ስለ ክርስቶስ እንናገራለን
አለም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አሳንሶ ሲያወራ እኛ አብልጠን እናውራ።
የተወደዳችሁ ጓደኞች እና አማኞች ፍቅሬን ለናንተ እገልጻለሁ። ባለፉት ወራት በአለም አቀፋዊው ወረርሽኝ ህወታችንን ሲያናውጥ እና ውድ የቤተሰብ አባላትን እና ጓደኞችን ሲወስድብን እምነታችሁን እና ተነሳሽነታችሁን አድንቅያለሁ።
በዚህ እርግጠኛ በማይኮንበት ወቅት ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ስለመሆኑ ላለኝ እርግጠኝነት እና እውቀት ያልተለመደ አመስጋኝነት ተሰምቶኛል። እንደዛ ተሰምቷችሁ ያውቃል? በእያንዳንዳችን ላይ የተጫኑ መከራዎች አሉ፣ ነገር ግን በትህትና “እኔ መንገድ፣ እውነት እና ህይወት ነኝ” ያለው ከፊታችን ነው።1 በዚህ እራሳችንን ከሌሎች በአካላዊ ዕርቀት በምንጠብቅበት ወቅት እየፀናን ቢሆንም እንኳን፣ በመንፈስ እራሳችንን “ወደ እኔ ኑ” በለማት በፍቅር ከሚጠራን ግን መራቅ የለብንም።2
በጠራ የጨለመ ሰማይ እንደሚመራ ኮከብ ክርስቶስ መንገዳችንን ያበራል። በከብቶች ግርግም ወደዚች ምድር መጣ። እርሱ ፍጹም ህይወትን ኖረ። የታመሙትን ፈወሰ እናም ሙታንን አስነሳ። እርሱ ለተረሳው ወዳጅ ነበር። መልካምን እንድንሰራ፣ እንድንታዘዝ እና እርስ በርስ እንድንዋደድ አስተምሮናል። በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ ከሶስት ቀን በኋላ በግርማ በመነሳት እኛ እና የምንወዳቸው ከመቃብር በላይ እንድንኖሩ አስቻለ። በማይነጻጸረው ምህረቱ እና ጸጋው በራሱ ላይ የኛን ሃጥያት እና መከራ በመቀበል ንስሃ ስንገባ ስርየትን እና ሰላምን ለህይወታችን ሰጠን። እኛ እንወደዋለን። እናመልከዋለን። እንከተለዋለን። እርሱ የነፍሳችን ደህንነት ምክንያት ነው።
በሚገርም ሁኔታ ይህ መንፈሳዊ እርግጠኝነት በኛ ዉስጥ ሲጠነክር በምድር ላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም ጥቂት የሚያውቁ የተወሰኑ አሉ፣ ስሙ ለዘመናት ሲታወጅ በነበሩ ብዙ የምድር ክፍሎች ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለ እምነት እየቀነሰ ነው። በአውሮፓ ያሉ ጀግና ጻድቃን በአስርት አመታት ወስጥ የእምነት መውደቅን በሃገራቸው ተመልክተዋል።3 በሚያሳዝን ሁኔታ እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ወስጥም እምነት እየቀነሰ ነው። የቅርብ ጊዜ ጥናት ባለፉት 10 አመታት በዩናይትድ ስቴትስ 30 ሚሊዮን ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊነት ማመን ማቆማቸውን ያሳያል።4 ሌላ ጥናት በአለም አቀፍ ደረጃ ስንመለከት በሚቀጥሉት አስርት አመታት ከሁለት እጥፍ በላይ የሚሆኑት ክርስትናን ከሚቀበሉት ይልቅ የሚተውት እንደሚበልጡ ይተነብያል።5
እኛ በእርግጥ የመምረጥ መብትን እናከብራለን ሆኖም የሰማይ አባታችን “የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት” ብሏል።6 ጉልበት ሁሉ የሚንበረከክበት እና ምላስ ሁሉ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ የሚመሰክርበት ጊዜ ይመጣል ብዬ እመሰክራለሁ።7
ለሚቀያየረው አለም እንዴት ነው መመለስ የምንችለው? አንዳንዶቹ እምነታቸውን ሲተው ሌሎች እውነትን እየፈለጉ ነው። በላያችን ላይ የአዳኝን ስም ወስደናል። ተጨማሪ ምን ማድረግ አለብን?
የፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን መዘጋጀት
የጥያቅያችን መልስ የተወሰነው ክፍል ጌታ ፕሬዝዳንት ራስል ኤም. ኔልሰንን ለቤተ ክርስትያኗ ፕሬዝዳንትነት ከመጠራቱ በፊት በነበሩት ወራት እንዴት እንዳስተማረው ስናስታውስ ሊመጣ ይችላል። ከጥሪው አንድ አመት ቀደም ብሎ ሲናገር ፕሬዝዳንት ኔልሰን በጥቅስ ማውጫ ላይ ለ2 ሺህ 200 ጊዜ የተጠቀሱትን የኢየሱስ ክርስቶስ ስምን በጥልቀት እንድናጠና ጋብዞን ነበር።8
ከሶስት ወር በኋላ በሚያዚያው አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ይህ ጥልቅ የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥናት ከአስርት አመታት ታማኝ ደቀመዝሙርነት እንኳን እንዴት ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ተናግሯል። እህት ዌንዲ ኔልሰን እንዴት ተጸዕኖ እንዳሳደረበት ጠይቃው ነበር። “እኔ ሌላ ሰው ነኝ!” ብሎ መለሰ። እሱ መልካም ሰው ነበር። በ92 አመትህ ሌላ ሰው ነህ? ፕሬዝዳንት ኔልሰን እንዲህ ገለፁ፥
“ስለ አዳኙ እና ስለ ቤዛነት መስዋዕቱ ለመማር ጌዜ ስንሰጥ ወደ እርሱ እንቀርባለን። …
“… ትኩረታችን በአዳኛችን እና በእርሱ ወንጌል ላይ የታሰረ [ይሆናል]።”9
አዳኝ “በሁሉ ሃሳብህ ወደ እኔ እይ” ብሏል።10
በስራ፣ በሃሳብ እና ዋጋ ባለው ጥረት አለም፤ ልባችን፣ አእምሯችን እና ሃሳባችን ተስፋችን እና መዳናችን በሆነው በሱ ላይ ነው።
የታደሰ የክርስቶስ ጥናት ፕሬዝደንት ኔልሰንን እንዲዘጋጅ ከረዳው እኛንስ ለመዘጋጀት አይረዳንም?
ስለ ቤተክርስትያኗ ስም ትኩረት በመስጠት ፕሬዝደንት ኔልሰን “ለኢየሱስ ክርስቶስ የሃጥያት ክፍያ ሃይል መዳረሻ እንዲኖረን እኛን እንዲያነጻን እና እንዲፈውሰን፣ እኛን እንዲያጠነክረን እና እንዲያጎላን እናም በመጨረሻም ከፍ እንዲያደርገን— እርሱ የዚያ ሀይል ምንጭ እንደሆነ በግልፅ ማስታወቅ ይገባናል።11 ፕረኢዘደንት ኔልሰን የቤተክርስትያኗን ትክክለኛ ስም ሁልጊዜ በመጠቀም ምንም እንኳን ትንሽ ነገር ቢመስልም ፈጽሞ ትንሽ ነገር እንዳልሆነ እና የዓለም ወደፊትን በትልቁ እንደሚቀርጽ አስተምሯል።
ለዝግጅታችሁ የተሰጠ የተስፋ ቃል
ፕሬዝዳንት ኔልሰን እንዳደረገው ራሳችሁን ካዘጋጃችሁ እናንተ የተለየን ትሆናላችሁ፣ ስለ አዳኙ የበለጠ ታስባላችሁ፣ ስለእርሱ የበለጠ በማዘወተርም ሳታመነቱ ትናገራላችሁ ብዬ ቃል እገባላችኋለሁ። በጥልቀት እያወቃችሁት እና እየወደዳችሁት ስትመጡ፣ ከልጆቻችሁ አንዱን ወይም ውድ ጓደኞቻችሁን እንደመነጋገር ቃላቶቻችሁ በምቾት ይፈሳሉ። እናንተን የሚያዳምጡትም እንደ ክርክር ወይም እንደ መባረር ሳይሆን እንደ እናንተ የመማር ስሜት ይሰማቸዋል።
እናንተ እና እኔ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እናወራለን ነገር ግን ምናልባት የተሻለ ማድረግ እንችላለን። አለም ስለሱ ያነሰ የሚያወራ ከሆነ ማነው ስለእርሱ በይበልጥ የሚያወራው? እኛ ነን! ከሌሎች ታማኝ ክርስትያኖች ጋር!
