ምዕራፍ ፮
ኔፋውያን በለፀጉ—ኩራት፤ ሀብት እናም በመደብ መለያየት ተጀመረ—በጥል የተነሳም ቤተክርስቲያኗ ተከፋፈለች—ሰይጣን ሰዎችን በአመጽ መራቸው—ብዙ ነቢያት ስለንሰሃ ጮሁ እናም ተገደሉ—ገዳዮቻቸውም የአስተዳደሩን ቦታ ለመያዝ አሴሩ። ፳፮–፴ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ የኔፊ ህዝብ እያንዳንዱ፣ ከነቤተሰቡ፣ ከብቶቻቸውና መንጎቻቸው፣ ፈረሶቻቸውና የቀንድ ከብቶቻቸው እናም የእነርሱ ከሆኑት ሁሉም ነገሮች ጋር በሃያ ስድስተኛው ዓመት ወደራሳቸው ቦታ ተመለሱ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ ስንቃቸውን በሙሉ አልተመገቡም ነበር፤ ስለዚህ ያልተመገቧቸውን ከሁሉም አይነት እህልና፣ ወርቃቸውን፣ እናም ብራቸውንና፣ የከበሩ ነገሮቻቸውን በሙሉ ወሰዱ፣ እናም ከሰሜንና ከደቡብ፣ ከምድሪቱ በስተሰሜን እንዲሁም ከምድሪቱ በስተደቡብ በኩል ወደራሳቸው ምድር እንዲሁም ወደ ይዞታዎቻቸው ተመለሱ።
፫ እናም ላማናውያን ሆነው ለመቅረት ይፈልጉ የነበሩት፣ የምድሪቱን ሠላም እንዲጠብቁ ቃል ኪዳን የገቡት ዘራፊዎች፣ ህይወታቸውን ለማቆየት ይሰሩበት ዘንድ በቁጥራቸው መጠን መሬት ተሰጣቸው፤ እናም እንደዚህ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ሠላምን አሰፈኑ።
፬ እናም በድጋሚ በታላቅ ሁኔታ መበልፀግና መጨመር ጀመሩ፤ እናም ሃያ ስድስተኛውና ሃያ ሰባተኛው ዓመት አለፈ፤ እናም በምድሪቱ ላይ ታላቅ የሆነ ስምምነት ነበር፤ ህግጋታቸውንም በሚዛናዊነትና በፍትሃዊ ፍርድ መሰረት ሰሩ።
፭ እናም አሁን ህዝቡ ወደመተላለፍ ካልወደቁ በስተቀር በምድሪቱ ላይ ሁሉ ያለማቋረጥ ለመበልጸግ የሚከለክላቸው ምንም ነገር አልነበረም።
፮ እናም እንግዲህ ጊድጊዶኒና፣ ዳኛው ላኮኔዎስ፣ እናም ተሹመው የነበሩት መሪዎች ነበሩ በምድሪቱ ላይ ይህንን ታላቅ ሠላም የመሰረቱት።
፯ እናም እንዲህ ሆነ በአዲስ ሁኔታም የተሰሩ ብዙ ከተሞች ነበሩ፤ እናም የታደሱ ብዙ አሮጌ ከተሞችም ነበሩ።
፰ እናም ብዙ አውራጎዳናዎችም ተሰርተው ነበር፤ እናም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላኛው ከተማና፣ ከአንደኛዋ ምድር ወደ ሌላኛዋ፣ እንዲሁም ከስፍራ ስፍራ የሚያመሩ ብዙ መንገዶች ተሰርተው ነበር።
፱ እናም ሃያ ስምንተኛው ዓመት እንደዚህ አለፈ፤ እናም ህዝቡ ዘለቄታ ያለው ሠላምን አገኘ።
፲ ነገር ግን በሃያ ዘጠነኛው ዓመት በህዝቡ መካከል ጥቂት ፀብ ተጀመረ፤ እናም አንዳንድ ሰዎችም እጅግ ሀብታም በመሆናቸው እስከ ታላቅ ማሳደድም ድረስ በኩራት እንዲሁም ትዕቢት ተነሳስተው ነበር፤
