አጠቃላይ ጉባኤ
ስለ ሰለስቲያል አስቡ!
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


19:15

ስለ ሰለስቲያል አስቡ!

ምርጫዎቻችሁ ለዘለአለም የት እንደምትኖሩ፣ ትንሳኤ ስታደርጉ የምትለብሱትን የአካል አይነት እና ከነማን ጋር ለዘለአለም እንደምትኖሩ።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዛሬ እናንተን ስለማናግር በጣም አመስጋኝ ነኝ። በእኔ ዕድሜ፣ እያንዳንዱ አዲስ ቀን አስደናቂ እንዲሁም ፈታኝ ድንገተኛ ነገሮችን ያመጣል። ከሶስት ሳምንታት በፊት የጀርባዬ ጡንቻዎች ተጎዱ። ስለዚህ፣ ከ100 በላይ የጠቅላላ ጉባኤ ንግግሮችን ቆሜ ያደረኩኝ ቢሆንም ዛሬ ተቀምጬ ለማድረግ አሰብኩ። መንፈስ ዛሬ መልእክቴን ወደ ልባችሁ እንዲወስድ እጸልያለሁ።

በቅርቡ የ99ኛ አመት ልደቴን አክብሪያለሁ፣ ስለዚህ 100ኛ አመቴን ጀምሪያለሁ። ብዙ ጊዜ ለረጅም አመት የመኖሬን ምስጢር እጠየቃለሁ። የተሻለው ጥያቄ “አንድ ምዕተ አመት በሚጠጋ ኑሮ ምን ተማርኩ?” የሚለው ነው።

ዛሬ ያለኝ ጊዜ ያንን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ እንድመልስ አይፈቅድልኝም፣ ነገር ግን ከተማርኳቸው በጣም ወሳኝ ትምህርቶች መካከል አንዱን ላካፍላችሁ።

የሰማይ አባት ለእኛ ያለው እቅድ ድንቅ እንደሆነ፣ በዚህ ህይወት የምናደርገው ነገር በእውነት አስፈላጊ ነገር እንደሆነ እንዲሁም የአዳኙ የሀጢያት ክፍያ የአባታችን እቅድ እንዲሳካ የሚያስችል መሆኑን ተምሬአለሁ።1

በቅርብ በደረሰብኝ ጉዳት ምክንያት በሚሰማኝ ከባድ ህመም ስሠቃይ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ከመረዳት በላይ ስለሆነው የኃጢያት ክፍያ ስጦታው ጥልቅ አድናቆት ተሰምቶኛል። አስቡበት! አዳኙ “በመከራና በሁሉም አይነት ህመምና ፈተናዎች”2 ተሰቃይቷልደ፣ ይህም በችግር ጊዜ እኛን ማፅናናት፣ መፈወስ እና ማዳን ይችል ዘንድ ነው።3 ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ እና በቀራንዮ የነበረውን ሁኔታ “ይህም ስቃይ እኔን እግዚአብሄርን ከስቃዪ የተነሳ እንድንቀጠቀጥ እናም ከእያንዳንዱ ቀዳዳ እንድደማ”4 አድርጎኛል በማለት ገልጿል። ጉዳቴ ደጋግሜ ስለ “እስራኤል ቅዱስ ታላቅነት” እንዳስብ አድርጎኛል።5 እያገገምኩ በነበረ ጊዜ፣ ጌታ መለኮታዊ ኃይሉን በሰላማዊ እና በማያጠራጥሩ መንገዶች አሳይቷል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ማለቂያ የሌለው የኃጢያት ክፍያ ምክንያት፣ የሰማይ አባታችን እቅድ ፍጹም እቅድ ነው! የእግዚአብሔርን ድንቅ እቅድ መረዳት፣ እንቆቅልሽን ከህይወት፣ እርግጠኛ አለመሆንን ደግሞ ከወደፊታችን ያስወግዳል። እያንዳንዳችን በዚህ ምድር ላይ እንዴት እንደምንኖር እንዲሁም ለዘለአለም የት እንደምንኖር እንድንመርጥ ያስችለናል። “ብሉ ጠጡ እናም ተደሰቱ ነገ እንሞታለንና ይህም ለእኛ መልካም ይሆናል”6 የሚለው በአጽናፈ ሰማይ ውስጥ ካሉ በጣም የማይረቡ ውሸቶች መካከል አንዱ ነው።

