ምዕራፍ ፲፱
ላሞኒ የዘለዓለማዊውን ህይወት ብርሃን አገኘ፣ እናም አዳኙን ተመለከተ—ቤተሰዎቹም ተመሰጡ፣ እናም ብዙዎች መላዕክትን ተመለከቱ—አሞን ተአምራት ሁኔታ ተጠበቀ—ብዙዎችን አጠመቀ፣ እናም በመካከላቸው ቤተክርስቲያኗን አቋቋመ። በ፺ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ከሁለት ቀናትና ከሁለት ምሽት በኋላ ሙታኖቻቸውን ለመቅበር ባዘጋጁት ስፍራ ሰውነቱን በመውሰድ በመካነ መቃብር ሊያሳርፉት ነበር።
፪ እንዲሁም ንግስቲቱ የአሞንን ዝና በመስማቷ፣ መልዕክተኛ ላከች እናም ወደ እርሷ እንዲመጣ ፈለገች።
፫ እናም እንዲህ ሆነ አሞን እንደታዘዘው አደረገና፣ ወደ ንግስቲቱ ሄደ፣ እርሱ ምን እንዲያደርግ እንደምትፈልገው ለማወቅም ፈለገ።
፬ እናም እርሷም አለችው፥ የባለቤቴ አገልጋዮች አንተ የቅዱሱ አምላክ ነቢይ መሆንህን አሳወቁኝ፣ እናም አንተ ብዙ ተአምራትን የማድረግ ኃይል እንዳለህም ነገሩኝ፤
፭ ስለዚህ፣ ሁኔታው ይህ ከሆነ፣ ባለቤቴን ሄደህ እንድትመለከተው እፈልጋለሁ፣ ምክንያቱም እርሱ ለሁለት ቀናትና ለሁለት ሌሊት በአልጋው ላይ ተኝቷልና፤ እናም አንዳንዶች አልሞተም ይላሉ፣ ነገር ግን ሌሎች ሞቷል እንዲሁም ሸቷል፤ እናም በመቃብሩ ማረፍ አለበት ይላሉ፤ ነገር ግን እንደ እኔ፣ ለእኔ አልሸተተኝም።
፮ እንግዲህ፣ ይህ አሞን የፈለገው ነበር፣ ምክንያቱም ንጉስ ላሞኒ በእግዚአብሔር ኃይል ስር እንደሆነ ያውቅ ነበርና፤ እርሱም ያለማመን ጥቁር መጋረጃው ከአዕምሮው እንደተወሰደ ያውቅ ነበር፣ እናም የእግዚአብሔር የክብር ብርሃን የሆነው፣ የቸርነቱ አስገራሚ ብርሃን የነበረው ብርሃን በአዕምሮው ውስጥ በርቷል—አዎን፣ ይህ ብርሃን በነፍሱ ውስጡ እንደዚያ ያለን ደስታ አምጥቷል፤ የጨለማው ዳመና ተበትኗል፣ እናም የዘለዓለማዊው ህይወት ብርሃን በነፍሱ ውስጡ ተቀጣጥሏል፤ አዎን፣ ይህ እራሱን እንዲስት እንዳደረገው አውቋል፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ተወስዷል—
፯ ስለዚህ፣ ንግስቲቱ ከእርሱ የፈለገችው የእርሱን ፍላጎት ብቻ ነበር። ስለዚህ፣ ንግስቲቱ እንደፈለገችው ንጉሱን ለመመልከት ሄደ፤ እናም ንጉሱን ተመለከተና ንጉሱ እንዳልሞተም አውቆ ነበር።
፰ እናም ለንግሥቲቱም አላት፥ እርሱ አልሞተም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ተኝቷል፣ እናም በማግስቱ በድጋሚ ይነሳል፤ ስለዚህ አትቅበሩት።
፱ አሞንም አላት፥ ይህን ታምኚአለሽን? እርሷም አለችው፥ ከአንተ ቃልና ከአገልጋዮቻችን ቃል በስተቀር ምንም ማረጋገጫ የለኝም፤ ይሁን እንጂ አንተ የተናገርከው እንደሚሆን አምናለሁ።
