መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እና ኢኒስቲትዩት
ትምህርቱን አስተምሩ


“ትምህርቱን አስተምሩ፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር፦ በቤት እና በቤተክርስቲያን ለሚያስተምሩ ሁሉ [2022 (እ.አ.አ)]

“ትምህርቱን አስተምሩ፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር

ትምህርቱን አስተምሩ

ምንም እንኳን ኢየሱስ ሕይወቱን ሙሉ በጥበብ እና በእውቀት ቢያድግም፣ በእርሱ ዘመን እንደነበሩት ሌሎች የሐይማኖት መሪዎች የተማረ አልነበረም። ሆኖም እርሱ ሲያስተምር ሰዎች “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” በማለት ተገርመዋል። የእርሱ ትምህርቶች በጣም ኃይለኛ የነበሩት ለምን ነበር? አዳኙ “ትምህርቴ ከላከኝ ነው እንጂ” “ከእኔ አይደለም” በማለት ገልጿል (ዮሃንስ 7:15–16)። ትምህርት እንደሰማይ አባታችን እንድንሆን እና ወደ እርሱ እንድንመለስ መንገዱን የሚያሳየን፣ በቅዱሳት መጻህፍት እና በኋለኛው ቀን ነቢያት ቃላት ውስጥ የሚገኝ ዘላለማዊ እውነት ነው። የአስተማሪነት ልምድ ኖራችሁም አልኖራችሁ፣ የአብን ትምህርት በማስተማር አዳኙ እንዳደረገው በኃይል ማስተማር ትችላላችሁ። የመማር ማስተማር ዘይቤያችሁ በእርሱ ቃል ላይ ሲመሰረት እናንተ እና የምታስተምሯቸው ሰዎች እግዚአብሔር በሚልከው በረከቶች ትገረማላችሁ።

ትምህርቱን አስተምሩ

  • የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ለራሳችሁ ተማሩ።

  • ከቅዱሳት መጻህፍትና ከኋለኛው ቀን ነቢያት ንግግሮች አስተምሩ።

  • ተማሪዎች ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲሹ፣ እንዲያውቁ እና ውስጡ ያሉትን እውነቶች እንዲረዱ አግዟቸው።

  • ወደ መለወጥ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነትን ወደመገንባት በሚመሩ እውነቶች ላይ አተኩሩ።

  • ተማሪዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮት ውስጥ ከነሱ ጋር የግል ዝምድና ያለውን ነገር እንዲያገኙ አግዙ።

አዳኙ ትምህርቱን ተማረ

አዳኙ በወጣትነቱ “በጥበብ … እና በእግዚአብሔር ሞገስ” ሲያድግ ከቅዱሳት መጻህፍት እንደተማረ ግልፅ ይመስላል (ሉቃስ 2፥52)። የእርሱ የአብን ትምህርት በጥልቅ መረዳት ግልፅ የሆነው ወላጆቹ በጨቅላ እድሜው በቤተመቅደስ ውስጥ የአይሁዶች አስተማሪዎችን ሲያስተምር እና ጥያቄያቸውን ሲመልስ ሲያገኙት ነበር ( የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም፣ ሉቃስ 2፥46 [በ ሉቃስ 2፥46፣ የግርጌ ፅሁፍ ])። በኋላም፣ ሰይጣን በምድረ በዳ ከባድ የሆነ ፈተና ሲያቀርብለት፣ ኢየሱስ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ያለው ትምህርት እውቀቱ ፈተናውን እንዲቋቋም ረድቶታል (ሉቃስ 4፥3-12ይመልከቱ)።

