ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ
ለሁሉም ሰዎች በዓለም ዙሪያ ላሉት ለእያንዳንዱ ሀገር እንዲጸልዩ ዛሬ ጥሪዬን በስፋት አቀርባለው።
ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ የመጨረሻ ሳምንቱ ወቅት ደቀመዛሙርቱን እንዲህ አስተማረ፣ “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ። ”1
ከዳግም ምፅዓቱ በፊት “የሚከሰቱ ነገሮች” እንደ “ጦር፣ የጦርም ወሬ፣ ራብና ቸነፈር እንዱሆም የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ” ናቸው።2
በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ ኣዳኙ እንዲህ አለ፣ “እና ሁሉም ነገሮች በሁከት ውስጥ ይሆናሉ፣ … ፍርሃት በሁሉም ሰዎች ላይ ይመጣልና።”3
በትክክል፣ ነገሮች በሁከት ውስጥ ተሞልተው ባለ ጊዜ ውስጥ ነው እየኖርን ያለነው። ብዙ ሰዎች ወደፊትን ይፈራሉ፣ እናም ብዙ ልቦች በእግዚአብሔርና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት አዙረዋል።
የዜና ዘገባዎች በብዙ ዓመፆች ተሞልተዋል። ስነ-ምጋባራዊ ንቀት ድህረ ገፅ ላይ እየታተመ ነው። መቃብር ስፍራዎች፣ ቤተክርስቲያኖች፣ መስጊዶች፣ ምኩራቦች፣ እና ሐይማኖታዊ መቅደሶች ተበላሽተዋል።
ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ በምድር ዳርቻ ሁሉ ደርሷል—በሚሊዮኖች የሚጠጉ ሰዎች ተይዘዋል፣ ከሚልዮን የሆኑ ሰዎችም ሞተዋል። የትምህርት ቤት ምርቃቶች፣ የቤተክርስቲያን አምልኮዎች፣ ጋብቻዎች፣ የሚስዮን አገልግሎቶች፣ እና ሌሎች ጠቃሚ የሕይወት ክስተቶች ተረብሸዋል። በተጨማሪም፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ለብቻቸው ቀርተዋል እንዲሁም ተገለዋል።
የኢኮኖሚ ሁከቶች ለብዙ ሰዎች ችግሮችን ፈጥረዋል በተለይም ለተጋለጡ የሰማይ አባታችን ልጆች።
ሰዎች በጋለ ስሜት በሰላም ተቃውሞ ለማሰማት መብታቸውን ሲጠቀሙ አይተናል እንዲሁም የተናደዱ መንጎች ሲያምፁ አይተናል።
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በዓለም ዙሪያ ግጭቶችን ማየታችንን ቀጥለናል።
በስቃይ፣ በጭንቀት፣ በፍርሃት ወይም በብቸኝነት ሁኔታ ላይ ያላችሁትን ሰዎች ብዙ ጊዜ አስባለው። ጌታ እንደሚያውቃችሁ፣ ችግራችሁንና ጭንቀታችሁን እንደሚያውቅ እና ግላዊ፣ ጥልቅ በሆነ ሁኔታ እና ለዘላለም እንደሚወዳችሁ ለእያንዳንዳችሁ አረጋግጥላችኋለው።
በየምሽቱ በምጸልይበት ወቅት፣ በሃዘን፣ በህመም፣ በብቸኝነት እና በስቃይ ላይ ያሉትን እንዲባርክ ጌታን እጠይቃለው። የቤተክርስቲያን መሪዎች ያንን ተመሳሳይ ጸሎት እንደሚያጸልዩ አውቃለው። ልባችን በግለሰብና በጋራ ለእናንተ ይደርሳል እንዲሁም ጸሎታችን እናንተን አስመልክቶ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል።
ባለፈው ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ምስራቃዊ ክፍል ውስጥ አሜሪካንና የቤተክርስቲያን ቦታዎችን እንዲሁም የመንግስትና የንግድ መሪዎችን በመጎብኘት ብዙ ቀናቶችን አሳልፊያለው።
