አጠቃላይ ጉባኤ
የእናንተ መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ዘላለማዊ እጣ ፈንታ
የሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:9

የእናንተ መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ዘላለማዊ እጣ ፈንታ

ሕይወታችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲያተኩር እንድታደርጉ እና በወጣት ሴቶች ጭብጥ ውስጥ ያሉትን መሰረታዊ እውነታዎች እንድታስታውሱ እጋብዛችኋለሁ።

ውድ እህቶች፣ እዚ ስላላችሁ አመሰግናለሁ። በዚህ የሴቶች አጠቃላይ ስብሰባ ውስጥ በመሳተፌ ክብር ይሰማኛል። በተወሰኑ አጋጣሚዎች የወጣት ሴቶች ክፍሎችን የመሳተፍ እድል አግኝቻለው። ነገር ግን ግልፁን ነገር ልጠቁም—ወጣት አይደለሁም እንዲሁም ሴት አይደለሁም! ይሁን እንጂ የወጣት ሴቶችን ጭብጥ ከወጣት ሴቶች ጋር አብሬ ካነበብኩኝ ካለቦታዬ የሆንኩኝ መስሎ እንደማይሰማኝ ተማርኩኝ። በወጣት ሴቶች ጭብጥ ውስጥ የሚሰጠው ጥልቅ ትምህርት1 ለወጣት ሴቶች ጠቃሚ ነው፣ ነገር ግን ወጣት ሴቶች ላልሆንነውም ጨምሮ ለሁሉም ተግባራዊ ነው።

የወጣት ሴቶች ጭብጥ እንዲህ ይጀምራል፣ “መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ዘላለማዊ እጣ ፈንታ ያለኝ የሰማይ ወላጆች ተወዳጅ ሴት ልጅ ነኝ።”2 ይህ ዓረፍተ ነገር አራት ጠቃሚ እውነታዎችን ይዟል። አንደኛ፣ እናንተ ተወዳጅ ሴት ልጆች ናችሁ። ምንም የምታደርጉት—ወይም የማታደርጉት ነገር—ያንን መቀየር አይችልም። እግዚአብሔር ይወድሻል ምክንያቱም እንቺ የእርሱ የመንፈስ ሴት ልጅ ነሽ። አንዳንድ ጊዜ የእርሱ ፍቅር ላይሰማን ይችላል፣ ነገር ግን ሁሌም እዛ አለ። የእግዚአብሔር ፍቅር ፍፁም ነው።3 ያንን ፍቅር የመረዳት ችሎታችን ግን ፍፁም አይደለም።

መንፈስ የእግዚአብሔርን ፍቅር ለኛ ለማስረዳት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።4 ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ ተፅዕኖ “እንደ ቁጣ፣ ጥላቻ፣ … [ወይም] ፍርሃት ባሉ ጠንካራ ስሜቶች ሊሸፈንና የሚያቃጥለውን የሃላፔነኖ ቃሪያ እየበሉ ወይንን ለማጣጣም እንደመሞከር ሊሆን ይችላል።… [የአንዱ ጣዕም] የሌላውን ሙሉ በሙሉ ይሸፍነዋል።”5 በመሆኑም ሃጢያትን ጨምሮ ከመንፈስ ቅዱስ የሚያርቁን ባህርያት፣6 እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ማወቃችንን ከባድ ያደርጉታል።

በተመሳሳይ መልኩ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር የመረዳት ችሎታችን ሌሎች ነገሮችም እንዳሉ ሆነው በፈታኝ ሁኔታዎች እና በአካላዊ ወይም በአዕምሮአዊ ህመሞች ሊደበዝዝ ይችላል። በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ውስጥ፣ የታማኝ መሪዎች ወይም የባለሞያዎች ምክር አብዛኛውን ጊዜ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የእግዚአብሔርን ፍቅር የመቀበል ችሎታችንን ለማሻሻል እራሳችንን ይህን መጠየቅ ልንሞክር እንችላለን፣ “ለእግዚአብሔር ያለኝ ፍቅር ቋሚ ነው ወይስ መልካም ቀን ሲኖረኝ እወደዋለሁ፣ ነገር ግን መጥፎ ቀን ሲኖረኝ ያን ያህል አልወደውም?”