ስለክርስቶስ በቤታችን ውስጥ መናገር
የአዳኙ ምስሎች በቤታችን ውስጥ አሉ? ስለ ኢየሱስ ምሳሌዎች አዘውትረን ለልጆቻችን እናወራለን? “የኢየሱስ ታሪኮች በልጆች ልብ እምነት ፍም ውስጥ እንደሚፈጥን ንፋስ ነው።”12 ልጆቻችሁ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ በንቃት አዳኙ ያስተማረውን ለማስተማር አስቡ። ለምሳሌ ልጃችሁ “አባዬ ለምንድነው የምንጸልየው?” ብሎ ከጠየቀ፣ እንዲህ ብላችሁ ልትመልሱ ትችላላችሁ “ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ኢየሱስ የፀለየበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? እስቲ ለምን እና እንዴት እንደጸለየ እናውራ።”
“ስለ ክርስቶስ እንናገራለን፣ በክርስቶስ እንደሰታለን፣ … ልጆቻችን ለሀጢያታቸው ስርየት የትኛውን መንገድ መመልከት እንዳለባቸው ያውቁ ዘንድ።”13
ስለክርስቶስ በቤተክርስቲያን ውስጥ መናገር
ይህ ተመሳሳይ ጥቅስ “ስለ ክርስቶስ እንሰብካለን” ብሎ ያክላል።14 በአምልኮ አገልግሎታችን ላይ በአዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ እና በቤዛነት መስዋዕቱ ስጦታ ላይ እናተኩር። ይህ ከራሳችን ህይወት ልምድ መናገር ወይም የሌሎችን ሃሳቦች ማካፈል አንችልም ማለት አይደለም። ርዕሳችን ስለ ቤተሰብ ወይም አገልግሎት ወይም ስለ ቤተመቅደስ ወይም ስለ ቅርብ ጊዜ ምስዮን አገልግሎት ቢሆንም በአምልኳችን ሁሉም ነገር ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማመልከት አለበት።
ከሰላሳ አመት በፊት ፕሬዝዳንት ዳለን ኤች. ኦክስ “ቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ተካፈልኩ ካለው እና አዳኙ ሳይጠራ አስራ ሰባት ምስክርነቶችን ከሰማ ሰው” ስለደረሰው ደብዳቤ ተናግሮ ነበር።15 ፕሬዝዳንት ኦክስ “ምናልባት ይህ የተጋነነ አገላለጽ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ይህን የጠቀስኩት ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ማስታወሻን ስለሚሰጥ ነው።”16 ከዚያም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ በንግግራችን እና በክፍል ውይይታችን ውስጥ እንድንናገር ጋበዘን። በቤተክርስትያን ስብሰባዎቻችን ላይ የበለጠ በክርስቶስ ላይ እያተኮርን መሆኑን ተመልክቻለሁ። በእነዚህ አወንታዊ ጥረቶች ንቁ እንሁን።
ስለክርስቶስ ከሌሎች ጋር መነጋገር
በዙርያችን ካሉት ጋር ስለ ክርስቶስ ለመናገር ግልጽ እና ፈቃደኞች እንሁን። ፕሬዝዳንት ኔልሰን “እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ጎልተው ለመታየት፣ በድፍረት ለመናገር፣ እና ከአለም ህዝቦች ለመለየት ፈቃደኞች ናቸው።”17
አንዳንድ ጊዜ ከሆነ ሰው ጋር ያለን ንግግር እነሱን ወደ ቤተክርስትያን ማምጣት ወይም ምስዮናውያንን የማግኘት ውጤት ማምጣት አለበት ብለን እናስባለን። እኛ አብልጠን ለእርሱ ድምጽ የመሆን ሃላፊነትን ስናስብ፣ ስለ እምነታችን ግልጽ እና ጠንቃቆች ስንሆን እንደፈቃደኝነታቸው ጌታ እንዲመራቸው እንተው። ሽማግሌ ዲተር ኤፍ. ኡክዶርፍ አንድ ሰው ስለ ሳምንት መጨረሻችን ሲጠይቀን በደስታ የህጻናት ክፍልን “እንደ ኢየሱስ ለመሆን እየጣርኩ ነው” የሚለውን መዝሙር መስማት እንደምንወድ ለመንገር ፈቃደኞች መሆን መቻል አለብን ብለው አስተምረዋል።18 በቅንነት በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት እንመስክር። አንድ ሰው በግል በህይወቱ ወይም በህይወቷ ስላለ ችግር ካካፈለ/ካካፈለች እንዲህ ማለት እንችላለን “ጆን፣ ሜሪ ታውቃላችሁ እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ። ጌታ ስለተናገረው እናንተን ሊረዳችሁ ስለሚችል ስለሆነ ነገር ሳስብ ነበር።”
