የሚስዮን ጥሪዎች
ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 4—የእድሜ ልክ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆን


“ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 4—የእድሜ ልክ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆን” ወንጌሌን ስበኩ፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለማካፈል መመርያ (2023 (እ.አ.አ))

“ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 4” ወንጌሌን ስበኩ

ምዕራፍ 3፥ ትምህርት 4

የእድሜ ልክ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆን

የጠፋው በግ በዳል ፓርሰን።

ይህን ትምህርት ማስተማር

ጥምቀት አስደሳች የተስፋ ሥርዓት ነው። ስንጠመቅ፣ እግዚአብሔርን ለመከተል እና ወደ ዘላለማዊ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ለመግባት ፍላጎታችንን እናሳያለን። በተጨማሪም የዕድሜ ልክ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ያለንን ቁርጠኝነት እናሳያለን።

ይህ ትምህርት በጥምቀት ወቅት በገባናቸው ቃል ኪዳኖች መሠረት ተደራጅቷል። የሚከተሉትን ዋና ዋና ክፍሎች ያጠቃልላል፣ እያንዳንዱም ንዑስ ክፍሎች አሉት።

ሰዎች የምታስተምሯቸው መርሆዎች እና ትእዛዛት በጥምቀት ጊዜ የሚገቡት ቃል ኪዳን አካል መሆናቸውን እንዲገነዘቡ እርዷቸው። እያንዳንዱ የዚህ ትምህርት ክፍል እንዴት ወደ [ክርስቶስ [እንዲመጡ]… እና የማዳኑን ሃይል [እንዲካፈሉ]” እንደሚረዳቸው አሳዩአቸው (ኦምኒ 1፡26፤ እንዲሁም 1 ኔፊ 15፡14 ተመልከቱ)።

ይህንን ትምህርት በተለያዩ ጉብኝቶች ማስተማር ይኖርባችኋል። የማስተማር ጉብኝት ከ45 ደቂቃ በላይ መሆን የለበትም። ብዙውን ጊዜ ትናንሽ ክፍሎችን የሚሸፍኑ አጭር የተደጋገሙ ጎብኘቶች የተሻሉ ናቸው።

ምን እንደምታስተምሩ፣ መቼ እንደምታስተምሩ እና ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅባችሁ አቅዱ። የምታስተምሯቸውን ሰዎች ፍላጎት ከግምት አስገቡ እንዲሁም የመንፈስን ምሪት ፈልጉ። ሰዎችን ለጥምቀት እና ለመረጋገጥ እንዲዘጋጁ ለመርዳት ከሁሉም በላይ ይጠቅማል ብላችሁ በምታስቡበት በማንኛውም መንገድ ትምህርቶችን ማስተማር ትችላላችሁ።

በዚህ ትምህርት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክፍሎች ልዩ ግብዣዎችን ያካትታሉ። ግብዣዎችን እንዴት እና መቼ እንደምታቀርቡ ለመወሰን መነሳሳትን ፈልጉ። የእያንዳንዱን ግለሠብ የመረዳት ደረጃ አስተውሉ። ደረጃ በደረጃ ወንጌልን እንዲኖሩ እርዱ።

አንዲት ሴት ቅዱስ ቁርባን እየተካፈለች

የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በላያችን ለመውሰድ ፈቃደኛ ለመሆን የኛ ቃል ኪዳን

በምንጠመቅበት ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን “በፍጹም ልብ” ለመከተል ቃል እንድገባለን። እንዲሁም “የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በላያችንይ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናችንን” (2 ኔፊ 31፡13ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፡37 ተመልከቱ) እንመሰክራለን።

የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳችን ላይ መውሰድ እርሱን ማስታወስ በተጨማሪም እንደ የእድሜ ልክ ደቀ መዛሙርቱ ለመኖር መጣር ማለት ነው። የእርሱ ብርሃን በእኛ በኩል ለሌሎች እንዲበራ እናደርጋለን። እኛ የእርሱ እንደሆንን እናያለን እናም በሕይወታችን እርሱን እናስቀድማለን።

የሚከተሉት ክፍሎች ኢየሱስ ክርስቶስን የምናስታውስበትን እና የምንከተልባቸውን ሁለት መንገዶች ይገልጻሉ።

ዘወትር ጸልዩ

ጸሎት ከልብ የሆነ ከሰማይ አባት ጋር የሚደረግ ቀላል ውይይት ሊሆን ይችላል። በጸሎት ከእርሱ ጋር በግልጽና በእውነት እንነጋገራለን። ለእሱ ያለንን ፍቅር እንገልጻለን እንዲሁም ለበረከታችን ምስጋና እናቀርባለን። እርዳታ፣ ጥበቃ እና መመሪያም እንጠይቃለን። ጸሎታችንን በምንጨርስበት ጊዜ ቆም ብለን ለማዳመጥ ጊዜ መውሰድ አለብን።

ኢየሱስ “ዘወትር በስሜ ወደ አብ መጸለይ አለባችሁ” በማለት አስተምሯል (3 ኔፊ 18፡19፣ አጽንዖት ተጨምሯል፤ ደግሞም ሙሴ 5፡8 ተመልከቱ)። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስንጸልይ እርሱን እና የሰማይ አባትን እናስታውሳለን።

ኢየሱስ በምንጸልይበት ጊዜ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የአዳኙን ጸሎቶች በማጥናት ስለ ጸሎት ብዙ መማር እንችላለን (ማቴዎስ 6፡9–13ዮሐንስ 17 ተመልከቱ)።

ጸሎታችን የሚከተሉትን ክፍሎች ሊያካትት ይችላል፥

  • የሰማይ አባትን በመጥራት ጀምሩ።

  • ለተቀበልናቸው በረከቶች ምስጋናን እንደማቅረብ ያሉ የልብን ስሜቶች ግለጹ።

  • ጥያቄዎችን ጠይቁ፣ ምሪትን ፈልጉ እንዲሁም የምትፈልጓቸውን በረከቶች ለምኑ።

  • “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን” በማለት ጨርሱ።

ቅዱሳት መጻሕፍት ጠዋት እና ማታ እንድንጸልይ ይመክሩናል። ነገር ግን በማንኛውም ጊዜ እና በማንኛውም ሁኔታ መጸለይ እንችላለን። በግል እና በቤተሰባችን ውስጥ ስንጸልይ መንበርከክ ትርጉም ያለው ነገር ሊሆን ይችላል። ሁል ጊዜ በልባችን ጸሎት ሊኖረን ይገባል። (አልማ 34:2737:36–373 ኔፊ 17:1319:16 ተመልከቱ)

ጸሎታችን የታሰበበት እና ከልብ የመነጨ መሆን አለበት። ስንጸልይ ተመሳሳይ ነገርን በተመሳሳይ መንገድ ከመናገር መቆጠብ አለብን።

የተቀበልናቸውን መልሶች ተግባራዊ ለማድረግ በእምነት፣ በቅንነት እና በእውነተኛ ፍላጎት እንጸልያለን። ይህን ስናደርግ እግዚአብሔር ይመራናል እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን እንድንወስን ያግዘናል። ወደ እርሱም እንደቀረብን ይሰማናል። ማስተዋልንና እውነትን ይሰጠናል። በማጽናናት፣ በሰላም እና በጥንካሬ ይባርክልናል።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፥ “ጸሎት

  • የመፅሐፍ ቅዱስ መዝገበ-ቃላት፥ “ጸሎት

  • የወንጌል ርዕሶች፥ “ጸሎት

የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት

ኔፊ “በክርስቶስ ቃላት እንድንደሰት ያበረታታናል፣ ምክንያቱም የክርስቶስ ቃላት ማድረግ ያለብንን ሁሉ ይነግሩናል” ( 2 ኔፊ 32፥331:20 ተመልከቱ) በማለት አስተምሯል።

