አባካኙ እና ወደ ቤት የሚወስደው መንገድ
ምንም እንኳን ምርጫዎች ከአዳኙ እና ከቤተክርስቲያኑ አርቀው ቢወስዷችሁም፣ ዋነኛው ፈዋሽ ወደ ቤት በሚወስደው መንገድ ላይ ቆሞ ይቀበላችኋል።
አንድ ሰው ሁለት ወንድ ልጆች ነበሩት
አንዳንዶች እስከ ዛሬ ከተነገሩት ታላላቅ አጭር ታሪኮች መካከል ይቆጥሩታል።1 በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በሺዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ከተተርጎመ ጀምሮ፣ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ፣ ታሪኩ በዓለም ላይ አንድ ቦታ ሳይጠቀስ ፀሐይ አልጠለቀችም ማለት ይቻላል።
“የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን” ወደ ምድር በመጣው በመድኃኒታችንና በአዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተነግሯል።2 እንዲህ በማለት ይጀምራል፦ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።”3
ወዲያውኑ ስለ አንድ ልብ የሚሰብር ግጭት እንማራለን። አንድ ልጅ4 ለአባቱ በቤት ውስጥ ህይወት እንደበቃው ይነግረዋል። ነፃነቱን ይፈልጋል። የወላጆቹን ባህል እና ትምህርት ትቶ መሄድ ይፈልጋል። አሁኑኑ—ከርስቱ ድርሻውን ጠየቀ።5
አባትየው ይህን ሲሰማ ምን እንደተሰማው መገመት ትችላላችሁ? ልጁ ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው ቤተሰቡን ጥሎ መሄድ እና ምናልባትም ተመልሶ እንደማይመጣ ሲያውቅ?
ታላቁ ጀብድ
ልጁ የጀብዱ እና የደስታ ስሜት ሳይሰማው አልቀረም። በመጨረሻ ፣ እሱ ብቻውን ሆነ። ከወጣትነት ባህል መርሆዎች እና ደንቦች ነፃ በመሆን በወላጆቹ ተጽዕኖ ሳይደርስበት በስተመጨረሻ የራሱን ምርጫ ማድረግ ይችላል። ከዚህ በኋላ ጥፋተኝነት አይኖርም። ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያለው ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት አግኝቶ በራሱ ፍላጎት መኖር ይችላል።
ሩቅ አገር እንደደረሰ በፍጥነት አዳዲስ ጓደኞችን ማፍራት እና ሁልጊዜም ሲመኘው የነበረውን ሕይወት መኖር ጀመረ። ገንዘብን ያባክን ስለነበረ የብዙዎች ተወዳጅ መሆን አለበት። አዲሶቹ ጓደኞቹ—የብክነቱ ተጠቃሚ የሆኑት—አልፈረዱበትም። ምርጫውን አከበሩ፣ ተቀበሉ እንዲሁም ደገፉ ።6
በዚያን ጊዜ ማኅበራዊ ሚዲያ ቢኖር ኖሮ፣ በእርግጠኝነት፣ ገጾቹን በአስቂኝ ጓደኞቹ አኒሜሽን ፎቶዎች ይሞላ ነበር፦ #ምርጥ ሕይወቴን መኖር! #ከዚህ በላይ ደስተኛ አይኮንም! #ይሄን ከረጅም ጊዜ በፊት ማድረግ ነበረብኝ!
ረሃቡ
ነገር ግን ሆይታው በጭራሽ አልዘለቀም፣ መቼም አይዘልቅም። ሁለት ነገሮች ተከሰቱ፡ አንደኛ፡ ገንዘቡ አለቀበት፡ ሁለተኛ፡ ረሃብ በምድሪቱ ላይ ተከሰተ።7
ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ ደነገጠ። በአንድ ወቅት የሚያስቆመው የሌለው፣ በደስታ ብዙ ገንዘብ የሚያጠፋ የነበረው አሁን ማረፊያ ይቅርና አንዲት ምግብ መግዛት አልቻለም። እንዴት ሊተርፍ ይችላል?