፲፩ በምድሪቱም ብዙ ነጋዴዎች፣ እናም ደግሞ ብዙ የህግ አዋቂዎች፣ እናም ብዙ ሹማምንት ነበሩና።
፲፪ እናም ህዝቡ እንደ ሀብቱና ለትምህርቱ ባለው ዕድል መሰረት በደረጃ መከፋፈል ጀመሩ፤ አዎን፣ አንዳንድ ሰዎች በድህነታቸው የተነሳ አላዋቂዎች ነበሩ፤ እናም ሌሎች ደግሞ ሀብታሞች በመሆናቸው ታላቅ ዕውቀትን ተቀብለዋል።
፲፫ አንዳንድ ሰዎች በኩራት ሲወጠሩ፣ እናም ሌሎች እጅግ ትሁት ነበሩ፤ ሌሎች ወቀሳን በወቀሳ ሲመልሱ እንዲሁም ሌሎች ስደትንና ሁሉንም አይነት ስቃዮች ይቀበሉ ነበር፣ እናም በድጋሚም ለመሳደብ አይመለሱም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ትሁት እንዲሁም የተጸጸቱ ነበሩ።
፲፬ እናም እንደዚህ በምድሪቱ ሁሉ ታላቅ ጥፋት መጣ፣ በዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያኗ መከፋፈል ተጀመረ፤ አዎን፣ በዚህም የተነሳ በሠላሳኛው ዓመት ወደ እውነተኛው እምነት ተለውጠው ከነበሩት ጥቂት ላማናውያን መካከል በስተቀር፣ በምድሪቱ በሙሉ ቤተክርስቲያኗ ተከፋፍላ ነበር፤ እናም እነርሱም ፅኑ፤ የማይለወጡ፤ እናም የማይነቃነቁ፣ ባላቸው ትጋት ሁሉ የጌታን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ፈቃደኞች በመሆናቸው ከእውነተኛው እምነታቸው አይሸሹም።
፲፭ እንግዲህ የህዝቡ የዚህ ክፋት መንስኤው ይህ ነበር—ይህን ህዝብ ሁሉንም ዐይነት ክፋት እንዲያደርግ ለማነሳሳት፣ እናም በኩራት እንዲወጣጠሩ ለማድረግ፤ ኃይልንና ስልጣንን፣ እናም ሀብትንና የዓለምን ከንቱ ነገሮች እንዲሹ ለመፈተን ሰይጣን ታላቅ ሀይል ነበረው።
፲፮ እናም ሰይጣን የሰዎችን ልብ ሁሉንም ዐይነት ክፋት እንዲሰሩ እንደዚህ መርቷቸዋል፤ ስለዚህ በሠላሙ ተደስተዋል፣ ነገር ግን ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነበር።
፲፯ እናም በሠላሳኛው ዓመት መጀመሪያ—ህዝቡም ዲያብሎስ ሊመራቸው በፈለገበት ወደማንኛቸውም ፈተናዎች እንዲገቡና፣ የፈለገውን የትኛውን ዐይነት ክፋት እንዲሰሩ ለረጅም ጊዜ ተለቀው ስለነበር፣ እናም በዚህ በሠላሳኛው ዓመት መጀመሪያ ላይ እንደዚህ አሰቃቂ በሆነ ኃጢያት ውስጥ ነበሩ።
፲፰ እንግዲህ ባለማወቅ ኃጢያትን አልሰሩም፤ ምክንያቱም እነርሱን በተመለከተ ተምረው ስለነበሩ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያውቁት ነበር፤ ስለዚህ ሆን ብለው በእግዚአብሔር ላይ አምጸዋል።
፲፱ እናም እንግዲህ ይህ በላኮኔዎስ ልጅ በላኮኔዎስ ዘመን ነበር፣ የላኮኔዎስ ልጅ የአባቱን ወንበር ይዞ እናም ህዝቡን በዚህ አመት ያስተዳደረው ነበርና።