ቅዱሳት መጻህፍትን ማጥናት ኢየሱስ ክርስቶስን ለማስታወስ እና ለመከተል ወሳኝ መንገድ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለ ህይወቱ፣ አገልግሎቱ እና ትምህርቱ እንማራለን። ስለ ቃል ኪዳኖቹም እንማራለን። ቅዱሳት መጻሕፍትን ስናነብ ፍቅሩን እንለማመዳለን። በእርሱ ላይ ያለን እምነት ይጨምራል፣ ነፍሳችን እና አእምሯችን ይረዳል። ስለ መለኮታዊ ተልእኮው ምስክርነታችን እየጠነከረ ይሄዳል።

ቃሉን በህይወታችን ውስጥ ስንተገበር ኢየሱስን እናስታውሳለን እንዲሁም እንከተላለን። በየቀኑ ቅዱሳት መጻህፍትን በተለይም መጽሐፈ ሞርሞንን ማጥናት አለብን።

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻህፍት መጽሐፍ ቅዱስ፣ መፅሐፈ ሞርሞን፣ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች እና የታላቅ ዋጋ ዕንቁ ናቸው። እነዚህም “መደበኛ ሥራዎች” በመባል ይጠራሉ።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ቅዱሳት መጻህፍት።”

  • የወንጌል ርዕሶች “ቅዱሳት መጻህፍት

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን እያስተማረ

የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጠበቅ የኛ ቃል ኪዳን

ማስታወሻ፡ በእዚህ ትምህርት ውስጥ ያሉትን ትእዛዛት የምናስተምርበት ብዙ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ፣ በጥቂት ጉብኝቶች ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ። ወይም አንዳንዶቹን እንደ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ትምህርቶች አካል ማስተማር ትችላላችሁ። ትእዛዛትን ስታስተምሩ፣ ከጥምቀት ቃል ኪዳን እና ከደህንነት እቅድ ጋር ማገናኘታችሁን አረጋግጡ።

እኛ ስንጠመቅ፣ “ትእዛዙን እንደምንጠብቅ” ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን (ሞዛያ 18፡10አልማ 7፡15)።

እግዚአብሔር ስለሚወደን ትእዛዛትን ሰጥቶናል። አሁንም ሆነ ለዘላለም እርሱ ለእኛ ከሁሉ ተተሻለውን ይፈልጋል። እንደ ሰማይ አባትነቱ፣ ለመንፈሳዊ እና አካላዊ ደህንነታችን የሚያስፈልገንን ያውቃል። እንዲሁም ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚያስገኝልንን ያውቃል። እያንዳንዱ ትዕዛዝ ውሳኔዎቻችንን የሚመራ፣ የሚጠብቅ እና እንድናድግ የሚረዳን መለኮታዊ ስጦታ ነው።

ወደ ምድር የመጣንበት አንዱ ምክንያት በጥበብ ነጻ ምርጫ በማድረግ ለመማር እና ለማደግ ነው (አብርሃም 3፡25 ተመልከቱ)። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመታዘዝ መምረጥ—እና ስንወድቅ ንስሃ መግባት—ይህን ብዙ ጊዜ ፈታኝ የሆነውን ምድራዊ ጉዞ እንድንጓዝ ይረዳናል።

የእግዚአብሔር ትእዛዛት የጥንካሬ እና የበረከት ምንጭ ናቸው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 82፡8–9 ተመልከቱ)። ትእዛዛትን ስንጠብቅ ነፃነታችንን የሚገድቡ ሸክም ህጎች እንዳልሆኑ እንማራለን። እውነተኛ ነፃነት የሚመጣው ትእዛዛትን በማክበር ነው። ታዛዥነት በመንፈስ ቅዱስ በኩል ብርሃን እና እውቀትን የሚያመጣልን የጥንካሬ ምንጭ ነው። እንደ እግዚአብሔር ልጆች የበለጠ ደስታን ያመጣልናል እንዲሁም ወደ መለኮታዊ አቅማችን እንድንደርስ ይረዳናል።

እግዚአብሔር ትእዛዛቱን ስንጠብቅ እንደሚባርከን ቃል ገብቷል። አንዳንድ በረከቶች ለተወሰኑ ትእዛዛት የተለዩ ናቸው። የእርሱ ትልቆቹ በረከቶች በዚህ ሕይወት ሰላም፣ በሚመጣው ዓለም ደግሞ የዘላለም ሕይወት ናቸው። (ሞዛያ 2:41አልማ 7:16; ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14:759:2393:28130:20–21ን ተመልከቱ።)

የእግዚአብሔር በረከቶች መንፈሳዊ እንዲሁም ስጋዊ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ እነርሱን ስንጠብቅ እንደ እርሱ ፈቃድ እና ጊዜ እንደሚመጡ በማመን መታገስ ይገባናል (ሞዛያ 7፡33ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፡68 ተመልከቱ)። አንዳንድ በረከቶችን ለማወቅ መንፈሳዊ ትኩረት መስጠት እና አስተዋዮች መሆን ይኖርብናል። ይህ በተለይ በቀላል እና ተራ በሚመስሉ መንገዶች ለሚመጡ በረከቶች እውነት ነው።

አንዳንድ በረከቶች ዞር ተብለው ሲታዩ ብቻ ግልጽ ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ ህይወት እስኪያልፍ ላይመጡ ይችላሉ። የእግዚአብሔር በረከቶች ጊዜ እና ተፈጥሮ ምንም ይሁን ምን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለመኖር ስንጥር እንደሚመጡ እርግጠኞች መሆን እንችላለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 82፡10 ተመልከቱ)።

እግዚአብሔር ልጆቹን በሙሉ ይወዳል። ድካማችንን ይታገሣል፣ ንስሐ ስንገባም ይቅር ይለናል።

ሁለቱ ታላላቅ ትዕዛዛት

ኢየሱስ “ከሕግ ማየትኛይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ተብሎ ሲጠየቅ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” በማለት መለሰ።

ከዚያም ኢየሱስ ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥አለ “እርስዋም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት”። (ማቴዎስ 22፥37–39)። “ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም” (ማርቆስ 12:31)።

የእግዚአብሔር የመንፈስ ልጆች እንደመሆናችን መጠን ለፍቅር ትልቅ አቅም አለን። የመንፈሳዊ ውርሳችን አካል ነው። ሁለቱን ታላላቅ ትእዛዛት መኖር—እግዚአብሔርን አስቀድሞ መውደድ እና ጎረቤታችንን መውደድ—የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መለያ ባህሪ ነው።

የእግዚአብሔር ፍቅር

ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ትእዛዛቱን መጠበቅ እንችላለን (ዮሐንስ 14፡15፣ 21 ተመልከቱ)። በሕይወታችን እርሱን በማስቀደም ፈቃዳችንን ለእርሱ ማስገዛት እንችላለን። ፍላጎታችንን፣ ሀሳቦቻችንን እና ልባችንን በእርሱ ላይ ማድረግ እንችላለን (አልማ 37፡36 ተመልከቱ)። ለሰጠን በረከቶች በአመስጋኝነት መኖር—እንዲሁም እነዚያን በረከቶች በማካፈል ቸር መሆን እንችላለን (ሞዛያ 2፡21–244፡16–21 ተመልከቱ)። በጸሎት እና ሌሎችን በማገልገል ለእርሱ ያለንን ፍቅር መግለፅ እና ጥልቅ ማድረግ እንችላለን።

ልክ እንደ ሌሎች ትእዛዛት፣ እግዚአብሔርን የመውደድ ትእዛዝ ለእኛ ጥቅም ነው። የምንወደው የምንፈልገውን ነገር ይወስናል። የምንፈልገው ነገር የምናስበውን እና የምናደርገውን ይወስናል። የምናስበው እና የምናደርገው ደግሞ ማን እንደሆንን—እንዱሁም ምን አይነት ሰው እንደምንሆን ይወስናል።

