አጠቃላይ ጉባኤ
በክርስቶስ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


16:12

በክርስቶስ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን

በመካከላችን ባለው መንፈሳዊ ዝምድና የበለጠ እንደሰት እንዲሁም ሁላችንም ላሉን ልዩ ልዩ ባህርያት እና የተለያዩ ስጦታዎች ዋጋ እንስጥ።

ውድ ጓደኞቼ፣ ዛሬ አስደናቂ የጉባኤ ክፍለ ጊዜዎችን አሳልፈናል። ሁላችንም የጌታ መንፈስ ተሰምቶናል እንዲሁም መሪዎቻችን ባካፈሉን ድንቅ መልዕክቶች አማካኝነት ፍቅሩ ተሰምቶናል። በዚህ ምሽት የዚህ ክፍለ ጊዜ የመጨረሻ ተናጋሪ በመሆን ንግግር የማቀርብላችሁ በመሆኔ ዕድለኛ ነኝ። በክርስቶስ እውነተኛ ወንድሞች እና እህቶች በመሆን በህብረት ስንደሰት የጌታ መንፈስ ከእኛ ጋር በመሆን እንዲቀጥል እጸልያለሁ።

ውዱ ነቢያችን ራስል ኤም. ኔልሰን እንዲህ ብለዋል፣ “በየትኛውም ቦታ ያሉ አባሎቻችን አመለካከቶችን እና የጭፍን ጥላቻ ድርጊቶችን ትተው በመውጣት እንዲመሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ። የሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆች ክብር እንድታሳድጉ እለምናችኋለሁ።”1 ዓለም አቀፋዊ እና ያለማቋረጥ እያደገች ያለች ቤተክርስቲያን እንደመሆኗ፣ ይህንን በነቢያችን የቀረበ ግብዣ መከተል በእያንዳንዱ የአለም ሀገራት የአዳኙን መንግስት ለመገንባት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሁላችንም ከልብ የሚወዱን የሰማያዊ ወላጆች መንፈሳዊ ወንድ እና ሴቶች ልጆች መሆናችንን 2 እና በዚህ ምድር ከመወለዳችን በፊት እንደ ቤተሰብ ከእግዚአብሔር ጋር እንኖር እንደነበር ያስተምራል። በተጨማሪም፣ ወንጌሉ ሁላችንም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ እንደተፈጠርን ያስተምራል።3 ስለዚህ፣ “በፊቱ እኩል ነን።”4 ምክንያቱም “የሰውን ወገኖች እና [ሴቶችን]ሁሉ ከአንድ [ስለ]ፈጠረ” 5 እናም፣ “ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ [በሁላችንም] የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት ስላለ”6 መለኮታዊ ውርስ እና አቅም አለን።

ልዩነቶች ቢኖሩብንም እንደ ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነታችን ልባችንን በእውነተኛ አንድነት እና ፍቅር በማጣበቅ በመንፈሳዊ ወንድማማችነታችን እና እህትማማችነታችን ላይ ያለንን እምነት እና ፍቅር እንድናሳድግ ተጋብዘናል። በዚህም፣ የሁሉንም የእግዚአብሔር ወንዶች እና ሴቶች ልጆችን ክብር ለመጠበቅ ያለንን አቅም እናሳድጋለን።7

የኔፊ ሕዝቦች ክርስቶስ ካገለገላቸው በኋላ ወደ ሁለት ለሚጠጉ ክፍለ ዘመናት ያህል ያጋጠማቸው ሁኔታ በትክክል ያ አይደለምን?

