አጠቃላይ ጉባኤ
መጠየቅ መሻት ማንኳኳት
የጥቅምት 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:9

መጠየቅ፣ መሻት እና ማንኳኳት

ከሰማይ አባት እቅድ አንዱ አስፈላጊ ክፍል በፈለግነው ጊዜ ሁሉ ከእሱ ጋር መነጋገር የመቻል እድል ነው።

ከአራት ወራተ በፊት በቅዱሳን መጻሕፍት ጥናቴ ፣ አልማ በአሞኒሃ ሰለነበረው የሚስዮን አገልግሎት እያነበብኩ በነበርኩበት ጊዜ ነበር በ ኑ! ተከተሉኝ “እግዚአብሄር ለኔፊ ህዝቦች ስለሰጠው ታላቅ በረከቶች በምታነቡበት ጊዜ፤ ( አልማ 9፣19­23ይመልከቱ) ለእናንተ የሰጣችሁን ታላቅ በረከቶች አሰላሰሉ” የሚለውን ያገኘሁት።1 እግዚአብሔር ለእኔ የሰጠኝን በረከቶች ለመዘርዘር እና በዲጂታል የመመሪያ መጽሃፌ ውስጥ ለመመዝገብ ወሰንኩ ፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ 16 በረከቶችን ዘርዝሬ ነበር፡፡

ከነዚህ መካከል ከሁሉም በፊት የአዳኙ ምህረት እና ስለእኔ የተደረገው የኃጢያት ክፍያ ታላቆቹ በረከቶች ነበሩ። በፖርቱጋል ወጣት ሚስዮናዊ ሆኜ አዳኙን ስለወከልኩበት እና በኋላም በብራዚል ፖርቶ አሌግሬ ደቡብ ሚስዮን ከአፍቃሪ ዘላለማዊ አጋሬ ፓትሪሽያ ጋር ሆነን ከ522 ጠንካራ እና ድንቅ ሚስዮናውያን ጋር ስለሰጠነው አገልግሎት በረከትም ጻፍኩኝ። ስለ ፓትሪሽያ ስናገር፣ የዚያን ቀን የመዘገብኳቸው አብዛኛዎቹ በረከቶች— በሳኦ ፓውሎ ብራዚል ቤተ መቅደስ ውስጥ መታተማችንን ፣ ሦስቱን አስደናቂ ልጆቻችንን ፣ የትዳር ጓደኞቻቸውን እና 13 የልጅ ልጆቻችንን ጨምሮ በ40 አመታት የትዳር ዘመናችን አብረን የተቋደስናቸው በረከቶች ነበሩ።

ሀሳቦቼ በወንጌል መርሆች ወደ አሳደጉኝ ወደ ጻድቆቹ ወላጆቼም ዞረ ፡፡ በተለይ የ 10 አመት አካባቢ ልጅ ሳለሁ አፍቃሪ እናቴ በአልጋዬ አጠገብ ለመጸለይ ከእኔ ጋር የተንበረከከችበትን ቅጽበት አስታወስኩ ፡፡ ጸሎቶቼ ወደ ሰማይ አባቴ እንዲደርሱ መሻሻል እንደሚያስፈልጋቸው ተሰምቷት መሆን አለበት። ስለዚህ እንዲህ አለች “በመጀመሪያ እኔ እጸልያለሁ ፣ከዚያም እኔ ከጸለይኩኝ በኋላ አንተ ትጸልያለህ፡፡” ከሰማይ አባት ጋር እንዴት ማውራት እንደሚቻል በመርህ ደረጃ እና በተግባር እንደተማርኩ እርግጠኛ እስክትሆን ድረስ ለብዙ ምሽቶች ይህን ዘይቤ ቀጠለች። የሰማይ አባቴ ጸሎቶቼን እንደሚሰማ እና እንደሚመልሳቸው ስለተማርኩ መጸለይ ስላስተማረችኝ ለዘላለም አመሰግናታለሁ።

