ጉድጓዱ አጠገብ ትምርቶች
እዚ ለማድረግ የተላክነውን ነገር ለማከናወን የሚያስችለንን ጥንካሬ እና ፈውስ ለማግኘት ወደ አዳኙ መዞር እንችላለን።
በዚህ የሴቶች ስብሰባ የአጠቃላይ ጉባኤ ውስጥ ከእያንዳንዳችሁ ጋር መሰብሰብ ምን ያህል ደስ ይላል።
በምዕራባዊ ኒው ዮርክ ውስጥ አደኩኝ እናም ከቤታችን 32 ኪሜ በሚርቀው የቤተክርስቲያኗን ትንሽዬ ቅርንጫፍ ተካፈልኩኝ። ባረጀው በተከራየ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከጓደኛዬ ፓቲ ጆ ጋር ብቻ በምድር ቤት ሰንበት ክፍል ውስጥ ተቀምጬ ሳለሁ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለም አቀፋዊ እህቶች አካል እሆናለው ብዬ አስቤ አላውቅም።
ከአምስት ዓመት በፊት፣ በምስራቅ አውሮፓ አካባቢ ከተባረኩ ቅዱሳን ጋር ሚስዮን እያገለገልን ሳለ ባለቤቴ ብሩስ በጠና ታመመ። ወደ ቤት ተመለስን እና ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ እሱ ሞተ። ሕይወቴ በአንድ ምሽት ውስጥ ተለወጠ። አዝኜ ነበር እናም የደከምኩኝ እና የተጋለጥኩኝ ያህል ተሰማኝ። ጌታ መንገዴን እዲመራኝ ለመንኩኝ፦ “ምን እንዳደርግ ትፈልጋለህ?”
ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ደብዳቤዎቼን ስመለከት አንድ ትንሽዬ ፎቶ ቀልቤን ያዘኝ። ቀረብ ብዬ ስመለከት፣ ሳምራዊ ሴት ከኢየሱስ ጋር በጉድጓዱ አጠገብ የሚያሳይ የሰዓሊ ፈጠራ እንደሆነ ተገነዘብኩኝ። በዛች ሰዓት መንፈስ በግልፅ እንዲህ ተናገረኝ፦ “ማድረግ ያለብሽ ያንን ነው።” አፍቃሪው የሰማይ አባት ወደ አደኙ እንድመጣ እና እንድማር እየጋበዘኝ ነበር።
ከእርሱ “ ከሚፈልቀው የሂወት ውኃ” ጉድጓድ መጠታቴን ስቀጥል እየተማርኩ ያለሁትን ሶስት ትምህርቶችን ለማካፈል እወዳለው።1
አንደኛ፦ የቀድሞው እና የአሁን ሁኔታችን የወደፊታችንን መወሰን አይችልም።
እህቶች፣ ብዙዎቻችሁ እኔ እንደተሰማኝ ሊሰማችሁ እንደሚችል አውቃለው፣ ከባድ ፈተናዎችን እንዴት እንደምትጋፈጡ እርግጠኛ ሳትሆኑ እና ስትሸነፉ— ምክንያቱም ህይወታችሁ እንዳሰባችሁት፣ እንደፀለያችሁት እና እንዳቀዳችሁት ባለመሆኑ።
ሁኔታችን ምንም ቢሆን እንኳን፣ ሕይወታችን ቅዱስ ነው እንዲሁም ትርጉም እና አላማ አለው። እያንዳንዳችን በነፍሳችን በመለኮት የተወለድን የእግዚአብሔር ተወዳጅ ሴት ልጆች ነን።
አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሃጢያት ክፍያው አማካኝነት እንድንነፃ እና እንድንፈወስ አስቻለን፣ የቤተሰብ አባሎች ውሳኔ፣ የትዳር ሁኔታችን፣ አካላዊ ወይም አእምሮአዊ ጤንነታችን ወይም ማንኛውም ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ምድራዊ አላማችንን እንድናሳካ አስቻለን።
ከጉድጓዱ አጠገብ ያለችውን ሴት አስቡ። ሕይወቷ እንዴት ነበር? አምስት ባሎች እንደነበሯት እና አብራው ከምትኖረው ሰው ጋር ጋብቻ እንዳልፈፀመች ኢየሱስ ተመለከተ። እናም የሕይወት ችግሮቿ ምንም ቢሆኑም፣ አዳኙ መሲህ እንደሆነ ለህዝብ ካወጀው አንዱ አዋጅ ለእሷ ነበር። እርሱ አለ “እኔ የማዋራሽ እሱ ነኝ።”2
በከተማዋ ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብላ በማወጅ ጠንካራ ምስክር ሆነች። “ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት።”3
የቀድሞ እና የወቅቱ ሁኔታዎቿ የወደፊቷን አልወሰኑትም። ልክ እንደሷ፣ እዚ እንድናደርግ የተላክነውን ሁሉ ለማከናወን እንድንችል ለጥንካሬ እና ለፈውስ ዛሬ ወደ አዳኙ ለመዞር መምረጥ እንችላለን።
ሁለተኛ፦ ኃይሉ በእኛ ውስጥ ነው።
በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች በተመሳሳይ ቁጥር ውስጥ ጌታ ሴቶችን እና ወንዶችን እንዲህ ያበረታታል “ኃይሉ በእነሱ ውስጥ ስላለ መልካም ስራን በጉጉት ማከናወን፣ እናም ብዙ ነገሮችን በራሳቸው ነጻ ምርጫ ማድረግ፣ እናም ብዙ ጽድቅንም መስራት።”4
እህቶች፣ ኃይሉ ብዙ ጽድቅን ሊያመጣ፣ በእኛ ውስጥ ነው ያለው!
