እግዚአብሔር ያሸንፍ
እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ እናንተ ፍቃደኞች ናችሁን? እግዚአብሔር በህይወታቸው በጣም ሃይለኛ ተጽዕኖ እንዲሆን እናንተ ፈቃደኞች ናችሁን?
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህ ጉባኤ ለተሰጡት አስደናቂ መልዕክቶች እና ለእናንተ እንድናገር ስላገኘሁት እድል ምንኛ አመስጋኝ ነኝ።
በሐዋርያነት እያገለገልኩባቸው ባሉት ከ36 በላይ ከሆኑት አመታት፣ እስራኤልን የማሰባሰብ ትምህርት ትኩረቴን ስቦታል።1 ስለዚህ ሁሉም ነገር፣ እንዲሁም አገልግሎቶች እና የአብርሃም፣ የይስሃቅ እና የያዕቆብ ስሞች2፤ ህይወታቸው እና ሚስቶቻቸው፤ እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር የገባው እና ለዘሮቻቸው ያደሰው ቃልኪዳን3፤ የአስራ ሁለቱ ነገዶች መበተን፤ እና በዘመናችን ስለመሰባሰባው የተነገሩ ብዙ ትንቢቶችን ጨምሮ፣ ጉጉቴን ይቀሰቅሰዋል።
ስለመሰባሰቡ አጥንቻለሁ፣ ጸልዬበታለሁ፣ ከእርሱ ጋር የተያያዙ የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶችንም አንብቤአለሁ እንዲሁም ግንዛቤዬን እንዲያሳድግልኝ ጌታን ጠይቄአለሁ።
ስለዚህ፣ በቅርቡ ወደ አዲስ ግንዛቤ ተመርቼ በነበረ ጊዜ ምን ያህል ተደስቼ እንደነበር ገምቱ። በሁለት ዕብራውያን ምሁራን ረዳትነት፣ እስራኤል የሚለው ቃል አንድ የዕብራይስጥ ትርጓሜ “እግዚአብሔር ያሸንፍ” ማለት እንደሆነ ተማርኩኝ።4 ስለዚህ እስራኤል የሚለው ስም ራሱ እግዚአብሔር በህይወት እንዲያሸንፍ ፍቃደኛ የሆነን ሰው ያመለክታል። ጽንሰ ሃሳቡ መንፈሴን አነሳሳው።
ፍቃደኛ የሚለው ቃል እስራኤል በዚሀ መልኩ ትርጉም እንዲያገኝ ወሳኝ ነው።5 ሁላችንም የመምረጥ ነጻነት አለን። እስራኤል ለመሆን ወይም ላለመሆን መምረጥ እንችላለን። እግዚአብሔር በህይወታችን እንዲያሸንፍ ወይም ተቃራኒው እንዲሆን ልንመርጥ እንችላለን። እግዚአብሔር በህይወታችን በጣም ሃይለኛ ተጽዕኖ እንዲሆን ወይም እንዳይሆን ልንመርጥ እንችላለን።
ለአፍታ የአብርሃም የልጅ ልጅ በሆነው በያዕቆብ ህይወት ውስጥ ወሳኝ ስለሆነው ሁኔታ ቀያሪ ነጥብ እናስታውስ። ያዕቆብ ጵኒኤል (“የእግዚአብሔር ፊት” ማለት ነው) ብሎ በጠራው ቦታ6 ያዕቆብ ከከባድ ፈተና ጋር ታገለ። የመምረጥ ነጻነቱ ተፈትኖ ነበር። በዚህ ትግል ያዕቆብ ለእሱ በጣም አስፈላጊ የነበረው ምን እንደሆነ አረጋገጠ። እርሱም እግዚአብሔር በህይወቱ እንዲያሸንፍ ፍቃደኛ እንደሆነ አሳየ። በምላሹም እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም “እግዚአብሔር ያሸንፍ” የሚል ትርጓሜ ወዳለው ወደ እስራኤል ለወጠው።7 ከዚያም እግዚአብሔር በአብርሃም ራስ ላይ ፈስሠው የነበሩት ሁሉም በረከቶች የእርሱም እንደሚሆኑ ለእስራኤል ተስፋ ሰጠው።8
በሚያሳዝን ሁኔታ የእስራኤል ትውልድ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን አፈረሱ። ነቢያትን በድንጋይ ወገሩ እንዲሁም እግዚአብሔር በህይወታቸው እንዲያሸንፍ ፍቃደኞች አልነበሩም። በመቀጠልም እግዚአብሔር በአራቱም የምድር ማዕዘናት በተናቸው።9 በኢሳይያስ እንደተመዘገበው በምህረት በኋላ እንደሚሰበስባቸው ተስፋ ሰጣቸው፥ “ለጥቂት ጊዜ ጣልኩሽ [እስራኤል]፤ ነገር ግን በታላቅ ምህረት እሰበስብሻለሁ።”10
