አጠቃላይ ጉባኤ
በክርስቶስ እና በወንጌሉ ድንቀት
የሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በክርስቶስ እና በወንጌሉ ድንቀት

ዓይኖቻችን ያዩትን እና ልባችን የተሰማውን ማስታወስ ለአዳኝ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት ያለንን መደነቅ ይጨምር።

አንድ ጎበዝ፣ በጡረታ የተገለለ ቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበረ፣ የተዋጣለት ደራሲና ከሁሉም በላይ ቁርጠኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ ውድ ጓደኛ አለኝ። በጉባኤዎች ለመሳተፍ፣ ትምህርታዊ ጥናትና ምርምር ለማድረግ እና ጉብኝቶችን ለመምራት በደርዘን ለሚቆጠሩ ጊዜያት ቅድስቲቷን ሀገር ጎብኝቷል። እንደ እሱ አባባል፣ ኢየሱስ በተመላለሰበት ምድር በሄደ ቁጥር ይደነቃል ምክንያቱም ስለ አዳኝ፣ ስለ ምድራዊ አገልግሎቱ እና ስለሚወደው የትውልድ አገሩ ያለጥርጥር አዲስ፣ አስገራሚ እና አስደናቂ ነገር ስለሚማር ይደነቃል። ጓደኛዬ በቅድስቲቷ ሀገር ስለተማረው ነገር ሁሉ ሲናገር የሚያሳየው ድንቀት ተላላፊ ነው፤ እናም ይህ መገረም በህይወቱ ውስጥ ባገኛቸው ታላላቅ ስኬቶች እና ባደረጋቸው አካዴሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሰረታዊ ነው።

ልምዶቹን ሳዳምጥ እና ጉጉቱ ሲሰማኝ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና በደቀመዝሙርነታችን ላይ እንዲሁም ወደ ዘላለም ህይወት በምናደርገው ጉዟችን ላይ ለሚያመጣው ለውጥ ምን ያህል የበለጠ መንፈሳዊ ድንቀት ሊሰማን አንደሚችል እና ሊሰማን እንደሚገባ አሰላስላለሁ። የጠቀስኩት ግርምት ህይወታቸውን በሙሉ ልብ በአዳኙና በትምህርቱ ላይ ያተኮሩ እንዲሁም በህይወታቸው ውስጥ መገኘቱን በትህትና ለሚገነዘቡት ሁሉ የሚሰማ የጋራ ስሜት ወይም ድንቀት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ የተነሳ እንዲህ ያለው የመደነቅ ስሜት የክርስቶስን ትምህርት በደስታ የመኖርን ጉጉት ያነሳሳል።1

ቅዱሳት መጻህፍት ይህ ስሜት እንዴት እንደሚገለጥ የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን ይዘዋል። ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ በእርሱ በመደሰት ለጌታ ያለውን ጥልቅ ምስጋና ገልጿል።2 ኢየሱስ በቅፍርናሆም በሚገኘው ምኩራብ ሲሰብክ የሰሙ ሰዎች በትምህርቱ እና ሲያስተምራቸው በነበረው ጥንካሬ ተገረሙ።3 ወጣቱ ጆሴፍ ስሚዝ የያዕቆብን የመጀመሪያ ምዕራፍ አንዳንድ ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ የእግዚአብሔርን ጥበብ እንዲፈልግ እንዲያነሳሳው በሰውነቱ ሁሉ ውስጥ የገባው ይህ ተመሳሳይ ስሜት ነበር።4

ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በእውነት በኢየሱስ ክርስቶስ እና በወንጌሉ ስንደነቅ፣ የበለጠ ደስተኞች እንሆናለን፣ ለእግዚአብሔር ስራ የበለጠ ጉጉት ይኖረናል፤ እንዲሁም በሁሉም ነገር የጌታን እጅ እናውቃለን። በተጨማሪም፣ የአምላክን ቃላት ማጥናታችን የበለጠ ትርጉም ያለው ነው፤ ጸሎታችን፣ የበለጠ ምክንያት ያለው፤ አምልኳችን፣ የበለጠ አክብሮት ያለው፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ያለን አገልግሎትም፣ የበለጠ ትጉ የሆነ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች በህይወታችን ውስጥ በብዛት እንዲኖሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው።5 ስለዚህ፣ የአዳኝ እና የወንጌሉ ምስክርነታችን ይበረታል፣ ክርስቶስን በውስጣችን እንጠብቀዋለን፣6 እንዲሁም “ሥር [በመስደድ] በእርሱ [በመታነጽ፣ እናም በእምነት [በመጽናት]፣ … በምስጋና [በመሞላት] ሕይወታችንን እንኖራለን።7 በዚህ መንገድ ስንኖር፣ የበለጠ በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንሆናለን እናም በመንፈሳዊ ግድየለሽነት ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ እንጠበቃለን።

