አጠቃላይ ጉባኤ
ስለ ራስን-መቻል ለልጆች እና ወጣቶች ማስተማር
የሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:11

ስለ ራስን መቻል ለልጆች እና ለወጣቶች ማስተማር

በህይወታችን ሙሉ ራሳችንን የቻልን በመሆን እና ይህንንም ለልጆቻችን እና ለወጣቶቻችን በማስተማር አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ወንጌሉን እንከተል።

ስለ ራስን መቻል እና እርሱንም ለልጆች እና ለወጣቶች እንዴት ማስተማር እንደሚቻል እናገራለሁ። ራስን-መቻል ጎልማሶችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ጎልማሶች የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሲማሩ እና ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲሁም በወጣትነታቸው በቤት ውስጥ ትምህርቱን እና መርሆቹን ሲለማመዱ በተሻለ እራስን የመቻል መንገድ ላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማወቅ ችያለሁ።

ታላቅ የእውነተኛ ህይወት ምሳሌ የተሻለ ማሳያ ነው። ዊልፍሬድ ቫኒ፣ ስድስት አመቱ ሳለ ሰባት ወንድሞቹና እህቶቹ፣ እንዲሁም እናቱ በአቢጃን፣ አይቮሪ ኮስት ቤተክርስቲያኗን ተቀላቀሉ። ስምንት አመት ሲሞላው ተጠመቀ። ዊልፍሬድ አሥራ አንድ ዓመት ሲሞላው በቤተሰቡ ውስጥ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የነበረው አባቱ ሞተ።

በቤተሰቡ ሁኔታ ቢያዝንም፣ ዊልፍሬድ በእናቱ ማበረታቻ እና በቤተክርስቲያን ድጋፍ ትምህርት ለመቀጠል ወሰነ። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀና የሙሉ ጊዜ ሚስዮን በጋና ኬፕ ኮስት ሚስዮን አገለገለ፣ እዛም እንግሊዘኛ ተማረ። የሚስዮን አገልግሎቱን ከጨረሰ በኋላ፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገባ እና በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ዲፕሎማ ተቀበለ። በዚህ የትምህርት መስክ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም፣ በቱሪዝምና እንግዳ አቀባበል ኢንዱስትሪ ውስጥ ሥራ አገኘ።

በባለ 5 ኮከብ ሆቴል ውስጥ እንደ አስተናጋጅ ስራ ጀመረ፣ ነገር ግን የመሻሻል ፍላጎቱ በዚያ የሁለት ቋንቋ ተናጋሪ እንግዳ ተቀባይ እስኪሆን ድረስ የበለጠ እንዲማር ገፋፍቶታል። አዲስ ሆቴል ሲከፈት፣ የማታ ኦዲተር ሆኖ ተቀጠረ። ከዚያም በ BYU-Pathway Connect ውስጥ ተመዝገበ እናም በአሁኑ ሰአት በእንግዳ አቀባበል እና ቱሪዝም ማናጅመንት ሰርተፍኬት ለማግኘት እየተማረ ይገኛል። ፍላጎቱ አንድ ቀን የከፍተኛ ደረጃ ሆቴል አስተዳዳሪ ለመሆን ነው። ዊልፍሬድ ዘላለማዊ ጓደኛውን እና ሁለት ልጆቹን እንዲሁም እናቱን እና ወንድሞቹን እና እህቶቹን መርዳት ይችላል። ባሁን ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ የካስማ ከፍተኛ አማካሪ ሆኖ ያገለግላል።

ራስን መቻል ማለት “ለራስ እና ለቤተሰብ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች የማሟላት ችሎታ፣ ቁርጠኝነት እና ጥረት”ማለት ነው።1 ራስን ለመቻል መጣር ወደሰማይ አባት እና ወደልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራን የቃል ኪዳን መንገድ ላይ የምንሰራው ስራ አካል ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክራል ብሎም በቃል ኪዳኖች እንዲሁም በመዳን እና በዘላለም ህይወት ከፍ ከፍ በመደረግ ስርዓቶች አማካኝነት ከእርሱ ጋር በደስታ ያስተሳስረናል። ራስን መቻል የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ትምህርት ነው፤ ፕሮግራም አይደለም። በህይወት ዘመን የሚዘልቅ ሂደት ነው፣ የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም።

በመንፈሳዊ ጥንካሬ፣ በአካላዊ እና በስሜታዊ ጤንነት በመሻሻል፣ ትምህርታችንን እና ስራችንን በመከታተል እንዲሁም በጊዜያዊነት በመዘጋጀት በህይወታችን ሙሉ እራሳችንን የቻልን እንሆናለን።2 ይህ ተግባር በህይወታችን ውስጥ ያበቃልን? አያበቃም፣ እድሜ ልክ የሚቆይ የመማር፣ የማድግ፣ እና የመስራት ሂደት ነው። መቼም አያልቅም፤ የሚቀጥል፣ እለታዊ ሂደት ነው።