የእስራኤልን የዕብራይስጥ ትርጉም በአዕምሮአችን በመያዝ፣ የእስራኤል መሰባሰብ ተጨማሪ ትርጉም እንደሚኖረው እናያለን። እግዚአብሔር በህይወታቸው እንዲያሸንፍ ፍቃደኞች የሆኑትን ጌታ በመሰብሰብ ላይ ነው። እግዚአብሔር በህይወታቸው በጣም ሃይለኛ ተጽዕኖ እንዲሆን የሚመርጡትን ጌታ በመሰብሰብ ላይ ነው።
ለዘመናት ነቢያት ስለዚህ መሰባሰብ አስቀድመው ተንብየው ነበር፤11 እና ይህም አሁን በመከናወን ላይ ይገኛል! ለጌታ ዳግም መመለስ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ እንደመሆኑ በአለም እጅግ በጣም አስፈላጊው ስራ ነው።
ይህ የቅድመ ሺህ ዓመቱ የማሰባሰብ ስራ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እምነት እና መንፈሳዊ ድፍረት ለማሳደግ የሚደረግ የግለሰብ የጀግንነት ታሪክ ነው። እናም እንደኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት ወይም “የኋለኛው ቀን የቃልኪዳን እስራኤል፣”12 በዚህ ወሳኝ ጠቀሜታ ያለው ስራ ጌታን እንድናግዝ ታዝዘናል።13
በመጋረጃው በሁለቱም በኩል ያለውን እስራኤል ሰለማሰብሰብ ስራ ስንናገር፣ በእርግጥ ስለሚስዮናዊ፣ ስለቤተመቅደስ እና ስለቤተሰብ ታሪክ ስራ እያመለከትን ነው። በተጨማሪም አብረናቸው በምንኖረው፣ አብረናቸው በምንሰራው እና አብረናቸው በምናገለግለው ሰዎች ልብ ውስጥ እምነትን እና ምስክርነትን ስለመገንባት እያመለከትን ነው። በመጋረጃው በሁለቱም በኩል ላሉት፣ በማንኛውም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ እና እንዲጠብቁ ማንንም የሚረዳ ነገር ስናደርግ፣ እስራኤልን ለማሰባሰብ እየረዳን ነን።
በቅርብ ጊዜ፣ ከልጅ ልጆቻችን የአንዱ ሚስት በመንፈሳዊነት እየታገለች ነበር። “ጂል” ብዬ እጠራታለሁ። ጾም፣ ጸሎት እና የክህነት በረከቶች ቢሰጡትም የጂል አባት በመሞት ላይ ነበር። አባቷንም ምስክርነቷንም አጣለሁ በሚል ፍርሃት ተይዛ ነበር።
በአንድ ምሽት ባለቤቴ እህት ዌንዲ ኔልሰን ስለ ጂል ሁኔታ ነገረችኝ። ጥዋት በነጋታው ስለመንፈሳዊ ትግሏ የሰጠኋት ምላሽ ቃል እንደሆነ ዌንዲ ለጂል የማጋራት ስሜት ተሰማት! ያም ቃል በሩቅ አለማየትነበር።
በኋላም ጂል በመጀመሪያ በሰጠኋት መልስ በጣም አዝና እንደነበር ለዌንዲ ነገረቻት። እንዲህ አለች “አያቴ ለአባቴ የተዐምራዊ ፈውስ ቃል እንዲገባልኝ ተስፋ እያደረኩኝ ነበር። በሩቅ አለማየት የሚለውን ቃል ለመናገር የተገደደው ለምን እንደሆነ ማሰቤን ቀጠልኩኝ።”
የጂል አባት ካረፈ በኋላ በሩቅ አለማየት የሚለው ቃል ወደ አእምሮዋ መመላለሱን ቀጠለ። በሩቅ አለማየት ማለት “የቅርቡን ብቻ ማየት መቻል” ማለት መሆኑን ለመረዳት ልቧን ይበልጥ በጥልቅ ከፈተች። እናም አስተሳሰቧ መቀየር ጀመረ። ከዚያም ጂል እንዲህ አለች፣ “በሩቅ አለማየት ቆም እንድል፣ እንዳስብ እና እንድፈወስ ምክንያት ሆነኝ። አሁን ያም አባባል በደስታ ይሞላኛል። እይታዎቼን እንዳሰፋ እና ዘላለማዊውን እንድሻ ያስታውሰኛል። መለኮታዊ እቅድ እንዳለ እንዲሁም አባቴ አሁንም እየኖረ እንደሆነ እና አኔንም እንደሚመለከተኝ ያስታውሰኛል።. በሩቅአለማየት ወደ እግዚአብሔር መርቶኛል።”
