አጠቃላይ ጉባኤ
መለወጥ ግባችን ነው
የሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:25

መለወጥ ግባችን ነው

መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ለእናንተ ሲናገር በመስማት በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እናንተ ለምታሳልፉት ጊዜ ምንም ምትክ የለውም።

ከዛሬ ሶስት አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ፣ እንደ ጌታ ቤተክርስቲያን አባላት በጉዞ ላይ ነበርን። የቀዳሚ አመራር እና የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ኑ፣ ተከተሉኝ የሚለውን የጥናት ምንጭ እንደ መመሪያ በመጠቀም በአዲስ እና በሚያነሳሳ መንገድ ቅዱሳት መጻህፍትን በማጥናት ስለኢየሱስ ክርስቶስ እንድንማር የጋበዙን በጥቅምት 2018 (እ.አ.አ) ነበር።

በማንኛውም ጉዞ፣ አንዳንዴ መቆምና የጉዞአችንን ሁኔታ መገምገም እንዲሁም ወደ ግባችን እየተጓዝን እንደሆንን ማረጋገጡ መልካም ልምድ ነው።

መለወጥ ግባችን ነው

ኑ ተከተሉኝ ከሚለው መግቢያ ላይ ይህን ጥልቅ አባባል አስቡበት፦

“ሁሉም የወንጌል መማር ማስተማር አላማ በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ በጥልቅ እንድንለወጥ እና እነርሱን እንድንመስል እኛን መርዳት ነው። …

“… ነገር ግን እምነታችንን የሚያጠናክር እና ወደ ተዓምራዊ ለውጥ የሚመራው የወንጌል ትምህርት እንዲያውበአንድ ጊዜ አይከሰትም። ከመማሪያ ክፍል በላይ ወደ ልባችን እና ቤታችን ይሰፋል። ወንጌልን መረዳት እና መኖር የማይቋረጥ የእለትተለት ጥረትን ይጠይቃል። ወደ ትክክለኛ መለወጥ የሚመራ የወንጌል ትምህርት የመንፈስ ቅዱስን ተፅዕኖ ይፈልጋል።”1

ያ ነው እኛ የምንፈልገው ተአምር —አንድ ሰው በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ልምድ ሲኖረው፣ 2 እና ያ ልምድ በመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ ሲባረክ። እንደዚህ አይነት ልምዶች ወደ አዳኝ እንድንለወጥ የከበሩ መሰረቶች ናቸው። እና ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን በቅርቡ እንዳስታውሱን፣ መንፈሳዊ መሠረቶች ያለማቋረጥ መጠናከር አለባቸው።3 ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መለወጥ የዕድሜ ልክ ሂደት ነው።4 መለወጥ ግባችን ነው

በጣም ውጤታማ ለመሆን፣ ከቅዱሳት መጻህፍት ጋር ያሏችሁ ልምዶች የራሳችሁ መሆን ይኖርባቸዋል።5 ስለሌላ ሰው ልምዶች እና ግንዛቤዎች ማንበብ ወይም መስማት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፣ ግን ያ ተመሳሳይ የመለወጥ ኃይል አያመጣም። መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ለእናንተ ሲናገር በመስማት በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እናንተ ለምታሳልፉት ጊዜ ምንም ምትክ የለውም።

መንፈስ ቅዱስ ምን እያስተማረኝ ነው?

በየሳምንቱኑ ተከተሉኝ የሚለውን የጥናት መርጃ መጽሃፍ ስከፍት በገጹ የላይኛው ክፍል “እነዚህን ምንባቦች ሳነብብ በዚህ ሳምንት መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረኝ ምንድን ነው” ብዬ እጽፋለሁ።

ቅዱሳት መጻህፍትን ሳጠና፣ ያንን ጥያቄ ደጋግሜ አሰላስላለሁ። ያለ ጥርጥር፣ መንፈሳዊ ግንዛቤዎች ይመጣሉ፣ እና በጥናት መርጃ መጽሃፌ ውስጥ ማስታወሻ እይዛለሁ።