“እናም በእርግጥ በእግዚአብሔር እጅ ከተፈጠሩት ሰዎች መካከል እንደዚህ ያለ ደስተኛ ሊሆን የቻለ ህዝብ አልነበረም። …

ላማናውያንም ሆኑ ማንኛውም ዓይነት በመደብ የተለዩ ሰዎች አልነበሩም፤ ነገር ግን ሁሉም በአንድነት የክርስቶስ ልጆች፣ እናም የእግዚአብሔርንም መንግስት ወራሾች ነበሩ።

እናም እነርሱ እንዴት የተባረኩ ነበሩ!”8

ፕሬዘደንት ኔልሰን የሚከተለውን በገለፁ ጊዜ ለሰው ልጆች ክብርን በማዳረስ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል፦ “የሁላችንም ፈጣሪ እያንዳንዳችን በማናቸውም የእግዚአብሔር ልጆች ቡድን ላይ ያሉትን የጥላቻ አመለካከቶች እንድንተው ጋብዘውናል። በሌላ ዘር ላይ ጥላቻ ያለን እያንዳንዳችን ንስሀ መግባት ያስፈልገናል። … እያንዳንዳችን፣ የእግዚአብሔር ወንዶች እና ሴት ልጆች የሚገባቸውን ክብር ለመጠበቅ በእኛ ተፅዕኖ ሥር በሆኑ ነገሮች የምንችለውን ሁሉ የማድረግ ግዴታ አለብን።”9 በርግጥ ሰብአዊ ክብር እንዲኖር በመጀመሪያ ልዩነቶቻችንን ማክበር ይኖርብናል።10

እንደ እርሱ ልጅነታችን እኛን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣምረንን የተቀደሰ ትሥሥር ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህ በፕሬዘደንት ኔልሰን የተሰጠው ነቢያዊ መመሪያ ያለጥርጥር በመካከላችን የጥላቻ እና የመለያየት ግንቦችን ከመፍጠር ይልቅ የመግባቢያ ድልድዮችን ለመገንባት የሚያስችል መሰረታዊ እርምጃ ነው።11 ይሁን እንጂ ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎችን እንዳስጠነቀቀው ይህንን ዓላማ ለማሳካት በትሕትና ሁሉና፣ በየዋህነት በትዕግሥትም ለመኖር የግል እና የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ልናውቅ ይገባል።12

ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በጠዋቷ ፀሀይ እየተዝናና ስለነበረ አይሁዳዊ አስተማሪ የሚናገር አንድ ታሪክ አለ። “ሌሊቱ መገባደዱን እና አዲስ ቀን መጀመሩን እንዴት ታውቃላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

አንደኛው “ወደ ምስራቅ ስትመለከት እና በግን ከፍየል መለየት ስትችል” ሲል መለሰ።

ሌላኛው “አድማሱን በምትመለከትበት ጊዜ የወይራ ዛፍን ከበለስ ዛፍ መለየት ስትችል” ሲል መለሰ።

ከዚያም ወደ ጠቢቡ አስተማሪ ሄደው ይህንኑ ጥያቄ ጠየቁት። ለረዥም ጊዜ ካሰላሰለ በኋላ፣ “ወደ ምሥራቅ በምትመለከትበት ጊዜ የሴት ወይንም የወንድ ፊት ስታይ እና ‘እርሷ እህቴ ናት፤ እርሱ ወንድሜ ነው’ ማለት ስትችል” ሲል መለሰ።13

ውድ ጓደኞቼ፣ የሰው ልጆችን በአክብሮት እንዲሁም በክርስቶስ እውነተኛ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አድርገን ስንመለከታቸው እና ስንይዛቸው የአዲስ ቀን ብርሃን በሕይወታችን ውስጥ የበለጠ ደምቆ እንደሚበራ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ።

በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት፣ ኢየሱስ የመጡበትን፣ ማህበራዊ መደባቸውን እና ባህላዊ መገለጫቸውን ግምት ውስጥ ሳያስገባ በሁሉም የሰው ልጆች መካከል “መልካም እያደረገ፣”14 ወደ እርሱ እንዲመጡ እና ከቸርነቱ ይካፈሉ ዘንድ በመጋበዝ የዚህ መርህ ፍጹም ምሳሌ ነው። ሁሉንም አገለገለ፣ ፈወሰ እንዲሁም የሁሉንም ሰዎች ፍላጎት በተለይም በወቅቱ የተለዩ፣ የተናቁ ወይም የተገለሉ ሆነው ይቆጠሩ ለነበሩት ሁል ጊዜ ትኩረት ይሠጥ ነበር። እንደ ወንድሞቹ እና እህቶቹ፣ እንደ አንድ አባት ወንዶች እና ሴቶች ልጆች አድርጎ ያያቸው ስለነበር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እና በፍቅር ያዛቸው እንጂ ማንንም አልገፋም።15