፲ አሞንም አላት፥ አንቺ በታላቁ እምነትሽ የተባረክሽ ነሽ፤ እኔም እልሻለሁ፣ አንቺ ሴት፣ በኔፋውያን ሁሉ መካከል እንደዚህ ያለ ታላቅ እምነት አልነበረም።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ከዚያ ሰዓት ጀምሮ አሞን ይነሳል ብሎ እስካለበት ሰዓት እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ የባሏን መኝታ ጠበቀች።
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ አሞን በተናገረው መሰረት ተነሳ፤ እናም በተነሳም ጊዜ እጁን በሴቲቱ ላይ ዘረጋና፣ አለ፥ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ነው፣ እንዲሁም አንቺም የተባረክሽ ነሽ።
፲፫ አንቺ ልክ በህይወት እንዳለሽ፣ እነሆ፣ አዳኜን አይቻለሁ፤ እናም እርሱ ይመጣል፣ ከሴትም ይወለዳል፣ እናም በስሙ የሚያምኑትን የሰው ዘር ሁሉ ያድናል። እንግዲህ፣ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ ልቡ በሀሴት ተሞላ፣ እንደገናም በደስታ ተዋጠ፣ እናም ንግስቲቱ ደግሞ በመንፈሱ በመሸነፏ ሰመጠች።
፲፬ እንግዲህ አሞን በወንድሞቹ በላማናውያን፣ በኔፋውያን መካከል እንዲሁም በእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ መካከል በክፋታቸውና በባህላቸው ታላቅ ሀዘን እንዲሆን ባደረጉት ላይ በፀሎት የጌታ መንፈስ በእነርሱ ላይ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ ተንበረከከ፣ እናም እግዚአብሔር ለወንድሞቹ ባደረገው በትጋት ፀለየ፣ እንዲሁም በምስጋና ነፍሱን አፍስሶ አቀረበ፤ እና እርሱም ደግሞ በደስታ ተዋጠ፤ ሶስቱም ወደ ምድር ወደቁ።
፲፭ እንግዲህ፣ የንጉሱ አገልጋዮች እንደወደቁ በተመለከቱ ጊዜ ወደ ጌታ መጮህ ጀመሩ፤ የጌታ ፍርሃት በእነርሱ ላይ ሆኗልና፤ በንጉሱ ፊት ቆመው ስለአሞን ታላቅ ኃይል የመሰከሩት እነርሱ ናቸውና።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ አባቷም በነበረው ታላቅ ራዕይ መሠረት ለብዙ ዓመታት ወደጌታ ከተለወጠችው አቢሽ ከተባለች ላማናዊት ሴት በስተቀር ሁሉም ወደ ምድር እስኪወድቁ ድረስ ባላቸው ሀይል በፀሎታቸው የጌታን ስም ጠሩ—
፲፯ ወደ ጌታ የተለወጠች በመሆኗና፣ እንዲታወቅ ባለማድረጓ የላሞኒ አገልጋዮች በሙሉ በመሬት ላይ መውደቃቸውን፣ እናም ደግሞ እመቤቷም፣ ንግስቲቱምና፣ ንጉሱ፣ እንዲሁም አሞን በመሬቱ ላይ መዘረሩን በተመለከተች ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን አውቃ ነበር፤ እናም ይህን ገምታ፣ ህዝቡን በመካከላቸው ምን እንደደረሰ በማሳወቅ ይህን አጋጣሚ ሰዎቹ ሲመለከቱ በእግዚአብሔር ኃይል እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል ብላ ገመተች፣ ስለዚህ ይህን ለህዝቡ ለማሳወቅ ከቤት ወደ ቤት ሮጠች።