አሁን፣ መንፈስ ቅዱስ ሲያስተምረኝ እንዴት አውቃለሁ? መልካም ብዙውን ጊዜ በትንሽ እና በቀላል መንገዶች ይከሰታል። አንዳንድ ጊዜ የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብ ከገጹ ላይ ዘሎ ትኩረቴን የሚይዝ ይመስላል። በሌላ ጊዜ፣ ስለወንጌል መርህ ሰፋ ባለ ግንዛቤ አእምሮዬ የበራ ያህል ይሰማኛል። ባለቤቴ አን ማሪ እና እኔ ስለምናነበው ነገር ስናወራም፣ የመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ ይሰማኛል። የእሷ አመለካከቶች ሁልጊዜ መንፈስን ይጋብዛሉ።

ነቢዩ እና ፋሲካ

በዚህ ዓመት ነፍሳችንን በብርሃን የሚሞላውን ብሉይ ኪዳንን እያጠናን ነው። ብሉይ ኪዳንን በማነብበት ጊዜ፣ ከታመኑ አስጎብኚዎች ከአዳም፣ ከሔዋን፣ ከሄኖክ፣ ከኖህ፣ ከአብርሃም እና ከሌሎች ከብዙዎች ጋር ጊዜዬን እንደማሳልፍ ይሰማኛል።

በዚህ ሳምንት ዘጸዓት ምዕራፎች 7–13ን እያጠናን እያለን፣ ግኤታ የእስራኤል ልጆችን ከብዙ መቶ አመታት የግብፅ ምርኮ ነፃ እንዳወጣቸው እንማራለን። ፈርዖን ልቡን ሳያለሰልስ ስለመሰከረላቸው ስለ ዘጠኝ መቅሰፍቶች፣ ማለትም ዘጠኝ አስደናቂ የአምላክ ኃይል መግለጫዎች፣ እናነባለን።

ከዚያም እግዚአብሔር ለነቢዩ ለሙሴ ስለ አሥረኛው መቅሠፍት እና እያንዳንዱ የእስራኤል ቤተሰብ ለበሽታው እንዴት እንደሚዘጋጅ ነገረው። እስራኤላውያን የፋሲካ በዓል ብለው ከሚጠሩት የአምልኮ ሥርዓት አንዱ እንክን የሌለበትን ተባዕት በግ መሥዋዕት አድርገው ማቅረብ ነበረባቸው። ከዚያም የቤታቸውን መቃን በበጉ ደም ምልክት ማድረግ ነበረባቸው። ጌታ በደም ምልክት የተደረገባቸው ቤቶች ሁሉ ሊመጣ ካለው አስከፊ መቅሰፍት እንደሚጠበቁ ቃል ገባ።

ቅዱሳት መጻህፍት እንደሚሉትም፣ “የእስራኤልም ልጆች … እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ” (ዘጸአት 12፥28)። በዚያ ቀላል የመታዘዝ መግለጫ ውስጥ በጣም ኃይለኛ ነገር አለ።

የእስራኤል ልጆች የሙሴን ምክር በመከተላቸው እና በእምነት ስላደረጉ፣ ከበሽታው ድነዋል፣ ከጊዜ በኋላም ከምርኮ ነፃ ወጡ።

ስለዚህ፣ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ በዚህ ሳምንት መንፈስ ቅዱስ ምን አስተማረኝ?

በአእምሮዬ ላይ ያረፉ ጥቂት ሃሳቦች እነሆ፦

  • ጌታ ህዝቡን ለመጠበቅ እና ለማዳን በነቢዩ በኩል ይሰራል።

  • ነቢዩን ለመከተል ያለ እምነት እና ትህትና የጥበቃ እና የመዳን ተአምርን ይቀድማል።

  • በበሩ ግንብ ላይ ያለው ደም በእግዚአብሔር በግ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለ የውስጣዊ እምነት ምልክት ነው።

ነቢዩ እና የጌታ ተስፋዎች

በዚህ የብሉይ ኪዳን ዘገባ ጌታ ህዝቡን የባረከበት መንገድ እና ዛሬም ህዝቡን እየባረከ ባለው መንገድ መካከል ያለው ተመሳሳይነት አስደንቆኛል።

