ምዕራፍ ፲፱
ኔፊ ሰሌዳዎችን ከብረት አፈር ሠርቶ የህዝቡን ታሪክ መዘገበ—የእስራኤል አምላክ ሌሂ ኢየሩሳሌምን ከለቀቀበት ከስድስት መቶ ዓመት በኋላ ይመጣል—ስለእርሱ መከራና ስቅለት ኔፊ ተናገረ—አይሁዶች ይጠላሉ፣ እናም ወደጌታ እስከሚመለሱ እስከ ኋለኞቹ ቀናት ድረስ ይበተናሉ። ከ፭፻፹፰–፭፻፸ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ጌታ አዘዘኝ፣ ስለዚህ የህዝቤን ታሪክ እፅፍባቸው ዘንድ ሰሌዳዎችን ከብረት አፈር ሰራሁ። እናም በሰሌዳዎቹ ላይ የአባቴን ታሪክ፣ ደግሞም የምድረበዳ ጉዞአችንንና የአባቴን ትንቢቶች ፃፍኩባቸው፤ ደግሞም ብዙዎቹን የእኔን ትንቢቶች ፃፍኩባቸው።
፪ እናም እነርሱንም በሰራሁ ጊዜ እነዚህን ሰሌዳዎች እንድሰራ ከጌታ እንደምታዘዝ አላወቅሁም ነበር፤ ስለዚህ የአባቴን ታሪክና የአባቶቹን የትውልድ ሐረግ፣ እናም በምድረበዳ የነበሩትን አብዛኞች ገጠመኞቻችን የተፃፉት በእነዚያ እኔ ባልኳቸው የመጀመሪያ ሰሌዳዎች ላይ ነው፤ ስለዚህ እኔ እነዚህን ሰሌዳዎች ከመስራቴ በፊት የተከሰቱት ነገሮች በይበልጥም በመጀመሪያዎቹ ሰሌዳዎች በእውነትም ተጠቅሰዋል።
፫ እናም እነዚህን ሰሌዳዎች በትዕዛዝ ከሰራሁ በኋላ፣ እኔ ኔፊ፣ አገልግሎትና ትንቢቶችን ግልፅና አስፈላጊ የሆኑትን ክፍሎች፣ በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ እንድፅፍ ትዕዛዝ ተቀበልኩ፤ እና የሚፃፉት ነገሮች ይህችን ምድር ለሚይዙት ህዝቦቼ መመሪያ ይሆኑ ዘንድ፣ ደግሞም እኔ ለማላውቀው፣ ጌታ ለሚያውቀው፣ ለመልካም ዓላማው ይሆኑ ዘንድ ይጠበቃሉ።
፬ ስለዚህ እኔ ኔፊ፣ በሌሎች ሰሌዳዎች ላይ የህዝቦቼን ጦርነት፣ ፀብ፣ እና ጥፋትን ታሪክ፣ ወይም የተዘረዘረ ታሪክ መዘገብኩ። እናም ይህን አደረኩ፣ ህዝቤንም እኔ ስሄድ ምን ማድረግ እንዳለባቸውና፣ ከጌታ ተጨማሪ ትዕዛዝ እስከሚመጣ ድረስ፣ እነዚህ ሰሌዳዎች ከአንዱ ትውልድ ወደሌላው ወይም ከአንዱ ነቢይ ወደሌላው መተላለፍ እንደሚገባቸው አዘዝኩኝ።
፭ እነዚህን ሰሌዳዎች እንዴት እንደሰራሁ ከዚህ በኋላ ይነገራል፣ እናም እነሆ እንደተናገርኩት እቀጥላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው እጅግ የተቀደሱትን ነገሮች ህዝቦቼ ያውቁት ዘንድ እንዲጠብቁ ነው።
፮ ይሁን እንጂ ቅዱስ ናቸው ብዬ የማስባቸውን ካልሆነ በስተቀር ምንም ነገር በሰሌዳዎቹ ላይ አልፅፍም። እና አሁን ስህተት ብሰራ፣ የጥንቶቹም ቢሆኑ ስህተት ሰርተዋል፤ በሌሎች ሰዎች ስህተት ግን ራሴን አላመካኝም፣ ነገር ግን በስጋ መሰረት በውስጤ ባለው ደካማነት ራሴ አመካኛለሁ።
