ወደ እግዚአብሔር እቅፍ ኑ
በእግዚሃብሄር እቅፍ ውስጥ ስንሆን የመልካሙ እረኛን በንቃት የሚጠብቅ አሳዳጊ እንክብካቤ እናገኛለን፤ እንዲሁም የእሱ ቤዛዊ ፍቅር ስለሚሰማን ተባርከናል።
እንደ ወጣት ወላጆች፣ ወንድም እና እህት ሳማድ 1 በሳማራንግ ኤንዶኔዚያ ሁለት ክፍል ባለው ቤታቸው ውስጥ ወንጌልን ተማሩ። በትንሽ ጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጠው ብርሃኑን ከመፈንጠቅ ይልቅ ክፍሉን በወባ ትንኝ በሚሞላው የላምባ ኣምፖል መብራት ስር ሆነው ሁለት ወጣት ሚስዮናውያን ዘላለማዊ እውነታን አስተማሯቸው። እውነተኛ በሆነ ጸሎት እና ከመንፈስ ቅዱስ በተገኘ የግል መንፈሳዊ መገለጥ በኩል፣ የተማሩትን ወደማመን መጡ፤ እንዲሁም ለመጠመቅ እና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን መረጡ። ያ ውሳኔ እና ከዚያ በኋላ የነበራቸው የአናናር ዘይቤ ወንድም እና እህት ሳማድን እና ቤተሰባቸውን በያንዳንዱ የህይወታቸው ገጽታ ባርኳቸዋል።2
በኤንዶኔዢያ ውስጥ ከነበሩት የመጀመሪያ መስራቾች ውስጥ ነበሩ። በኋላም የቤተ መቅደስ ስርዓትን ተቀበሉ፤ እናም ወንድም ሳማድ የቅርንጫፍ ፕሬዚዳንት ከዚያም የአውራጃ ፕሬዘዳንት በመሆን በመላው መካከለኛው ጃቫ ዙሪያ እየተዘዋወረ ግዴታውን ያከናውን ነበር። ላለፉት አስር አመታት የሱርካታ ኢንዶኔዚያ ካስማ ፓትሪያርክ ሆኖ አገልግሏል።
ከ49 ዓመታት በፊት በዚያ ትሑት እና እምነት በተሞላ ቤት ውስጥ ከነበሩት ሚስዮናውያን አንዱ እንደመሆኔ፣ ንጉሥ ቢንያም በመፅሐፈ ሞርሞን ያስተማረውን በእነርሱ ውስጥ ተመልክቻለሁ፡- “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የተባረከና አስደሳቹን ሁኔታ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። እነሆም እነርሱ በሁሉም ነገሮች፣ በጊዜያዊም ሆነ በመንፈሳዊው፣ የተባረኩ ናቸውና፤3 የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እና ምሳሌ ለሚከተሉት፣ ከደቀመዛሙርቱ ውስጥ መቆጠርን በሚመርጡት ሰዎች ህይወት ውስጥ የሚፈሱ ብዙ የሆኑ፣ አስደሳች እና ዘላለማዊ በረከቶች አሉ።4
የእግዚአብሔር እቅፍ
በሞርሞን ውሃ አጠገብ ተሰብስበው ለነበሩት አልማ አቅርቦት የነበረው የጥምቀት ቃል ኪዳን ግብዣ የሚጀምረው በዚህ ሐረግ ነው፡- “አሁን፣ ወደ እግዚአብሔር በረት መምጣት ስለፈለጋችሁ።”5
በረት ማለት በጎች በሌሊት ጥበቃ የሚያገኙበት በድንጋይ ግድግዳዎች የሚሠራ ትልቅ አጥር ነው። አንድ መግቢያ በር ብቻ አለው። በቀኑ መጨረሻ እረኛው በጉን ይጠራል። ድምፁን ያውቃሉ እናም በበሩ አልፈው ደህንነትን ወደሚያስገኘው በረት ውስጥ ይገባሉ።
የአልማ ሰዎች በጎቹ ወደ ውስጥ ሲገቡ እንዲቆጠሩ እንዲሁም ቁስላቸው እንዲታይላቸውና በዚያም አንድ በአንድ መታከም ይችሉ ዘንድ እረኞች በመንጋው ጠባብ መግቢያ ላይ እንደሚቆሙ ያውቁ ነበር።6 የበጎቹ ደህንነት አና ጤና በእነሱ የመመለስ እና መንጋ ውስጥ የመቆየት ፍላጎት ላይ ይወሰናል።