በልጅ ልጃችን ውድ ሚስት በጣም አኮራባታለሁ። ለራስዋ ህይወት ዘላለማዊ እይታን ጨምሮ ውድ ጂል በሕይወቷ ውስጥ በዚህ በሚያደናቅፍ ወቅት እግዚአብሔር ለአባቷ ያለውን ፈቃድ መቀበልን እየተማረች ነች። እግዚአብሔር እንዲያሸንፍ በመምረጥ ሰላም እያገኘች ነች።
ብንፈቅድለት የዕብራይስጡ የእስራኤል ትርጉም እኛን የሚረዳበት ብዙ መንገዶች አሉ። ለሚስዮናውያኖቻችን—እንዲሁም እራሳችን እስራኤልን ለማሰባሰብ በምናደርገው ጥረት—የምናደርጋቸው ጸሎቶቻችን በአእምሮ ባለው በዚህ ጽንሰ ሃሳብ እንዴት እንደሚቀየሩ አስቡ። አብዛኛውን ጊዜ እኛ እና ሚስዮናውያን በዳግም የተመለሰውን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እውነት ለመቀበል ወደተዘጋጁት እንድንመራ እንጸልያለን። እንዲህም አስባለሁ፣ እግዚአብሔር በህይወታቸው እንዲያሸንፍ ፍቃደኞች የሆኑትን ለማግኘት ስንማጸን ወደማን እንመራ?
በእግዚአብሔር ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ወደማያውቁ ሆኖም አሁን ስለእነርሱ እና ስለደስታ እቅዳቸው ለመማር ወደሚናፍቁ ልንመራ እንችላለን። ሌሎች “በቃልኪዳኑ ውስጥ የተወለዱ”14 ነገር ግን ከቃል ኪዳኑ መንገድ ያፈነገጡ ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን ንስሃ ለመግባት፣ ለመመለስ እና እግዚአብሔር እንዲያሸንፍ ለማድረግ ዝግጁ ሊሆኑ ይችላሉ። በተከፈቱ እጆች እና ልቦች እነርሱን በመቀበል ልንረዳቸው እንችላለን። አንዲሁም የምንመራባቸው አንዳንዶች ሁል ጊዜ በህይወታቸው አንዳች የጎደለ ነገር እንዳለ የሚሰማቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አነሱም እግዚአብሔር በህይወታቸው እንዲያሸንፍ ፍቃደኞች ለሆኑት የሚመጣውን ሙሉነትን እና ደስታን እየናፈቁ ናቸው።
የተበተነውን እስራኤል ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ የሚውለው ወንጌል ብዙ ቦታን መሸፈን የሚችል ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሙሉ በሙሉ ለሚቀበል ለእያንዳንዱ ሰው ቦታ አለ። በውልደትም ይሁን በማደጎ፣ እያንዳንዱ አዲስ ተቀያሪ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ልጆች አንዱ ይሆናል።15 እያንዳንዱም እግዚአብሔር ለታመኑ የእስራኤል ልጆች የሰጠውን የተስፋ ቃል ሁሉ ሙሉ ወራሽ ይሆናሉ!16
እያንዳንዳችን የእግዚያብሄር ልጆች በመሆናችን መለኮታዊ አቅም አለን። በእርሱ አይኖች እያንዳንዱ እኩል ነው። የዚህ እውነት አንድምታ ጥልቅ ነው። ወንድሞች እና እህቶች፣ እባካችሁ የምናገረውን በትኩረት አዳምጡ። እግዚአብሔር አንዱን ዘር ከሌላው አስበልጦ አይወድም። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ትምህርት ግልጽ ነው። እናም ወደ እርሱ የሚመጡትን ማንንም፣ “ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያውንና ነፃውን፤ ወንድን እና ሴትን” ወደእርሱ እንዲመጡ ይጋብዛል።17