የእግዚአብሔር እቅድ ታላቅ ዜና ይኸውና፦ ምድራዊ ህይወታችሁ ሊሆን የሚችለውን ያህል ከሁሉ የተሻለ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ህይወታችሁን በዘለአለምም የተሻለ የሚያደርጉት ተመሳሳይ ነገሮች ናቸው! ዛሬ፣ የሰማይ አባት ለእናንተ ላለው ውድ በረከቶች ብቁ እንድትሆኑ እንዲረዳችሁ፣ “ስለ ሰለስቲያል [የማሰብን]” ልምምድ እንድትከተሉ እጋብዛችኋለሁ!7 ስለ ሰለስቲያል ማሰብ ማለት መንፈሳዊ መሆን ማለት ነው። ከመፅሐፈ ሞርሞን ነቢይ ከያዕቆብ “ስለ መንፈሳዊ ነገር ማሰብ ዘላለማዊ ህይወት እንደሆነ”8 እንማራለን።

የምድር ህይወት፣ ከሁሉ የላቁ ዘላለማዊ ነገሮችን መምረጥን የምንማርበት ዋነኛው ክፍል ነው። በጣም ብዙ ሰዎች፣ ከዚህ ሕይወት ውጪ ሌላ እንደሌለ አድርገው ይኖራሉ። ነገር ግን፣ የዛሬ ምርጫዎቻችሁ ሶስት ነገሮችን ይወስናሉ፦ ለዘለአለም የት እንደምትኖሩ፣ ትንሳኤ ስታደርጉ የምትለብሱትን አካል እና ከነማን ጋር ለዘለአለም እንደምትኖሩ። ስለዚህ፡ ስለ ሰለስቲያል አስቡ።

እንደ ቤተክርስቲያኗ ፕሬዘደንት ባስተላለፍኩት መጀመሪያ መልእክቴ፣ መጨረሻውን በማሰብ እንድትጀምሩ አበረታትቻችኋለሁ። ይህ ማለት የሰለስቲያል መንግስትን ዘላለማዊ ግብ ማድረግ ከዚያም በምድር ላይ ስትኖሩ የምታደርጓቸው እያንዳንዳቸው ውሳኔዎች በሚቀጥለው አለም ላይ የት እንደሚያስቀምጧችሁ በጥንቃቄ ማሰብ ማለት ነው።9

በቤተመቅደስ ውስጥ እንደ ባል እና ሚስት የታተሙ እንዲሁም ቃል ኪዳናቸውን የሚጠብቁ ወንዶች እና ሴቶች ብቻ ለዘለአለም አብረው እንደሚሆኑ ጌታ በግልፅ አስተምሯል። እንዲህ ብሏል፦ “የቅዱስ ተስፋ መንፈስ ያልተሰሩ፣ ያልገቡና ያልታተሙ ቃል ኪዳናት፣ ስምምነቶች፣ የተፈረመባቸው መረጃዎች፣ ግዴታዎች፣ መሃላዎች፣ ስእለቶች፣ ግንኙነቶች፣ ተባባሪነቶዎች … ሰዎች በሞቱ ጊዜ መጨረሻው ይሆናል።”10

ስለዚህ፣ ጥበብ በጎደለው መንገድ አሁን የቴሌስቲያል ህጎችን ለመኖር ከመረጥን የቴሌስቲያል አካልን ለብሰን መነሳትን እየመረጥን ነው። ከቤተሰቦቻችን ጋር ለዘለአለም ላለመኖር እየመረጥን ነው።

ስለዚህ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንዴት እና የት እንዲሁም ከማን ጋር ለዘለአለም መኖር ትፈልጋላችሁ ? መምረጥ ትችላላችሁ።11