፯ አንዳንድ ሰዎች ለስጋም፣ ለነፍስም ታላቅ ዋጋ አለው ብለው የሚያስቡትን ነገሮች ሌሎች ይንቁታል፣ በእግራቸውም ይረግጡታል። አዎን የእስራኤልንም አምላክ እንኳን ሰዎች በእግራቸው ይረግጡታል፤ በእግራቸው ይረግጡታል እላለሁ ነገር ግን በሌላ አባባል እናገረዋለሁ—ንቀውታል፣ እናም የምክሩን ድምፅ አላዳመጡም።
፰ እናም እነሆ እንደመልአኩ ቃላት፣ አባቴ ኢየሩሳሌምን ከለቀቀበት ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላ፣ እርሱ ይመጣል።
፱ እናም በኃጢኣታቸው ምክንያት ዓለም ሁሉ ዋጋ እንደሌለው ነገር ይፈርዱበታል፤ ስለዚህ ይገርፉታል፣ እርሱም ይህን ይቀበላል፤ እናም ይመቱታል፣ እርሱም ይህን ይቀበላል። አዎን ይተፉበታል፣ እና በቸርነቱና ለሰው ልጆች ባለው ፅናት ምክንያት ይህንንም ይቀበለዋል።
፲ እናም ከግብፅ ከባርነት የወጡትና ደግሞም በምድረበዳ ውስጥ በእርሱ የተጠበቁት አባቶቻችን አምላክ፣ አዎን የአብርሃም አምላክ፣ የይስሀቅም፣ እና የያዕቆብ አምላክ እንደዜኖቅ ቃላት መሰረት እንዲሰቀል፣ እና እንደ ኔዩም ቃላት መሰረት እንዲሰዋና፣ በባህር ደሴቶች ለሚኖሩ በተለይም ለእስራኤል ቤት የሞቱ ምልክት ስለሚሰጠው የሶስት ቀን ጨለማ እንደተናገረው እንደ ዜኖስ ቃል በመቃብር እንዲቀበር፣ በመልአኩ ቃላት መሰረት፣ እራሱን እንደሰው በኃጢኣተኞች እጅ አሳልፎ ይሰጣል።
፲፩ ነቢዩ እንዲህ ተናገረ—ጌታ እግዚአብሔር በዚያ ቀን የእስራኤልን ቤት ሁሉ አንዳንዶቹን በቅንነታቸው የተነሳ፣ ለታላቅ ደስታቸው፣ ለደህንነታቸው በድምፁ፣ ሌሎቹን በነጎድጓድና በወጀብ ኃይሉ መብረቅ፣ በማዕበል በእሳትና በጭስና፣ በጨለማ ጭጋግ፣ እንዲሁም ምድርን በመክፈትና በሚነሱት ተራሮች ይጎበኛቸዋል።
፲፪ እናም ነቢዩ ዜኖስ እነዚህ ነገሮች ሁሉ መሆን አለባቸው ብሏል። የምድርም ዓለቶች መከፈል አለባቸው፤ እና በምድር ሁከት ምክንያት፣ በባህር ደሴቶች የሚገኙት ንጉሶች እንዲህ እንዲጮሁ በእግዚአብሔር መንፈስ ተፅዕኖ ይሰማቸዋል፣ የፍጥረት አምላክ ይሰቃያል ይላሉ።
፲፫ እናም ነቢዩ፣ በኢየሩሳሌም ስላሉት እንዲህ ይላል፥ የእስራኤልን አምላክ ስለሰቀሉና፣ ምልክቶቹን፣ ድንቆቹን በማስወገድና፣ የእስራኤልን አምላክ ክብርና ኃይል በመቃወም ልቦቻቸው ስለሳቱ፣ በሁሉም ህዝቦች ይሰቃያሉ።
፲፬ እናም ልባቸው ስለሳቱና፣ የእስራኤልን ቅዱስ ስለናቁ በስጋ ይንከራተታሉ፣ እናም ይጠፋሉ፣ እናም የሚፏጭባቸውና የተራቁም ይሆናሉ፣ በሁሉም ሀገሮች የተጠሉም ይሆናሉ ይላል ነቢዩ።