ራስን የመቻልን ትምህርት እና መርሆችን ለእኛ ልጆች እና ወጣቶች እንዴት ማስተማር እንችላለን? አንዱ አስፈላጊ መንገድ የህፃናት እና ወጣቶች የእድገት ፕሮግራም መርህን በየወቅቱ በተግባር ላይ ማዋል ነው። ወላጆች እና ልጆች የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ይማራሉ፣ በአገልግሎት እና በእንቅስቃሴዎች ይሳተፋሉ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ልጅ ልዩ በሆነው አራት የግል እድገት ዘርፎች አብረው ይሰራሉ። እንደበፊቱ ለሁሉም አንድ አይነት ሆኖ የተዘጋጀ ፕሮግራም አይደለም።

ልጆች መምሪያ “ኢየሱስ በእናንተ እድሜ ሳለ፣ ተማረ እናም አደገ ይላል። እናንተም እየተማራቸሁ እና እያደጋችሁ ነው። ቅዱሳት መጽሐፍት እንደሚሉት፣ “ኢየሱስ በጥበብና በቁመት፣ እና በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።” (ሉቃስ 2:52).”3 ይህ ጥቅስ በመንፈሳዊ ገጽታው እድገትን እና መማርን፣ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን፤ በማህበራዊ ገጽታው፣ በሰው ፊት ሞገስን፤ በአካላዊ ገጽታው፣ ቁመትን፤ እንዲሁም በአዕምሯዊ ገጽታው፣ ጥበብን ያመለክታል። እነዚህ የእድገት ክፍሎች በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ብንሆን ለሁላችንም የሚሰሩ ናቸው። እነርሱን መቼ ነው የምናስተምራቸው? በ ዘዳግም 6፥6–7 እንዲህ እናነባለን፤

“እኔም ዛሬ አንተን የማዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ።

“ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።”

በመልካም አርአያነታችን፣ ከእነርሱ ጋር በመስራት እና በማገልገል፣ ቅዱሳት መጻህፍትን በማጥናት እና ነብያት እንዳስተማሩት የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት በመከተል እነዚህን ነገሮች ለልጆች እናስተምራለን።

እንደጠቀስኩት በልጆች እና ወጣቶች የእድገት ፕሮግራም ውስጥ ልጆች በያንዳንዳቸው በአራቱም የእድገት ዘርፎች ውስጥ የተለያዩ ግቦችን ይመርጣሉ። በእያንዳንዱ ክፍሎች የራሳቸውን ግብ መፍጠራቸው አስፈላጊ ነው፡፡ ወላጆች እና መሪዎች ማስተማር፣ መምከር እና መደገፍ ይችላሉ።

ለምሳሌ፣ የልጅ ልጃችን ሚራንዳ በየእለቱ በማለዳ የሴሚናሪ ክፍሎች በመሳተፍ በመንፈሳዊ ለማደግ በጣም የተነሳሳች ነች። በአጥቢያዋ ውስጥ ካሉ ሌሎች የሴሚናሪ ተማሪዎች አወንታዊ አስተያየቶችን በመስማቷ ነበር ፍላጎት ያደረባት። እናቷ ለክፍል እርሷን ማስነሳት አይጠበቅባትም። ይህንን ለማድረግ የሚረዳትን ጥሩ ልምዶች ስላዳበረች፣ ጠዋት 6፡20 በተባለው ሰዓት ላይ በራሷ ትነሳና በቪዲዮ ኮንፈረንስ ትገናኛለች። ሚራንዳ አሁን በራስ የመተማመን ስሜቷ ስላደገ ስትጎበኛቸው የበለጠ እንደምትናገር የራሴ ወላጆች በቅርቡ ነገሩኝ። እነዚህ ለህይወት እና እድገት ጉልህ ውጤቶችን የሚያመጡ ትምህርቶች ናቸው።

ወላጆች፣ አያቶች፣ መሪዎች እና ጓደኞች በልጆች ለውጥ እና እድገት ላይ እገዛ ያደርጋሉ። ሙሉ በሙሉ የሚሳተፉ የአገልግሎት ወንድሞች እና እህቶች ከክህነት እና ከአጥቢያው የድርጅት መሪዎች ጋር በመሆን ድጋፍ ይሰጣሉ። “ቤተስብ፤ ለአለም የተላለፈ አዋጅ” እንዲህ ይላል፤ “በመለኮታዊ እቅድ፣ አባቶች በፍቅር እና በጻድቅነት ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድራሉ እና ለቤተሰቦቻቸው የህይወት መሰረታዊ ፍላጎት የማሟላት እና ጥበቃ ሀላፊነት አለባቸው።” እናቶች በቀደምትነት ልጆቻቸውን የመንከባከብ ሀላፊነት አለባቸው። በእነዚህ ቅዱስ ሀላፊነቶች አባቶች እና እናቶች እንደእኩል አጋር የመረዳዳት ሀላፊነት አለባቸው። … የቅርብ ዘመዶች አስፈላጊ ሲሆን እርዳታ መስጠት ይገባቸዋል።”4 ያ የመጨረሻው መስመር ሌሎችንም ጨምሮ አያቶችንም ይመለከታል።