ሁለተኛው እውነት የሰማይ ወላጆች አባት እና እናት ያለን መሆኑ ነው።7 የሰማይ እናት ትምህርት በራዕይ ይመጣል እናም በኋለኛው ቀን ቅዱሳን ውስጥ ለየት ያለ እምነት ነው። ፕሬዝደንት ዳለን ኤች. ኦክስ የዚህን እውነታ ጠቀሜታ እንዲህ ገልጸዋል፦ “መንፈሳዊ ትምህርታችን በሰማይ ወላጆች ይጀምራል። ከፍተኛው ምኞታችን እንደእነርሱ መሆን ነው።”8

ስለሰማይ እናት ትንሽ ነው የተገለፀው፣ ነገር ግን የምናውቀው በወንጌል ቤተ መጻህፍት መተግበሪያ ውስጥ በሚገኘው የወንጌል ርዕስ ጽሁፍ ውስጥ ተጠቃሏል።9 እዚያ ያለውን ስታነቡ ስለርዕሱ እኔ የማውቀውን በሙሉ ታውቃላችሁ። የበለጠ ባውቅ እመኛለው። እናንተም እስካሁን ጥያቄ ሊኖራችሁ ይችላል እናም ብዙ መልሶችን ለማግኘት ትሻላችሁ። ታላቅ እውቀትን መሻት የመንፈሳዊ እድገት ጠቃሚ አካል ነው፣ ነገር ግን እባካችሁን ተጠንቀቁ። ምክንያት ራዕይን አይተካም።

ግምታዊ ምክንያት ወደ ታላቅ እውቀት አይመራም፣ ነገር ግን ወደ መታለል ሊመራ ወይም ትኩረታችንን ከተገለጠው ሊያስቀይር ይችላል10። ለምሳሌ፣ አዳኙ ደቀ መዛሙርቶቹን እንዲህ አስተምሯል፣ “ሁሌም ለአብ በስሜ ጸልዩ።”11 ይህንን ንድፍ እንከተላለን እናም አምልኳችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወደ ሰማይ አባታችን እናደርጋለን እናም ለሰማይ እናት አንፀልይም።12

እግዚአብሔር ነብያትን ከመረጠ ጊዜ ጀምሮ በእርሱ ምትክ እንዲናገሩ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን “[ከራሳቸው] አዕምሮ” የተገለፀ ትምህርቶችን አይናገሩም13 ወይም ያልተገለፀን አያስተምሩም። ሞአብን ለመጥቀም እስራኤሎችን እንዲረግም ጉቦ የተሰጠውን የብሉይ ኪዳን ነብይ የለዓምን ቃላት አስቡ። በለዓምም እንዲህ አለ፣ “[የሞአብ ንጉሥ] በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም።”14 የኋለኛው ቀን ነብያት በተመሳሳይ ሁኔታ ግዴታ አለባቸው። የእግዚአብሔር ራዕይ በግድ እንዲገለጥ መፈለግ እብሪተኝነት እና ውጤት አልባ ነው። በምትኩ የእርሱን እውነቶች እርሱ በመሰረተው መንገድ እንዲገልፅ ጌታን እና የእርሱን ሰዓት እንጠብቃለን።15