በእግዚአብሔር ፊት አቋማችሁ በቆዳችሁ ቀለም እንደማይወሰን አረጋግጥላችኋለሁ። በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ሞገስ ወይም አለመውደድ ለእግዚአብሔር እና ለትእዛዛቱ ባደረዳችሁት ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ ነው እንጂ በቁዳችሁ ቀለም ላይ የተመካ አይደለም።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ጥቁር ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የዘረኝነት እና የጭፍን ጥላቻ ጉዳቶችን በጽናት እየተቋቋሙ መሆናቸው ያሳዝነኛል። በዛሬው ጊዜ በየትኛውም ቦታ ያሉ አባሎቻችን አመለካከትን እና የጭፍን ጥላቻ ድርጊቶችን ትተው በመውጣት እንዲመሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ለሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች አክብሮት እንዲያሳድጉ እለምናችኋለሁ።
ዘር ከዘር ሳይለይ ለእያንዳንዳችን የቀረበው ጥያቄ አንድ ነው። እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ እናንተ ፍቃደኞች ናችሁን? እግዚአብሔር በህይወታቸው በጣም ሃይለኛ ተጽዕኖ እንዲሆን እናንተ ፈቃደኞች ናችሁን? ቃላቶቹ፣ ትዕዛዛቱ፣ እና ቃል ኪዳኖቹ በየዕለቱ በምታደርጉት ነገር ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ትፈቅዳላችሁን? ድምጹ ከሌሎች ድምጽች በላይ ቅድሚያውን እንዲይዝ ትፈቅዱለታላችሁን? እርሱ እንድታደርጉ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ከሌላው ግብ ሁሉ በፊት ለማስቀደም ፈቃደኞች ናችሁን? የእናንተ ፍላጎት በእርሱ ውስጥ እንዲዋጥ ፍቃደኞች ናችሁን?18
እንዲህ አይነት ፈቃደኝነት እንዴት ሊባርካችሁ እንደሚችል አስቡ። ያላገባችሁ እና ዘላለማዊ ጓደኛ እየፈለጋችሁ ከሆነ፣ “ከእስራኤል” የመሆን ፍላጎታችሁ ከማን ጋር እና እንዴት እንደምትጠናኑ እንድትወስኑ ይረዳችኋል።
ቃል ኪዳኖችን ካፈረሰ ወይም ካፈረሰች የትዳር ጓደኛ ጋር የምትኖሩ ከሆነ፣ እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ ያላችሁ ፈቃደኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የገባችኋቸው ቃል ኪዳኖች ቋሚ እንዲሆኑ ያደርገዋል። አዳኝ የተሰበረ ልባችሁን ይፈውሳል። እንዴት ወደፊት ለመሄድ እንደምትችሉ ለማወቅ ስትሹ ሰማያት ይከፈታሉ። መባዘንም ሆነ መገረም አያስፈልጋችሁም።
ስለወንጌል ወይም ስለቤተክርስቲያኗ ቅን ጥያቄዎች ካሏችሁ፣ እግዚአብሔር እንዲያሸንፍ በምትፈቅዱበት ጊዜ ሕይወታችሁን የሚመሩ እና በቃል ኪዳኑ ጎዳና ላይ በጽናት እንድትቆዩ የሚረዷችሁን ፍጹም፣ ዘላለማዊ እውነቶች ወደማግኘት እና ወደመረዳት ትመራላችሁ።
ከፈተና ጋር በምትጋፈጡበት ጊዜ—ፈተናው የሚመጣው ሲደክማችሁ ወይም ብቸኝነት ሲሰማችሁ ወይም ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዷችሁ ቢሆንም እንኳን—እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ ስትፈቅዱ እና እንዲያጠነክራችሁ ስትማጸኑት ለማሰባሰብ የምትችሉትን ድፍረት አስቡ።