እንዲህ ዓይነቱ ግድየለሽነት የሚታወቀው ቀስ በቀስ በጌታ ወንጌል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመሳተፍ ያለንን ደስታ በማጣት ነው። በአጠቃላይ የሚጀምረው በዚህ ሕይወት ውስጥ ለደስታችን ሁሉንም አስፈላጊ እውቀትን እና በረከቶችን እንዳገኘን ሲሰማን ነው። ይህ ቸልተኝነት የወንጌልን ስጦታዎች እንደቀላል እንድንወስድ ያደርገናል፣ እና ከዚያ በኋላ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አስፈላጊ ነገሮች ውስጥ ራሳችንን አዘውትረን ከማሳተፍ8 እና የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች ችላ የማለት አደጋ ውስጥ እንገባለን። በዚህም ምክንያት “እሱን [የ]መስማት”9 አቅማችንን በማዳከም፣ ለሥራው ታላቅነት ግድየለሽ እና ደንታ ቢስ በመሆን፣ ቀስ በቀስ ከጌታ ራሳችንን እናርቃለን። ቀደም ሲል የተቀበልነው እውነቶችን በተመለከተ ጥርጣሬ ወደ አእምሯችን እና ልባችን ዘልቆ በመግባት ለጠላት ፈተናዎች ተጋላጭ ያደርገናል።10

ታዋቂው ጸሐፊ እና ጀግና ክርስቲያን ፓስተር አይደን ዊልሰን ቶዘር እንደጻፈው፣ “ቸልተኛነት የመንፈሳዊ እድገት ሁሉ ገዳይ ጠላት ነው።”11 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ብዙም ሳይቆይ በኔፊ ህዝብ ላይ የሆነው ይህ አይደለምን? እነርሱም “ከሰማይ በሆነው ምልክት ወይም አስገራሚ ነገር መደነቃቸውን መቀነስ ጀመሩ፣” በመጠራጠርም “ያዩአቸውንና የተመለከቱአቸውን በሙሉ አለማመን ጀመሩ።” በዚህም ሰይጣን “አሳውሮአቸዋልና የክርስቶስን ትምህርት በተመለከተ የሞኝ እናም ከንቱ ነገር መሆኑን እንዲያምኑ መርቷቸዋል።”12

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ፍፁም በሆነው እና ማለቂያ በሌለው ፍቅሩ እንዲሁም የእኛን ሰብአዊ ተፈጥሮ በማወቅ፣13 አዳኙ በመንፈሳዊ ግድየለሽነት ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ መንገዱን አዘጋጅቶልናል። በተለይም የምንኖርበትን ውስብስብ ዓለም ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የአዳኝ ግብዣ ሰፋ ያለ አመለካከት ይሰጠናል፦ “ከእኔ ተማር፣ እናም ቃላቴን አድምጥ፤ በመንፈሴ በትህትና ተጓዝ፣ እናም በእኔ ሰላምን ታገኛለህ።”14 የአዳኙን ግብዣ ስንቀበል፣ ትህትናችንን፣ ለመማር ያለንን ፍላጎት እና እሱን ለመምሰል ያለንን ተስፋ እናሳያለን።15 ይህ ግብዧ “በሙሉ ልባችን፣ ጉልበታችን፣ አዕምሮአችን እና ጥንካሬአችን” እርሱን እና የእግዚአብሔር ልጆችን ማገልገልን ያካትታል።16 በዚህ ጉዞ በምናደርገው ጥረት ውሰጥ ዋና ነገሮቹ በርግጥ ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት ናቸው፦ አምላካችንን እግዚአብሔርን መውደድ እና ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ ናቸው።17