በእውነቱ ያ በዝርዝሬ ውስጥ ያካተትኩት ሌላ በረከት ነበር ፣ ይህም የጌታን ፈቃድ መስማት እና መማር የመቻል ስጦታ ነው። የሰማይ አባት እቅድ አንድ አስፈላጊ ክፍል በማንኛውም ጊዜ ከእሱ ጋር የመነጋገር እድል ነው።

ከጌታ የቀረበ ግብዣ

አዳኙ ከትንሳኤው በኋላ አሜሪካን ሲጎበኝ በገሊላ ለደቀመዛሙርቱ ያቀረበውን ግብዣ ደገመው፡፡ እንዲህም አለ፦

“ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።

“የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ እናም የሚፈልግም ያገኛል፤ እናም ለሚያንኳኩ ይከፈትላቸዋል“ (3 ኔፊ 14:7–8፤ በተጨማሪም ማቴወስ 7:7–8)።

ነቢያችን ፕሬዘዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በዘመናችን ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ስለ ጭንቀቶቻችሁ፣ ስለ ፍርሃቶቻችሁ፣ ስለ ድክመቶቻችሁ — አዎ፣ ስለልባችሁ ምኞቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጸልዩ። ከዚያም አዳምጡ! ወደ አእምሯችሁ የሚመጡትን ሀሳቦች ጻፉ፡፡ ስሜታችሁን መዝግቡ እና እንድትወሰዱ የተጠየቃችሁትን እርምጃዎች ተከተሉ። ይህን ሂደት ከቀን ወደ ቀን፣ ከወር ወደ ወር፣ ከዓመት ወደ ዓመት ስትደግሙት ‘ወደ ራዕይ መርህ ታድጋላችሁ።’ ”2

ፕሬዚዳንት ኔልሰን “በቀጣዮቹ ቀናት ያለመንፈስ ቅዱስ መሪነት፣ መመሪያ፣ ማጽናኛ እና የማያቋርጥ ተጽዕኖ በመንፈሳዊነት መቀጠል አይቻልም።” ሲሉ አክለዋል3

መገለጥ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ምክንያቱም ዓለም ግራ የሚያጋባ እና በጫጫታ፣ በማታለል እና በማዘናጋት የተሞላ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ ከሰማይ አባታችን ጋር መገናኘት የትኛው እውነተኛ እንዲሁም የትኛው ሐሰተኛ እንደሆነ፣ ጌታ ለእኛ ላቀደው እቅድ አግባብነት ያለውን እና የሌለውን ለመለየት ያስችለናል ፡፡ ዓለምም ጨካኝ እና ልብ ሰባሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ልባችንን በጸሎት ስንከፍት፣ ከሰማይ አባታችን የሚመጣው ማጽናኛ ይሰማናል እንዲሁም እሱ እንደሚወደን እና ዋጋ እንደሚሰጠን ማረጋገጫ እናገኛለን።

መጠየቅ

ጌታ “የሚለምን ሁሉ ይቀበላል” ብሏል። መጠየቅ ቀላል ይመስላል፣ ሆኖም ግን ፍላጎታችን እና እምነታችንን ስለሚገልፅ ኃይለኛ ነው። ሆኖም፣ የጌታን ድምፅ ለመረዳት መማር ጊዜን እና ትዕግስትን ይጠይቃል። ወደ አእምሯችን እና ወደ ልባችን ለሚመጡ ሀሳቦች እና ስሜቶች ትኩረት እንሰጣቸዋለን ከዚያም ነቢያችን እንድናደርግ እንደመከሩን እንጽፋቸዋለን፡፡ የእኛን ግንዛቤ መመዝገብ የመቀበል አስፈላጊ ክፍል ነው። ጌታ የሚያስተምረንን እንድናስታውስ፣ እንድንገመግም እና እንደገና እንዲሰማን ይረዳናል።