ምርጫዎችን በምታደርጉበት ጊዜ ረዘም ያለ— ዘላለማዊ እይታ እንዲኖራችሁ እጋብዛችኋለሁ። የዘለአለም ህይወታችሁ በእሱ ላይ ባላችሁ እምነት እና በኃጢያት ክፍያው ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ኢየሱስ ክርስቶስን አስቀድሙት።12 እንዲሁም ለህጎቹ ባላችሁ ታዛዥነት ላይም የተመሰረተ ነው። መታዘዝ ለዛሬ አስደሳች ሕይወት፣ ለነገ ደግሞ ታላቅ የዘላለማዊ ሽልማት መንገድን ይከፍታል።

አጣብቂኝ ውስጥ ስትገቡ ስለ ሰለስቲያል አስቡ! በፈተና ስትፈተኑ ስለ ሰለስቲያል አስቡ! ህይወት ወይም የምትወዳቸው ሰዎች ሲያሳዝኗችሁ ስለ ሰለስቲያል አስቡ! አንድ ሰው ያለጊዜው ሲሞት ስለ ሰለስቲያል አስቡ። አንድ ሰው በአሰቃቂ ህመም ሲቆይ ስለ ሰለስቲያል አስቡ። የህይወት ጫናዎች ሲደራረቡባችሁ፣ ስለ ሰለስቲያል አስቡ! ልክ እንደኔ ከአደጋ ወይም ከጉዳት በማገገም ላይ ስትሆኑ፣ ስለ ሰለስቲያል አስቡ!

በሰለስቲያል አስተሳሰብ ላይ ስታተኩሩ፣ ተቃውሞ እንደሚገጥማችሁ ጠብቁ።13 ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት፣ አንድ የሙያ ባልደረባዬ በውስጤ “እጅግ ብዙ ቤተመቅደስ” እንዳለኝ ተችቶኛል፣ እንዲሁም ከአንድ በላይ ተቆጣጣሪዎች በእምነቴ ምክንያት ቀጥተውኛል። ነገር ግን የሰለስቲያል አስተሳሰብ ስራዬን እንዳሳደገው እርግጠኛ ነኝ።

ስለ ሰለስቲያል ስታስቡ ልባችሁ ቀስ በቀስ ይለወጣል። በብዛት እንዲሁም ይበልጥ በቅንነት ለመጸለይ ትፈልጋላችሁ። እባካችሁ ጸሎቶቻችሁ የግዢ ዝርዝር እንዲመስሉ አታድርጉ። የጌታ እይታ ከምድራዊ ጥበባችሁ ይልቃል። ለጸሎታችሁ የሚሰጠው ምላሽ ሊያስገርማችሁ ይችላል እንዲሁም ስለ ሰለስቲያል እንድታስቡ ይረዳችኋል።

ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ እፎይታ ለማግኘት ሲለምን ጌታ የሰጠውን ምላሽ ተመልከቱ። እየተፈጸመበት የነበረው ኢሰብአዊ ድርጊት ልምድ እንደሚሰጠው እና ለጥቅሙ እንደሚሆን ጌታ ለነብዩ አስተምሮታል።14 “በመልካም ይህን ብትጸና፣ እግዚአብሔርም ወደ ላይ ዘለአለማዊ ክብር ይሰጥሀል”15 በማለት ጌታ ቃል ገብቷል። ጆሴፍ በጊዜው በነበረው ከባድ ችግር ላይ ከማተኮር ይልቅ ስለ ሰለስቲያል እንዲያስብ እና ዘለአለማዊ ሽልማት እንዲያገኝ ጌታ እያስተማረው ነበር ። ጸሎቶቻችን ከሰማይ አባታችን ጋር የሚደረጉ ህያው ውይይቶች ሊሆኑ ይችላሉ፣ መሆንም አለባቸው።