ሌሎችን መውደድ

ሌሎችን መውደድ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር አካል ነው። አዳኙ ሌሎችን የምንወድበት ብዙ መንገዶችን አስተምሮናል (ለምሳሌ ሉቃስ 10፡25–37 እና ማቴዎስ 25፡31–46 ተመልከቱ)። እንደርስላቸዋለን እንዲሁም ወደ ልባችን እና ወደ ህይወታችን እንቀበላቸዋለን። በትንንሽ መንገዶች እንኳን ቢሆን በማገልገል ራሳችንን በመስጠት እንወዳለን። ሌሎችን የምንወዳቸው እነሱን ለመባረክ እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታ በመጠቀም ነው።

ሌሎችን መውደድ ታጋሽ፣ ደግ እና ታማኝ መሆን ነው። እንዲሁ ይቅር ማለትን ይጨምራል። ሁሉንም ሰው ማክበር ማለት ነው።

አንድን ሰው ስንወድ እኛንና ያ ሰው እንባረካለን። ልባችን ይሰፋል፣ ህይወታችን የበለጠ ትርጉም ያለው ይሆናል፣ ደስታችንም ይጨምራል።

በረከቶች

ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት-እግዚአብሔርን እና ባልንጀራችንን መውደድ—ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ሁሉ መሰረት ናቸው (ማቴዎስ 22፡40 ተመልከቱ)። እግዚአብሔርን መጀመሪያ ስንወድና ሌሎችን ስንወድ በህይወታችን ሁሉም ነገር ትክክለኛውን ቦታ ይይዛል። ይህ ፍቅር በአመለካከታችን፣ በጊዜ አጠቃቀማችን፣ በፍላጎቶች እና ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ነቢይን መከተል

እግዚአብሔር ነቢያትን በምድር ላይ የእርሱ ወኪሎቹ እንዲሆኑ ጠራቸው። በነቢያቱ በኩል እውነትን ይገልጣል፣መመሪያ እና ማስጠንቀቂያም ይሰጣል።

እግዚአብሔር ጆሴፍ ስሚዝ የኋለኛው ቀን የመጀመሪያ ነቢይ እንዲሆን ጠርቶታል (ትምህርት 1 ተመልከቱ)። ዛሬ ቤተክርስቲያኑን የሚመራውን ነቢይን ጨምሮ የጆሴፍ ስሚዝ ተተኪዎችም እንዲመሩ በእግዚአብሔር ተጠርተዋል። በህይወት ባለው ነቢይ መለኮታዊ ጥሪ ላይ እምነት ሊኖረን እና ትምህርቶቹን ልንከተል ይገባናል።

በህይወት ያሉ ነቢያት እና የሐዋርያት ትምህርቶች የሚለዋወጡ እሴቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ የዘላለም እውነት መልህቅን ይሰጣሉ። የእግዚአብሔርን ነቢያት ስንከተል፣ የዓለም ግራ መጋባትና ውዝግብ አያጨናንቀንም። በዚህ ህይወት የበለጠ ደስታን፣ ለዚህ የዘላለም ጉዟችን ክፍል ደግሞ ምሪትን እናገኛለን።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

አስርቱን ትዕዛዛት አክብሩ

እግዚአብሔር ሕዝቡን ይመራ ዘንድ ሙሴ ለተባለ የጥንት ነቢይ አሥርቱን ትእዛዛት ገለጠ። እነዚህ ትእዛዛት በዘመናችንም ተግባራዊ ናቸው። እግዚአብሔርን እንድናመልክ እና እንድናከብር ያስተምሩናል። ደግሞም እርስ በራስ ምን አይነት ግንኙነት መኖር እንደሚገባንም ያስተምረናል።

  • “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” (ዘጸአት 20፥3) ሌሎች “አማልክት” እንደ ንብረት፣ ኃይል ወይም ታዋቂነት ያሉ ብዙ ነገሮችን ሊያካትቱ ይችላሉ።

  • “የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ” (ዘጸአት 20፥4)።

  • “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ” (ዘጸአት 20፥7)።

  • “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” (ዘጸአት 20፥8)።

  • “አባትህንና እናትህን አክብር” (ዘጸአት 20፥12)።

  • “አትግደል” (ዘጸአት 20፥13)።

  • “አታመንዝር” (ዘጸአት 20፥14)።

  • “አትስረቅ” (ዘጸአት 20፥15)።

  • “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር” (ዘጸአት 20፥16)።

  • “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ” (ዘጸአት 20፥17)።

የቅዲስን መጻህፍት ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

አንድን ሴት የተሸከመ ሰው

የንጽህናን ህግ ኑሩ

የንጽህና ህግ ለደህንነታችን እና ከፍ ከፍ ለመደረግ የእግዚአብሔር እቅድ ወሳኝ አካል ነው። በባልና በሚስት መካከል ያለ ፆታዊ ግንኙነት ልጆችን ለመፍጠር እና በትዳር ውስጥ ፍቅርን ለመግለጽ በእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው። ይህ የቀረበ ግንኙነት እና የሰውን ህይወት የመፍጠር ሃይል ውብ እና የተቀደሰ እንዲሆን የታሰበ ነው።

የአምላክ የንጽሕና ሕግ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ካለ ሕጋዊ ጋብቻ ውጪ ከጾታዊ ግንኙነት መራቅ ነው። ይህ ህግ ከጋብቻ በኋላ ለትዳር አጋር ፍጹም ታማኝነት ማለትም ነው።

የንጽህና ህግን እንድንጠብቅ ይረዳን ዘንድ ነቢያት በሀሳባችን እና በቃላችን ንፁህ እንድንሆን አሳስበዋል። በማንኛውም መልኩ ወሲባዊ ምስሎችን ማስወገድ አለብን። የንጽህና ህግን ስናከብር በባህሪያችን እንዲሁም በገጽታችን ስርዓት ያለን መሆን አለብን።

ተጠማቂዎች የንጽህና ህግን መኖር አለባቸው።

ንስሃ እና ይቅርታ

በእግዚአብሔር ፊት፣ የንጽህና ህግን መጣስ በጣም ከባድ ነገር ነው (ዘጸአት 20፡14ኤፌሶን 5፡3 ተመልከቱ)። ሕይወትን ለመፍጠር እርሱ የሰጠውን ቅዱስ ኃይል አለአግባብ ይጠቀማል። ይህን ህግ ብንጥስም እንኳን እርሱ እኛን መውደዱን ይቀጥላል። ንስሀ እንድንገባ እና በኢየሱስ ክርስቶስ የሃጥያት መስዋዕትነት ንፁህ እንድንሆን ይጋብዘናል። በኃጢአት የመጣ ተስፋ መቁረጥ በእግዚአብሔር ይቅርታ ጣፋጭ ሰላም ሊተካ ይችላል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፡42–43 ተመልከቱ)።

በረከቶች

እግዚአብሔር እኛን እና ወደ ምድር የሚልካቸውን የመንፈስ ልጆች ይባርክ ዘንድ የንጽሕና ህግን ሰጠ። ይህንን ህግ መጠበቅ ለግል ሰላም እንዲሁም በቤተሰብ ግንኙነታችን ውስጥ ፍቅር፣ እምነት እና አንድነት እንዲኖረን አስፈላጊ ነው።

የንጽህና ህግን ስንኖር ከጋብቻ ውጪ ባለ ፆታዊ ግንኙነት ከሚመጣ መንፈሳዊ ጉዳት እንጠበቃለን። እንዲህ ዓይነት ግንኙነትን ተከትለው ከሚመጡ ስሜታዊና አካላዊ ችግሮችም እንርቃለን። በእግዚአብሔር ፊት ልበ ሙሉነታችን እያደገ ይሄዳል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፡45 ተመልከቱ)። ለመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ የበለጠ ዝግጁ እንሆናለን። በቤተመቅደስ ውስጥ ቤተሰቦቻችንን ለዘለአለም አንድ የሚያደርገውን ቅዱስ ቃል ኪዳን ለመግባት በተሻለ ሁኔታ እንዘጋጃለን።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ጌተሰማኔ።”

