ምዕራፍ ፳
ኢየሱስ በተአምራት ዳቦና ወይኑን አቀረበ፣ እናም በድጋሚ ለህዝቡ ቅዱስ ቁርባንን ሰጣቸው—የያዕቆብ ቅሪት የሆኑትም ጌታ አምላካቸውን ወደማወቁ ይመጣሉና አሜሪካንም ይወርሳሉ—ኢየሱስ እንደሙሴ ዓይነት ነቢይ ነው፣ እናም ኔፋውያን የነቢያቱ ልጆች ናቸው—ሌሎቹ የጌታ የሆኑት ህዝቦችም በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡን እንዲሁም ደቀመዛሙርቱን ፀሎታቸውን እንዲያቆሙ አዘዛቸው። እናም በልባቸው መፀለይም እንዳያቆሙ አዘዛቸው።
፪ እናም እንዲነሱና በእግራቸው እንዲቆሙ አዘዛቸው። እናም ተነሱና በእግራቸው ቆሙ።
፫ እናም እንዲህ ሆነ በድጋሚ ዳቦውን ቆረሰውና ባረከው፣ እናም ደቀመዛሙርቱ እንዲበሉት ሰጣቸው።
፬ እናም በተመገቡም ጊዜ ዳቦውን እንዲቆርሱና፣ ለህዝቡ እንዲሰጡ አዘዛቸው።
፭ እናም ዳቦውን ለህዝቡ በሰጡ ጊዜ እርሱ ደግሞ ወይኑን እንዲጠጡ ሰጣቸው፣ እናም ለህዝቡ እንዲሰጡም አዘዛቸው።
፮ አሁን፣ በደቀመዛሙርቱም ይሁን በህዝቡ የመጣ ምንም ዳቦም ሆነ ወይን አልነበረም።
፯ ነገር ግን እርሱ በእውነት ዳቦ እንዲበሉ፣ እናም ደግሞ ወይን እንዲጠጡ ሰጣቸው።
፰ እናም እንዲህ አላቸው፥ ይህንን ዳቦ የተመገበ ለነፍሱ ስጋዬን ይመገባል፣ ይህንን ወይን የጠጣም ለነፍሱ ደሜን ይጠጣል፤ እናም ነፍሱ አትራብም እንዲሁም አትጠማም፣ ነገር ግን ትጠግባለች።
፱ እንግዲህ፣ ህዝቡም በሙሉ በተመገቡና በጠጡ ጊዜ፣ እነሆ፣ በመንፈስ ተሞሉ፤ በአንድም ድምፅ ጮሁ፤ እናም ላዩትና ለሰሙት ኢየሱስ ክብርን ሰጡ።
፲ እናም እንዲህ ሆነ ሁሉም ለኢየሱስ ክብርን በሰጡ ጊዜ፣ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ አሁን የእስራኤል ቤት ቅሪት ስለሆኑት ስለነዚህ ሰዎች አብ ያዘዘኝን ትዕዛዝ እፈፅማለሁ።
፲፩ እናም የኢሳይያስም ትንቢት ይፈፀማሉ ብዬ የተናገርኳችሁን አስታውሱ—እነሆ እነርሱ ተፅፈዋል፤ እነርሱም ከፊታችሁ ናቸው፤ ስለዚህ መርምሩዋቸው—
፲፪ እናም የእስራኤል ቤት ሆይ፣ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እነርሱም ሲፈፀሙ አብም ለህዝቡ የገባው ቃል ኪዳን ይፈፀማል።
፲፫ እናም ቅሪቶቹ፣ በምድር ገፅ ላይ የተበተኑት ሁሉ ከምስራቅ፣ ከምዕራብና፣ ከደቡብ፣ እና ከሰሜን ይሰበሰባሉ፤ እናም አዳኛቸው ወደሆነው ወደ ጌታ አምላካቸው እውቀት ይመጣሉ።
፲፬ እናም አብም ለርስታችሁ ይህችን ምድር እንድሰጣችሁ አዞኛል።
፲፭ እናም እንዲህ እላችኋለሁ፣ አህዛብ በረከቱን በሚቀበሉበት ሁኔታ ህዝቤንም ከበተኑ በኋላ ንሰሃ ካልገቡ—
፲፮ ከዚያም እናንተ የያዕቆብ ቤት ቅሪት የሆናችሁ ከእነርሱም መካከል ትሄዳላችሁ፤ ብዙ ከሚሆኑትም መካከል ትሆናላችሁ፤ እናም አንበሳ ከዱር አውሬዎች መካከል እንደሚሆነውና፣ በመካከላቸው ሲሄድ እንደሚረጋግጣቸውና እንደሚቆራርጣቸው፣ እናም ማንም ሊያድናቸው እንደማይቻለው እንደ አንበሳ ገልግል በበጎች መንጋ መካከል እንደሚሆን እናንተም በእነርሱ መካከል ትሆናላችሁ።
፲፯ እጅህ በጠላቶችህ ላይ ከፍ ይላል፣ እናም ጠላቶችህ ሁሉ ይጠፋሉ።
፲፰ እናም ሰው አውድማውን በሜዳው ላይ እንደሚሰበስብ ህዝቤን በአንድነት እሰበስባለሁ።