እናንተም እውነተኛ ትምህርትን ከማስተማራችሁ በፊት የበለጠ በጥልቀት እንድታውቁት መሻት ትችላላችሁ። ሌሎችን ለማስተማር እንዲሁም ከሌሎች ለመማር ስትዘጋጁ፣ ጌታ ስለምታስተምሯቸው እውነቶች የተናገረውን በጥንቃቄ ተመልከቱ። ማብራሪያ እና ምክር ለማግኘት በቅዱሳት መጻህፍት እና በሕያው ነብያት ቃላት ውስጥ ፈልጉ። የምታጠኗቸውን እውነቶች መኖር እና መተግበር ትምህርትን ጥልቅ በሆነ ሁኔታ ሊያስተምራችሁ እና የትምህርቱን እውነተኝነት በምታስተምሯቸው ሰዎች ልብ ውስጥ ሊያረጋግጥ መንፈስን ይጋብዛል።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ የወንጌልን እውነቶች በራሳችሁ መረዳት የሚያስፈልጋችሁ ለምንድን ነው? የወንጌልን እውነቶች ጥልቅ መረዳት ያገኛችሁት እንዴት ነው? የቅዱሳት መጻህፍትን እና በሕይወት ያሉ ነቢያት ቃላት ጥናታችሁን ለማሻሻል ምን ለማድረግ መነሳሳት ይሰማችኋል?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ መጽሐፈ ምሳሌ 7፥1–32 ኛ ኔፊ 4፥15–16ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11፥2188፥118

አዳኙ ከቅዱሳት መጻህፍት አስተማረ

ከአዳኙ ሞት በኋላ ሁለት የእርሱ ደቀመዛሙርት ልባቸው በሃዘን እና በመገረም ተሞልቶ እየተራመዱ እና እየተነጋገሩ ነበር። ስለተከሰተው ነገር እንዴት ሊረዱ ይችላሉ? ቤዛቸው እንደሆነ ያመኑት ሰው፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ከሞተ ሶስት ቀናት ሆነው። ከዚያ በኋላም መቃብሩ ባዶ እንደሆነ የሚገልጽ ዘገባ መጣ መላዕክትም በሕይወት እንዳለ ተናገሩ። በእነዚህ ደቀመዛሙርት የእምነታቸው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ አንድ እንግዳ በጉዞአቸው ላይ ተቀላቀለ። “በመጻህፍት ሁሉ [ስለአዳኙ] የተጻፈውን [በመተርጎም]” አፅናናቸው። መጨረሻ ላይ ተጓዦቹ አስተማሪያቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነበረ እና በእርግጥ ከሞት እንደተነሳ ተገነዘቡ። እንዴት ነው ያወቁት? “በመንገድ ሲናገረን መጻህፍትንም ሲከፍትልን” “ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” በማለት አገናዘቡ። (ሉቃስ 24፥27፣ 32)።

ሽማግሌ ዲ. ታድ ክርስቶፈርሰን እንዲህ አስተምረዋል፣ “የሁሉም ቅዱሳት መጻህፍት ማዕከላዊ አላማ በእግዚአብሔር አብ እና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ነፍሳችንን መሙላት ነው” (“The Blessing of Scripture፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2010 (እ.አ.አ)፣ 34)። በመላው አገልግሎቱ ውስጥ ኢየሱስ ሌሎችን ለማስተማር፣ ለማረም እና ለማነሳሳት ቅዱሳት መጻህፍትን ተጠቅሟል። ትምህርታችሁ ከቅዱሳት መጻህፍት እና ከነቢያት ቃላት እንዳያፈነግጥ ተጠንቀቁ። በምታስተምሩበት ጊዜ በእግዚአብሔር ቃላት ላይ በእምነት ስትደገፉ አዳኙ ያደረገውን ለሌሎች ማድረግ ትችላላችሁ። እርሱን እንዲያውቁት ልትረዷቸው ትችላላችሁ ምክንያቱም እኛ ሁላችንም በአዳኙ ላይ ያለን እምነት ሁልጊዜ ጠንካራ እንዲሆን ያስፈልጋል። ለቅዱሳት መጻህፍት ያላችሁ ፍቅር ለምታስተምሯቸው ሰዎች ግልፅ ይሆናል፣ እንዲሁም ትምህርታችሁ በአብ እና በወልድ ምስክርነት ልባቸው እንዲቃጠል መንፈስን ይጋብዛል።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ አዳኙን የበለጠ እንድታውቁት ለመርዳት ቅዱሳት መጻህፍትን የተጠቀመ አስተማሪ ተፅዕኖ ያሳደረባችሁ እንዴት ነው? ስታስተምሩ የበለጠ በቅዱሳት መጻህፍት እና በነቢያት ቃላት ላይ ለመሞርከዝ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የምታስተምሯቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያውቁ እና እንዲወዱ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ሉቃስ 4፥14–21አልማ 31፥5ሔለማን 3፥29–303 ኛ ኔፊ 23