በወጣት ሴቶች ጭብጥ የመክፈቻ አንቀፅ ውስጥ ሶስተኛው እውነታ “መለኮታዊ ተፈጥሮ” ያለን መሆናችን ነው። ይህ ለማንነታችን አስፈላጊ ነው። ከሰማይ ወላጆቻችን የወረስነው መንፈሳዊ “ዘረ መል” ነው16 እና በኛ በኩል ምንም ጥረትን አይሻም ። እራሳችንን ምንም በሌላ ነገር ለመለየት ብንመርጥም ይህ የእኛ በጣም ወሳኝ የሆነ ማንነታችን ነው። ይህን ጥልቅ እውነታ መረዳት ለእያንዳንዱ ጠቃሚ ነው፣ በተለይ በታሪክ የተገለሉ፣ የተጨቆኑ ወይም የተገዙ ቡድኖች አካል ለሆኑ ግለሰቦች። የእናንተ ወሳኝ ማንነት እንደ የእግዚአብሐር ልጅ ከመለኮታዊ ተፈጥሮአችሁ ጋር እንደሚዛመድ አስታውሱ።

አራተኛው እውነታ “ዘላለማዊ እጣ ፈንታ” ያለን መሆኑ ነው። እንደዚህ ዓይነቱ እጣ ፈንታ በግዴታ በእኛ ላይ አይሆንም። ከሞት በኋላ፣ ብቁ የሆንበትን ነገር እንቀበላለን እናም “ለመቀበል ፍቃደኛ የሆነውን [ብቻ] እናጣጥማለን።”17 ዘላለም እጣ ፈንታችንን በምጫዎቻችን ላይ የተመረኮዘ መሆኑን በመገንዘብ። ቅዱስ ቃልኪዳኖችን መግባት እና መጠበቅ ይጠይቃል። ይህ የቃልኪዳን መንገድ ወደ ክርስቶስ የምንመጣበት መንገድ ነው እናም በፍፁም እውነታ እና ዘላለማዊ የማይቀየር ህግ ላይ የተመሰረተ ነው። የራሳችንን መንገድ በመፍጠር በእግዚአብሔር ቃል የተገቡ ወጤቶችን መጠበቅ አንችልም። የዘላለም ህጎችን ሳይከተሉ የተያያዙትን የእርሱን በረከቶች መጠበቅ18 የተሳሳተ ነው፣ ልክ ትኩስ ምድጃን በመንካት አንቃጠልም ብሎ “እንደመወሰን” ያክል ነው።

የልብ ችግር ያለባቸውን ታማሚዎች እንደምንከባከብ ልታውቁ ትችላላችሁ። የእነሱ የተሻለ ውጤት የሚገኘው የተደነገገ፣ ማስረጃን መሰረት ያደረገ የህክምና ዕቅዶችን በመከተል ነው። ይህንን ቢያውቁም የተወሰኑ ህሙማን የተለየ የህክምና ዕቅድን ለመደራደር ይሞክራሉ። “ብዙ መዳኒቶችን መውሰድ አልፈልግም” ወይም “ብዙ የክትትል ምርመራዎችን ማድረግ አልፈልግም” ይላሉ። በእርግጥ ህሙማን የራሳቸውን ውሳኔ ለመወሰን ነፃ ናቸው፣ ነገር ግን ከጥሩ የህክምና ዕቅዶች ከራቁ ውጤታቸው አስከፊ ይሆናል። የልብ ችግር ያለባቸው ህሙማን ዝቅ ያለን መንገድ መምረጥ እና ዝቅ ያለ ውጤታቸውን በልብ ሀኪማቸው ላይ ማሳበብ አይችሉም።

ይህ ለእኛም ተመሳሳይ ነው። በሰማይ አባት የተነደፈው መንገድ ወደተሻሉ ዘላለማዊ ውጤቶች ይመራል። ለመምረጥ ነፃ ነን፣ ነገር ግን የተገለጠውን መንገድ ባለመከተል የሚመጣውን ውጤት አለመምረጥ አንችልም።19 ጌታ እንዲህ ብሏል፣ “ህግን የሚሰብርና በህግ የማይጸናው፣ በራሱ ህግ ለመሆን የሚፈልገው፣ … በህግ ወይም በምህረት፣ በፍትህ፣ ወይም በፍርድ ሊቀደስ አይችልም።”20 ከሰማይ አባት መንገድ ከራቅን በኋላ የሚመጡትን ዝቅ ያሉ ውጤቶች በእርሱ ላይ ማሳበብ አንችልም።