የጌታ ህያው ነቢይ፣ ፕሬዘደንት ኔልሰን፣ ቅዱሳት መጻህፍትን ለማጥናት እንዲያስችሉን ኑ፣ ተከተሉኝን ሲያስተዋውቁን፣ ቤቶቻችንን ወደ እምነት መቅደስ እና የወንጌል ትምህርት ማዕከላት እንድንለውጥ ጋብዘውናል።

ከዚያም የአራት ልዩ በረከቶችን ተስፋ ሰጥተዋል፦

  1. የእናንተ ሰንበት ቀናት አስደሳች ይሆናሉ፣

  2. የእናንተ ልጆች የአዳኝን ትምህርቶች በመማር እና በእነዚህም በመኖር ይደሰታሉ፣

  3. ጠላት በእናንተ ህይወት እና በእናንተ ቤት ውስጥ ያለው ተፅዕኖ ይቀንሳል፣ እንዲሁም

  4. እነዚህ በእናንተ ቤተሰብ ውስጥ ያሉት ለውጦች ታላቅ እና የሚቀጥሉይሆናሉ።6

አሁን፣ በግብፅ ከሙሴ ጋር የፋሲካን በዓል ከተካፈሉት ሰዎች የተገኙ ምንም ዓይነት የመጽሔት ማስታወሻ የለንም። ነገር ግን፣ በእኩል እምነት፣ ዛሬ የፕሬዘደንት ኔልሰንን ምክር እየተከተሉ እና ቃል የተገቡትን በረከቶች ከሚቀበሉ ቅዱሳን ብዙ ምስክርነቶች አሉን።

እነዚህም ምስክሮች ጥቂቶቹ እነሆ፦

የአንድ ወጣት ቤተሰብ እናት እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ክርስቶስ እናወራለን እናም በቤታችንም በክርስቶስ ደስ ይለናል። ልጆቼ ወደ አዳኝ እንዲቀርቡ በሚያደርጉ፣ የወንጌል ንግግሮች በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ያድጋሉ—ያ ለእኔ ትልቁ በረከት ነው።”7

አንድ አረጋዊ ወንድም የቅዱሳት መጻህፍት ጥናታቸውን በኑ ተከተሉኝ በኩል “ለመንፈሳዊ ደህንነታችን አስፈላጊ የሆነውን የወንጌል ትምህርት እንድናይ የሚረዳን በመለኮታዊ ብርሃን የተሞላ ቱቦ” ነው በማለት ጠርተውታል።8

አንዲት ወጣት ሚስት በትዳሯ ውስጥ ያሉትን በረከቶች እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “የባለቤቴን ልብ በጥልቀት ማወቅ ችያለሁ፤ እንዲሁም አብረን ስናጠና ልቤን ለእሱ ይበልጥ ግልጽ ማድረግ ችያለሁ።”9

ብዙ የቤተሰብ አባላት ያላት እናት ቤተሰቧን ለማስተማር ያላት ጥረት እንዴት እንደተቀየረ አስተዋለች። እንዲህም አለች፦ “ወደኋላ ሳስብበት፣ የበረዶ ጓንት እጄን ሸፍኖ ፒያኖውን እንደምጫወት አይነት ነበር። እየተንቀሳቀስኩኝ ነበር፣ ሆኖም ሙዚቃው በጣም ትክክል አልነበረም። አሁን ጓንቶቹ ወልቀዋል፣ እናም ሙዚቃዬ አሁንም ፍጹም ባይሆንም፣ ልዩነቱን እሰማለሁ። ኑ፣ ተከተሉኝ ራዕይ፣ ችሎታ፣ ትኩረት፣ እና አላማ ሰጥቶኛል።”10

አንድ ወጣት ባል እንዲህ ብሏል፦ “ ኑ፣ ተከተሉኝ ን በመደበኛነት በማለዳ የማስቀድመው ነገር ካደረግኩት ጊዜ ጀምሮ፣ በቤቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጣቸው በጣም አስፈላጊው ነገሮች ይበልጥ ግልጽ ሆነዋል። ማጥናት ለእኔ በጣም አስፈላጊ ስለሆኑት ስለቤተመቅደስ፣ ከባለቤቴ ጋር ስላለኝ ግንኙነት እና ስለ ጥሪዬ የበለጠ ወደማሰብ ይመራኛል። ቤቴ እግዚአብሔር የሚቀድምበት መቅደስ በመሆኑ አመስጋኝ ነኝ።”11