ፕሬዝደንት ረስልኤም ኔልሰን እንዲህ መሰከሩ፣ “ከእግዚአብሄር ጋር ቃል-ኪዳኖችን የገቡ እያንዳንዳቸው ሴቶች እና ወንዶች እንዲሁም እነዚያን ቃል ኪዳኖች የሚጠብቁ እና በክህነት ስርዓቶች ውስጥ በብቃት የሚሳተፉ ሁሉ የእግዚአብሔርን ኃይል በቀጥታ የመጠቀም ስልጣን አላቸው።”5
በጥምቀት እና በቅዱስ ቤተመቅደሶች ውስጥ የገባነውን ቅዱስ ቃልኪዳኖች ለማክበር ስንጥር፣ “በፈዋሽ አጠናካሪ ኃይሉ”6 እና “ከዚህ ቀደም ባልነበረን መንፈሳዊ ሃሳቦች እና ማነሳሻዎች” ጌታ ይባርከናል።7
ሶስተኛ፦ “ከትንሽ ነገሮች ታላቅ የሆነ ነገር ይወጣል።”7
በተራራ ላይ ትምህርቱ፣ ኢየሱስ እንዲህ አስተማረ፣ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ”8 እና “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ።”9 በኋላ ለይ የመንግስተ ሰማያትን እድገት ከእርሾ ጋር አነፃፀረ፣ “እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሶስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።”10
-
ጨው
-
እርሾ
-
ብርሀን
በትንሹም ቢሆን እንኳን እያንዳንዱ በዙሪያቸው ያሉትን ሁሉንም ነገሮች ላይ ተፅዕኖ ያደርጋሉ። አዳኙ የእርሱን ኃይል እንደ ጨው፣ እርሾ፣ እና ብርሃን እንድንጠቀም ይጋብዘናል።
ጨው
በምንበላው ምግብ ጣዕም ውስጥ ጨው የሚያደርገው ለውጥ አስደናቂ ነው። እናም ይሁን እንጂ፣ ጨው በጣም እርካሽ እና ቀላል የሆነ ንጥረ ነገር ነው።
በ2ኛ ነገሥት ውስጥ፣ በሶሪያዎች ተማርካ ለሶሪያ ጦር አዛዝ ለንዕማን፣ ሚስት አገልጋይ ስለሆነች ስለ “አንዲት ብላቴና” እናነባለን።11 እሷ እንደ ጨው ነበረች፤ እድሜዋም ትንሽ ነበር፣ዓለማዊ ጠቀሜታ ያልነበራት ወጣት ነበረች እናም በባዕድ አገር ውስጥ እንደ ባሪያ የነበረው ሕይወቷ በግልፅ ተስፋ ያደረገችው አልነበረም።
ይሁን እንጂ፣ እሷ ለንዕማን ሚስት ሁለት ዓረፍተ ነገሮችን በእግዚአብሔር ኃይል እንዲህ ተናገረች “ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በተፈወሰው ነበር።”12
የእሷ የእምነት ቃላት ወደ ነዕማን ደረሰ፣ ከዛ ቃላቷን በተግባር ላይ በማዋል በአካል እና በመንፈስ እንዲፈወስ አስቻለው።
ነብዩ ኤልሳዕ እንደጠቆመው፣ ብዙውን ጊዜ ንዕማንን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንዲታጠብ ያሳመኑት አገልጋዮች ላይ እናተኩራለን፣ ነገር ግን ንዕማን “በትንሽ ብላቴናዋ” አማካኝነት ባይሆን ኖሮ የኤልሳዕ ደጃፍ ላይ አይደርስም ነበር።
ወጣት ልትሆኑ ትችላላችሁ ወይም የማትረቡ ሊሰማችሁ ይችላል፣ ነገር ግን በሕይወታችሁ በትምህርት ቤት እና በማህበረሰባችሁ ውስጥ እንደ ጨው መሆን ትችላላችሁ።
እርሾ
