽም52 እና ሌሎችን እንድንወድ አስተምሮናል።53 ለኃጢአታችን ዋጋን በመክፈል54 በፈቃዱም ነፍሱን በመስቀል ላይ አሳልፎ ሰጥቷል።55 ከሞም በሶስተኛው ቀን ተነሳ።56 በክርስቶስ እና በጸጋው፣ እኛም ከሞት እንነሳለን፣57 ይቅርታ ለማግኘት እንችላለን፣58 እናም በስቃያችን ጥንካሬ ማግኘት እንችላለን።59
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ቤተክርስቲያኑን አቋቋመ።60 በጊዜ ሂደት፣ ቤተክርስቲያኑ ተለወጠች፣ እውነቶችም ጠፉ።61 ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን እና የወንጌል እውነቶችን በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል በዳግም መለሰ።62 እናም ዛሬ፣ ክርስቶስ በህያዋን ነቢያት እና ሐዋርያት አማካኝነት ቤተክርስቲያኑን መምራት ቀጥሏል።63
ወደ ክርስቶስ ስንመጣ በመጨረሻ “በእርሱ ፍፁማን [ልንሆን]”(ሞሮኒ 10፥32)፣ “የደስታን ሙላት” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥33)ልናገኝ እንዲሁም “አብ ያለውን ሁሉ” ልንቀበል እንደምንችል አውቃለሁ። (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥38)። ስለዚህ ዘለዓለማዊ እውነታ በኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሰ ስም እመሰክራለሁ፣ አሜን።