እንደዚህ ከሆነባቸው በጣም አስደናቂ ከሆኑት አጋጣሚዎች አንዱ አዳኙ ወደ ገሊላ ሲሄድ ሆነ ብሎ በሰማርያ ውስጥ የሚያልፈውን መንገድ ይዞ በሄደበት ወቅት ነበር።16 ከዚያም ኢየሱስ ለማረፍ ከያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ለመቀመጥ ወሰነ። በዚያም ሳለ፣ አንዲት ሳምራዊት በእንስራዋ ውሃ ልትቀዳ መጣች። ሁሉን የሚያውቀው፣ ኢየሱስ “የምጠጣው ስጪኝ” ሲል ጠየቃት።17

ይህቺ ሴት አንድ አይሁዳዊ አንዲትን ሳምራዊት ሴት እርዳታ እንድትሰጠው በመጠየቁ በጣም ተገረመችና አግራሞቷን እንዲህ ስትል ገለፀለች፣ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና።18

ኢየሱስ ግን በሳምራውያን እና በአይሁዳውያን መካከል ያለውን የጥላቻ ልማድ ከቁብ ሳይቆጥር እርሱ በእውነት ማን እንደ ሆነ ይኸውም ሁሉንም ነገር የሚናገር እና መምጣቱን እየጠበቀችው የነበረው መሲሑ እንደነበር እንድትገነዘብ በመርዳት ይህችን ሴት በፍቅር አገለገላት።19 ያ የደግነት አገልግሎት ያስከተለው ትፅዕኖ ሴቲቱ “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” በማለት የሆነውን ነገር ለሰዎች ለመናገር ወደ ከተማዋ እንድትሮጥ አድርጓታል።20

ምክንያቱም፣ በሕይወት መንገዴ ላይ ጥሩ ሰዎች በተለያየ መንገድ በመናገራቸው፣ ተለይተው ስለሚታዩ ወይም አኗኗራቸው የተለየ በመሆኑ ምክንያት ስሜትና ሀሳብ በሌላቸው ሰዎች ለሚጎሳቆሉት፣ ለሚሠቃዩትን፣ ወይም ለሚሰደዱት ዝልቅ ርህርሄ ይሰማኛል፣ ይህን ሥቃይ እኔ በራሴ ላይ አይቼዋለሁና። ደግሞም አዕምሯቸው ለጨለመ፣ እይታቸው ውሱን ለሆነ እና ከእነሱ የተለዩ የሆኑት ዝቅተኛ እንደሆኑ በማመን ልባቸው ለደነደነ በልቤ ውስጥ እውነተኛ ሀዘን ይሰማኛል። በእርግጥ ስለሌሎች ያላቸው ውስን አመለካከት በእግዚአብሔር ልጆችነታቸው ማን እንደሆኑ የማየት ችሎታቸውን ይገድባል።

በነቢያቱ አስቀድሞ እንደተነገረው የምንኖረው ወደ አዳኙ ዳግም ምጽአት በሚመራን አስጨናቂ ቀናት ውስጥ ነው።21 በአጠቃላይ ዓለም በዘር፣ በፖለቲካ እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጥረት ያለባትና በተካረሩ ክፍፍሎች ፅንፍ የረገጠች ሆናለች። እንደእነዚህ ያሉ ክፍፍሎች አንዳንድ ጊዜ በሰዎች የአስተሳሰብ መንገድ እና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በዚህ ምክንያት በመረጃ ያልተደገፉ ድምዳሜዎች፣ የተሳሳቱ እና ብዙ ጊዜ የስላቅ ሃሳቦችን የሚጠቀሙ፣ ንቀት፣ ቸልተኝነት የሚያሳዩ፣ ክብር የሚነፍጉና እንዲያውም ለእነሱ ጭፍን ጥላቻ በማንፀባረቅ የሌሎችን ባህሎች፣ ዘር እና ብሄረሰቦች የአስተሳሰብ፣ የድርጊት እና የንግግር መንገድ ዝቅ አድርገው ሲመለከቱ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። እንደዚህ ያሉ አመለካከቶች ምንጫቸው ኩራት፣ ከእኔ በላይ ላሳር ማለት፣ ቅናት ፣ ምቀኝነት እና የሥጋዊ ተፈጥሮ ባሕርያት ሲሆን22 ከክርስቶስ መሰል ባሕርያት ጋር ፈጽሞ የሚቃረኑ ናቸው። ይህ ምግባር የእሱ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ለሚጥሩ ተገቢ አይደለም።23 በእርግጥ፣ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በቅዱሳን ማህበረሰብ ውስጥ ለጭፍን የጥላቻ አስተሳሰቦች ወይም ድርጊቶች ቦታ የለም።