በቅርቡ አንድ ወዳጄ የሆነ ሰው እንዲህ አለኝ ፣ “የግል ራዕይ እውነት እንደሆነ አምናለሁ። ማድረግ ያለብኝን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ያሳየኛል ብዬ አምናለሁ።4 በማያጠራጥር ጠንካራ እምነት ደረቴ ሲቃጠል ሲሰማኝ ማመን ቀላል ነው።5 ሆኖም መንፈስ ቅዱስ ሁል ጊዜ በዚህ ደረጃ እንዴት ሊናገረኝ ይችላል? ”

ለወዳጄ እና ለሁላችሁም፣ እኔም እነዚያ ጠንካራ ስሜቶች ከመንፈሱ ያለማቋረጥ እንዲሰሙኝ እና መከተል ያለብኝን መንገድ ሁል ጊዜ በግልፅ ማየት እፈልጋለሁ እላለሁ። ግን እንደዚያ አይሆንልኝም። ሆኖም፣ ብዙ ጊዜ ሊሰማን የሚችለው በአእምሮአችን እና በልባችን ላይ የሚንሾካሾከው እንዲህ የሚለው ዝምተኛው የጌታ ድምፅ ነው፦ “እኔ እዚህ ነኝ። እወዳችኋለሁ። ቀጥሉ፣ ማድረግ የሚቻላችሁን አድርጉ። እደግፋችኋለሁ።” ሁል ጊዜ ሁሉንም ነገር ማወቅ ወይም ሁሉንም ነገር ማየት አያስፈልገንም።

አነስተኛ እና ለስላሳው ድምፅ እንደገና የሚያረጋግጥ፣ የሚያበረታታ እና የሚያጽናና ነው —እንዲሁም ብዙ ጊዜ ለቀኑ ብቻ የሚያስፈልገን ነው። መንፈስ ቅዱስ በእውነት ያለ ነው፣ እንዲሁም ትላልቆቹ እና ትናንሾቹ የእርሱ ግንዛቤዎች እውነተኛ ናቸው-።

መሻት

የጌታ ተስፋ ቀጠለ ፣ “የሚሻ ያገኛል።” መሻት አእምሯዊ እና መንፈሳዊ ጥረትን —ማሰላሰልን፣ መፈተሽን፣ መሞከርን እና ማጥናትን ያመለክታል። እኛ የምንሻው የጌታን ተስፋዎች ስለምናምን ነው። “ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና”(ዕብራውያን 11፥6)። ስንሻ፣ ገና ብዙ መማር ያለብን ነገር እንዳለ፣ እንዲሁም የበለጠ እንድንቀበል በማዘጋጀት ጌታ ግንዛቤያችንን እንደሚያሰፋልን በትህትና እውቅና እየሰጠን ነው። “እነሆም፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል—ለሰው ልጆች በትዕዛዝ ላይ ትዕዛዝ፣ በስርዐት ላይ ስርዐት፣ ጥቂት በዚህ፣ ጥቂት በዚያ እሰጣለሁ፤ ለሚቀበልም ተጨማሪ እሰጣለሁና”(2 ኔፊ፦ 28:30).

ማንኳኳት

በመጨረሻም ጌታ “ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል” አለ። ማንኳኳት በእምነት ማድረግ ማለት ነው፡፡ እሱን በንቃት ስንከተለው ጌታ መንገዱን ከፊታችን ይከፍታል። “እንድንነሳ እና ከላይ ያለውን [የኛን] መኖሪያ ከማለም የበለጠ አንድ ነገር እንድናደርግ የሚያስተምረን አንድ ደስ የሚል መዝሙር አለ፡፡ ጥሩ ማድረግ አስደሳች፣ መመዘን የማይቻል ደስታ፣ የግዴታ እና የፍቅር በረከት ነው።”6 የአስራ ሁለቱ ጉባኤ አባል የሆኑት ሽማግሌ ጌሪት ደብሊው. ጎንግ ራእይ ብዙውን ጊዜ የሚመጣው መልካም ነገርን በማድረግ ተግባር ላይ በምንሆንበት ጊዜ እንደሆነ በቅርቡ አብራርተዋል። እርሳቸው እንዲህ ብለዋል፦ “በአጠገባችን ላሉት ሰዎች በአገልግሎት ለመድረስ ስንሞክር ጌታ ለእነሱ እና ለእኛ ያለውን ተጨማሪ የፍቅር መጠን ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ። ሊመልሳቸው ከሚፈልጋቸው ጸሎቶች አንዱ በመሆኑ በዙሪያችን ያሉትን ለመርዳት ስንጸልይ ድምፁን የምንሰማ ይመስለኛል፣ በተለየ መንገድ ስለእርሱ ይሰማናል ፡፡”7