  • የወንጌል ርዕሶች “የንጽህና ህግ

የአስራት ህግን ማክበር

የቤተክርስቲያኑ አባል የመሆን ታላቅ አጋጣሚ አስራትን የመክፈል እድል ነው። አሥራት ስንከፍል የእግዚአብሔር ሥራ እንዲስፋፋ የበለጠ በመርዳት ልጆቹን እንባርካለን።

የአስራት ህግ መነሻ የብሉይ ኪዳን ዘመን ነው። ለምሳሌ፣ ነቢዩ አብርሃም ከነበረው ሁሉ አሥራትን ከፍሏል (አልማ 13፡15ዘፍጥረት 14፡18–20 ተመልከቱ)።

አስራት የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም አንድ አስረኛ ማለት ነው። አሥራት ስናወጣ፣ ከገቢያችን አንድ አስረኛውን ለቤተክርስቲያኗ እንሰጣለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 119፡3–4 ተመልከት፤ ወለድ ገቢ እንደማለት ነው)። ያለን ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። አሥራት ስንከፍል፣ እርሱ የሰጠንን የተወሰነ ክፍል በመመለስ ምስጋና እናሳያለን።

አስራትን መክፈል የእምነት መገለጫ ነው። እግዚአብሔርን የምናከብርበትም መንገድ ነው። ኢየሱስ “[አስቀድመን] የእግዚአብሔርን መንግሥት … [መፈለግ] እንዳለብን” (ማቴዎስ 6፡33)፣ አሥራት ማውጣት ደግሞ ይህን የምናደርግበት መንገድ እንደሆነ አስተምሯል።

የመበለቷ ሳንቲም፣ በሳንድራ ራስት

የአስራት ገንዘብ አጠቃቀም

የአስራት ገንዘብ የተቀደሰ ነው። አስራትን ለኤጲስ ቆጶስ አባል እንሰጣለን ወይም በብዙ ቦታዎች በበይነ መረብ መክፈል እንችላለን። ኤጲስ ቆጶስ አሥራት ሲቀበል፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ዋና መሥሪያ ቤት ያስተላልፋል።

የቀዳሚ አመራር፣ የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን እና የኤጲስ ቆጶስ አመራር የአስራት በእግዚአብሔር ስራ ገንዘቡ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ይወስናሉ ( ትምህርት አና ቃል ኪዳኖች 120፡1 ተመልከቱ)። እነዚህ አጠቃቀሞች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡

  • ቤተመቅደሶችን እና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን መገንባት እና ማስተዳደር።

  • ቅዱሳት መጻሕፍትን መተርጎም እና ማተም።

  • የአካባቢ ቤተክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሚሳተፉበትን አክቲቪቲ እና ክንውኖች መደገፍ።

  • በዓለም ዙሪያ የከናወነውን የሚስዮናዊ ሥራ መደገፍ።

  • የቤተሰብ ታሪክ ሥራን መደገፍ።

  • ትምህርት ቤቶች እና ትምህርትን በገንዘብ መደገፍ።

አስራት የአካባቢ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ለመክፈል አይውልም። እነሱ ያለምንም ክፍያ በፈቃደኝነት ያገለግላሉ።

በረከቶች

አሥራት ስንከፍል እግዚአብሔር ከምንሰጠው እጅግ የሚበልጥ በረከትን ሊሰጠን ቃል ገብቷል። እርሱ “የሰማይን መስኮት [ይከፍታል]፣ … [መቀበያ ቦታ እስክናጣ ድረስ በረከትን አትረፍርፎ ያፈሳል]” (ሚልክያስ 3፡10ቁጥር 7–12 ተመልከቱ)። እነዚህ በረከቶች መንፈሳዊ እና ምድራዊ ሊሆኑ ይችላሉ።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

የጥበብ ቃልን ማክበር

የጌታ የጤና ህግ

ሰውነታችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ስጦታዎች ናቸው። እርሱን ለመምሰል እያንዳንዳችን ሥጋዊ አካል ያስፈልገናል። ሰውነታችን በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ቅዱሳት መጻህፍት ከቤተመቅደሶች ጋር ያወዳድሯቸዋል (1 ቆሮንቶስ 6፡19–20 ተመልከቱ)።

ጌታ ሰውነታችንን በአክብሮት እንድንይዝ ይፈልጋል። ይህንም ማድረግ እንችል ዘንድ የጥበብ ቃል የተሰኘውን የጤና ህግ ገለጠ። ይህ መገለጥ ጤናማ ምግቦችን ስለመመገብ እና ሰውነታችንን የሚጎዱ ንጥረ ነገሮችን -በተለይ አልኮል፣ ትምባሆ እና ትኩስ መጠጦችን (ሻይ እና ቡና ማለት ነው) አለመጠቀምን ያስተምረናል።

በጥበብ ቃል መንፈስ የዘመናችን ነቢያት ጎጂ፣ ሕገወጥ ወይም ሱስ የሚያስይዙ ሌሎች ነገሮችን እንዳንጠቀም አስጠንቅቀዋል። ነቢያት በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን አላግባብ መጠቀምንም አስጠንቅቀዋል። (በአካባቢያችሁ ያሉ ሌሎች ንጥረ ነገሮች ጥቅም ላይ መዋል አለመዋላቸውን በተመለከተ የሚስዮን ፕሬዘዳንታችሁ ጥያቄዎችን ይመልሳል።)

በረከቶች

ጌታ ለሥጋዊ እና መንፈሳዊ ደህንነታችን የጥበብን ቃል ሰጥቷል። ይህንን ትእዛዝ ስንጠብቅ ታላቅ በረከቶችን ቃል ገብቷል። እነዚህ በረከቶች ጤናን፣ ጥበብን፣ የእውቀት ሀብትን እና ጥበቃን ያካትታሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 89፡18–21 ተመልከቱ)።

የጥበብን ቃል መታዘዝ የመንፈስ ቅዱስን መነሳሳት የበለጠ እንድንቀበል ይረዳናል። ምንም እንኳን ሁላችንም የጤና ችግሮች ቢያጋጥሙንም ይህን ህግ መታዘዝ በአካል፣ በአእምሮ እና በመንፈስ ጤናማ እንድንሆን ይረዳናል።

ተጠማቂዎች የጥበብን ቃል መታዘዝ አለባቸው።

የሱስ ችግር ያለባቸው ሰዎችን ስለመርዳት መመሪያ ለማግኘት፣ ምዕራፍ 10ን ተመልከቱ።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳን መጻህፍት መመሪያ፡ “የጥበብ ቃል

  • የወንጌል አርእስቶች “ጤና፣” “የጥበብ ቃል

  • የህይወት እርዳታ፥ “ሱስ

ሰንበትን መቀደስ

የዕረፍት እና የአምልኮ ቀን

ሰንበት እግዚአብሔር በየሳምንቱ ከዕለት ተዕለት ድካማችን እንድናርፍ እና እንድናመልከው የለየልን ቅዱስ ቀን ነው። ለሙሴ ከተሰጡት አስር ትእዛዛት መካከል አንዱ “የሰንበትን ቀን ፣ ትቀድሰውም ዘንድ አስብ” (ዘጸአት 20፡8፤ እንዲሁም ቁጥር 9–11 ተመልከቱ) የሚለው ነው ።

በጊዜያችን መገለጥ፣ ጌታ “በእውነት ከስራህ እንድታርፍ እናም ለልዑልም አምልኮህን እንድትሰጥ ይህ ቀን ተሰጥቶሀልና“ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 59፡10) በማለት ስለ ሰንበት እንደገና አረጋግጧል። ሰንበት የደስታ፣ የጸሎት እና የምስጋና ቀን መሆን እንዳለበትም ተናግሯል (ቁጥር 14-15 ተመልከቱ)።