በማህበራዊ ገጾች ላይ በክርስቶስ ስላላችሁ እምነት ይበልጥ በግልጽ ተናገሩ። አብዛኛዎች እምነታችሁን ያከብራሉ ነገር ግን ስለ አዳኙ ስታወሩ የሆነ ሰው ከተቃወማችሁ ድፍረትን ከቃልኪዳኑ ውሰዱ፤ “በእኔ ምክንያት ሲነቅፉአችሁ… ብፁዓን ናችሁ። … ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና።“19 እኛ በተከታዮቻችን ከመወደድ ይልቅ የእርሱ ተከራዮች መሆን የበለጠ ያሳስበናል። ጳውሎስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ” ብሏል።20 እስቲ ስለ ክርስቶስ እንናገር።
መፅሐፈ ሞርሞን የኢየሱስ ክርስቶስ ሀይለኛ ምስክር ነው። እያንዳንዱ ገጽ ስለ አዳኙ እና ስለ መለኮታዊ ተልዕኮው ይመሰክራል።21 የሃጥያት ክፍያው እና የጸጋው መረዳት ገጾቹን ሞልቷል። ከአዲስ ኪዳን ጋር አብሮ በመሆን መጽሃፈ ሞርሞን አዳኙ እኛን ለማዳን ለምን እንደመጣ እና ወደሱ እንዴት በጥልቀት መምጣት እንደምንችል ይበልጥ እንድንረዳ ያደርገናል።
አንዳንድ የክርስትያን ጓደኞቻችን አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነታችን እና ተነሳሽነታችን እርግጠኞች አይደሉም። በምንካፈለው የኢየሱስ ክርስቶስ እምነታችን እና ሁላችንም በምንወደም የአዲስ ኪዳን መጽሃፍ በቀናነት ከእነርሱ ጋር ሃሴት እናድርግ። ከፊታችንም በሚመጡት ቀናት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ጓደኝነት እና የእርስ በርስ መደጋገፍ ያስፈልጋቸዋል።22
አለም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አሳንሶ ሲያወራ እኛ አብልጠን እናውራ። እንደሱ ደቀመዝሙሮች እውነተኛ ቀለማችን ሲገለጥ በዙሪያችን ያሉ ብዙዎች ለመስማት የተዘጋጁ ይሆናሉ። ከርሱ የተቀበልነውን ብርሃን ስናካፍል የእርሱ ብርሃን እና የሚያቀናው የማዳን ሃይሉ ልባቸውን ለመክፈት ፈቃደኞች በሆኑት ላይ ያበራል። ኢየሱስ እንዳለው፣ “እኔ … እንደ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።”23
ስለክርስቶስ ለመናገር ያለንን ፍላጎት ከፍ ማድረግ
የእርሱን መመለስ በአይነ ህሊናዬ እንደማየት ስለ ክርስቶስ እንዳወራ ፍላጎቴን የሚያነሳ ነገር የለም። አዳኙ መቼ እንደሚመለስ ባናውቅም የመመለሱ ሁኔታዎች አስደናቂ ይሆናሉ። በሰማይ ደመና በግርማ እና ሞገስ ከቅዱሳን መላዕክቱ ጋር ይመጣል። ጥቂት መላዕክት ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ቅዱሳን መላዕክት። እነዚህ በራፋኤል ስለተሳሉት በቫለንታይን ካርዳችን ላይ ቀይ ጉንጭ ስላላቸው ኪሩቤል አይደለም። እነዚህ የክፍለ ዘመናት መላዕክት ናቸው፤ የአናብስትን አፎች እንዲዘጉ የተላኩ፣24 የወኅኒ በሮችን እንዲከፍቱ25 ለረጅም ጊዜ የተጠበቀውን ልደቱን ኢንዲያበስሩ26 በጌተሴማኒ እንዲያጽናኑት27 ስለ እርገቱ ለደቀመዛሙርቱ ሊያረጋግጡ፣28 እና ታላቅ የሆነውን የወንጌል ዳግም መመለስ ለመክፈት የተላኩ ናቸው።29
በዚህኛውም ሆነ በሌላኛው የመጋረጃ አቅጣጫ እርሱን ለማግኘት እንደምንነጠቅ ማሰብ ትችላላችሁን?30 ያ ለፃድቆች የገባው ቃል ኪዳኑ ነው። ይህ አስደናቂ ድርጊት ነፍሳችንን ለዘላለም ምልክት ያደርጋል።
አዳኙን እንድንወድ እና መለኮታዊነቱን እንድናውጅ ልባችንን ከፍ ስላደረገ ለተወደደው ነብያችን ፕሬዝዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን አመስጋኞች ነን። የጌታ እጅ በሱ ላይ ስለመሆኑ እና ስለሚመራው የመገለጥ ስጦታ የአይን እማኝ ነኝ። ፕሬዝዳንት ኔልሰን ያንተን ምክሮች በጉጉት እንጠብቃለን።
በዓለም ዙሪያ ያላችሁ ውድ ጓደኞቼ፣ “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” የሚለውን የእርሱን ታላቅ የተስፋ ቃል በመገመት ስለክርስቶስ እንናገር።31 እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።