አዳኙ ሰዎች እውነትን እንዲሹ፣ እንዲገነዘቡ እና እንዲረዱ አግዟል

አንድ ህግ አዋቂ ኢየሱስን፣ “መምህር፣ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው። በምላሹ፣ አዳኙ ጠያቂውን ወደ ቅዱሳት መጻህፍት መራው፦ “በህግ የተፃፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነባለህ?” ይህ ሰውዬውን “ጌታ አምላክህን … ባልንጀራህን በፍፁም ነፍስህ ውደድ” ወደሚለው መልስ ብቻ ሳይሆን የመራው ነገር ግን “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” ወደሚል ቀጣይ ጥያቄም ነበር። አዳኙ ይህን ጥያቄ አንድ እርዳታ የሚፈልግን ተጓዥ ስለተመለከቱ ሶስት ሰዎች ምሳሌ በመናገር መለሰ። በመጣበት ቦታ ምክንያት ብቻ በአይሁዶች የተጠላው ከሶስቱ አንዱ የሆነው ሳምራዊ ለመርዳት ቆመ። ከዚያም ኢየሱስ ህግ አዋቂውን የራሱን ጥያቄ እንዲመልስ ጋበዘው፦ “ከሶስቱ [ለእርሱ]ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል” ( ሉቃስ 10፥25–37)።

አዳኙ ለቀረቡለት ጥያቄዎች እንዲመረምሩ፣ እንዲያሰላስሉ እና እንዲያገኙ በመጋበዝ መልስ እየሰጠ ያስተማረው ለምን ይመስላችኋል? ጌታ እውነትን ለመሻት ለሚደረግ ጥረት ቦታ ስለሚሰጥ ነው የሚለው የመልሱ አካል ነው። “ፈልጉ ታገኙማላችሁ” በማለት በተደጋጋሚ ጋብዟል (ለምሳሌ ማቴዎስ 7፥7ሉቃስ 11፥9ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 4፥7ይመልከቱ)። የፈላጊውን የእምነት ተግባር እና ትዕግስት ይሸልማል።

ልክ እንደ አዳኙ የምታስተምሯቸው ሰዎች እውነትን እንዲገነዘቡ እና እንዲረዱ መርዳት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ቅዱሳት መጻህፍት በወንጌል እውነቶች የተሞሉ ናቸው፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እነሱን ለማግኘት የታሰበበት ጥረትን ይጠይቃል። ከቅዱሳት መጻህፍት አብራችሁ እየተማራችሁ በመሆኑ ቆም ብላችሁ የምታስተምሯቸው ሰዎች ልብ ስላሏቸው የወንጌል እውነቶች ጠይቋቸው። እነዚህ እውነቶች ከሰማይ አባት የደህንነት ዕቅድ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ እንዲመለከቱ እርዷቸው። አንዳንድ ጊዜ ዘላለማዊ እውነቶች በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ተገልጸዋል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምናነባቸው የሰዎች ታሪኮች እና ሕይወቶች ውስጥ ይታያሉ። ስለምታነቧቸው ጥቅሶች ታሪካዊ አመጣጥ እና ትርጉም በጋራ ማሰስ እና ዛሬ ለእኛ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆኑ መፈለግ ሊረዳ ይችላል።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ በቅዱሳት መጻህፍት ወይም በነብያት ቃላት ውስጥ ያሉትን ዘላለማዊ እውነቶች እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ? እነዚያ እውነቶች ሕይወታችሁን እየባረኩ ያሉት እንዴት ነው? ተማሪዎች ለእነሱ ትርጉም ያላቸውን እውነቶች እንዲገነዘቡ እና እንዲረዱ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር የበለጠ እንዲቀርቡ የምትረዱባቸው የተወሰኑ መንገዶች ምን ምን ናቸው?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ ዮሐንስ 5፥391 ኛ ኔፊ 15፥14ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥12

