አጠቃላይ ጉባኤ
ክርስቶስ የተሰበረውን ይፈውሳል
የሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:39

ክርስቶስ የተሰበረውን ይፈውሳል

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የተበላሹ ግንኙነቶችን፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት እና የተሰበረውን የእራሳችንን ክፍሎች መፈወስ ይችላል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ በቤተሰብ ስብሰባ ላይ፣ የዚያን ጊዜ የስምንት ዓመቱ የወንድሜ ልጅ ዊልያም ታላቅ ልጃችን ብሪተን ከእርሱ ጋር ኳስ መጫወት ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀው። ብሪተን በጋለ ስሜት፣ “አዎ! ደስ ይለኛል!” አለ። ለተወሰነ ጊዜ ሲጫወቱ ከቆዩ በኋላ ኳሱ ከብሪተንን በድንገት አመለጠና ከአያቶቹ ጥንታዊ ማሰሮዎች አንዱን ሰበረ።

ብሪተን ባደርገው ምክንያት በጣም አዝኖ ነበር። የተሰባበሩትን ቁርጥራጮች ማንሳት ሲጀምር ዊልያም ወደ ዘመዱ ሄዶ በፍቅር አቅፎ ጀርባውን መታ አደረገ። ከዚያም “አትጨነቅ፣ ብሪተን፣ አንድ ጊዜ በሴቷ እና ወንዱ አያቴ ቤት የሆነ ነገር ሰበረሁ፣ እናም አያቴ በእጇ አስጠጋችኝ እና ‘ምንም አይደለም ዊልያም፣ አምስት አመትህ ብቻ ነው’ አለችኝ ” በማለት አጽናናው።

ብሪተን “ግን ዊልያም 23 አመቴ ነው!” ሲል መለሰ።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እድሜያችን ምንም ቢሆን በህይወታችን ውስጥ ያሉትን የተበላሹትን ነገሮች በስኬት እንድናልፍ እንዴት እንደሚረዳን ከቅዱሳን መጻህፍት ብዙ መማር እንችላለን። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የተበላሹ ግንኙነቶችን፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት እና የተሰበረውን የእራሳችንን ክፍሎች መፈወስ ይችላል።

ከእግዚአብሔር ጋር የተቋረጠ ግንኙነት

አዳኙ በቤተመቅደስ ውስጥ እያስተማረ ሳለ ጸሐፍት እና ፈሪሳውያን አንዲት ሴትን ወደ እርሱ አመጡ። ሙሉ ታሪኳን አናውቅም፤ “ስታመነዝር ተገኝታ” እንደተያዘች ብቻ ነው የምናውቀው።1 ብዙ ጊዜ፣ ቅዱሳን መጻህፍት የአንድን ሰው ህይወት ትንሽ ክፍል ብቻ ያሳያሉ፣ እናም በዚህ ክፍል ላይ በመመስረት፣ አንዳንድ ጊዜ ከፍ ለማድረግ ወይም ለማውገዝ እንጥራለን። የማንንም ሰው ህይወት በአንድ አስደናቂ ጊዜ ወይም በአንድ በሚያሳዝን የህዝብ ፊት ውርደት መረዳት አይቻልም። የእነዚህ የተቀደሱ ምዕራፎች ዓላማ ክርስቶስ በዚያን ጊዜ መልስ እንደነበረ እና አሁንም እርሱ መልስ እንደሆነ እንድንገነዘብ ለመርዳት ነው። እሱ የእኛን ሙሉ ታሪክ፣ እና ምን እየተቸገርን እንደሆነ በትክክል ያውቃል፣ እንዲሁም አቅማችንን እና ድካማችንን ያውቃል።

ክርስቶስ ለዚች ውድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰጠው ምላሽ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ሀጢአት አትስሪ “ 2 የሚል ነበር። “ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ሀጢአት አትስሪ” በሌላ አባባል ማለት “ሂጂ እና ተለወጪ” ማለት ሊሆን ይችላል። አዳኙ ንስሀ እንድትገባ፣ ባህሪዋን፣ ማህበሯን ፣ለራሷ ያላትን ስሜት፣ ልቧን እንድትቀይር እየጋበዛት ነበር።