ለጓደኞቹ ለጋስ ነበር— አሁን ይረዱት ይሆን? በእግሩ መቆም እስኪችል ድረስ ለትንሽ ድጋፍ ሲጠይቅ ይታየኛል።
ቅዱሳት መጻሕፍት ይህን ይነግሩናል፣ “ማንም አልሰጠውም።”8
በሕይወት ለመቀጠል ተስፋ ቆርጦ እሪያ እንዲመግብ የቀጠረውን የአካባቢውን ገበሬ አገኘ።9
ወጣቱ አሁን በጣም ተርቦ፣ በብቸኝነት ነገሮች እንዴት በአስከፊና፣ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ሊበላሹ እንደቻሉ ሳያስበው አልቀረም።
እሱን ያስጨነቀው ባዶ ሆድ ብቻ አልነበረም። ባዶ ነፍስ ነበር። ለዓለማዊ ምኞቱ መሰጠቱ ደስተኛ እንደሚያደርገው፣ እና የሥነ ምግባር ሕጎች ለዚያ ደስታ እንቅፋት እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነበር። አሁን የተሻለ አወቀ። እናም ለዚያ እውቀት ምን የመሰለ ዋጋ ከፍላል!10
ሥጋዊ እና መንፈሳዊው ረሃቡ እያደገ ሲመጣ ሀሳቡ ወደ አባቱ ተመለሰ። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ እርሱን ይረዳው ይሆን? ከአባቱ አገልጋዮች መካከል በጣም አነስተኛ የነበሩት እንኳ የሚበሉት ምግብ እና ከአውሎ ነፋስ መጠለያ ነበራቸው።
ነገር ግን ወደ አባቱ ሊመለስ?
በፍጹም።
ርስቱን እንዳባከነ ለመንደሩ ሊናዘዝ?
የማይቻል ነው።
ቤተሰቡን እንደሚያሳፍር እና የወላጆቹን ልብ እንደሚሰብር በእርግጠኝነት ያስጠነቀቁትን ጎረቤቶች ፊት ለፊት ሊጋፈጥ? እንዴት ነፃ እንደወጣ ከፎከረ በኋላ ወደ ቀድሞ ጓደኞቹ ሊመለሰ?
ሊቋቋሙት የማይቻል ነው።
ነገር ግን ረሃቡ፣ ብቸኝነቱ እና ጸጸቱ በቀላሉ አይጠፋም—”ወደ ልቡም [እስኪመለስ] ድረስ።11
ምን ማድረግ እንዳለበት አወቀ።.
መመለስ
አሁን ልቡ የተሰበረ የቤት አለቃ ወደነበረው ወደ አባቱ እንመለስ። ስንት በመቶዎች ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰአታትን ለልጁ ሲጨነቅ አሳልፏል?
ስንት ጊዜ ልጁ የተጓዘበትን መንገድ ተመልክቶ ልጁ ሲሄድ የተሰማውን ጥልቅ የማጣት ስሜት ደጋግሞ ተሰምቶታል? ልጁ እንዲድን፣ እውነትን እንዲያገኝ፣ እንዲመለስ እግዚአብሔርን በመማጸን በጥልቁ ሌሊት ስንት ጸሎቶችን አቀረበ?
እናም አንድ ቀን አባትየው ያንን ብቸኛ መንገድ ተመለከተ—ወደ ቤት የሚወስደው መንገድ ተመለከተ—እናም አንድ ሰው ከሩቅ ወደ እሱ ሲመጣ አየ።
ሊሆን የሚችል ነው?