አንዲት እህት እንዲህ ብላ ተናግራለች፦ “የኑ፣ ተከተሉኝ የዕለት ተዕለት ልምዶቼ እምብዛም ትኩረት የሚስቡ አይደሉም፣ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ እንዲህ ባለው የማያቋርጥና ትኩረት የታከለበት የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት እንዴት እንደተለወጥኩ ለማየት ችያለሁ። እንዲህ ዓይነቱ ጥናት ትሁት ያደርገኛል፣ ያስተምረኛል እንዲሁም ትንሽ በትንሽ ይለውጠኛል።”12

አንድ ከሚስዮን የተመለሰም እንዲህ ብሏል፦ “የኑ፣ ተከተሉኝ ፕሮግራም በሚስዮን ላይ ወዳረግኩት የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ደረጃ ይበልጥ እንድቀርብ አድርጎኛል፣ እናም የቅዱሳት መጻህፍትን ጥናት የተነበቡትን ካልተነበቡት ከማረጋገጥ አስተሳሰብ እግዚአብሔርን ወደማወቅ እውነተኛ የበለጸገ የመማሪያ ክፍለ ጊዜዎች መሸጋገር ችያለሁ። ”13

አንድም ወንድም እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ በህይወቴ ውስጥ የበለጠ ተቀባይነት እንዳለው እና ውሳኔዎችን ለማድረግ የእግዚአብሔር መገለጥ መመሪያ እንዳለኝ ይሰማኛል። በቀላል የክርስቶስ ትምህርት እና በኃጢያት ክፍያው ውስጥ ስላለው ውበት የበለጠ ጥልቅ ውይይቶች አድርጊያለሁ።14

የሰባት ዓመት ልጅ እንዲህ ብሏል፦ “በቅርቡ እጠመቃለሁ፣ እና ኑ፣ ተከተሉኝ እያዘጋጀኝ ነው። እኔና ቤተሰቤ ስለ ጥምቀት እንነጋገራለን፣ እና አሁን ለመጠመቅ አልፈራም። ኑ፣ ተከተሉኝ መንፈስ ቅዱስ ወደ ልቤ እንዲገባ ረድቶኛል፣ እናም ቅዱሳት መጻህፍትን ሳነብ ሞቅ ያለ ስሜት ይሰማኛል።”15

እና በመጨረሻም፣ ከብዙ ልጆች እናት፦ “የእግዚአብሔርን ቃል ስናጠና፣ ቤተሰባችን ከስጋት ወደ ሀይል፤ ከፈተና እና ከፈታኝ ሁኔታዎች ነጻ ወደመውጣት፤ ከክርክር እና ትችት ወደ ፍቅር እና ሰላም፤ እንዲሁም ከጠላት ተጽዕኖ ወደ አምላክ ተጽዕኖ እንዲሸጋገር ረድቶታል።”16

እነዚህ እና ሌሎች ብዙ ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች የእግዚአብሔርን በግ ደም በምሳሌያዊ ሁኔታ በቤታቸው መግቢያ ላይ አስቀምጠዋል። አዳኝን ለመከተል ያላቸውን ውስጣዊ ቁርጠኝነት እያሳዩ ናቸው። እምነታቸው ታዓምሩን ይቀድማል። ያም አንድ ሰው በቅዱሳት መጻህፍት ያለው ልምድ እና በመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ የመባረክ ተአምር ነው።

ቅዱሳት መጻህፍትን ስናጠና፣ በምድር ላይ ምንም መንፈሳዊ ራብ አይኖርም። ኔፊ እንዳለው፣ “የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰሙ ሁሉና፣ እርሱን አጥብቆ የያዘ በፍፁም አይጠፋም፤ ፈተናዎችና የጠላት ክፉ ፍላፃ እነርሱን ወደጥፋት ለመውሰድ በማሳወር ሊያሸንፏቸው አይችሉም” (1 ኔፊ 15፥24)።