እንደ ሰንበት አምልኮአችን ክፍል፣ በየሳምንቱ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንገኛለን። በዚህ ስብሰባ፣ እግዚአብሔርን እናመልካለን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስን እና የኃጢያት ክፍያውን ለማስታወስ ቅዱስ ቁርባንን እንካፈላለን። ቅዱስ ቁርባንን ስንካፈል፣ ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን እናድሳለን፣ ለኃጢአታችንም ንስሃ ለመግባት ፈቃደኛ መሆናችንን እናሳያለን። የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት የሰንበት ቀን አከባበራችን ዋና አካል ነው።

በቤተ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የበለጠ በምንማርባቸው ክፍሎችም እንሳተፋለን። ቅዱሳት መጻሕፍትን በአንድነት ስናጠና እምነታችን ያድጋል። አንዳችን ሌላችንን ስናገለገል እና ስናበረታ ፍቅራችን ያድጋል።

በዕለተ ሰንበት ከድካማችን ከማረፍ በተጨማሪ ከመገበያየትም ሆነ የተለመደ ቀን ከሚያስመስሉ ከሌሎች ሥራዎች መቆጠብ አለብን። የአለምን ተግባራት ወደ ጎን በመተው ሀሳባችንን እና ድርጊታችንን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እናተኩራለን።

መልካም የመስራት ቀን

በሰንበት ቀን መልካምን ማድረግ ቢያንስ ለመቀደስ እንደማናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ አስፈላጊ ነው ወንጌልን እንማራለን፣ እምነትን እናጠናክራለን፣ ግንኙነቶችን እንገነባለን፣ አገልግሎት እንሰጣለን እንዲሁም ከቤተሰብ እና ከጓደኞቻችን ጋር በሌሎች አነቃቂ ተግባሮች እንሳተፋለን።

ጥንዶች ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበቡ

በረከቶች

የሰንበትን ቀን መቀደስ ለሰማይ አባት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለን ታማኝነት መግለጫ ነው። የሰንበት ተግባራችንን እግዚአብሔር ለቀኑ ካለው ዓላማ ጋር የሚስማማ ስናደርግ ደስታና ሰላም ይሰማናል። በመንፈስ እናድጋለን፣ በአካልም እንታደሳለን። በተጨማሪም ወደ እግዚአብሔር የበለጠ እንቀርባለን፣ ከአዳኛችንም ጋር ያለንን ግንኙነት እናጠናክራለን። “ከአለም ነገሮች … ንጹህ እና ነውር [የሌለብን]” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 59፥9ን ተመልከቱ) መሆን እንችላለን። ሰንበት “ደስታ” ትሆናለች (ኢሳይያስ 58:13፤ እንዲሁም ቁጥር 14⁠ን ተመልከቱ)።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የወንጌል አርዕስቶች፥ “የሰንበት ቀን

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “የሰንበት ቀን

ህግን ተከተሉ እንዲሁም አክብሩ

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ህግን በመታዘዝ እና ጥሩ ዜጋ በመሆን ያምናሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 134የእምነት አንቀጾች 1፡12 ተመልከቱ)። የቤተክርስቲያኗ አባላት ማህበረሰባቸውን እና ሀገራቸውን ለማሻሻል አገልግሎት እንዲሰጡ ይበረታታሉ። በህብረተሰቡ እና በመንግስት ላይ የመልካም ስነ ምግባር እሴቶች ተፅእኖ እንዲያኖሩም ይበረታታሉ።

የቤተክርስቲያን አባላት በህግጉመሰረት በመንግስት እና በፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ይጋበዛሉ። በመንግስት የኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ አባላት የሚሠሩት እንደ ሚመለከታቸው ዜጋ እንጂ እንደ ቤተ ክርስቲያኗ ተወካዮች አይደለም።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ ክፍል 38.8 “የፖለቲካ እና የሲቪክ እንቅስቃሴ

  • የወንጌል ርዕሶች “ዜግነት

በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ፣ በጄ. ከርክ ሪቻርድስ

እግዚአብሔርን እና ሌሎችን ለማገልገል የኛ ቃል ኪዳን

አገልግሎት

ስንጠመቅ፣ እግዚአብሔርን እና ሌሎችን ለማገልገል ቃል እንገባለን። ሌሎችን ማገልገል እግዚአብሔርን ከምናገለግልባቸው መንገዶች አንዱ ነው (ሞዛያ 2፡17 ተመልከቱ)። ነቢዩ ጆሴፍ “አንዳችሁ የአንዳችሁን ሸክም … ለመሸከም፣ … ከሚያዝኑት ጋር ለማዘን … መጽናናትን ለሚፈልጉ ለማጽናናት” ፈቃደኞች [ሁኑ]” (ሞዛያ 18፡8–9) ሲል የመጠመቅ ፍላጎት ለነበራቸው አስተምሯቸዋል።

ከጥምቀቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ አዲስ አባላት በቤተክርስቲያን ውስጥ የማገልገል ጥሪ ይቀበሉ ነበር። እነዚህ ጥሪዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረቱ እና ያለ ክፍያ ናቸው። እነርሱን ስንቀበል እና በትጋት ስናገለግል፣ በእምነት እናድጋለን፣ መክሊታችንን እናዳብራለን እንዲሁም ሌሎችን እንባርካለን።

በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ሌላው የአገልግሎታችን ክፍል “አገልጋይ ወንድም” ወይም “አገልጋይ እህት” መሆን ነው። በዚህ ኃላፊነት ውስጥ፣ የተመደቡ ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን እናገለግላለን።

የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን በየቀኑ ለማገልገል አጋጣሚዎችን እንፈልጋለን። እንደ እርሱ፣ “መልካም [እያደረግን]” (ሐዋ. 10፡38) መዞር አለብን። በማህበረሰባችን ውስጥ ጎረቤቶቻችንን እና ሌሎች እናገለግላለን። በJustServe በኩል የአገልግሎት አጋጣሚዎች ካሉ መሳተፍ እንችላለን። የቤተክርስቲያኗን የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ መደገፍ እና በአደጋ ጊዜ ምላሽ ላይ መሳተፍ እንችላለን።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

ሰዎች እያወሩ

ወንጌልን ማጋራት

እንደ የጥምቀት ቃል ኪዳናችን አካል፣ “የእግዚአብሔር ምስክር በመሆን” (ሞዛያ 18፡9) ለመቆም ቃል ገብተናል። እንደ ምስክር የምንቆምበት አንዱ መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በማካፈል ነው። ሌሎች ወንጌልን እንዲቀበሉ መርዳት ልንሰጣቸው ከምንችላቸው በጣም አስደሳች የአገልግሎት ዓይነቶች አንዱ ነው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 18፡15–16 ተመልከቱ)። የፍቅራችንን ሃይለኛ መግለጫ ነው።

ወንጌልን የመኖርን በረከቶች ስናገኝ እነዚያን በረከቶችን ለማካፈል እንፈልጋለን። ታማኝ ምሳሌ ስንሆን እና ወንጌሉ ህይወታችንን እንዴት እንደሚባርክ ሲመለከቱ የቤተሰብ አባላት፣ ጓደኞች እና የምናውቃቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ፍላጎት ያድርባቸዋል። ወንጌልን ተቀባይነት ባለው እና በተለመደ መልኩ ማካፈል እንችላለን (አጠቃላይ መመሪያ መጽሐፍምዕራፍ 23 ተመልከቱ)።

ሌሎች ከእኛ ጋር በአገልግሎት፣ በማህበረሰብ፣ በመዝናኛ እና በቤተክርስቲያን አክቲቪቲዎች እንዲሳተፉ እንጋብዛለን። ወደ ቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ወይም የጥምቀት አገልግሎት ልንጋብዛቸው እንችላለን። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የሚያብራራ ቪዲዮ እንዲመለከቱ ፣ መፅሐፈ ሞርሞንን እንዲያነቡ፣ ወይም ቤተመቅደስ ክፍት ሲሆን እንዲጎበኙ ልንጋብዛቸው እንችላለን። ሌሎች ልናቀርብላቸው የምንችላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ግብዣዎች አሉ። ብዙውን ጊዜ መጋበዝ ማለት ቤተሰባችንን፣ ጓደኞቻችንን እና ጎረቤቶቻችንን እያደረግን ባለው ነገር ውስጥ ማሳተፍ ማለት ነው