በጥቅምት 20 በእሁድ ቀን በቦስተን ማሳቹሴት አቅራቢያ ለሞገኙ በብዛት ለተሰበሰቡ ሰዎች ንግግር አደረኩኝ። በምናገርበት ሰዓት፣ ይህንን ለመናገር ተነሳስቼ ነበር፣ “ለዚህ ሀገር፣ ለመሪዎቻችን፣ ለህዝባችን እና በዚህ እግዚአብሔር በመሰረተው ሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ቤተሰቦች እንድትጸልዩ እማጸናችኋው።”4
እንዲሁም አሜሪካና የምድር ብዙ ሀገራት ልክ እንደዚ ቀደሙ በወሳኝ መንታ መንገዶች ላይ እንዳሉ እና ጸሎታችንን እንደሚሹ ተናገርኩ።5
ልመናዬ በተዘጋጀሁበት አስተያየት ላይ የሰፈረ አልነበረም። እነዛ ቃላት በዛ ያሉትን ሰዎች ለሀገራቸውና ለመሪዎቻቸው እንዲጸልዩ ለመጋበዝ የመንፈስ ግፊት ሲሰማኝ ወደ እኔ መጡ።
ለሁሉም ሰዎች በዓለም ዙሪያ ላሉት ለእያንዳንዱ ሀገር እንዲጸልዩ ዛሬ ጥሪዬን በስፋት አቀርባለው። እንዴትም ትጸልዩ ለማንም ትጸልዩ እባካችሁ እምነታችሁን ተለማመዱ—እምነታችሁ ምንም ይሁን ምን—እና ለሀገራችሁና ለሀገር መሪዎቻችሁ ጸልዩ። ባለፈው ጥቅምት በማሳቹሴት እንደተናገርኩት፣ ዛሬ በታሪክ ታላቅ መንታ መንገዶች ላይ ቆመናል እና የምድር ሀገራት ለመለኮታዊ መነሳሳትና ምሪት በጉጉት ፍላጎት ላይ ናቸው። ይህ ስለ ፖለቲካ ወይም ስለ ፖሊሲ አይደለም። ይህ በሰላም ልዑል እና የሁሉም ፈውስ ምንጭ በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማክኝት ስለሚመጣው ሰላም እንዲሁም ለእያንዳንዱ ነፍሳት እና ሀገሮች ነፍስ—ለከተሞቻቸው እና መንደራቸው—ፈውስ ነው።
ባለፉት ወራት ውስጥ በአሁን ሰዓት ያለውን የዓለም ሁኔታ ለመርዳት ጥሩው መንገድ ሁሉም ሰዎች በበለጠ ሁኔታ በእግዚአብሔር ላይ እንዲመረኮዙ እና ከልብ በመነጨ ጸሎት ልባቸውን ወደ እርሱ እንዲያዞሩ እንደሆነ መነሳሳት ወደ እኔ መጥቶ ነበር። ከፊታቸን ያለውን ነገር በጽናት ለመወጣት ወይም ለማሸነፍ፣ እራሳችንን ትሁት ማድረግ እና የሰማይን አነሳሽነት መሻት በዚህ ጊዜ ውስጥ በመተማመን ወደፊት ለመጓዝ ደህናውና እርግጠኛው መንገዳችን ይሆናል።
ቅዱሳን መጻህፍት በኢየሱስ የተደረገውን ጸሎቶች እና በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ስለጸሎት ያስተማረው ላይ ያሰምራሉ። የጌታን ጸሎት ታስታውሳላችሁ።
“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ።
“መንግሥትህ ትምጣ። ፍቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን።
“እንጀራችንን ስጠን ዛሬ።
እናም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን።
“ወደ ፈተናም አታግባን፣ ከክፉ አድነን እንጂ፤ መንግሥት ያንተ ናትና፣ እና ሀይልም፣ ክብርም ለዘላለሙ አሜን።”6
ይህ ደስ የሚለው በክርስትና ብዙ ጊዜ የተደጋገመው ጸሎት “በሰማይ ለሚኖረው አባታችን” ለሚያስቸግረን ነገር ምላሽ ለማግኘት በቀጥታ ጸሎት ማድረስ ተገቢ እንደሆነ ግልፅ ያደርጋል። ስለዚህ፣ ለመለኮታዊ ምሪት እንጸልይ።
ሁሌም እንድትጸልዩ እጋብዛችኋለው።7 ለቤተሰባችሁ ጸልዩ። ለሀገራት መሪዎች ጸልዩ። በዓለም ዙሪያ ሀብታም፣ ድሃ፣ ወጣት እና አዛውንትን ሳይለይ ሁሉንም ህዝብ በማጥቃት ላይ ባለው ከማህበራዊ፣ አካባቢያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባዮሎጂያዊ መቅሰፍት ጋር ባለው ፍልሚያ ላይ በግንባር ላይ ላሉት ደፋር ሰዎች ጸልዩ።