ከእኛ መካከል እደማያስፈልጉ ወይም ዋጋ እንደሌላቸው በማሰብ በመንጋው ጫፍ ላይ እንዳሉ የሚሰማቸው ወይም በመንጋው ውስጥ እንዳልሆኑ የሚሰማቸው አንዳንዶች ሊኖሩ ይችላሉ። እናም በበጎች በረት ውስጥ እንደሚሆነው፣ በእግዚአብሔር በረት ውስጥም አንዳንድ ጊዜ አንዳችን የሌላችንን ጣቶች እንረግጣለን እናም ንስሃ መግባት ወይም ይቅር ማለት ያስፈልገናል።
ነገር ግን መልካሙ እረኛ7እውነተኛው የኛ እረኛ ሁሌም መልካም ነው። በእግዚአብሄር መንጋ ውስጥ የእሱን ተንከባካቢ፣ አሳዳጊ እንክብካቤውን እናገኛለን፤ እንዲሁም የእሱ ቤዛዊ ፍቅር ስለሚሰሰማን ተባርከናል። “እነሆ እኔ በእጄ መዳፍ ቀርጬሻለሁ፣ ግንቦችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ”8ብሏል። አዳኛችን ኃጢአታችንን፣ ህመማችንን፣ መከራችንን9 እና በህይወት ውስጥ ያሉ ፍትሃዊ ያልሆኑ ነገሮችን ሁሉ በእጆቹ ላይ ቀርጿል።10 “ለመምጣት [የ]ሚፈልጉ” እና በመንጋው ውስጥ ለመሆን የሚመርጡ ሁሉ እነዚህን በረከቶች ለመቀበል የተጋበዙ ናቸው።11 የነጻ ምርጫ ስጦታ በቀላሉ የመምረጥ ነጻነት አይደለም፤ ነገር ግን ትክክል የሆነውን የመምረጥ እድል ነው። ስለዚህ የበረቱ ግድግዳዎች ገደቦዎች አይደሉም፤ ነገር ግን የመንፈሳዊ ደህንነት ምንጭ ናቸው።
ኢየሱስ ክርስቶስ “አንድ መንጋ እና፣ አንድ እረኛ እንዳለ” አስተምሯል።12 እንዲህ ብሏል፦
“በበሩ የሚገባ የበጎች እረኛ ነው። …
“በጎቹም ድምጹን ይሰማሉ … ፣
…፣ በጎቹም ይከተሉታል፥ ድምፁንም ያውቃሉና።”13
ኢየሱስ በመቀጠል “በሩ እኔ ነኝ ማንም በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል” በማለት ወደ እግዚአብሔር መንጋ የሚገቡበት አንድ መንገድ ብቻ እና ለመዳን አንድ መንገድ ብቻ እንዳለ በግልፅ ያስተምራል።15 እርሱም በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው።15
በረከት በእግዚሃብሄር እቅፍ ውስጥ ላሉት ይመጣል።
ወደ መንጋው እንዴት መምጣት እንዳለብን ከእግዚአብሔር ቃል እንማራለን፤ እርሱም በኢየሱስ ክርስቶስ እና በነቢያቱ የተሰጠው ትምህርት ነው።19 የክርስቶስን ትምህርት ስንከተል እና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን፣ በንስሃ፣ በጥምቀት እና የመንፈስ ቅዱስ ማረጋገጫን በመቀበል እንዲሁም በታማኝነት በመቀጠል ወደ መንጋው ስንመጣ አራት ልዩ የሆኑ የግል በረከቶች እንደሚመጡ አልማ ቃል ገብቷል።17 እናንተ (1) “በእግዚአብሔር የተዋ[ጃችሁ]” (2) “የመጀመሪያው ትንሣኤ ካገኙት ጋር [የም]ትቈጠሩ” (3) “የዘላለም ሕይወት የምታገኙ” እና (4) ጌታ “መንፈሱን በእናንተ ላይ አብዝቶ የሚያፈስስ” ልትሆኑ ትችላላችሁ።18
አልማ ስለእነዚህ በረከቶች ካስተማረ በኋላ ሰዎቹ በደስታ እጃቸውን አጨበጨቡ። ምክንያቱ ይኼውና፡-