ዳቦን ካለ እርሾ በልታችሁ ታውቃላችሁ? እንዴት መግለፅ ትችላላችሁ? ጥቅጥቅ ያለ? ከባድ? ጠንካራ? በትንሽዬ እርሾ ብቻ ዳቦው ከፍ ይላል፣ ቀላል እና ለስላሳም ይሆናል።
የእግዚአብሔርን ኃይል በሕይወታችን ውስጥ ስንጋብዝ፣ “የክብደትን መንፈስ”13 ሌሎችን ከፍ በሚያደርጉ እና ልብን እንዲፈወስ ቦታ በሚሰጡ በተነሳሱ ምልከታዎች መተካት እንችላለን።
በቅርብ አንድ ጓደኛዬ በገና በዓል ጠዋት ላይ በሃዘን ተሞልታ አልጋ ላይ ተኝታ ነበር። ልጆቿ ከአልጋው እንድትነሳ ለመኗት፣ ይሁን እንጂ ትዳሯን ልትፈታ ስለሆነ በህመም ተሞልታ ነበር። በአልጋው ውስጥ ሆና በመንሰቅሰቅ፣ ስለ ተስፋ መቁረጧ እየነገረችው ነፍሷን በጸሎት ወደ የሰማይ አባት አደረገች።
ጸሎቷን ስትጨርስ እግዚአብሔር ዕቅዷን እንደሚያውቅ መንፈሱ በሹክሹክታ ነገራት። ለእርሷም ባለው ርህራሔ ተሞላች። ይህ የተቀደሰ ልምድ ስሜቶቿን አረጋገጠላት እና ብቻዋን እያዘነች እንዳልሆነ ተስፋ ሰጣት። ተነስታ ወደ ውጪ ወጣች እና የጠዋቱን ክብደት በሳቅ እና በደስታ በመተካት ከልጆቿ ጋር የበረዶ ሰውን ሰራች።
ብርሀን
በአንድ ክፍል ውስጥ ያለውን ጨለማ ለመስበር ምን ያህል ብርሃን ያስፈልጋል? አንድ ትንሽ ጨረር። እናም ያ የብርሃን ጨረር በጨለማ ስፍራ ውስጥ በውስጣችሁ ባለው የእግዚአብሔር ኃይል ይመነጫል።
ብቸኝነት ቢሰማችሁም እንኳን የሕይወት ወላፈኖች ቢከፉም በአለመግባባት፣ በግራ መጋባት እና በአለማመን ጨለማ ውስጥ ብርሃናችሁን ማንፀባረቅ ትችላላችሁ። በክርስቶስ ያላችሁ የእምነት ብርሃናችሁ በዙሪያችሁ ያሉትን ሰዎች ወደ ደህንነት እና ሰላም በመምራት ዘላቂ እና እርግጠኛ መሆን ይችላል።
እህቶች፣ ትንሽዬ ጨው፣ አንዲት ማንኪያ እርሾ እና የብርሃን ጨረር ስንሰጥ፣ ልቦች ሊቀየሩ እናም ሕይወቶች ሊባረኩ ይችላሉ።
አዳኙ የሕይወታችን ጨው እንደሆነ፣ የእርሱን ደስታ እና ፍቅር እኛ እንድንቀምስ እየጋበዘንእንድንቀምስ እየጋበዘን እንደሆነ እመሰክራለሁ።14 ሕይወታችን ከባድ ሲሆን እርሱ እርሾ የሚሆነው እርሱ ነው፣ ለእኛ ተስፋ ያመጣልናል15 እናም ሸክማችንን ያነሳል16 አቻ በሌለው ኃይሉ እና የቤዛነት ፍቅሩ አማካኝነት።17 እርሱ ብርሃናችን ነው፣18 ወደ ቤት የሚወስደውን የእኛን መንገድ ያበራዋል።
ልክ በጉድጓዱ አጠገብ እደነበረችው ሴት እኛም ወደ አዳኙ እንድንመጣ እና የእርሱን ዘላለማዊ ውኃን እንድንጠጣ እጸልያለሁ። ከሰማርያ ሰዎች ጋር እኛም እንዲህ ማወጅ እንችላለን፣ “አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፣ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና እርሱ በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን።”19 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።