እንደ ቃል ኪዳኑ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች በመካከላችን ያለውን በገሃድ የሚታይ ልዩነት አዳኙ በሚያይበት መንገድ በማየትና 24የጋራችን በሆነው—መለኮታዊ ማንነት እና ዝምድና ላይ በመመስረት እንደዚህ አይነት ባህርይን ለማስወገድ መርዳት እንችላለን። ከሁሉም በላይ በባልንጀራችን ህልሞች፣ ተስፋዎች፣ ሀዘኖች እና ሕመም ውስጥ የኛን ነፀብራቅ ለማየት ልንጥር እንችላለን። ሁላችንም ፍፅምና በሌለው ሁኔታችን እና ለማደግ ባለን ችሎታችን እኩል የሆንን እንደ እግዚአብሔር ልጆች አብረን የምንጓዝ ነን። በአንድነት፣ በሰላም፣ ልባችን ለእግዚአብሔር እና ለሰው ሁሉ በፍቅር ተሞልተን እንድንሄድ ተጋብዘናል—ወይም አብርሃም ሊንከን እንደተናገረው፣ “በማንም ላይ በክፋት እና ለሁሉም ምጽዋት” ኖሮን።25

በጌታ ቤት ውስጥ በምንለብሰው ልብስ ቀላል በሆነ መንገድ ሰብአዊ ክብርን እና እኩልነትን የማክበርን መርህ እንዴት በተግባር እንደሚታይ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ሁላችንም ወደ ቤተመቅደስ የምንመጣው ለአንድ አላማ አንድ ሆነን እንዲሁም በቅዱስ መገኘቱ ፊት ንፁህ እና ቅዱሳን ለመሆን ባለን ፍላጎት ተሞልተን ነው። ነጭ ልብስ በመልበስ፣ ሁላችንንም እንደ ተወዳጅ ልጆቹ፣ የእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች፣ የክርስቶስ ዘሮች አድርጎ ጌታ ራሱ ተቀብሎናል።26 ተመሳሳይ ሥርዓቶችን የመፈጸም፣ ተመሳሳይ ቃል ኪዳኖችን የመግባት፣ ከፍ ያለ እና የተቀደሰ ህይወት ለመኖር ራሳችንን የመስጠት እንዲሁም ተመሳሳይ ዘላለማዊ ተስፋዎችን የመቀበል እድል አለን። በዓላማ አንድ በመሆን በአዲስ እይታ እንተያያለን እንዲሁም በአንድነታችን እንደ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጆች ልዩነታችንን እናከብራለን።

በቅርቡ በብራዚሊያ ብራዚል ቤተመቅደስ በተደረገ ጉብኝት ታዋቂ ሰዎችን እና የመንግስት ባለስልጣናትን በማስጎብኘት ረድቻለሁ። ከብራዚል ምክትል ፕሬዘደንት ጋር በልብስ መቀየሪያው ቦታ ላይ ለአፍታ ቆም አልን እና ሁሉም ሰው በቤተመቅደስ ውስጥ ስለሚለብሰው ነጭ ልብስ ተነጋገርን። ይህ በተመሳሳይ ሁኔታ ነጭ ልብስ መልበሳችን እኛ ሁላችንም እግዚአብሔርን እንደምንመስል እና በቤተመቅደስ ውስጥ ያለን ማንነት እንደ አንድ ሀገር ምክትል ፕሬዘደንት ወይም እንደ ቤተክርስቲያን መሪ ሳይሆን ዘላለማዊ ማንነታችን የአፍቃሪ የሰማይ አባት ልጆች መሆናችንን እንደሚያሳይ አብራራሁለት።