፳ እናም ስለህዝቡ ኃጢያትና ክፋት በምድሪቱ ላይ በህዝቡ መካከል በመቆም በድፍረት በመስበክና በመመስከር እናም ጌታ ለህዝቡ የሚያደርገውን ቤዛነት በሌላ አነጋገር የክርስቶስን ትንሳኤ በተመለከተ ከሰማይ ተነሳስተው የተላኩ ሰዎች ነበሩ። እናም እርነሱም በድፍረት ስለሞቱና ስለስቃዩ መሰከሩ።
፳፩ እንግዲህ ስለነዚህ ነገሮች በመመስከራቸው ምክንያት እጅግ የተቆጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እናም ተቆጥተው የነበሩት በአብዛኛው ዋና ዳኞች፣ እናም የካህናት አለቆች፣ እንዲሁም ጠበቃዎች ነበሩ፤ አዎን፣ ጠበቃዎች የነበሩት በሙሉ እነዚህን ነገሮች በመሰከሩት ተቆጥተው ነበር።
፳፪ እንግዲህ ቅጣቱም በምድሪቱ ገዢ ካልተፈረመበት በቀር ማንንም በሞት የመቅጣት ስልጣን ያላቸው ጠበቃ፣ ዳኛም ሆነ የካህናት አለቃ አልነበሩም።
፳፫ እንግዲህ ክርስቶስን የሚመለከቱ ነገሮችን የመሰከሩ፤ በድፍረት የተናገሩ፣ የመሞታቸው እውቀት ወደ አስተዳዳሪው ከሞቱ በኋላ ብቻ እንዲመጣም በዳኛዎችም በሚስጥር የተገደሉ ብዙዎች ነበሩ።
፳፬ አሁን እነሆ፣ ይህ ማንም ሰው ከምድሪቱ አስተዳዳሪ ስልጣን ካልተሰጠው መገደል የለበትም ከሚለው ከምድሪቱ ህግጋት ጋር የሚቃረን ነበር—
፳፭ ስለዚህ የጌታን ነቢያት እንዲሞቱ ከህጉ ውጪ በፈረዱባቸው ዳኞች ላይ በዛራሄምላ ምድር ለነበረው አስተዳዳሪ አቤቱታ ቀረበ።
፳፮ እንግዲህ እንዲህ ሆነ እነርሱም ተወሰዱ፣ እናም በህዝቡ በተሰጠው ህግ መሰረት በሰሩት ወንጀል ላይ እንዲፈረድባቸው በዳኛው ፊት ቀረቡ።
፳፯ እንግዲህ እንዲህ ሆነ እነዚያም ዳኞች ብዙ ጓደኞችና ወገን ነበሩአቸው፤ እናም ቀሪዎቹ አዎን፣ ሁሉም ጠበቆችና፣ የካህናት አለቆች፣ እራሳቸውን በአንድነት ሰብስበው እናም በህጉም እንዲፈረድባቸው ከቀረቡት ዳኞች ወገኖች ጋር ተቀላቅለው ነበር።
፳፰ እናም በአንድነት ወደ ቃል ኪዳኑ፣ አዎን፣ በጥንት ጊዜ በነበሩት ወደተሰጠው ቃል ኪዳን፣ በጻድቅነት ላይ ለመተባበር በዲያብሎስ ወደተሰጠው እና ወደሚተዳደረው ቃል ኪዳን ገቡ።
፳፱ ስለዚህ እነርሱም በጌታ ሰዎች ላይ በአንድነት ተባበሩ፣ እናም እነርሱንም ለማጥፋትና በህጉ መሰረት ሊፈረድባቸው አጥብቆ ከያዛቸው ከፍትህ በግድያ ጥፋተኛ የነበሩትን ለማዳን ቃል ኪዳን ገብተው ነበር።
፴ እናም ህጉንና የሀገር መብታቸውን ለማስጠበቅ አልተቀበሉም፤ እናም አስተዳዳሪውን ለማጥፋትና ምድሪቱም ከእንግዲህ በነፃነት እንዳትሆን፣ ነገር ግን በንጉስ አገዛዝ ስር እንድትሆን ንጉስ በምድሪቷ ላይ ለመመስረት እርስ በርሳቸው ቃል ኪዳን ገቡ።