በምዕራብ አፍሪካ ስናገለግል፣ ባለቤቴ ኑሪያ በውቅያኖስ ዙሪያ ያሉ ቤተሰቦቻችንን እና የልጅ ልጆቻችንን በማገልገል እና ከነርሱ ጋር ያላትን ግንኙነት በመጠበቅ ረገድ አስደናቂ የሆነ ስራ ሰርታለች። ይህን የምታደርገው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ነው። ለትንንሽ የልጅ ልጆች መጻህፍትን ታነባለች። ተለቅ ተለቅ ላሉት ሴት የልጅ ልጆቿ የቤተሰባችንን ታሪክ፣ ሳይንስን፣ የፖርቶ ሪኮን ታሪክ፣ የእምነት አንቀጾችን እና የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ታስተምራለች። በዘመናችን፣ ርቀት መገናኘትን፣ አብሮ መሆንን፣ ማገልገልን እና በቤተሰቦቻችን ውስጥ ያለውን በማደግ ላይ ያለ ትውልድ ማስተማርን አይገድብም። እንዲሁም ውድ የልጅ ልጆቻችንን ለማስተማር፣ ለመውደድ፣ ለመንከባከብ እና እንዲስቁ ለማድረግ በምችልበት ጊዜ ከኑሪያ ጋር እሆናለሁ።

በልጆች እና ወጣቶች እድገት ፕሮግራም እና በራስ መተማመን ግንባታ መካከል ያለውን ተነሳሽ ተመሳሳይነት ማስተዋል አለባችሁ። በእያንዳንዳቸው ውስጥ ያሉት አራት የእድገት ዘርፎች በጣም ተመሳሳይ ናቸው። ራስን በመቻል ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ጥንካሬ በልጆች እና ወጣቶች ውስጥ ካለው መንፈሳዊ ገጽታ ጋር ይዛመዳል። ራስን በመቻል ውስጥ ያለው አካላዊ እና ስሜታዊ ጤንነት በህጻናት እና ወጣቶች ውስጥ ካሉት አካላዊ እና ማህበራዊ ገጽታዎች ጋር ይዛመዳል። ራስን በመቻል ውስጥ ያሉት ትምህርት፣ ሥራ እና ጊዜያዊ ዝግጁነት በልጆችና ወጣቶች እድገት ፕሮግራም ውስጥ ካለው የእውቀት ገጽታ ጋር ይዛመዳል።

ለማብቃት፣ በህይወታችን ሙሉ ራሳችንን የቻልን በመሆን፣ እና ይህንንም ለልጆቻችን እና ለወጣቶቻችን በማስተማር አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ወንጌሉን እንከተል። እነዚህን በማድረግ ይህንን በተሻለ ማከናወን እንችላለን፤

  1. ሌሎችን የማገልገል መልካም ምሳሌዎች በመሆን።

  2. ራስን የመቻል ትምህርቶችን እና መርሆችን መኖር እና ማስተማር እንዲሁም

  3. ራስን መቻልን እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ክፍል አድርጎ ለመገንባት የተሰጠውን ትዕዛዝ አክባሪ መሆን።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 104፥15-16 እንዲህ ይላል፤

“እና ቅዱሳኔን ማስተዳደር አላማዬ ነው፣ ሁሉም ነገሮች የእኔ ናቸውና።

“ነገር ግን፣ ይህም በእኔ መንገድ መደረግ አለበት፤ እና እነሆ እኔ ጌታ ቅዱሳኔን ለማስተዳደር፣ ድሀዎቹን ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ በዚያም ሀብታሞችንም ለማውረድ ይህን መንገድ አውጃለሁ።”

ይህች የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ናት። የእርሱ ወንጌል በዚህ ምድር እንዲሁም ለዘላለም ቤተሰቦችን ይባርካል። ለዘለአለም የተጣመርን ቤተሰቦች ለመሆን ስንጥር በህይወታችን ውስጥ ይመራናል። ይህ እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፤ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል22.0፣ ChurchofJesusChrist.org

  2. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ22.1ይመልከቱ።

  3. Personal Development: Children’s Guidebook [2019], 4.

  4. ቤተሰብ፦ ለአለም የተላለፈ አዋጅ፣” ChurchofJesusChrist.org።