በወጣት ሴቶች ጭብጥ ውስጥ ሁለተኛው አንቀፅ እንዲህ ይላል፦ “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙርነቴ እንደ እሱ ለመሆን እጥራለሁ። ግላዊ ራእይ እሻለሁ በሱም መሰረት እተገብራለሁ እንዲሁም በተቀደሰ ስሙ ሌሎችን አገለግላለሁ። በእምነት በመተግበር ስለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ምስክርነትን ማዳበር እንችላለን።21 “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ እና ለአለምም ኃጢአት እንደተሰቀለ ለማወቅ” መንፈሳዊ ስጦታን መጠየቅ እንችላለን። ወይም በራሳችን ማወቅ እስከምንችል ድረስ የሚያውቁ ሰዎችን ቃላት ለማመን የሚያስችል ስጦታን መቀበል እንችላለን።22 የአዳኙን ትምህርቶች መከተል እና ሌሎችን ወደ እርሱ እንዲመጡ መርዳት እንችላለን። በዚህ መንገድ፣ እርሱን በስራው እንቀላቀለዋለን።23

የወጣት ሴቶች ጭብጥ እንዲህ ይቀጥላል፣ “በሁሉም ጊዜ እና በሁሉም ነገር እና በሁሉም ቦታ የእግዚአብሄር ምስክር ሆኜ እቆማለሁ።” ሁሉም የቤተክርስቲያን አባሎች እንደ እግዚአብሔር ምስክሮች ያስፈልጋሉ፣24 ምንም እንኳን ሐዋርያቶች እና ሰባዎች እንደ ክርስቶስ ስም ልዩ ምስክሮች ቢሾሙም።25 አንድ ጎል ጠባቂ ጎል የሚጠብቅበትን የእግር ኳስ ግጥሚያ አስቡ። ያለቡድን አባሎች እርዳታ ጎል ጠባቂው በበቂ ሁኔታ ጎሉን መጠበቅ አይችልም እንዲሁም ቡድኑ ሁሌም ይሸነፋል። ስለሆነም እያንዳንዱ ሰውም በጌታ ቡድን ውስጥ ይፈለጋል።26

የወጣት ሴቶች ጭብጥ የመጨረሻው አንቀፅ እንዲህ ይጀምራል፣ “ከፍ ለመደረግ ብቁ ለመሆን ስጥር፣ ለንስሀ ስጦታ ከፍተኛ ቦታ እሰጣለው፣ እናም በየቀኑ ለመሻሻል እፈልጋለሁ።” በኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ አማካኝነት ንስሃ መግባት፣ ከስህተታችን መማር እና በእነሱ አለመኮነን እንችላለን። ፕሬዝደንት ረስል ኤም ኔልሰን እንዲህ አስተምረዋል፦ “ብዙ ሰዎች ንስሃ መግባትን እንደ ቅጣት ይቆጥራሉ።… ነገር ግን ይህ ቅጣት ነው የሚለው ስሜት በሰይጣን የተፈጠረ ነው። ሊያድነን፣ ይቅር ሊለን፣ ሊያጸዳን፣ ሊያነጻን እና ሊቀድሰን እየፈለገ እና ተስፋ እያደረገ እጆቹን ከፍቶ ወደ ቆመው ወደ ኢየሱስ ክርስቶሰ እንዳንመለከት ሊገድበን ይሞክራል።”27