በመጀመሪያ ማዳን ማለት ዕዳን ወይም ግዴታን መክፈል ወይም ከሚያስጨንቅ ወይም ከሚጎዳ ነገር ነፃ መውጣት ማለት ነው።.19 ከኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ውጭ የቱንም ያህል የግል መሻሻል መጠን በእኛ በኩል ብናደርግ ከሰራነው ኃጢያት ወይም ከደረሰብን ቁስሎች ንፁህ ሊያደርገን አይችልም። እርሱም አዳኝችን ነው።20
ሁለተኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ አማካኝነትም ሁሉም ትንሳኤን ያገኛሉ።21 መንፈሳችን ሟች የሆነውን ሰውነታችንን ከለቀቀ በኋላ ከሞት በተነሳ አካላችን የምንወዳቸውን ሰዎች ማቀፍ የምንችልበትን ጊዜ ያለምንም ጥርጥር በጉጉት እንጠባበቃለን። ከመጀመሪያው ትንሳኤ መካከል ለመሆን በጉጉት እንጠባበቃለን።
ሶስተኛ የዘላለም ህይወት ማለት ከእግዚሐብሄር ጋር መኖር እና እንደሱ መኖር ማለት ነው። ይህ “ከእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጠው ስጦታ ነው።”22 እናም የደስታ ሙላትን ያመጣል።23 የሕይወታችን ታላቁ ምክንያት እና ዋናው አላማ ነው፡፡
አራተኛ የመለኮት አባል የሆነው መንፈስ ቅዱስ፣ በዚህ ሟች ህይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊውን መመሪያ እና መጽናኛ ይሰጣል።24
ደስተኛ ያለመሆንን አንዳንድ ምክንያቶች ተመልከቱ፡- መከራ የሚመጣው ከኃጢአት፣ ከሀዘን፣ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ከሚሰማን ብቸኝነት እና በምንሞትበት ጊዜ ምን እንደሚፈጠር እርግጠኛ ካለመሆን ከሚመጣ ፍርሃት ነው።22 ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር እቅፍ ስንገባ እና ከእርሱ ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን ስንጠብቅ ክርስቶስ ከኃጢአታችን እንደሚያድነን ከማወቅ የሚመጣ ሰላምና እምነት እንዲሁም የስጋችን እና የመንፈሳችን መለያየት በፍጥነት እንደሚያበቃና ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር እጅግ በታላቅ ክብር እንደምንኖር ይሰማናል።
በክርስቶስ ታመኑና በእምነት ተግብሩ።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ቅዱሳት መጻህፍት በአዳኙ ግርማ ኃይል እና ርህሩህ ምህረት እና የጸጋ ምሳሌዎች ተሞልተዋል። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የፈውስ በረከቶቹ በእርሱ ለታመኑት እና በእምነት ላደረጉት መጥተዋል። ለምሳሌ በቤተሳዳ ገንዳ የነበረ ደካማ ሰው ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ የሚለውን የአዳኙን ትእዛዝ በእምነት ሲከተል ተራመደ።26 በበረከት ምድር ላይ በማንኛውም መልኩ የታመሙ ወይም የተጎዱ የተፈወሱት “በአንድ ልብ” “በወጡ” ጊዜ ነው።27