ምስል
ተማሪዎች ሲያጠኑ

የምናስተምራቸው ሰዎች እውነትን ራሳቸው እንዲያገኙ እና እንዲገነዘቡ መርዳት እንችላለን።

አዳኙ ወደ መለወጥ እና እምነትን ወደመገንባት የሚመሩ እውነቶችን አስተማረ

አንድ የሰንበት ቀን፣ አዳኙ እና ደቀ መዛሙርቱ ተርበው በሆነ ማሳ አጠገብ እየሄዱ ሳለ እሸት ቀጥፈው መብላት ጀመሩ። ፈሪሳውያን ሁሌም በሙሴ ህግ ጥቃቅን ዝርዝሮች ላይ ለማተኮር ስለሚጓጉ በሰንበት ቀን ሰብል መሰብሰብ እንደስራ እደሚቆጠር እና እንደተከለከለ ተናገሩ (ማርቆስ 2፥23–24 ይመልከቱ)። የመጽሐፈ ሞርሞን ነብይ የሆነውን የያዕቆብን ቃላት ለመጠቀም፣ ፈሪሳውያን “ከሚገባው በላይ እያተኮሩ” ነበር (ያዕቆብ 4፥14)። በሌላ አነጋገር፣ በባህላዊ የትዕዛዛት አተረጓጎም ላይ በጣም በማተኮራቸው ምክንያት የእነዚያን ትዕዛዛት እኛን ወደ እግዚአብሔር የማቅረብ መለኮታዊ ዓላማ ስተው ነበር። በእርግጥ፣ ሰንበትን እንዲያከብሩ ትዕዛዝ የሰጠው ሰው ከፊታቸው እንዳለ እንኳን ፈሪሳውያን አልተገነዘቡም ነበር።

አዳኙ ስለመለኮታዊ ማንነቱ ለመመስከር እና ሰንበት ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ለማስተማር ይህን ዕድል ተጠቀሟል። የሰንበት ጌታ የሆነውን እራሱን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናመልክበት ለኛ የተፈጠረ ቀን ነው (ማርቆስ 2፥27–28ይመልከቱ)። እንደዚ ዓይነት እውነቶች የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ከውጫዊ ባህሪያችን የበለጡ እንደሆኑ እንድንረዳ ያግዙናል። የታቀዱት ልባችንን እንድንቀይር እና የበለጠ የተለወጥን እንድንሆን እንዲረዱን ነው።

ለማተኮር የወሰናችሁትን ትምህርት እና መርሆዎች በጥንቃቄ አስቡ። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ውይይት ሊደረግባቸው የሚችሉ ብዙ እውነቶች ቢኖሩም፣ ወደ መለወጥ እና እምነትን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ወደመገንባት በሚያመሩ የወንጌል እውነታዎች ላይ ማተኮር የተሻለ ነው። አዳኙ ያስተማራቸው እና በምሳሌ ያሳያቸው ቀላሎቹ መሰረታዊ እውነቶች ሕይወታችንን የመቀየር ታላቅ ኃይል አላቸው፤ እነሱም የሃጢያት ክፍያው፣ የደህንነት ዕቅድ፣ እግዚአብሔርን እና ባልንጀራችንን የመውደድ ትዕዛዛት እና የመሳሰሉት እውነቶች ናቸው። በምታስተምሯቸው ሰዎች ልቦች ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ እንዲረዳቸው ስለእነዚህን እውነቶች እንዲመሰክር መንፈስን ጋብዙ።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ እንድትለወጡ እና በእርሱ ታላቅ እምነት እንዲኖራችሁ የረዷችሁ አንዳንድ የወንጌል እውነቶች ምን ምን ናቸው? አንድ አስተማሪ በወንጌል በጣም ወሳኝ እውነቶች ላይ እንድታተኩሩ የረዳችሁ እንዴት ነው? ሌሎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ በጥልቅ እንዲለወጡ የሚረዳቸውን ምን ማስተማር ትችላላችሁ?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ 2 ኛ ኔፊ 25፥263 ኛ ኔፊ 11፥34–41ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥31–3268፥25–28133፥57ሙሴ 6፥57–62