ይህ ዓይነት ባህሪ የመለኮታዊ ባህሪው አካል ሲሆን ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ባደረገው ነገር ሁሉ በግልጽ የሚታይ ነበር።18 ስለዚህ፣ ሆን ብለን እና በእውነት ወደ እርሱ ለመመልከት ራሳችንን ስናተጋ እና ከፍፁም ምሳሌው ስንማር፣19 እርሱን የበለጠ እናውቀዋለን። እንዴት መኖር እንዳለብን፣ ሌሎች የሚከተሉትን ምሳሌ እንዴት እንደምናስቀምጥ፣ እና ልንከተላቸው የሚገቡን ትእዛዛት በህይወታችን ውስጥ እንደ መጨረሻው መስፈርት ለማካተት በጉጉት እና ፍላጎት እናድጋለን። ስለእግዚአብሔር እና ስለጎረቤቶቻችን ተጨማሪ መረዳትን፣ ጥበብን፣ መለኮታዊ ባህሪን እና ጸጋን እናገኛለን።20 እምነታችንን፣ በጽድቅ ለመስራት ያለንን ፍላጎት እንዲሁም እሱን እና ሌሎችን ለማገልገል ያለንን መነሳሳት በማጉላት የአዳኝን ተፅእኖ እና ፍቅር የመሰማት ችሎታችን በህይወታችን እንደሚጠናከር አረጋግጥላችኋለሁ።21 በተጨማሪም፣ በስጋዊ ህይወት ውስጥ ለምናገኛቸው በረከቶች እና ተግዳሮቶች ያለን አድናቆት ይጠናከራል እናም የእውነተኛው አምልኳችን አካል ይሆናል።22

ውድ ጓደኞቼ፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የወንጌልን መንፈሳዊ ድንቀታችንን ያጠናክሩናል እናም ከጌታ ጋር የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች በደስታ እንድንጠብቅ ያነሳሱናል—በሚያጋጥሙን ፈተናዎች እና ችግሮች ውስጥም ጭምር። በእርግጥም፣ እነዚህ ውጤቶች እንዲደርሱ በአዳኝ ትምህርቶች ውስጥ ራሳችንን ማጥለቅ ያስፈልገናል፣23 ይህን የምናደርገውም ባህሪያቱን በህይወታችን ለማካተት በመትጋት ነው።24 በተጨማሪም፣ በንስሐ ወደ እርሱ መቅረብ፣ 26 በህይወታችን ውስጥ የእርሱን ይቅርታ እና የመቤዠት ኃይሉን መፈለግ እና ትእዛዛቱን መጠበቅ ያስፈልገናል። በፍጹም ልባችን በእርሱ የምንታመን፣ በመንገዶቻችን ሁሉ ለእርሱ እውቅና ከሰጠን እና በራሳችን መረዳት ላይ ካልተደገፍን መንገዳችንን እንደሚመራ ጌታ እራሱ ቃል ገብቷል።26

ምስል
ሽማግሌ ጆንሰ ከዌስ ጋር

ዛሬ በጉባኤው እየተሳተፈ ያለ ስሙ ዌስ የተባለ በቅርቡ ያገኘሁት ሰው፣ ስለ እርሱ እና ስለወንጌሉ ለመማር የቀረበለትን የክርስቶስን ግብዣ ተቀበለ፤ ለ27 ዓመታት ራሱን ከቃል ኪዳኑ መንገድ ከራቀ በኋላም የፍቅሩን ድንቀት ማጣጣም ጀመረ። አንድ ቀን በፓናማ ወደ ተመደበው ተልእኮ ከመሄዱ በፊት በጊዜያዊነት ወደ ዌስ አካባቢ የተመደበው ሽማግሌ ጆንስ በፌስቡክ እንዳገኘው ነገረኝ። ሽማግሌ ጆንስ የዌስን መገለጫ ሲያገኝ፣ አስቀድሞ የቤተክርስቲያኗ አባል መሆኑን እንኳን ሳያውቅ፣ የመንፈስ ቅዱስ መመሪያ ተሰማው እንዲሁም ወዲያውኑ ዌስን ማግኘት እንዳለበት አወቀ። በዚህ ስሜት ላይ በፍጥነት እርምጃ ወሰደ። ዌስ በዚህ ያልተጠበቀ ግንኙነት ተገረመ እንዲሁም ከቃል ኪዳኑ መንገድ የራቀ ቢሆንም ጌታ እንደሚያውቀው ተረዳ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ዌስና ሚስዮናውያን በተደጋጋሚ መገናኘት ጀመሩ። ሽማግሌ ጆንስ እና ጓደኛው ዌስ የአዳኙን እና የወንጌሉን አግራሞት እንዲያድስ የረዳውን ሳምንታዊ የአገልግሎት ተግባራትን እና መንፈሳዊ መልእክቶችን አቅርበዋል። የእውነትን ምስክርነት እና አዳኝ ለእሱ ያለውን ፍቅር አደሰ። ዌስ ከአፅናኙ የሚመጣው ሰላም ተሰማው እናም ወደ መንጋው ለመመለስ የሚያስፈልገውን ጥንካሬ አገኘ። ይህ ተሞክሮ በመንፈሳዊ እና በስሜት ወደ ህይወት እንዲመለስ እንዳደረገው እና ባሳለፉት አስቸጋሪ ገጠመኞች ምክንያት ባለፉት ዓመታት የተጠራቀመውን የምሬት ስሜት እንዲያስወግድ እንደረዳው ነገረኝ።