በክርስቶስ ምክንያት፣ “ለመውጣና ለመለወጥ” ያደረግነው ውሳኔ “ለመወጣትና ለፈውስ” እንዲሆን ሊፈቅድልን ይችላል፤ በሕይወታችን የተሰበሩትን ሁሉ የመፈወስ ምንጭ እርሱ ነውና። እንደ ታላቅ አስታራቂ እና ከአብ ዘንድ ጠበቃ፣ ክርስቶስ የተበላሹ ግንኙነቶችን ይቀድሳል እናም ያድሳል— ከሁሉም በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት።

የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም ሴቲቱ የአዳኙን ምክርነት እንደተከተለች እና ህይወቷን እንደለወጠች ግልፅ አድርጓል፡- “ሴቲቱም ከዚያ ሰአት ጀምሮ እግዚአብሔርን አከበረች፣ እናም በስሙ አመነች።3 ከዚህ ክስተት በኋላ ስሟን ወይም ሌሎች ዝርዝሮችን አለማወቃችን በጣም ያሳዝናል ምክንያቱም እሷ ንስሃ እንድትገባ እና እንድትለወጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ታላቅ ቁርጠኝነትን፣ ትህትና እና እምነትን ይጠይቅ ስለነበር ነው። እኛ የምናውቀው ነገር እሷ የማያልቀው እና ዘላለማዊ መስዋዕቱ ሊደርስባት እንደሚችል በመረዳት “በስሙ ያመነች” ሴት እንደነበረች ነው።

ከሌሎች ጋር የተበላሹ ግንኙነቶች

ሉቃስ ምእራፍ 15 ላይ ሁለት ልጆች የነበሩትን የአንድ ሰው ምሳሌ እናነባለን። ታናሹ አባቱን ከገንዘብቡ የሚደርሰውን ክፍል እንዲሰጠው ጠየቀው፣ ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፣ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ።4

“ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር።

“ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።

“እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።

“ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ።

“ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥

“ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።

“ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።”5

አባቱ ወደ ልጁ መሮጡ ትልቅ ነገር እንደሆነ አምናለው። ልጁ በአባቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት ጥልቅ እና ትልቅ ነበር። በተመሳሳይም አባቱ በልጁ ድርጊት በእውነት አፍሮ ሊሆን ይችላል።

ታዲያ አባቱ ልጁ ይቅርታ እስኪጠይቅ ድረስ ለምን አልጠበቀም? ለምንድነው ይቅርታንና ፍቅርን ከማሳየቱ በፊት ለፍርድ እና ለእርቅ መባ ያልፈለገው? ይህ ብዙ ጊዜ ያሰላሰልኩት ነገር ነው።

“እኔ ጌታ ይቅር የምለውን ይቅር እላለሁ፣ ነገር ግን እናንተ ለሁሉም ሰዎች ይቅርታን ታደርጉ ዘንድ ይጠበቅባችኋል” 6 በማለት ሌሎችን ይቅር ማለት ዓለም አቀፋዊ ትእዛዝ እንደሆነ ጌታ ያስተምረናል፡ ። ይቅርታን ማድረግ ትልቅ ድፍረት እና ትህትና ይጠይቃል። ጊዜ ሊወስድም ይችላል። ለልባችን ሁኔታ ሃላፊነት ስንሰጥ በጌታ ላይ እምነት እንድንጥል እና እንድንታመን ይፈልጋል። የመምረጥ መብታችን አስፈላጊነት እና ኃይል እዚህ ላይ ነው።

በአባካኙ ልጅ ምሳሌ ላይ በተገለጹት እኚህ አባት ምሳሌዎች አዳኙ ይቅርታ እርስ በርሳችን ልንሰጥ ከምንችላቸው እና በተለይም ለራሳችን ከምንሰጠው እጅግ የላቀ ስጦታዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቷል። በይቅርታ ልባችንን ማቅለል ሁልጊዜ ቀላል አይደለም፣ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስችል ኃይል ይቻላል።

የራሳችን የተሰበሩ ክፍሎች

ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3ላይ አንካሳ ሆኖ ስለተወለደ ሰው “ወደ መቅደስ ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ መልካም በሚባለው በመቅደስ ደጅ በየቀኑ [ይኖር ስለነበር]” ሰው እንማራለን።7