፲፭ ይሁን እንጂ በእስራኤሉ ቅዱስ ላይ ልባቸውን የማይስቱበት ቀን ሲመጣ፣ ያኔም ከአባታቸው ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ያስታውሳሉ፣ ይላል ነቢዩ።
፲፮ አዎን በዚያን ጊዜ የባህር ደሴቶችንም ያስታውሳል፤ በነቢዩ ዜኖስ ቃል መሰረት፣ አዎን የእስራኤልንም ቤት በሙሉ ከአራቱም የምድር ማዕዘናት እሰበስባቸዋለሁ አለ ጌታ።
፲፯ አዎን እናም ምድር በሙሉ የጌታን መድኃኒት ያያሉ፣ አለ ነቢዩ፤ እያንዳንዱ ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ህዝብም ይባረካል።
፲፰ እናም እኔ ኔፊ እነዚህን ነገሮች ለህዝቤ የፃፍኩት ምናልባት ጌታ መድኃኒታቸውን እንዲያስታውሱ ለማስረዳት ነው።
፲፱ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ያገኟቸው እንደሆነ ለሁሉም ለእስራኤል ቤት እናገራለሁ።
፳ እነሆ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት መገጣጠሚያዬ እስከሚደክም ድረስ የሚያስጨንቀኝ የመንፈስ ስራ አለኝ፤ እነሆ ጌታ እንደጥንት ነቢያት ስለእነርሱ በማሳየት መሀሪ ባይሆንልኝ ኖሮ እኔም ደግሞ በጠፋሁ ነበር።
፳፩ እናም እርሱ በእርግጥ ለጥንት ነቢያት ስለእነርሱ ገልጦላቸዋል፤ ደግሞም ለብዙዎች ስለእኛ አሳይቷቸዋል፣ ስለዚህ እኛም ደግሞ በነሀስ ሰሌዳዎች ላይ ተፅፈዋልና ልናውቃቸው ያስፈልገናል።
፳፪ አሁን እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ ለወንድሞቼ እነዚህን ነገሮች አስተማርኳቸው፤ እና እንዲህ ሆነ ጌታ በጥንት ሰዎች መካከል በሌሎች ምድር ውስጥ ያደረጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ያውቁ ዘንድ በነሀስ ሰሌዳዎች ላይ የተቀረፁትን ብዙ ነገሮች አነበብኩላቸው።
፳፫ እናም በሙሴ መፅሐፍት ላይ ከተፃፉት ብዙ ነገሮችን አነበብኩላቸው፤ ነገር ግን በይበልጥ ስለጌታ ስለመድኃኒታቸው እንዲያምኑ አስረዳቸው ዘንድ በነቢዩ ኢሳይያስ የተፃፉትን አነበብኩላቸው፤ እነሆ ለእኛ ጥቅምና ትምህርት ይሆኑ ዘንድ ሁሉንም ጥቅሶች ከእኛ ጋር አመሳሰልኩ።
፳፬ ስለዚህ ለእነርሱ እንዲህ ስል ተናገርኩ—እናንተ የተገነጠላችሁ ቅርንጫፎች የሆናችሁ የእስራኤል ቤት ቅሪቶች የተፃፉትን የነቢዩን ቃል አድምጡ፤ እናንተም ተገንጥላችሁ እንደመጣችሁባቸው ወንድሞቻችሁ አይነት ተስፋ ይኖራችሁ ዘንድ ለመላው ለእስራኤል ቤት የተፃፉትን የነቢዩን ቃል አድምጡ፣ ከእናንተም ጋር አመሳስሏቸው፤ እንደዚህም ነቢያት ፅፈዋልና።