አዳኙ የምንጸልይላቸው ሰዎች እንዳንገድብ አስተማረን። “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁንም ባርኩ፤ ለሚጠሏችሁም መልካምን አድርጉ፣ እናም በከንቱ የሚነቅፉአችሁን እናም የሚያሳድዱአችሁን ውደዱ ብሏል።”8
በቀራንዮ መስቀል ላይ ለእኛ ሃጢያት ተሰቅሎ ሳለ ያስተማረውን ነገር እንዲህ ብሎ በመጸለይ ጠበቀ፣ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምን ይቅር በላቸው።”9
ጠላቶቻችን ተብለው ለሚፈረጁ ሰዎች ከልብ የሆነ ጸሎትን ማቅረብ እግዚአብሔር የእኛንና የሌሎችን ልቦች እንደሚቀይር ያለንን እምነት ያሳይል። እንደዚህ ዓይነት ጸሎቶች በሕይወታችን፣ በቤተሰባችን እና በማህበረሰባችን ውስጥ የሚያስፈልገውን ለውጦች ለማድረግ የእኛን ውሳኔ ማጠንከር አለባቸው።
የትም ኑሩ የት፣ ምንም ዓይነት ቋንቋ ተናገሩ ወይም ምንም ዓይነት ችግሮች ይግጠማችሁ፣ እግዚአብሔር በራሱ መንገድና ጊዜ ጸሎጻችሁን ይሰማል እንዲሁም ይመላሳል። የእርሱ ልጆች ስለመሆናችን በዓለም ላይ አወንታዊ የሆነ ልዩነትን ለማምጣት እርዳታን፣ መጽናናትን እና የታደሰን ምኞትን ለመሻት ልንቀርበው እንችላለን።
ለፍትህ፣ ለሰላም፣ ለድሆችና ለታመሙ መጸለይ ብዙውን ጊዜ በቂ አይደለም። ለጸሎት ከተንበረከክን በኋላ ከጉልበታችን ተነስተን እራሳችንን እና ሌሎችን የምንችለውን ያህል ለመርዳት መስራት አለብን።10
መጽሐፍ ቅዱሳት በራሳቸው እና በሌሎች ሕይወት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት በአማኝ ሰዎች ጸሎትና ተግባር ምሳሌዎች የተሞሉ ናቸው። ለምሳሌ፣ በመጽሐፈ ሞርሞን ውስጥ ስለኢኖስ እናነባለን። “የአጭር መጽሐፉ ሁለት ሶስተኛው ክፍል ስለ ጸሎት ወይም ስለተከታታይ ጸሎቶች እንደሚገልፅ እና ሚዛን ያለው ክፍል ደግሞ የተቀበለው ምላሾች ላይ ተንተርሶ ምን እንዳደረገ እንደሚገልፅ” ተመልክተናል።11
ጆሴፍ ስሚዝ ከወላጆቹ ቤት አቅራቢያ በፀደይ 1820 (እ.አ.አ) በጫካ ሜዳ ውስጥ ካቀረበው የመጀመሪያው የድምፅ ጸሎት አንስቶ በገዛ የቤተክርስቲያን ታሪካችን ውስጥ ጸሎት እንዴት ለውጥ እንዳመጣ ብዙ ምሳሌዎች አሉን። ይቅርታንና መንፈሳዊ አቅጣጫን በመሻት የጆሴፍ ጸሎት ሰማያትን ከፈተ። ዛሬ የነብዩ ጆሴፍ እና የሌሎች አማኝ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ወንዶችና ሴቶች የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንዲመሰረት ለመርዳት ባበረከቱት ጸሎትና ተግባር ተጠቃሚዎች ነን።
በእግዚአብሔር እርዳታ በድፍረት ቤተሰቧን በስደት ከኢለኖይ ውስጥ ወደ የመንፈሳዊና ምድራዊ ብልፅግና እንዲሻገሩ ወደ አዚህ ሸለቆ ውስጥ በደህንነት ስለመራችው እንደ ሜሪ ፊልዲንግ ስሚዝ ስላሉ አማኝ ሴቶች ብዙውን ጊዜ አስባለው። በጉልበቷ ተንበርክካ ከልቧ ከጸለየች በኋላ ችግሮቿን ለማሸነፍ ጠንክራ ሰራችና ቤተሰቧን ባረከች።