ትልቁ ፍላጎታችሁ እግዚአብሔር እንዲያሸንፍ፣ የእስራኤል አካል ለመሆን በሚሆንበት ጊዜ ብዙ ውሳኔዎች ቀላል ይሆናሉ። ብዙ ችግሮች ችግር የለሽ ይሆናል! ራሳችሁን እንዴት በተሻለ ሁኔታ እንደምታስተካክሉ ታውቃላችሁ። ምን መመልከት እና ማንበብ እንዳለባችሁ፣ ጊዜያችሁን የት ማሳለፍ እንዳለባችሁ እና ከማን ጋር መወዳጀት እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ። ምን ለማከናወን እንደምትፈልጉ ታውቃላችሁ። ምን አይነት ሰው ለመሆን እንደምትፈልጉ ታውቃላችሁ።
አሁን ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ እግዚአብሔር እንዲያሸንፈፍ ለመፍቀድ እምነት እና ድፍረት ይጠይቃል። ንስሐ በመግባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ በኩል ተፈጥሮአዊውን ሰው ለመተው የማያቋርጥ፣ ከባድ መንፈሳዊ ስራን ይጠይቃል።19 ወንጌልን ለማጥናት፣ ስለሰማይ አባት እና ስለኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ለማወቅ እንዲሁም የግል መገለጥን ለመፈለግ እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የግል ልምዶችን ለማዳበር ዘላቂነት ያለው፣ የቀን ተቀን ጥረትን ይጠይቃል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በተነበየላቸው በእነዚህ አደገኛ ጊዜያት፣20 ሰይጣን በእግዚአብሔር እቅድ ላይ የሚያደርገውን የማጥቃት ሙከራ ለመደበቅ እንኳን ጥረት አያደርግም። የማደፋፈር ድጋፍ ያገኘ ክፋት ተንሰራፍቷል። ስለዚህ፣ በመንፈሳዊ የመትረፍ ብቸኛው መንገድ ቢኖር እግዚአብሔር በህይወታችን እንዲያሸንፍ፣ ድምጹን መስማትን እንድንማር፣ እና ሃይላችንን እስራኤልን ለማሰባሰብ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆን ነው።
አሁን እግዚአብሔር እንዲያሸንፍ ስለሚፈልጉ ሰዎች ጌታ ምን ስሜት አለውው? ኔፊ በሚገባ አጠቃሎታል፥ “[ጌታ] አምላካቸው አድርገው የሚቀበሉትን ሰዎች ይወዳቸዋል። እነሆ እርሱ አባቶቻችንን ወደዳቸው፣ እናም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፣ አዎን፣ ለአብርሃም፣ ለይስሀቅ፣ እና ለያዕቆብ እንኳን፤ እናም የገባቸውን ቃል ኪዳኖች [አስታውሷል]።”21
እናም ጌታ ለእስራኤል ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ነው? ጌታ “[የእኛን] ጦርነት፣ እና እስከ ሶስት እና አራት ትውልድ፣ [የእኛን] ልጆች ጦርነት፣ እና [የእኛን] የልጅ ልጆች ጦርነት፣ … እንደሚዋጋ”ቃል ገብቷል!22
ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ቅዱሳት መጻህፍቶቻችሁን ስታጠኑ፣ እግዚአብሔር ለቃል ኪዳን እስራኤል የሰጠውን ቃል ኪዳኖች ዝርዝር እንድታዘጋጁ አበረታታችኋለሁ። ትደነቃላችሁ ብዬ አስባለሁ! እነዚህን ተስፋዎች አሰላስሉ። ከቤተሰባችሁ እና ከጓደኞቻችሁ ጋር ስለእነሱ ተነጋገሩ። ከዚያም ኑሩ እናም እነዚህ ተስፋዎች በሕይወታችሁ ውስጥ ሲፈጸሙ ተመልከቱ።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ ስትመርጡ አምላካችን “የተአምራት አምላክ” እንደሆነ ራሳችሁ ታዩታላችሁ።23 እንደህዝብ፣ እኛ የእርሱ የቃል ኪዳን ልጆች ነን፤ እናም በስሙ እንጠራለን። ይህንም በትህትና የምመሰክረው በቅዱሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።