እግዚአብሔርን ከጠየቅን፣ ወንጌልን ለማካፈል እና ህይወታችንን እንዴት እንደሚባርክ ለሌሎች ለመንገር እድሎችን እንድናውቅ ይረዳናል።

የመውደድ፣ የማካፈል እና የመጋበዝ መርሆዎችን ስለመተግበር የበለጠ መረጃ ለማግኘት በምዕራፍ 9 ውስጥ ያለውን “ከአባላት ጋር ተባበሩ” የሚለውን ተመልከቱ።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ሚስዮናዊ ስራ

  • የወንጌል አርዕስቶች፥ “የሚስዮናዊ ስራ

ጾም እና የጾም ቁርባኖች/ጾም እና የጾም መስዋዕት

መንፈሳዊ ጥንካሬን የምናዳብርበት እና የተቸገሩትን የምንረዳበት መንገድ እንዲሆን እግዚአብሔር የጾም ሕግን አዘጋጅቷል።

መጾም ማለት ለተወሰነ ጊዜ ያለ መጠጥ እና ያለ ምግብ መቆየት ማለት ነው። በቤተክርስቲያኗ አብዛኛውን ጊዜ የወሩ የመጀመሪያ እሁድ የጾም ቀን ነው። የጾም ቀን ከቻልን ለ24 ሰአታት ያህል ያለ ምግብ እና ያለ መጠጥ መቆየትን ያጠቃልላል። ሌሎች የጾም እሑድ አስፈላጊ ክፍሎች ጸሎት እና ምስክርነት ናቸው። አስፈላጊ ሆኖ ሲሰማን በሌላ ጊዜም እንድንጾም እንበረታታለን።

መንፈሳዊ ጥንካሬን መገንባት

ጾም ትሁት እንድንሆን፣ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ እና በመንፈስ እንድንታደስ ይረዳናል። ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ጾሟል (ማቴዎስ 4፡1-2 ተመልከቱ)። ቅዱሳት መጻህፍት መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውን እንዲያሳድጉ እና ለራሳቸው ወይም ለሌሎች ልዩ በረከቶችን ፍለጋ ስለጾሙ ነቢያት እንዲሁም ስለሌሎች ብዙ ዘገባዎችን ይዘዋል።

ጾም እና ጸሎት የተያያዙ ናቸው። በእምነት ስንጾም እና ስንጸልይ፣ የበለጠ የግል መገለጥን መቀበል እንችላለን። እንዲሁም እውነትን ለማወቅ እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመረዳትና ለመቀበል የበለጠ እንችላለን።

የተቸገሩትን መርዳት

ስንጾም፣ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ለቤተክርስቲያን ገንዘብ እንለግሳለን። ይህ የጾም በኩራት በመባልም ይታወቃል። ከተጾመው ምግብ ዋጋ ጋር ቢያንስ እኩል የሆነ መባ እንድንሰጥ ተጋብዘናል። ለጋስ እንድንሆን እና ከተቻለን ከእነዚህ ምግቦች ዋጋ በላይ እንድንሰጥ እንበረታታለን። የጾም በኩራቶችን መስጠት ሌሎችን የምናገለግልበት አንዱ መንገድ ነው።

የጾም በኩራቶች በአካባቢና በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚገኙት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ምግብና ሌሎች ነገሮችን ለመስጠት በጥቅም ላይ ይውላሉ። የጾም በኩራቶች እንዴት መስጠት እንደሚቻል መረጃ ለማግኘት በዚህ ትምህርት ውስጥ “አሥራትን መስጠት እና ሌሎች መባዎችን” ተመልከቱ።

የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት

መጾም

እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መንከባከብ።

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ጾም፣ የጾም በኩራቶች

  • አጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ: 22.2.2

  • እንዲሁም የወንጌል ርዕሶች፣ “ፆም እና የፆም በኩራቶች

ቤተሰብ ከቤተመቅደስ ውጪ

እስከ መጨረሻው ለመጽናት የኛ ቃል ኪዳን

ስንጠመቅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመኖር “እስከ መጨረሻው ለመጽናት” ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን (2 ኔፊ 31፡20፤ በተጨማሪም ሞዛያ 18፡13 ተመልከቱ)። የእድሜ ልክ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንጥራለን።

የመፅሐፈ ሞርሞን ነቢይ ኔፊ ጥምቀት ወደ ወንጌል መንገድ የምንገባበት በር እንደሆነ ገልጿል (2 ኔፊ 31፡17 ተመልከቱ)። ከጥምቀት በኋላ “በክርስቶስ [ባለን] ፅኑነት [እንቀጥላለን]” (2 ኔፊ 31፥20)።

በደቀመዝሙርነት መንገድ ላይ “[ስንቀጥል]” ወደ ቤተመቅደስ ለመሄድ እንዘጋጃለን። የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን ስንቀበል እዚያ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን። በቤተመቅደስ ውስጥ ሀይል እንቀበላለን፣ እንደ ቤተሰብም ለዘለአለም ልንታተም እንችላለን። በቤተመቅደስ ውስጥ የምንገባቸውን ቃል ኪዳኖች መጠበቅ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን እያንዳንዱን መንፈሳዊ እድል እና በረከት በር ይከፍታል።

በወንጌል መንገድ በታማኝነት ስንቀጥል፣ የእግዚአብሔርን ትልቁን ስጦታ—የዘላለም ህይወት ስጦታን እንቀበላለን (2 ኔፊ 31፡20ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14፡7 ተመልከቱ)።

የሚከተሉት ክፍሎች በምድራዊ ጉዟችን እስከ መጨረሻው ድረስ እንድንጸናና በዚህም ደስተኞች እንድንሆን እግዚአብሄር የሰጠንን አንዳንድ ነገሮችን ያብራራሉ።

ክህነት እና የቤተክርስቲያን አደረጃጀት

ክህነት የእግዚያብሔር ሃይል እና ስልጣን ነው። በክህነት በኩል የሰማይ አባት “የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት [የ]ማምጣት” (ሙሴ 1፥39) ስራውን ይፈጽማል። እግዚአብሔር በምድር ላይ ላሉ ወንድና ሴት ልጆቹ ይህን ሥራ እንዲያከናውኑ ሥልጣንን እና ኃይልን ይሰጣል።

ክህነት ሁላችንንም ይባርካል። እንደ ጥምቀት እና ቅዱስ ቁርባን ያሉ ሥርዓቶች የሚከናወኑት ክህነት በያዙ ሰዎች ነው። የፈውስ፣ የመጽናናት እና የምክር በረከቶችንም እንቀበላለን።

የክህነት እና የቤተክርስቲያን አመራር እና ጥሪዎች

ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በነቢያትና በሐዋርያት ነው። እነዚህ መሪዎች በእግዚአብሔር የተጠሩ፣ የተሾሙ እና በአዳኙ ስም እንዲሰሩ የክህነት ስልጣን የተሰጣቸው ናቸው።

በጥንት ጊዜ፣ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ቤተክርስቲያኗን እንዲመሩ የሚያስችላቸውን ይህንኑ የክህነት ስልጣን ለሐዋርያቱ ሰጥቷቸዋል። በኋላም ሰዎች ወንጌልን ሲቃወሙ እና ሐዋርያት ሲሞቱ ያ ስልጣን ተወሰደ።

የሰማይ መልእክተኞች በ1829 (እ.አ.አ) ክህነትን በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል መለሱ እንዲሁም ጌታ ዳግም ቤተክርስቲያኑን በሐዋርያት እና በነቢያት አቋቋመ። (ትምህርት 1 ን ተመልከቱ።)