ጸሎት ከፍ ያደርገናል እንዲሁም እንደ ግለሰቦች፣ እንደ ቤተሰቦች፣ እንደ ቤተክርስቲያን እና እንደ ዓለም እንድንቀራረብ ያደርገናል። ጸሎት ሳይንቲስቶች ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል እንዲሁም ይህንን ወረርሽኝ የሚያቆም ክትባቶችንና መድሐኒቶችን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ጸሎት የሚወዱትን ሰው ያጡ ሰዎችን ያፅናናል። ስለግል ደህንነታችን ምን ማድረግ እንዳለብን እንድናውቅ ይመራናል።
ወንድሞችና እህቶች፣ ለጸሎት ያላችሁን ቁርጠኝነት እጥፍ ድርብ እንድታደርጉ አበረታታችኋለው። በድብቅ ቦታችሁ፣ በየቀኑ እርምጃችሁ፣ በቤታችሁ፣ በዋርዳችሁ፣ እና ሁሌም በልባችሁ እንድትጸልዩ አበረታታችኋለው።12
በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን መሪዎች ስም ለእኛ ስለምታደርጉት ጸሎቶች አመሰግናችኋለው። ቤተክርስቲያኗን በዚህ ከባድ ጊዜያት ውስጥ ለመምራት መነሳሳትን እና ራዕይን እንቀበል ዘንድ መጸለያችሁን እንድትቀጥሉ አበረታታችኋለው።
ጸሎት የገዛ ሕይወቶቻችንን መለወጥ ይችላል። ከልብ በመነጨ ጸሎት በመበረታታት፣ መለወጥ እንችላለን ሌሎችንም እንዲለወጡ መርዳት እንችላለን።
ስለጸሎት ኃይል በገዛ ልምዴ አማካኝነት አውቃለው። ቅርብ ጊዜ በቢሮዬ ውስጥ ለብቻዬ ነበርኩኝ። እጄን ታክሜ ነበር። ጠቁሮና ሰማያዊ ሆኖ፣ አብጦ እንዲሁም የሚያም ሆኖ ነበር። በዴስኬ ላይ ተቀምጬ ሳለው በዚህ ህመም ተረብሼ ስለነበረ በጠቃሚና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አልቻልኩም ነበር።
ስራዬን ማከናውን እችል ዘንድ ጌታን ማተኮር እንድችል እንዲረዳኝ በጸሎት ተንበረከኩኝና ጠየቅኩኝ። ቆምኩኝና ዴስኬ ላይ ወደተከመሩት ወረቀቶች ተመለስኩኝ። በፍጥነት ወደ አዕምሮዬ ግልፅነትና ትኩረት መጣና ከፊቴ ያሉትን አስቸኳይ ነገሮች መጨረስ ቻልኩኝ።
ብዛት ያላቸውን ጉዳዮችና ችግሮች ስናስብ የዓለም ወቅታዊ ትርምስ አስፈሪ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ከጸለይንና የሰማይ አባትን ለአስፈላጊ በረከቶችና ምሪት ከጠየቅን፣ ቤተሰባችንን፣ ጎረቤቶቻችንን፣ ማህበረሰባችንን እንዲሁም የምንኖርበትን ሀገር ጨምሮ እንዴት መርዳት እንደምንችል ማወቅ እንደምንችል ከልብ የመነጨ ምስክርነቴ ነው።
እየቀረበ አዳኙ ጸለየና፣ ከዛም ድሃዎችን እየመገብ፣ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ብርታትንና እርዳታን እየሰጠ፣ እና ወደ እርሱ ለሚመጡት ሁሉ በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በሰላምና በእረፍት እየቀረበ “መልካም ነገርን ማድረጉን ቀጠለ።”13 እርሱ ወደእኛ መቅረቡን ይቀጥላል።
ሁሉንም የቤተክርስቲያን አባሎች እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ጎረቤቶቻችንን እና ጓደኞቻችንን አዳኙ ደቀማዛሙርቱን እንደመከረ እንድታደርጉ፤ ለሰላም፣ ለመፅናናት፣ ለደህንነት እና እርስ በእርስ ለማገልገል እድል “ስትጸልዩ ሁል ጊዜ እንድትተጉ”14 እጋብዛለው።
የጸሎት ኃይል ምን ያህል ታላቅ ነው እንዲሁም በአሁኑ ዓለም ውስጥ በእግዚአብሔርና በውድ ልጁ የእምነት ጸሎቶች ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው። የጸሎትን ሀይል እናስታውስ እና ለዚህም ምስጋና ይኑረን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።