ኢጓዙ ፏፏቴ

የኢጓዙ ወንዝ ደቡባዊ ብራዚልን ያቋርጣል ከዚያም በመላው ዓለም ኢጓዙ ፏፏቴ ተብሎ የሚጠራውን በምድር ላይ ካሉ እጅግ ውብ እና አስደናቂ ከሆኑት የአምላክ ፍጥረቶች አንዱ የሆነውን ከሰባቱ የዓለም አስደናቂ ነገሮች አንዱ ተደርጎ የሚወሰደውን የፏፏቴ ስርዓት ወደሚፈጥረው ፕላቷማ ቦታ ይፈሳል። እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ወደ አንድ ወንዝ ይገባል ከዚያም በመቶዎች የሚቆጠሩ አቻ የማይገኝላቸው ፏፏቴዎችን በመፍጠር ይለያያል። ከመለኮታዊ ውርስ እና ዝምድና በመገኘታችን አንድ ዓይነት መንፈሳዊ አመጣጥ እና እውነታን ስለምንጋራ በዘይቤአዊ አነጋገር፣ ይህ አስደናቂ የፏፏቴ ሥርዓት በምድር ላይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተሰብ ማሳያ ነው። ሆኖም፣ እያንዳንዳችን የተለያየ አመለካከት፣ ልምድ እና ስሜት በመያዝ በተለያዩ ባህሎች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ውስጥ እንፈሳለን። ይህም ቢሆንም፣ የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን እንዲሁም በክርስቶስ ወንድሞች እና እህቶች እንደመሆናችን፣ ልዩ ህዝብ እና ውድ ማህበረሰብ የሚያደርገንን መለኮታዊ ግንኙነታችንን ሳናቋርጥ ወደፊት እንጓዛለን።27

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ሁላችንም በእግዚአብሔር ፊት እኩል መሆናችንን፣ አንድ አይነት ዘላለማዊ አቅም እና ውርስ ሙሉ በሙሉ የተሰጠን መሆኑን በማወቅ እና በምስክርነት ልባችንን እና አእምሮአችንን በዚህ መሠረት እናስተካክል። በመካከላችን ባለው መንፈሳዊ ዝምድና የበለጠ እንደሰት እንዲሁም ሁላችንም ላሉን ልዩ ልዩ ባህርያት እና የተለያዩ ስጦታዎች ዋጋ እንስጥ። ይህን ካደረግን እንደ ክርስቶስ ልጆች እና የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንደ ተመረጠ ሕዝብ የሚለየንን መለኮታዊ ትስስር ሳናጠፋ እንደ ኢጓዙ ፏፏቴ ውኃ በራሳችን መንገድ እንደምንፈስ ቃል እገባላችኋለሁ። 28

በምድራዊ ህይወታችን በዚህ መንገድ መፍሰሱን ስንቀጥል፣ በአዲስ ብርሃን ህይወታችንን ብሩህ የሚያደርግ እና የበለጠ ዋጋ እንድንሰጥ ድንቅ እድሎችን የሚገልጥ አዲስ ቀን እንደሚጀምር እንዲሁም እግዚአብሔር በልጆቹ መካከል በፈጠረው ልዩነት በተሟላ ሁኔታ እንደምንባረክ እመሰክርላችኋለሁ። 29 በሁሉም ወንዶች እና ሴቶች ልጆቹ መካከል ያለውን ክብር ለማሳደግ በርግጠኝነት የእጆቹ መሳሪያዎች እንሆናለን። እግዚአብሔር ህያው ነው። ኢየሱስ የዓለም አዳኝ ነው። ፕሬዘደንት ኔልሰን በዘመናችን የእግዚአብሔር ነቢይ ናቸው። ስለእነዚህ እውነቶች የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።