በአካባቢ ደረጃ፣ ኤጲስ ቆጶሶች እና የካስማ ፕሬዘዳንቶች የቤተክርስቲያን ጉባኤዎችን የመምራት የክህነት ስልጣን አላቸው።

ወንዶች እና ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል ሲጠሩ እና ሲለዩ፣ በዚያ ጥሪ ውስጥ እንዲሰሩ ከእግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ይህ ስልጣን ሚስዮናውያን፣ መሪዎች፣ አስተማሪዎች እና ሌሎች ከጥሪያቸው እስኪሸኙ ድረስ ይሰጣቸዋል። የክህነት ቁልፎችን በያዙ ሰዎች መሪነት ይወከላል።

የክህነት ስልጣን በጽድቅ ብቻ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፡34–46 ተመልከቱ)። ይህ ስልጣን አዳኙን ለመወከል እና በስሙ ለሚሰራት የተቀደሰ አደራ ነው። ሁልጊዜ ሌሎችን እንዲባርክ እና እንዲያገለግል የታሰበ ነው።

ወጣት ወንዶች በሰንበት ትምህርት ቤት

የአሮናዊ እና የመልከ ጼዴቅ ክህነት

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ፣ ክህነት የአሮናዊ እና የመልከ ጼዴቅ ክህነትን ያካትታል። የክህነት ቁልፎችን በያዙ ሰዎች አመራር ስር፣ የአሮናዊ እና የመልከ ጼዴቅ ክህነት ብቁ ለሆኑ ወንድ የቤተክርስቲያን አባላት ይሰጣሉ። ተገቢው ክህነት ከተሰጠ በኋላ፣ ያ ግለሰብ በዚያ የክህነት አገልግሎት እንደ ዲያቆን ወይም ሽማግሌ ይሾማል። አስፈላጊው ሥልጣን ባለው ሰው መሾም አለበት።

አንድ ወንድ ወይም ወጣት ክህነትን ሲቀበል፣ የተቀደሱ ተግባራትን ለመፈጸም፣ ሌሎችን ለማገልገል እና ቤተክርስቲያንን በመገንባት ለመርዳት ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ይገባል።

ወንዶች የአሮናዊ ክህነት ሥልጣንን መቀበል እና ዲያቆናት እንዲሆኑ12 አመት በሚሞላቸው ጥር ጀምሮ ሊሾሙ ይችላሉ። 14 በሚሆናቸው ዓመት አስተማሪዎች፣ 16 ዓመት በሚሆናቸው ዓመት ደግሞ ካህናት ሆነው ሊሾሙ ይችላሉ። በዕድሜ ከፍ ያሉ ወንዶች ከተጠመቁ እና ማረጋገጫን ከተቀበሉ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ የአሮናዊ ክህነት ሊቀበሉ ይችላሉ። የአሮናዊ ክህነት ተሸካሚዎች እንደ ቅዱስ ቁርባን እና ጥምቀት ያሉ ሥርዓቶችን ያካሂዳሉ።

ለተወሰነ ጊዜ በአሮናዊ ክህነት ካገለገሉ በኋላ፣ ቢያንስ 18 የሆናቸው ብቁ ወንዶች የመልከ ጼዴቅን ክህነት በመቀበል ሽማግሌ ሊባሉ ይችላል። የመልከ ጼዴቅን ክህነት የተቀበሉ ወንዶች እንደ ፈውስና ማጽናኛ ያሉ በረከቶችን ለቤተሰብ አባላት እና ለሌሎች መስጠትን የመሳሰሉ የክህነት ሥርዓቶችን ማከናወን ይችላሉ።

ክህነትን ስለሚቀበሉ አዳዲስ አባላት መረጃ ለማግኘት አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ38.2.9.1 ተመልከቱ።

ምልአተ ጉባኤዎች እና የቤተክርስቲያን አደረጃጀቶች

የክህነት ምልአተ ጉባኤ ምልአተ ጉባኤ የተደራጀ የክህነት ተሸካሚዎች ቡድን ነው። እያንዳንዱ አጥቢያ ለአዋቂ ወንዶች የሽማግሌዎች ምልአተ ጉባኤ ስብስብ አለው። ዲያቆናት፣ አስተማሪዎች እና የካህናት ምልአተ ጉባኤዎች ለታዳጊ ወጣቶች ናቸው።

የሴቶች መረዳጃ ማህበር የሴቶች መረዳጃ ማህበር እድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶችን ያካትታል። የሴቶች መረዳጃ ማህበር አባላት ቤተሰቦችን፣ ግለሰቦችን እና ማህበረሰቡን ያጠናክራሉ።

ወጣት ሴቶች ወጣት ሴቶች 12 ዓመት ሲሞላቸው ከጥር ወር ጀምሮ የወጣት ሴቶችን ድርጅት ይቀላቀላሉ።

አንዲት ሴት እያስተማረች

የህጻናት ክፍል። ከ3 እስከ 11 አመት ያላቸው ልጆች ሁሉ በመጀመሪያ ክፍል ድርጅት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው።

የሰንበት ትምህርት ቤት ሁሉም አዋቂቆች እና ወጣቶች ሰንበት ትምህርት ቤት አብረው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠናሉ።

ስለ ክህነት ተጨማሪ መረጃን ከአጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍመዕራፍ 3 ተመልከቱ)።

ስለ ክህነት ምልአተ ጉባኤዎች እና የቤተክርስቲያን ድርጅቶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ከ አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍመዕራፍ 8-13 ተመልከቱ።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • አጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ , “የክህነት መርሆች

  • የወንጌል አርእስት “አሮናዊ ክህነት”፣”የመልከ ጼዴቅ ክህነት” “ክህነት

ጋብቻ እና ቤተሰቦች

ጋብቻ

በወንድ እና በሴት መካከል የሚደረግ ጋብቻ በእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። ለልጆቹ ዘላለማዊ እድገት የእርሱ እቅድ ዋና አካል ነው።

በጋብቻ ውስጥ የባልና የሚስት ጥምረት በጣም የተወደደ ምድራዊ ግንኙነነታቸው መሆን አለበት። አንዳቸው ለሌላው እንዲሁም ለትዳራቸው ቃል ኪዳን ታማኝ የመሆን ቅዱስ ሀላፊነት አለባቸው።

ባልና ሚስት በእግዚአብሔር ዓይን እኩል ናቸው። አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ሊሆን አይገባም። ውሳኔዎቻቸው በአንድነትና በፍቅር በሁለቱ ሙሉ ተሳትፎ መሆን አለበት።

ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ሲዋደዱ እና አብረው ሲሰሩ፣ ትዳራቸው የደስታ ምንጭ ሊሆን ይችላል። አንዳቸው ሌላቸውን እንዲሁም ልጆቻቸው ወደ ዘላለማዊ ህይወት እንዲያድጉ መርዳት ይችላሉ።

ቤተሰብ

ልክ እንደ ጋብቻ፣ ቤተሰብም በእግዚአብሔር የተቀደሰ እና ለዘላለማዊ ደስታችን የእሱ እቅድ ዋና አካል ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ስንኖር ቤተሰቦቻችን ደስተኞች የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ያስተምራሉ እናም በመኖር ምሳሌ ይሆናሉ። ቤተሰቦች እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እና እንድናገለግል እድሎችን ይሰጡናል።

ወላጆች ለቤተሰባቸው ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለባቸው። ወላጆች ሊወልዷቸው ወይም በማደጎ ሊያሳድጓቸው የሚችሏቸውን ልጆች መንከባከብ የተቀደሰ ዕድል እና ኃላፊነት ነው።