በጥንት ዘመን፣ የእስራኤል ልጆች በነቢዩ ሙሴ በኩል የጌታን መመሪያ ሲከተሉ፣ በደህንነት እና በነጻነት ተባርከዋል። ዛሬ፣ በህያው ነቢያችን፣ ፕሬዘደንት ኔልሰን፣ በኩል የተሰጠውን የጌታን መመሪያ ስንከተል፣ በልባችን በመለወጥ እና በቤታችን ውስጥ ጥበቃ በማድረግ በእኩል ተባርከናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ እመሰክራለሁ። ይህቺም በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ምድር በኩል በዳግም የተመለሰች የእርሱ ቤተክርስቲያን ናት። ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልስን የዚህ ቀን የጌታ ነቢይ ናቸው። እወዳቸዋለሁ እናም እደግፋቸዋለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ብሉይ ኪዳን 2022 (እ.አ.አ)፣ vii።

  2. “ለመንፈሳዊ እድገታችን እያንዳንዳችን ተጠያቂዎች ነን” (ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “መክፈቻ ንግግር፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2018 (እ.አ.አ)፣ 8)።

  3. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ቤተመቅደስ እና መንፈሳዊ መሰረታችሁ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2021 (እ.አ.አ)፣ 93–96።

  4. “ለጌታ ጊዜ ስጡ! መንፈስ ቅዱስ ሁል ጊዜ፣ ከእናንተ ጋር እንዲኖር የሚፈቅዱትን ነገሮች በማድረግ፣ የራሳችሁን መንፈሳዊ መሠረት ጽኑ እና የጊዜን ፈተና መቋቋም የሚችል አድርጉ” በማለት ፕሬዘደንት ኔልሰን የተማፀኑበት አስፈላጊ ምክንያት ነው (“ለጌታ ጊዜ ስጡ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2021 (እ.አ.አ)፣ 120)።

  5. “ሌሎች የሚናገሩትም ሆነ የሚያደርጉት ምንም ይሁን ምን፣ ማንም ስለ እውነቱ በልባችሁና እና በአዕምሮአችሁ የተመሰከራላችሁን ምስክር ሊወስድባችሁ አይችልም” (ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ራዕይ ለቤተክርስቲያኗ እና ራዕይ ለህይወታችን፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2018 (እ.አ.አ)፣ 95)።

  6. ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “የኋለኛው ቀን ቅዱሳን አርአያ መሆን፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2018 (እ.አ.አ)፣ 113–14 ይመልከቱ። ፕሬዘደንት ኔልሰን ይህን ግብዣ ባለፈው ሚያዝያ ደግመዋል፦ “በቤታችሁን የመጀመሪያ የእምነት መሸሸጊያ ለማድረግ ልባዊ ውሳኔአችሁ በምንም መፈጸም አይገባቸውም። እምነት እና ቅድስና በዚህን በወደቀው አለም ውስጥ ሲቀንስ፣ የቅዱስ ቢታዎች ፍላጎታችሁ ይጨምራል። ከዚያም አስፈላጊ እቅድ ቤታችሁን እውነተኛ ቅዱስ ቦታ እንድታደርጉ ‘እና [እንዳትነቃነቁ]’ [ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 87፥8 አትኩሮት ተጨምሮበታል] እገፋፋችኋለሁ” (“እየተማርናቸው ያለነው እና በፍጹም የማንረሳቸው፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2021 (እ.አ.አ)፣ 79)።

  7. የግል ደብዳቤ፤ እንዲሁም 2 ኔፊ 25፥26ን ይመልከቱ።

  8. የግል ደብዳቤ።

  9. የግል ደብዳቤ።

  10. የግል ደብዳቤ።

  11. የግል ደብዳቤ።

  12. የግል ደብዳቤ።

  13. የግል ደብዳቤ።

  14. የግል ደብዳቤ።

  15. የግል ደብዳቤ።

  16. የግል ደብዳቤ።