በተመሳሳም፣ ወደ እግዚአብሄር እቅፍ ለሚመጡት የተገባውን አስደናቂ በረከቶች ለማግኘት ያንን እንድናደርግ ይጠይቃል— ለመምጣት መምረጥ ይኖርብናል። ታናሹ አልማ እንዲህ ሲል አስተምሯል፣ “እናም አሁን እላችኋለሁ፣ መልካም እረኛ ይጠራችኋል። ቃሉንም ብትሰሙ እርሱ ወደ መንጋው ያገባችኋል።28
ከብዙ ዓመታት በፊት፣ አንድ ውድ ጓደኛዬ በካንሰር ሳቢያ ህይወቱ አለፈ። ባለቤቱ ሳሮን በመጀመሪያ ስለምርመራው ስትጽፍ ፣ ይህን ተናግራለች፣ “እምነትን እንመርጣለን። በአዳኝችን በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት። በሰማይ አባታችን እቅድ ላይ እምነት እንዲሁም እሱ ፍላጎታችንን እንደሚያውቅ እና የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እምነት።29
እንደ ሳሮን ያሉ፣ በተለይም ፈተና፣ ተቃውሞ፣ ወይም መከራ ሲመጣ በእግዚአብሔር በረት ውስጥ ደህና የመሆን ውስጣዊ ሰላም የሚሰማቸው ብዙ የኋለኛው ቀን ቅዱሳንን አግኝቻለሁ።30 በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመን እና የእግዚአብሔርን ነብይ ለመከተል መርጠዋል። ውዱ ነብያችን ራስል ኤም ኔልሰን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል-- በህይወት ውስጥ ያለ ጥሩ ነገር ሁሉ–የዘለአለም ጠቀሜታ ያለው በረከት ሁሉ–በእምነት ይጀምራል።31
ወደ እግዚአብሔር እቅፍ ሙሉ በሙሉ ኑ
የወንድ ቅድመ አያቴ ቅድመ አያት ቅድመ አያት ጄምስ ሳውየር ሆልማን በ1847በ(እ.አ. እ) ወደ ዩታ መጣ፤ ነገር ግን በሐምሌ ወር ከብሪገም ያንግ ጋር ከመጡት መካከል አልነበረም። በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይ መጣ፤ በቤተሰብ መዛግብት መሠረትም በጎቹን የማምጣት ኃላፊነት ነበረበት። እስከ ኦክቶበር ድረስ ወደ ሳልት ሌክ ሸለቆ አልደረሰም ነበር፤ ነገር ግን እሱ እና በጎቹ መድረሳቸው አልቀረም።32
በምሳሌያዊ አነጋገር፣ አንዳንዶቻችን አሁንም ሜዳ ላይ ነን። ሁሉም ሰው በመጀመሪያ በሚደርሰው ቡድን ውስጥ አይኖርም። ውድ ጓደኞቼ፣ እባካችሁ ጉዟችሁን ቀጥሉ—እና ሌሎችም ሙሉ በሙሉ ወደ እግዚአብሔር መንጋ እንዲመጡ—እርዷቸው። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በረከቶች ዘላለማዊ ስለሆኑ የማይለኩ ናቸው።
የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርሰቲን አባል በመሆኔ ጥልቅ ምስጋና ይሰማኛል። ስለሰማዩ አባታችን እና ስለአዳኛችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንዲሁም ከነሱ ብቻ ስለሚመጣው ውስጥዊ ሰላም ማለትም በእግዚአብሔር መንጋ ውስጥ ስለሚገኘው ሰላም እና በረከቶች እመሰክራለው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።