አዳኙ፣ ሰዎች በትምህርቱ ውስጥ ከነሱ ጋር የግል ዝምድና ያለውን ነገር እንዲያገኙ አግዟል

“ይህስ ሃጢያተኞችን ይቀበላል ከእነሱም ጋር ይበላል” ሲሉ ፈሪሳውያን በኢየሱስ ላይ ቅሬታቸውን አቀረቡ—ከአንድ መንፈሳዊ አስተማሪ የሚጠበቅ ተገቢ ባህሪ እንዳልሆነ በመግለፅ ማለት ነው (ሉቃስ 15፥2)። ኢየሱስ ይህ ኃይለኛ መንፈሳዊ እውነቶችን የማስተማሪያ እድል እንደሆነ ተመለከተ። ይህን እንዴት ያድርገው? ንፁህ ያልሆነው እና ፈውስን የሚሻው የእርሱ ሳይሆን የእነሱ ልብ እንደነበር እንዲያዩ ፊረሳውያንን እንዴት ይርዳቸው? አስተሳሰባቸው እና ባህሪያቸው መለወጥ እንዳለበት እንዲያሳያቸው የእርሱን ትምህርት እንዴት ይጠቀም?

ይህን ያደረገው ከመንጋው ስለጠፋ አንድ በግ እና ስለጠፋ አንድ የብር መሐለቅ ለእነሱ በመንገር ነበር። ይቅርታን ስለፈለገ ዓመፀኛ ልጅ እና እሱን ለመቀበል ወይም አብሮት ለመብላት አሻፈረኝ ስላለ ታላቅ ወንድም ተናገረ። እያንዳንዱ እነዚህ ምሳሌዎች እያንዳንዱ ነፍስ ትልቅ ዋጋ እንዳለው በማስተማር ፈሪሳውያን ሌሎችን ከሚመለከቱበት መንገድ ጋር የተያያዙ እውነቶችን ይዘዋል (ሉቃስ 15)። አዳኙ በምሳሌው ካሉት ውስጥ ከማን ጋር መመሳሰል እንደሚገባ ለፈሪሳውያን ወይም ለእኛ አልነገረንም። አንዳንድ ጊዜ እኛ እንደተጨነቀው አባት ነን። አንዳንድ ጊዜ እኛ እንደተጨነቀው ወንድም ነን። ብዙ ጊዜ እኛ እንደጠፋው በግ ወይም እንደ ሞኙ ልጅ ነን። ነገር ግን ሁኔታዎቻችን ምንም ይሁኑ ምን በምሳሌዎቹ አማካኝነት ከትምህርቶቹ ምን እንድንማር እንደሚፈልግ ወይም ከአስተሳሰባችን እና ከባህሪያችን ምን መቀየር እንዳለብን ማግኘት እንችል ዘንድ ከእኛ ጋር የሚዛመዱ ነገሮችን እንድናገኝ አዳኙ ይጋብዘናል።