ግለሰቡ በጣም ሩቅ ቢሆንም፣ አባትየው ልጁ መሆኑን በቅጽበት አወቀ።
ወደ እሱ ሮጦ በእጁ አቅፎ ሳመው።12
ልጁም አንድ ሺህ ጊዜ ተለማምዶበት ይሆን በሚመስል ቃላት፣ “አባቴ ሆይ፣ እኔ በሰማይና በፊትህ በደልሁ። ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም። ከሙያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ”13
አባቱ ግን እንዲጨርሰው አልፈቀደለትም። አይኑ በእምባ ተሞልቶ፣ አገልጋዮቹን እንዲህ አዘዘ፣ “ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት። ለእጁ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ ስጡት። እንብላ ደስም ይበለን። ልጄ ተመልሶ መጥቷል! ”14
አከባበሩ
ቢሮዬ ውስጥ በጀርመናዊው አርቲስት ሪቻርድ ቡርዴ የተሰራ ሥዕል ተሰቅሏል። እኔ እና ሃሪየት ይህን ስእል እንወደዋለን። በጥልቅ እይታ ከአዳኙ ምሳሌ መካከል አንድ ልብ የሚነካ ትዕይንትን ያሳያል።
በልጁ መመለስ በይበልጥ ሁሉም ሰው በጣም ደስተኛ ቢሆንም አንድ ሰው ግን አልነበረም—ታላቅ ወንድሙ።15
አንዳንድ ስሜታዊ ሻንጣዎችን ተሸክሟል።
ወንድሙ ርስቱን በጠየቀ ጊዜ እዚያ ነበረ። በአባቱ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ የሃዘን ጫና በአይኑ ተመልክቷል።
ወንድሙ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ የአባቱን ሸክም ለማንሳት ሞክሯል። በየቀኑ፣ የአባቱን የተሰበረ ልብ ለመጠገን ይሠራ ነበር።
እና አሁን፣ ግድየለሹ ልጅ ተመለሰና ሰዎች ለዓመፀኛው ወንድሙ ትኩረት መስጠታቸውን ማቆም አልቻሉም።
አባቱንም እንዲህ አለ፣ “እነሆ ይህን ያህል ዓመታት ከትእዛዝህም አንዱን እንኳ አላጓደልሁም። ሆኖም፣ በዚያን ጊዜ ሁሉ፣ ለእኔ ስትል አላከበርክም።”16
አባትየው እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “ልጄ ሆይ፣ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው! ይህ ሽልማቶችን ወይም የደስታ አከባበርን ስለማወዳደር አይደለም። ይህ ስለ ፈውስ ነው። ለነዚህ ሁሉ ዓመታት በተስፋ ስንጠብቀው የነበረው ጊዜ ይህ ነው። ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ሆነ! ጠፍቶም ነበር ግን እሱ [ተገኝቷል]!”17
ለዘመናችን የሚሆን ምሳሌ
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ውድ ጓደኞቼ፣ ልክ እንደ ሁሉም የአዳኙ ምሳሌዎች፣ ይህ ከረጅም ጊዜ በፊት ስለኖሩ ሰዎች ብቻ አይደለም። ዛሬ ስለ እናንተ እና ስለ እኔ ነው።
ከኛ መካከል ከቅድስና መንገድ ያልራቀ፣ በራሳችን ላይ በማሰብ የበለጠ ደስታን እናገኛለን ብሎ በማሰብ ከመካከላችን ያለ ማን አለ?
ከመካከላችን ያልተዋረደ፣ ልቡ ያልተሰበረ፣ እና ይቅርታ እና ምህረትን የማይፈልግ ማን አለ?
ምናልባት አንዳንድ እንዲህ አሰላስለው ይሆናል፣ “መመለስ ይቻል ይሆን? በቀድሞ ጓደኞቼ ለዘላለም የተጠላሁ፣ የተገለልኩ እና ስም የወጣልኝ ሆኜ እቀራለሁ? ዝም ብሎ መጥፋት ይሻላል? ለመመለስ ብሞክር እግዚአብሄር ምን አይነት ምላሽ ይሰጣል?”
ይህ ምሳሌ መልሱን ይሰጠናል።
የሰማይ አባታችን ልቡ በፍቅር እና በርህራሄ ተሞልቶ ወደ እኛ ይሮጣል። እቅፍ ያደርገናል፣ መጎናጸፊያችንን በትከሻችን፣ በጣታችን ላይ ቀለበት እና በእግራችን ጫማ በማድረግ፣ “ዛሬ እንደሰታለን! አንድ ጊዜ ሞቶ የነበረው ልጄ እንደገና ሕያው ሆኖአልና!”