በትህትና ንስሃ ስንገባ፣ ምንም ብናደርግም፣ ምንም ያህል የከፋ ቢሆንም ወይም ለምንም ያህል ጊዜ ንስሃ ብንገባም እንኳን ምንም መንፈሳዊ ጠባሳ አይኖርም።28 ንስሃ በገባን እና ከልብ ይቅርታን በፈለግን ቁጥር፣ ይቅር ልንባል እንችላለን።29 ከአዳኛችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ እንዴት ያለ አስደናቂ ስጦታ ነው!30 መንፈስ ቅዱስ ይቅር እንደተባልን ሊያረጋግጥልን ይችላል። ደስታን እና ሰላምን ስናጣጥም፣31 የጥፋተኝነት ስሜት ይጠፋል፣32 እንዲሁም በሃጢያታችን አንሰቃይም።33

ይሁን እንጂ፣ ልባዊ ንስሃ ከገባን በኋላም እንኳ ልንሰናከል እንችላለን። መሰናከል ንስሃው በቂ አልነበረም ማለት አይደለም፣ ነገር ግን የሰውን ድካም ብቻ ሊያሳይ ይችላል። “ጌታ ድክመትን ከአመጻ በተለየ መልኩ እንደሚመለከት” ማወቅ እንዴት አፅናኝ ነው። አዳኙ ድክመታችንን አስመልክቶ ያለውን የመርዳት ችሎታ መጠራጠር የለብንም ምክንያቱም “ጌታ ስለ ድክመቶች ሲናገር፣ ሁሌም በምህረት ነው።”34

የወጣት ሴቶች ጭብጥ እንዲህ ያጠቃልላል፣ “በእምነት ቤቴን እና ቤተሰቤን አጠነክራለሁ፣ የተቀደሱ ቃልኪዳኖችን እገባለሁ እናም እጠብቃለሁ፣ እናም የቤተመቅደስ ትእዛዛትን እና በረከቶችን እቀበላለሁ።” ቤትን እና ቤተሰብን ማጠናከር ማለት በአማኝነት ሰንሰለት ውስጥ የመጀመሪያውን ቀለበት ማስገባት፣ የእምነትን ቅርስ መጠበቅ ወይም መመለስ ማለት ሊሆን ይችላል።35 ይሁን እንጂ ጥንካሬ የሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እና ቅዱስ ቃልኪዳኖችን በማድረግ ነው።

በቤተ መቅደስ ውስጥ ማን እንደሆንን እና የት እንደነበርን እንማራለን። የሮሙ ፈላስፋ ሲሴሮ እንዲህ ብሏል፣ “ከመወለዳችሁ በፊት ስለተከሰተው ነገር ቸልተኛ መሆን፣ ሁሌም ህፃን ልጅ ሆኖ መቅረት ነው።”36 በእርግጥ ስለአለማዊ ታሪክ ነበር እየተናረ የነበረው፣ ነገር ግን የእርሱ አስተዋይ አመለካከቱ መስፋት ይችላል። በቤተመቅደስ ውስጥ የተገኘውን ዘላለማዊ እይታ ችላ ካልን እንደ መጨረሻ እንደሌለው ልጆች እንኖራለን። እዚያ በጌታ እናድጋለን፣ የመንፈስ ቅዱስን ሙላት እንቀበላለን37 እናም እንደ አዳኙ ደቀ መዛሙርት የበለጠ ቆራጦች እንሆናለን።38 ቃልኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ፣ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ኃይል እንቀበላለን።39

ሕይወታችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲያተኩር እንድታደርጉ እና በወጣት ሴቶች ጭብጥ ውስጥ ያሉትን መሰረታዊ እውነታዎች እንድታስታውሱ እጋብዛችኋለሁ። ፍቃደኛ ከሆናችሁ መንፈስ ቅዱስ ይመራችኋል። የሰማይ አባታችን የእርሱ ወራሾች እንድትሆኑ እና እርሱ ያለውን ነገር በሙሉ እንድትቀበሉ ይፈልጋል።40 ከዚህ በላይ ሊሰጣችሁ አይችልም። ከዚህ በላይ ቃል ሊገባላችሁ አይችልም። ከምታውቁት የበለጠ ይወዳችኋል እናም በዚህ እና በሚመጣው ሕይወት ውስጥ ደስተኛ እንድትሆኑ ይፈልጋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።