፲፱ አብ ቃል ኪዳን የገባላቸውን ህዝቦቼን፣ አዎን፣ ቀንድሽን ብረት፥ ጥፍርሽንም ናስ አደርጋለሁ። ብዙ ህዝቦችን ታደቅቂአለሽ፤ ትርፋቸውንም ለጌታ፣ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ እቀድሳለሁ። እናም እነሆ፣ ይህን የማደርገውም እኔ ነኝ።
፳ እናም እንዲህ ሆነ፣ አብ እንዲህ አለ፣ በዚያ ቀን የፍርዴ ጎራዴ በእነርሱ ይመዘዛል፤ እናም አብም ንሰሃ ካልገቡ በእነርሱ ላይ ይወድቃል ይላል፤ አዎን፣ በአህዛብ ሀገር ሁሉ ላይም ይወድቃል።
፳፩ እናም እንዲህ ይሆናል የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ህዝቤንም እመሰርታለሁ።
፳፪ እናም እነሆ፣ ከአባታችሁ ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን እፈፅም ዘንድ ይህን ህዝብ በዚህች ምድር እመሰርታለሁ፤ እርሷም አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ትሆናለች። እናም የሰማይ ስልጣናትም በዚህ ህዝብ መካከል ይሆናሉ፤ አዎን፣ እኔም በመካከላችሁ እሆናለሁ።
፳፫ እነሆ፣ ሙሴ እንዲህ ሲል የተናገረለት እኔ ነኝ፥ ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለን ነቢይ ጌታ አምላካችሁ ከመካከላችሁ ያስነሳል፤ እርሱ የሚላችሁን ሁሉ ታደምጡታላችሁ። እናም ይህን ነቢይ የማትሰማ ነፍስ ብትኖር ከዚህ ህዝብ ተለይታ ትጠፋለች።
፳፬ እውነት እላችኋለሁ፤ አዎን፣ እናም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱ በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ስለእኔ መስክረዋል።
፳፭ እናም እነሆ፣ እናንተ የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እናም የእስራኤል ቤት ናችሁና፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ከአባቶቻችሁ ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ፤
፳፮ አብም ወደእናንተ በመጀመሪያ እንድነሳ አደረገኝ፣ እናም ከክፋቶቹ እያንዳንዳችሁን እንዳርቅ እናንተን እንድባርክ ላከኝ፤ እናም ይህም የሆነው እናንተ የቃል ኪዳን ልጆች ስለሆናችሁ ነው—
፳፯ እናም ከተባረካችሁ በኋላ እንዲህም ሲል አብ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ተፈፅሟል፥ በዘርህ የምድር ወገኖች በሙሉ ይባረካሉ—በእኔም በኩል ወደ አህዛብ መንፈስ ቅዱስን ወደማፍሰስ፣ ይህም በአህዛብ ላይ ያለው በረከት ከሁሉም በላይ ሀይለኛ ሆነው ህዝቤን፣ አቤቱ የእስራኤል ቤትን፣ ይበትናሉ።
፳፰ እናም ለዚህች ምድር ህዝቦች ጅራፍ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ፣ አብም የወንጌሌን ሙሉነት በሚቀበሉበት ጊዜ ልባቸውን በእኔም ላይ ካጠጠሩ፣ ክፋታቸውን በእራሳቸው ላይ እመልስባቸዋለሁ ይላል።
፳፱ እናም ከህዝቤ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ፤ አብም እንዲህ ይላል፥ በራሴም ጊዜ በአንድ ላይ እነርሱን እንድሰበስብ፤ ለዘሮቻቸውም በድጋሚ የኢየሩሳሌምን ምድር የሆነውን፣ እናም ለዘለዓለም የቃል ኪዳን ምድር የሆነችላቸውን የአባቶቻቸውን ምድር ለመስጠት ቃል ኪዳን ገብቻለሁና።