ስለ ሰለስቲያል ስታስቡ፣ የመምረጥ ነፃነታችሁን የሚሰርቅባችሁን ማንኛውንም ነገር ስትርቁ ራሳችሁን ታገኙታላችሁ። ማንኛውም ሱስ—የጌም፣ የቁማር፣ የዕዳ፣ የአደንዛዥ ዕፅ፣ የአልኮል፣ የቁጣ፣ የብልግና ምስል፣ የወሲብ ወይም የምግብ እንኳ ቢሆን— እግዚአብሄርን ያሳዝነዋል። ለምን? ምክንያቱም ሱሳችሁ አምላካችሁ ስለሚሆን ነው። ለእርዳታ ወደ እርሱ ሳይሆን ወደ ሱሳችሁ ትመለከታላችሁ። በሱስ የምትቸገሩ ከሆነ የሚያስፈልጋችሁን መንፈሳዊ እና ሙያዊ እርዳታ ፈልጉ። እባካችሁ የእግዚአብሄርን ድንቅ እቅድ የመከተል ነፃነታችሁን ሱስ እንዲሰርቅባችሁ አትፍቀዱ።

ስለ ሰለስቲያል ማሰብ የንጽህና ህግን እንድትታዘዙም ይረዳችኋል። ይህን መለኮታዊ ህግ እንደመጣስ ያሉ በበለጠ በፍጥነት ህይወታችሁን የሚያወሳስቡ ነገሮች ጥቂት ናቸው። ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለገባችሁ ሰዎች ዝሙት ምስክርነታችሁን ከምታጡባቸው ፈጣን መንገዶች አንዱ ነው።

ብዙዎቹ የተቃዋሚው የማያቋርጥ ፈተናዎች የሞራል ንጽሕና መጣስን ያካትታሉ። ህይወትን የመፍጠር ሃይል የሰማይ አባት ምድራዊ ልጆቹ እንዲለማመዱ የሚፈቅደው ብቸኛው መለኮታዊ እድል ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ይህንን ሕያው መለኮታዊ ኃይል ለመጠቀም ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን አስቀምጧል። ጾታዊ ግንኙነት የሚፈቀደው በተጋቡ ወንድ እና ሴት መካከል ብቻ ነው።

አብዛኛው አለም ይህንን አያምንም፣ የህዝብ አስተያየት ግን የእውነት ዳኛ አይደለም። ጌታ ንጹሕ ያልሆነ ሰው ወደ ሰለስቲያል መንግሥት እንደማይገባ ተናግሯል። ስለዚህ ስነምግባርን በተመለከተ ውሳኔዎችን በምታደርጉበት ጊዜ እባካችሁ ሰለ ስቲያልን አስቡ። እንዲሁም ንጹሕ ካልነበራችሁ ንስሐ እንድትገቡ እለምናችኋለሁ። ወደ ክርስቶስ ኑ፣ ለኃጢአታችሁ ሙሉ በሙሉ ንስሐ ግቡ እንዲሁም ቃል የገባውን ፍጹም ምህረት ተቀበሉ።16

ስለ ሰለስቲያል ስታስቡ፣ ፈተናዎችን እና ተቃውሞዎችን በአዲስ መልኩ ታያላችሁ። የምትወዱት ሰው እውነትን ሲቃወም ስለ ሰለስቲያል አስቡ እንዲሁም የእናንተን ምስክርነት አትጠራጠሩ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ” ሲል ተንብዮአል።17

የጠላት ማታለል መጨረሻ የለውም። እባካችሁ የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ከማያምኑትም ፈጽሞ ምክር አትቀበሉ። ልምታምኗቸው ከምትችሏቸው—ከነቢያት፣ ከባለ ራእዮች እና ከገላጮች ድምጾች እንዲሁም “ልታደርጉት የሚገባችሁን ሁሉ [ከሚያሳያችሁ]”18 ከመንፈስ ቅዱስ ሹክሹክታ መመሪያን ፈልጉ። እባካችሁ፣ የግል መገለጥን የመቀበል አቅማችሁን ለማሳደግ መንፈሳዊውን ስራ ስሩ።19

ስለ ሰለስቲያል ስታስቡ እምነታችሁ ይጨምራል። ወጣት ተለማማጅ በነበርኩ ጊዜ ገቢዬ በወር 15 ዶላር ነበር። አንድ ምሽት፣ ባለቤቴ ዳንዘል ከዚያ በቂ ያልሆነ ደሞዜ አሥራት እየከፈልኩ እንደሆን ጠየቀችኝ። እየከፈልኩ አልነበረም። በፍጥነት ንስሀ ገብቼ ተጨማሪውን 1 ዶላር 50 ሳንቲም በወር ለአስራት መክፈል ጀመርኩ።