ከላይ የተጠቀሱት ጥሩ ጓደኛዬ እና አሳቢ አስተማሪው እንዳስተዋሉት፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለ ወንጌሉ ሁል ጊዜ የምንማረው አስደናቂ እና አስገራሚ ነገር አለ።27 ጌታ፣ እኛን ጨምሮ፣ ስለእርሱ ለመማር እና ቃላቶቹን በህይወታቸው ውስጥ ለማካተት ለሚፈልጉ ሁሉ የተዘረጋ አስደናቂ ተስፋዎችን ሰጥቷል። ለሔኖክም እንዲህ አለ፣ “እነሆ መንፈሴ በአንተ ላይ አርፏል፣ ስለዚህ ቃላትህን ሁሉ አጸድቃለሁ፤ ተራሮችም ከአንተ ፊት ይሸሻሉ፣ እናም ወንዞችም ከሚሄዱበትም ይዞራሉ፤ አንተም ከእኔ ጋር ሁን፣ እና እኔም ከአንተ ጋር።”28 በእርሱ አገልጋይ በንጉስ ቢንያም አማካኝነት እንዲህ አወጀ፣ “በገባችሁት ቃል ኪዳን የተነሳ የክርስቶስ ልጆች፣ ወንዶችና ሴት ልጆቹ፣ ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ እነሆም በዚህ ቀን እናንተን በመንፈስ ወልዷችኋል፤ ልባችሁ በስሙ በማመን ተለውጧል ብላችኋልና፤ ስለዚህ እናንተ ከእርሱ ተወልዳችኋል እናም የእርሱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሆናችኋል።”29

ስለዚህ፣ በእውነት እና በቀጣይነት ስለ አዳኝ ለመማር እና ምሳሌውን ለመከተል ስንጥር፣ የእርሱ መለኮታዊ ባህሪያቶች በአእምሯችን እና በልባችን እንደሚጻፉ፣30 እኛም እንደ እርሱ እንደምንሆን፣ እና ከእርሱ ጋር እንደምንራመድ በስሙ ቃል እገባላችኋለሁ።31

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በእርሱ ሙሉ፣ ወሰን የለሽ እና ፍጹም ፍቅር በድንቀት እንገኝ ዘንድ እጸልያለሁ። ከመንፈሳዊ እና ስሜታዊ ቁስላችን ሊፈውሱን እና ወደ እርሱ እንድንቀርብ ሊረዱን የሚችሉትን ዓይኖቻችን ያዩትን እና ልባችን የተሰማውን ማስታወስ ለአዳኝ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት ያለንን መደነቅ ይጨምር። አብ በእጁ ባለው እና ታማኝ ለሆኑት ባዘጋጀው ታላቅ ተስፋዎች እንደነቅ።

“መንግስት የእናንተ ናት እናም በእዚያም ያሉ በረከቶች የእናንተ ናቸው።

እናም ሁሉንም ነገሮች በምስጋና የሚቀበል እርሱ የከበረ ይሆናል።”32

ኢየሱስ የዓለም ቤዛ ነው፣ እና ይህችም የእርሱ ቤተክርስቲያን ናት። እነዚህን እውነቶች በአስደናቂው፣ በተቀደሰው እና በሚያስደንቅ በመድኃኒታችን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመሰክራለሁ፣ አሜን።

አትም