8 አንካሳው ለማኝ እድሜው ከ40 አመት በላይ የነበረ ሲሆን ህይወቱን በሙሉ በማያቋርጥ መፈለግ እና መጠባበቅ አሳልፏል፣ ምክንያቱም እሱ በሌሎች ልግስና ላይ የሚመካ ስለነበር ነው።

አንድ ቀን “ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ ሲሉ አየና ምጽዋት ለመኑ።

“ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ። ወደ እኛ ተመልከት አለው።

“እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ።

‘ጴጥሮስ ግን። ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው።

“በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥

“ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ።”9

ብዙ ጊዜ ልክ እንደ አንካሳው ለማኝ በቤተመቅደስ ደጃፍ በትግስት—ወይም አንዳንዴ ትዕግስት በማጣት—“ጌታን እየጠበቅን”10 ራሳችንን ልናገኝ እንችላለን። በአካል ወይም በስሜት ለመፈወስ በመጠባበቅ ላይ.። ወደ ጥልቅ የልባችን ክፍል የሚገቡ መልሶችን በመጠባበቅ ላይ። ተአምር በመጠበቅ ላይ።

ጌታን መጠበቅ የተቀደስ ቦታ ለመሆን ይችላል—በጥልቅ ግላዊ መንገድ አዳኙን የምናውቅበት የማጥራት እና የማጣራት ቦታ። ጌታን መጠበቅ “አምላክ ሆይ፣ የት ነህ?”11 ብለን የምንጠይቅበት ቦታ ሊሆን ይችላል—ሆን ብለን ደጋግመን በመምረጥ በክርስቶስ ላይ እምነት እንድንለማመድ መንፈሳዊ ጽናት የሚፈልግበት ቦታ። እኔ ይህን ቦታ አውቃለሁ፣ እና እኔ ይህን አይነት መጠበቅ ይገባኛል።

ለመፈወስ ከሚጓጉ ሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ስቃዬን አንድ ላይ በመሆን በአንድ የካንሰር ሕክምና ተቋም ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዓታት አሳልፍያለሁ። አንዳንዶቹ ኖረዋል፣ ሌሎቹ አልኖሩም። ከፈተናዎቻችን ነጻ መውጣት ለእያንዳንዳችን የተለየ እንደሆነ በጥልቅ ተማርኩ፣ ስለዚህ ትኩረታችን ነጻ ስለምንወጣንበት መንገድ ሳይሆን የበለጠ ስለ አዳኙ እራሱ መሆን አለበት። ትኩረታችን ሁል ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መሆን አለበት!

በክርስቶስ ማመን ማለት በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ጊዜ መተማመን ነው። ልክ ምን እንደምንፈልግ እና ልክ መቼ እንደሚያስፈልገን ያውቃልና። ለጌታ ፈቃድ ስንገዛ፣ በመጨረሻ ከፈለግነው እጅግ የሚበልጠውን እንቀበላለን።

ውድ ጓደኞቼ፣ ሁላችንም በህይወታችን ውስጥ መስተካከል፣ መጠገን ወይም መፈወስ ያለበት የተሰበረ ነገር አለን። ወደ አዳኙ ስንዞር፣ ልባችንን እና አእምሯችንን ከእሱ ጋር ስናስተካክል፣ ንስሃ ስንገባ፣ “ፈውስ በክንፎቹ ውስጥ ይዞ” 12 ወደእኛ ይመጣል፣ የፍቅር እጆቹን በዙሪያችን አድርጎ “አይዞዋችሁ። እናንተ ገና 5 ወይም 16፣ 23፣ 48፣ 64፣ 91 አመታችሁ ነው። ይህንን በጋራ መጠገን እንችላለን!” ይለናል።

በህይወታችሁ ውስጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ የመፈወስ፣ የመዋጀት እና ከማስቻል ሃይል በላይ የሆነ ምንም ነገር እንደሌለ እመሰክራለሁ። ለመፈወስ ብርቱ በሆነው በተቀደሰ እና ቅዱስ ስም በኢየሱስ ክርስቶስ አሜን።