አስራታችንን በመጨመራችን ቤተክርስቲያኗ የተሻለች ሆነች? በጭራሽ። ሆኖም ግን ሙሉ የአሥራት ከፋይ መሆኔ እኔን ለውጦኝ ነበር። አሥራትን መክፈል ስለ እምነት እንጂ ስለ ገንዘብ እንዳልሆነ የተረዳሁት ያኔ ነበር። ሙሉ አሥራት ከፋይ በመሆኔ የሰማይ መስኮቶች ይከፈቱልኝ ጀመር። ቀጥለው የመጡ በርካታ የሙያ እድሎች አስራትን በታማኝነት በመክፈላችን ያገኘነው እንደሆነ አምናለሁ20

አስራት መክፈል እምነትን ይጠይቃል፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር እና በተወዳጅ ልጁ ላይ ያለን እምነት ይገነባል

በጾታዊ ግንኙነትና በፖለቲካ በተሞላ ዓለም ውስጥ ንጹህ ሕይወትን ለመኖር መምረጥ እምነትን ይገነባል።

በቤተመቅደስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ እምነትን ይገነባል። እናም በቤተመቅደስ ውስጥ ያላችሁ አገልግሎት እና አምልኮ ስለ ሰለስቲያል እንድታስቡ ይረዳችኋል። ቤተመቅደስ የመገለጥ ቦታ ነው። እዚያ ወደ ሰለስቲያል ሕይወት እንዴት ማደግ እንደምትችሉ ያሳዩአችኋል። እዚያ ወደ አዳኙ ትቀርባላችሁ እንዲሁም ኃይሉን የበለጠ ታገኛላችሁ። እዚያ በጣም ግራ የሚያጋቡ ችግሮቻችሁን እንኳን ሳይቀር በህይወታችሁ ያሉ ችግሮችን ወደመፍታት ትመራላችሁ።

የቤተመቅደስ ስርአቶች እና ቃል ኪዳኖች ዘላለማዊ ጠቀሜታ አላቸው። እነዚህ ቅዱስ እድሎች በእያንዳንዳችሁ ህይወት ውስጥ እውን እንዲሆኑ ተጨማሪ ቤተመቅደሶችን መገንባታችንን እንቀጥላለን። በሚከተሉት ሥፍራዎች አዲስ ቤተመቅደሶችን ለመገንባት ያለንን ዕቅድ ዛሬ ስናሳውቅ አመስጋኝ ነን፦

  • ሳቫኢ፣ ሳሞአ

  • ካንኩን፣ ሜክሲኮ

  • ፒዩራ፣ ፔሩ

  • ዋንካዮ፣ ፔሩ

  • ቪንያ ዴል ማር፣ ቺሊ

  • ጎያኒያ፣ ብራዚል

  • ጆአ ፔሶአ፣ ብራዚል

  • ካላባር፣ ናይጄሪያ

  • ኬፕ ኮስት፣ ጋና

  • ሉዋንዳ፣ አንጎላ

  • ምቡጂ ማዪ፣ የኮንጎ ዲሚክራሲያዊ ሪፐብሊክ

  • ላኦአግ፣ ፊሊፒንስ

  • ኦሳካ፣ ጃፓን

  • ካሁሉይ፣ ማዊ፣ ሀዋኢ

  • ፌይርባንክስ፣ አላስካ

  • ቫንኩቨር፣ ዋሺንግተን

  • ኮሎራዶ ስፕሪንግስ፣ ኮሎራዶ

  • ቱልሳ፣ ኦክላሆማ

  • ሮአኖክ፣ ቨርጂኒያ

  • ኡላንባታር፣ ሞንጎሊያ

ጌታ ስለ ስለስቲያል እንድናስብ ለመርዳት እነዚህን ቤተመቅደሶች ወደመገንባት እየመራን ነው። እግዚአብሔር ህያው ነው። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው። ሁሉንም የእግዚአብሔርን ልጆች ትባርክ ዘንድ የእርሱ ቤተክርስቲያን ዳግም ተመልሳለች። ይህንን የምመሰክረው ቅዱስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ዮሀንስ 6፥38 ተመልከቱ።