የአልማ ምሳሌ

ያ በ ኑ! ተከተሉኝ ውስጥ ያሰፈረው በረከቶቼን ስለማሰብ የተሰጠ ቀላል አስተያየት ጣፋጭ መንፈስን እና አንዳንድ ያልተጠበቁ መንፈሳዊ ግንዛቤዎችን አመጣ፡፡ ስለአልማ እና በአሞኒሃ ሰስለነበረወው አገልግሎቱ ማንበቤን ስቀጥል አልማ መጠየቅ፣ መፈለግ እና ማንኳኳት ምን ማለት እንደሆነ ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆን ተገነዘብኩ፡፡ “አልማ እግዚያብሄር በሰዎች ላይ መንፈሱን ያፈስ ዘንድ በሃያሉ ጸሎቱም ከእግዚያብሄር ጋር ታገለ” የሚል እናነባለን፡፡ ሆኖም ያ ጸሎት እርሱ ተስፋ ባደረገው መንገድ አልተመለሰም፣ እናም አልማ ከከተማው ተባረረ። አንድ መልአክ “አልማ አንተ የተባረክህ ነህ፣ ስለዚህ ራስህን አቅና እናም ሃሴትን አድርግ፣ የምትደሰትበት ትልቅ ምክንያት አለህና፡፡” የሚለውን መልእክት ሲያስተላልፍ አልማ “በሐዘን ተጨንቆ” ተስፋ ሊቆርጥ ነበር። ከዚያም መልአኩ ወደ አሞኒሃ እንዲመለስ እና እንደገና እንዲሞክር ነገረው፣ እናም አልማ “በፍጥነት ተመለሰ”8

ስለመጠየቅ፣ ስለመሻት እና ስለማንኳኳት ከአልማ ምን እንማራለን? ጸሎት መንፈሳዊ ትግልን እንደሚጠይቅ፣ እና ሁል ጊዜ ወደጠበቅነው ውጤት እንደማይመራን እንማራለን። ሆኖም ተስፋ ስንቆርጥ ወይም በሀዘን ስንጨነቅ ጌታ በተለያየ መንገድ መጽናናትን እና ብርታትን ይሰጠናል፡፡ ሁሉንም ጥያቄዎቻችንን ላይመልሳቸው ወይም ሁሉንም ችግሮቻችንን ወዲያውኑ ላይፈታቸው ይችላል፤ ይልቁንም መሞከራችንን እንድንቀጥል ያበረታታናል፡፡ እንግዲያው እቅዳችንን ከእቅዱ ጋር በፍጥነት የምናስማማ ከሆነ ለአልማ እንዳደረገው ለእኛም መንገዱን ይከፍትልናል።

ይህ የወንጌል ሙላት ዘመን እንደሆነ ምስክርነቴ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ በረከቶች በሕይወታችን ውስጥ መቋደስ እንችላለን። ቅዱሳት መጻህፍት ለእኛ በስፋት ይገኛሉ ፡፡ ለምንኖርበት አስቸጋሪ ጊዜ የሚሆነውን የጌታ ፈቃድ በሚያስተምሩን ነቢያት እንመራለን ፡፡ በተጨማሪም፣ ጌታ እኛን በግል ማጽናናት እና መምራት እንዲችል የራሳችንን መገለጥ በቀጥታ መቀበል እንችላለን፡፡ መልአኩ ለአልማ እንደተናገረው፣ “የምንደሰትበት ትልቅ ምክንያት አለን”።9 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።