ሁሉም ቤተሰብ ፈተና አለበት። የእግዚአብሔርን ድጋፍ ስንፈልግ እና ትእዛዛቱን ስንጠብቅ፣ የቤተሰብ ፈተናዎች እንድንማር እና እንድናድግ ሊረዱን ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ፈተናዎች ንስሐ መግባትን እና ይቅር ማለትን እንድንማር ይረዱናል።

አባት ቤተሰብን ሲያስተምር

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባላት ሳምንታዊ የቤተሰብ ምሽት እንደያዘጋጁ አበረታተዋል። ወላጆች ይህን ጊዜ ልጆቻቸውን ወንጌል ለማስተማር፣ ከእነርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናክር፣ እና አብረው ለመደሰት ይጠቀማሉ። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለቤተሰብ ጠቃሚ እውነቶችን የሚያስተምር አዋጅ አውጥተዋል (“ቤተሰብ: ለአለም የተላለፈ አዋጅ” ChurchofJesusChrist.org ላይ ተመልከቱ)።

ቤተሰብን ለማጠናከር የሚረዱ ሌሎች መንገዶች የቤተሰብ ጸሎት፣ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት እና በቤተክርስቲያን በአንድነት ማምለክን ያካትታሉ። እንዲሁም የቤተሰብ ታሪክን ማጥናት፣ የቤተሰብ ታሪኮችን መሰብሰብ እና ሌሎችን ማገልገል እንችላለን።

ብዙ ሰዎች ለትዳር ወይም በፍቅር ለተሞላ የቤተሰብ ግንኙነቶች እድላቸው ውስን ነው። ብዙዎች ፍቺና ሌሎች አስቸጋሪ የቤተሰብ ሁኔታዎች አጋጥሟቸዋል። ሆኖም ግን፣ የቤተሰባችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ወንጌል በግለሰብ ደረጃ ይባርከናል። እናም ታማኝ በመሆን ስንቀጥል፣ በዚህም ሆነ በሚመጣው ህይወት የአፍቃሪ ቤተሰቦችን በረከት የምናገኝበትን መንገድ እግዚአብሄር ያዘጋጃል።

የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት

ጋብቻ

ቤተሰብ

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ፣ “ቤተሰብ፣ “ጋብቻ

  • General Handbook, chapter 2: “Supporting Individuals and Families in the Work of Salvation and Exaltation

  • የወንጌል ርዕሶች “ጋብቻ፣” “ቤተሰብ”“ልጆችን ማሳደግ

ቤተመቅደስ እና ለሟች ቅድመ አያቶች የቤተሰብ ታሪክ ስራ

የሰማይ አባት ልጆቹን ሁሉ ስለሚወዳቸው መዳናቸውን እና ከፍ ከፍ መደረጋቸውን ይፈልጋል። ሆኖም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሳይሰሙ ወይም የወንጌልን የማዳን ሥርዓቶች ሳይቀበሉ ሞተዋል። እነዚህ ሥርዓቶች ጥምቀትን፣ ማረጋገጫን፣ ለወንዶች የሚሰጡ የክህነት ሹመትን፣ የቤተመቅደስ ቡራኬን እና የዘላለም ጋብቻን ያካትታሉ።

ጌታ በጸጋውና በምሕረቱ እነዚህ ሰዎች ወንጌልን እና ሥርዓቶቹን የሚቀበሉበትን ሌላ መንገድ አዘጋጅቷል። በመንፈስ ዓለም፣ ወንጌልን ሳይቀበሉ ለሞቱት ይሰበካል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 138 ተመልከቱ)። በቤተመቅደስ ውስጥ፣ በሞቱ ቅድመ አያቶቻችን እና በሌሎች ስም ሥርአቶቹን መፈጸም እንችላለን። እነዚህ በመንፈስ ዓለም ውስጥ ያሉ የሞቱ ሰዎች ወንጌልን እና ለእነሱ የተደረገላቸውን ሥርዓቶች መቀበል ወይም አለመቀበል ይችላሉ።

ቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍትን እያጠኑ

እነዚህን ሥርዓቶች ከመፈጸማችሁ በፊት፣ ሥርዓቶቹን ያልተቀበሉ ቅድመ አያቶቻችንን መለየት አለብን። ሥርዓቱን ይቀበሉ ዘንድ የቤተሰባችንን አባላት መለየት የቤተሰብ ታሪክ ስራችን ዋና አላማ ነው። ስለእነሱ መረጃ ስናገኝ፣ በFamilySearch.org ላይ ወደ ቤተክርስቲያን ዳታ ቤዝ እንጨምራለን። ከዚያ እኛ (ወይም ሌሎች) በቤተመቅደስ ውስጥ የውክልና ሥርዓቶችን ልናከናውንላቸው እንችላለን።

ቅድመ አያቶቻችንን ስንለይ እና ሥርዓቶችን ስንፈጽም ቤተሰቦቻችን ለዘለአለም አንድ ሊሆኑ ይችላሉ።

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • አጠቃላይ መመሪያ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 28፡ “ለሙታን የሚደረጉ የቤተመቅደስ ሥርዓቶች

  • የወንጌል ርዕሶች፣ “ለሙታን ጥምቀት፣” “የቤተሰብ ታሪክን ተመልከቱ።

ቤተመቅደሶች፣ ቡራኬ፣ ዘላለማዊ ጋብቻ እና ዘላለማዊ ቤተሰብ

ቤተመቅደሶች

ቤተመቅደስ የጌታ ቤት ነው። የእርሱን ቅዱስ ሥርዓቶች ስንቀበል ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን የምንገባበት ቅዱስ ቦታ ነው። እነዚህን ቃል ኪዳኖች ስንጠብቅ፣ እግዚአብሔርን የመምሰል ኃይል በህይወታችን ይገለጣል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፡19–22109፡22–23 ተመልከቱ)።

ቡራኬ

ከቤተመቅደስ ሥርአቶች መካከል አንዱ የቤተመቅደስ ቡራኬ ነው። ቡራኬ የሚለው ቃል “ስጦታ” ማለት ነው። ይህ የእውቀት እና የሃይል ስጦታ የሚመጣው ከእግዚአብሔር ነው። በቡራኬ ወቅት፣ ከእግዚአብሔር እና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያስተሳስረንን ቃል ኪዳን እንገባለን (ምዕራፍ 1ን ተመልከቱ)።

አዋቂዎች ቢያንስ ከአንድ አመት የቤተክርስቲያኑ አባልነት በኋላ የራሳቸውን የቤተመቅደስ ቡራኬ ለማግኘት ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለ ቡራኬ የበለጠ መረጃ ለማግኘት አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ27.2 ተመልከቱ።

ዘላለማዊ ጋብቻ እና ዘላለማዊ ቤተሰብ

የእግዚአብሔር የደስታ እቅድ የቤተሰብ ግንኙነቶች ከመቃብር በላይ እንዲጸኑ ያስችላቸዋል። በቤተመቅደስ ውስጥ ለጊዜው እና ለዘለአለም ልንጋባ እንችላለን። ይህም ቤተሰቦች ለዘለዓለም አንድ ላይ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

ባለትዳሮች የቤተመቅደስ ቡራኬያቸውን ከተቀበሉ በኋላ፣ ለዘለአለም ሊታተሙ ወይም ሊጋቡ ይችላሉ። ልጆቻቸውም ሊታተሙ ይችላሉ።

በቤተመቅደስ ውስጥ የታተሙ ባል እና ሚስት የዘላለም ጋብቻን በረከት ለማግኘት የገቡትን ቃል ኪዳኖች መጠበቅ አለባቸው።

ጥንዶች በመንገድ ላይ እየሄዱ

የቅዱስ መጽሀፍ ጥናት

ስለዚህ መርህ የበለጠ ተማሩ

  • አጠቃላይ መመሪያ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 27፡ “በሕያዋን የሚደረጉ የቤተ መቅደስ ሥርዓቶች

  • የወንጌል ርዕሶች “ቤተ መቅደሶች፣” “ቡራኬ” “ጋብቻ

  • temples.churchofjesuschrist.org