፴ እናም የወንጌሌ ሙሉነት ለእነርሱ የሚሰበክበት ጊዜ ይመጣል፤
፴፩ እናም እኔም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆንኩኝ በእኔ ያምናሉ፣ እናም በስሜም ወደ አብ ይፀልያሉ።
፴፪ ጠባቂዎቻቸውም ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፣ እናም በአንድ ድምፅም ይዘምራሉ፤ ዐይን ለዐይንም ይተያያሉና።
፴፫ ከዚያም አብ በድጋሚ በአንድነት ይሰበስባቸዋል፣ እናም ለርስታቸውም ምድር ኢየሩሳሌምን ይሰጣቸዋል።
፴፬ እነርሱም እልል ይላሉ—እናንት የተበላሻችሁ የኢየሩሳሌም ስፍራዎች በአንድነት ዘምሩ፤ አብም ህዝቡን አፅናንቷል፤ ኢየሩሳሌንም አድኗልና።
፴፭ አብም ቅዱስ የሆኑ ክንዶቹን በሀገር ሁሉ ፊት አሳይቷል፤ እናም በዓለም ጫፍ ያሉት ሁሉ የአብን መድሀኒት ይመለከታሉ፤ እናም እኔና አብም አንድ ነን።
፴፮ እና ከዚያም የተፃፉትም ይፈፀማሉ፤ ፅዮን ሆይ ንቂ፣ በድጋሚ ንቂና፣ ጥንካሬሽን ልበሺ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ቅዲሲቷ ከተማ ሆይ፣ ያጌጠ ልብስሽንም ልበሺ፤ ከእንግዲህ ያልተገረዘና ርኩስ ወዳንቺ ዘንድ አይመጣምና።
፴፯ ኢየሩሳሌም ሆይ ትቢያሽን አራግፊ፣ ተነሺ፣ ተቀመጪ፤ ምርኮኛይቱ የፅዮን ልጅ ሆይ የአንገትሽን እስራት ፍቺ።
፴፰ ጌታ እንዲህ ይላልና፥ በከንቱ ተሽጣችሁ ነበር፤ ያለገንዘብም ትቤዣላችሁ።
፴፱ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ህዝቤ ስሜን ያውቃሉ፤ አዎን በዚያ ቀን የምናገረው እኔ እንደሆንኩም ያውቃሉ።
፵ እናም ከዚያም እንዲህ ይላሉ፥ ሰላምን ያበስር፤ መልካም የሆነውን መልካም የምስራች ወሬ ያመጣ፣ ደህንነትን ያወጀ፣ ለፅዮንም አምላካችሁ ነግሶአል! ያለው፣ መልካም የምስራች ይዞ የመጣው በተራራው ላይ ያለው እግሮቹ እንዴት ያማሩ ናቸው።
፵፩ እናም እንዲህ የሚልም ጬኸት ይሆናል፥ ሽሹ፣ ሽሹ፣ ከዚህ ስፍራ ተለዩ፣ ርኩስ የሆነውንም አትንኩ፤ ከመካከልዋም ውጡ፤ የጌታን ዕቃ የምትሸከሙ ንፁሃን ሁኑ።
፵፪ በችኮላም ሆነ በመሸሽ አትሄዱም፤ ጌታ ከፊታችሁ ይሄዳልና፣ እናም የእስራኤል አምላክም ከኋላችሁ ይሆናል።
፵፫ እነሆ አገልጋዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከበራል እናም ከፍ ከፍም ይላል፤ እጅግ ታላቅም ይሆናል።
፵፬ ብዙዎች በአንተ ተደንቀው ነበር—ፊቱም ከማንኛውም ሰው የበለጠ፣ እናም የሰውነቱም ገጽ ከሰው ልጆች የበለጠ የተበላሸ ነበር—
፵፭ በብዙ ሀገርም ላይ ያርከፈክፋል፤ ያልተነገረላቸውንም ያያሉና፥ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና፣ ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ።
፵፮ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ አብ እንዳዘዘኝ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በእርግጥ ይመጣሉ። አብም ከህዝቡ ጋር የገባው ይህ ቃል ኪዳን ይፈፀማል፤ እናም ህዝቦቼም በድጋሚ ኢየሩሳሌምን ይኖሩባታል፤ እናም እርሷም የርስት ምድራቸው ትሆናለች።