የተወሰኑ ተማሪዎች የተወሰኑ እውነቶች ለምን ለእነሱ አስፈላጊ እንደሆኑ እንደማይመለከቱ ልታስተውሉ ትችላላችሁ። የምታስተምሯቸውን ሰዎች ፍላጎት ስታስቡ፣ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ያሉት እውነቶች በሁኔታዎቻቸው ውስጥ እንዴት ትርጉም እንደሚሰጡ እና ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስቡ። ተማሪዎች የሚያገኟቸውን እውነቶች አግባብነት እንዲመለከቱ የምታግዙበት አንደኛው መንገድ እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን በመጠየቅ ነው “ይሄ አሁን ባጋጠማችሁ ነገር ላይ እንዴት ሊረዳችሁ ይችላል?” “ይህንን ማወቅ ለእናንተ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?” “ይህ በሕይወታችሁ ውስጥ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?” የምታስተምሯቸውን ሰዎች አድምጡ። ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ ፍቀዱላቸው። በአዳኙ ትምህርቶች እና በሕይወታቸው መካከል ግንኙነትን እንዲያደርጉ አበረታቷቸው። በምታስተምሩት ነገር ውስጥ ለራሳችሁ ሕይወት አግባብነት ያለውን ነገር እንዴት እንዳገኛችሁ ማካፈልም ትችላላችሁ። ይህን ማድረግ ትምህርቱ በሕይወታቸው ውስጥ እንዴት ለውጥ እንደሚያመጣ ተማሪዎችን በግል ለማስተማር መንፈስን ሊጋብዝ ይችላል።

የማሰላሰያ ጥያቄዎች፦ ለእናንተ፣ የወንጌል እውነቶችን ትርጉም ያላቸው እና ጠቃሚ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ወንጌልን ስታጠኑ የግል አግባብነት ያለውን ነገር እንድታገኙ የሚረዳችሁ ምንድን ነው? ለምታስተምሯቸው ሰዎች የግል አግባብነት ባላቸው እውነቶች ላይ ለማተኮር ምን እያደረጋችሁ ነው?

ከቅዱሳት መጻህፍት፦ 1 ኛ ኔፊ19፥23; 2 ኛ ኔፊ 32፥3ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 43፥7–9

የምትማሩትን ነገር ተግባራዊ የምታደርጉባቸው አንዳንድ መንገዶች

  • ትክክለኛ ትምህርት እያስተማራችሁ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ የምታስተምሩትን ነገር ገምግሙ። እነዚህ ጥያቄዎች ሊረዱ ይችላሉ፦

    • ለማስተማር የማቅደው ነገር በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እና በኋለኛው ቀን ነብያት ቃላት ላይ የተመሰረቱ ናቸው?

    • ብዙ ነብያት ይህን አስተምረዋልን? በዚህ ወቅት ያሉት የቤተክርስቲያን መሪዎች ስለሱ የሚያስተምሩት ምንድን ነው?

    • ሌሎች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነትን እንዲገነቡ፣ ንስሃ እንዲገቡ እና በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ ወደ ፊት እንዲጓዙ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

    • ይህ መንፈስ ቅዱስ ከሚያመጣው መነሳሳት ጋር ተመሳሳይ ነው ወይስ በመንፈስ ስለሱ እርግጠኛ ያለመሆን ስሜት ይሰማኛልን?

  • ለራሳችሁ እውነተኛ ትምህርትን ለመማር በየቀኑ የእግዚአብሔርን ቃል አጥኑ።

  • ስታስተምሩ ተማሪዎች ቅዱሳት መጻህፍትን እና የዚህን ዘመን ነቢያት ቃላት እንዲያነቡ ጠይቁ።

  • ተማሪዎች ቅዱሳት መጻህፍትን ሲያጠኑ የግርጌ ማስታወሻዎችን፣ የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያን እና ሌሎች ግብዓቶችን እንዴት እንደሚጠቀሙ አስተምሩ።

  • ተማሪዎች በቅዱስ ጽሁፍ ምንባቦች ወይም ታሪክ ውስጥ እውነቶችን እንዲያገኙ ጋብዙ።

  • አንድ ትምህርት እውነት እንደሆነ እንዴት እንዳወቃችሁ መስክሩ።

  • ተማሪዎች የወንጌልን እውነታዎች ጥልቅ መገንዘብ እንዲያገኙ ለመርዳት ታሪኮችን ወይም ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ተጠቀሙ።

አትም