በመመለሳችን ሰማያት ደስ ይላቸዋል።
በክብር የተሞላ እና የማይነገር ደስታ
አሁን ትንሽ ጊዜ በመውሰድ በግላችሁ ላናግራችሁ?
በህይወታችሁ ምንም አይነት ነገር ቢፈጠር፣ የምወደው ጓደኛዬን እና የባልንጀራዬን ሐዋርያ ሽማግሌ ጄፍሪ አር. ሆላንድን ቃል አስተጋባለሁ፣ እንዲሁም አውጃለሁ፦ “ከማያልቀው የክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት ብርሃን ዝቅ ብላችሁ መስመጥ አትችሉም።”18
ምንም እንኳን ምርጫዎች ከአዳኙ እና ከቤተክርስቲያኑ አርቀው ቢወስዷችሁም፣ ዋነኛው ፈዋሽ ወደ ቤት በሚወስደው መንገድ ላይ ቆሞ ይቀበላችኋል። እናም እኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት እንደመሆናችን መጠን የእሱን ምሳሌ ለመከተል እና እናንተን እንደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ እንደ ጓደኞቻችን ልንቀበላችሁ እንፈልጋለን። ከእናንተ ጋር በደስታ ሃሴት እናደርጋለን።
መመለሳችሁ የሌሎችን በረከት አይቀንስም። የአብ ልግስና ወሰን የለሽ ስለሆነ ለአንዱ የሚሰጠው ነገር የሌሎችን የብኩርና መብት ቅንጣት ያህል አይቀንስም።19
መመለስ ቀላል ነገር ነው ብዬ አላስመስልም። ስለዚህም እመሰክራለሁ። በእውነቱ እናንተ ልታደርጉት ከምትችሉት ምርጫ በጣም ከባድ ምርጫ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ለመመለስ እና በአዳኛችሁ እና በቤዛችሁ መንገድ ለመጓዝ በወሰናችሁበት ቅጽበት ኃይሉ ወደ ህይወታችሁ እንደሚገባ እና እንደሚለውጠው እመሰክራለሁ።20
የሰማይ መላእክት ደስ ይላቸዋል።
እኛም እንደዚሁ በክርስቶስ ቤተሰባችሁ የሆንን እንደሰታለን። ከሁሉም በላይ አባካኝ መሆን ምን እንደሚመስል እናውቃለን። ሁላችንም በተመሳሳይ በየቀኑ የምንመካው በክርስቶስ የማስተሰረያ ኃይል ነው። ይህን መንገድ እናውቃለን፣ እናም ከእናንተ ጋር እንጓዛለን።
መንገዳችን ከሀዘን ከትካዜ እና ከመከራ ፈጽሞ የጸዳ አይሆንም። እኛ ግን እስከዚህ ድረስ የደረስነው “በክርስቶስ ቃል በማይናወጥ እምነት ለማዳን ሃያል በሆነው በመታመን” ነው። እናም አብረን “ፍጹም የሆነ የተስፋ ብርሃን፣ እናም የእግዚአብሔርና [የሰዎች] ሁሉ ፍቅር [እየኖረን] በክርስቶስ [ባለን] ጽኑነት መቀጠል [አለብን]። 21 አብረን፣ “በማይነገርና ክብር በተሞላበት ሐሤት ደስ [ይለናል]፣”22 ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንካሬአችን ነውና!23
እያንዳንዳችን በዚህ ጥልቅ ምሳሌ፣ ወደ ቤት ወደሚያመራው መንገድ እንድንገባ የሚጠራንን የአብን ድምጽ እንድንሰማ—ንስሃ ለመግባት፣ ይቅርታን ለመቀበል እና ወደሚምር እና የሚራራ አምላካችንየሚወስደውን መንገድ እንድንከተል ድፍረት እንዲኖረን ጸሎቴ ነው። ስለዚህ ምስክርነቴን እና በረከቴን እተውላችኋለሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።