  2. አልማ 7፥11

  3. አልማ 7፥12 ተመልከቱ።

  4. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥18

  5. 2 ኔፊ 9፥40

  6. 2 ኔፊ 28፥7

  7. መንፈሳችን ከአካላችን ጋር እዚህ በአንድነት እያለ ንስሃ መግባት እና ማደግ፣ ከሞትንበት ትንሳኤ እስከምናደርግበት ባለው ጊዜ ውስጥ በቀጣይ አለም ከማድረግ ይቀላል። አሙሌክ ከሃዲውን ዞራማውያንን እንዳስተማራቸው፣ “ይህ ህይወት… እግዚአብሔርን ለመገናኘት የዝግጅት ወቅት ነው” (አልማ 34፥32–35 ተመልከቱ)።

  8. 2 ኔፊ 9፥39

  9. “ራሳችሁን፣ ሀሳባችሁንና፣ ቃላችሁን፣ እናም ድርጊታችሁን የማታስተውሉና፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የማትጠብቁ፣ እናም የሚመጣውን ጌታችንን በተመለከተ የሰማችሁትን እስከ ህይወታችሁ መጨረሻ በእምነት የማትቀጥሉ ከሆናችሁ፣ መጥፋት ይገባችኋል” በማለት ንጉስ ብንያም ህዝቡን ያስጠነቀቀበትን ሞዛያ 4፥30ን ተመልከቱ።

  10. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 132፥7፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  11. እርግጥ ነው፣ የእናንተ የመምረጥ መብት የሌላውን ሊሽር እና የሚመጡ ውጤቶችን መሻር አይችልም። ከወላጆቼ ጋር ለመታተም በጣም ፈልጌ ነበር። ሆኖም ግን ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ እስኪሆናቸው እና የራሳቸውን የቤተመቅደስ ቡራኬ ለመውሰድ እስኪመርጡ ድረስ መጠበቅ ነበረብኝ። ከዚያም እነርሱ እንደ ባልና ሚስት እንዲሁም እኛ ከእነርሱ ጋር እንደ ልጆች ታተምን።

  12. ቅዱሳት መጻህፍት የዘለአለም ሕይወት ስጦታ በአዳኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ምሕረት ብቻ እንደሚገኝ ደጋግመው ይመሰክራሉ (ለምሳሌ፣ ሞሮኒ 7፥41 ተመልከቱ፤ እንዲሁም 2 ኔፊ 2፥6–8፣ 27 ተመልከቱ)።

  13. 2 ኔፊ 2፥11 ተመልከቱ።

  14. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 122፥7 ተመልከቱ።

  15. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥8

  16. ኢሳያስ 1፥16–18ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥42–43 ተመልከቱ።

  17. 1 ጢሞቴዎስ 4፥1፡፡ የሚቀጥለው ጥቅስ “ግብዝነት … በገዛ ህሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው ” (ቁጥር 2) በማለት ይቀጥላል። ጳውሎስ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” በማለት ተናግሯል (2 ጢሞቴዎስ 3፥12)።

  18. 2 ኔፊ 32፥5፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል። ጌታ ቃል እንደገባው፣ “ብትጠይቁ … በራዕይ ላይ ራዕይን፣ በእውቀት ላይ እውቀትን [እንቀበላለን] ” (ትምህርትና ቃል ኪዳኖች 42፥61)።

  19. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ራዕይ ለቤተክርስቲያኗ፣ ራዕይ ለህይወታችን፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2018 (እ.አ.አ)፣ 96 ይመልከቱ።

  20. ይህ የመንስኤ-እና-ውጤት ግንኙነትን ለማመልከት አይደለም። አሥራት የማይከፍሉ ሆነው ሙያዊ እድሎች የሚያገኙ ሲኖሩ እየከፈሉ የማያገኙ አሉ። የተስፋው ቃል ለአስራት ሰጪው የሰማይ መስኮቶች እንደሚከፈቱ ነው። የበረከቶቹ አይነት ይለያያል።