፲፰ እናም ህዝቡ በንጉሱ ቤት ራሳቸውን በአንድ ላይ መሰብሰብ ጀመሩ። እናም ብዙዎች መጡና፣ ለመገረማቸው፣ ንጉሱን፣ ንግሥቲቱንና አገልጋዮቻቸው በመሬት ላይ እንደተዘረጉና፣ ሁሉም እንደሞተ በመሬት ላይ ተዘርግተው እንደነበር ተመለከቱ፤ ደግሞም አሞንን ተመለከቱት፣ እናም እርሱ ኔፋዊያን እንደነበረ ተመለከቱ።
፲፱ እናም አሁን ህዝቡ እርስ በርስ ማጉረምረም ጀመሩ፣ ጥቂቶች በእነርሱ ላይ እንዲሁም በንጉሱ ላይ እና በቤቱ ላይ እርሱ ኔፋውያን በምድሪቱ ላይ እንዲቀሩ ስለፈቀደ የመጣ ታላቁ ክፋት ነው አሉ።
፳ ነገር ግን ሌሎች እንዲህ በማለት ወቀሱአቸው፥ ንጉሱ ይህን ክፉ ነገር በቤቱ ላይ ያመጣው ራሱ ነው፣ ምክንያቱም በሲበስ ውሃ አካባቢ ከብቶቹን የተበተነባቸውን አገልጋዮቹን ገድሏልና።
፳፩ እናም ደግሞ እነርሱም የንጉሱ የሆኑትን ከብቶች ያባረሩት በውሃው አጠገብ በቆሙት ተወቀሱ፣ እናም በሲበስ ወንዝ አጠገብ የንጉሱን ከብቶች በሚጠብቅበት ጊዜ ብዙ ወንድሞቻቸውን ስለገደለባቸው በአሞን ተቆጥተውት ነበር።
፳፪ እንግዲህ፣ በአሞን ጎራዴ ወንድሙ ከተገደለበት አንዱ በአሞን በመቆጣቱ አሞንን ለመግደል ጎራዴውን አውጥቶ ሊያሳርፍበት ወደ እርሱ ሄደ፤ እናም ሊመታው ጎራዴውን ባነሳ ጊዜ፣ እነሆ፣ ሞቶ ወደቀ።
፳፫ አሁን ጌታ ለአባቱ ለሞዛያ፣ አድነዋለሁ፣ እናም እንደ እምነትህም ይሆንለታል ብሎታልና፣ አሞን ሊገደል እንደማይችል እንመለከታለን—ስለዚህ ሞዛያ እርሱን ለጌታ በአደራ ሰጥቷል።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ አሞንን ለመግደል ጎራዴውን ያነሳውን መሞቱን ህዝቦቹ በተመለከቱ ጊዜ፣ በሁሉም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፣ እናም፣ እርሱን ወይም እነዚያን የወደቁትን ለመንካት አልደፈሩም፤ የዚህ የታላቁ ኃይል መንስኤም ምን ሊሆን እንደሚችል፣ ወይም እነዚህ ነገሮች ሁሉ ምን ማለት ሊሆኑ እንደሚችሉ በድጋሚ እርስ በርስ መገረም ጀመሩ።
፳፭ እናም እንዲህ ሆነ አሞን ታላቅ መንፈስ ነው የሚሉ ብዙዎች በመካከላቸው ነበሩ፣ እናም ሌሎች በታላቁ መንፈስ ተልኳል ይሉ ነበር፤
፳፮ ነገር ግን ሌሎች እንዲህ በማለት ይወቅሱታል፣ እርሱም ከኔፋውያን እነርሱን ለመቅጣት የተላከ ጭራቅ ነበር።
፳፯ እናም ጥቂቶች አሞን በታላቁ መንፈስ በክፋታቸው የተነሳ እነርሱን ለማሰቃየት የተላከ ነው፤ እናም ሁልጊዜ ኔፋውያንን የሚጠብቅ፣ ከእጃቸው ምንጊዜም የሚያስለቅቃቸው ታላቅ መንፈስ ነው፤ እናም ይህ ታላቁ መንፈስ በጣም ብዙ የላማናውያን ወንድሞቻቸውን ያጠፋ ነው ይሉ ነበር።
፳፰ እናም ፀቡ በመካከላቸው እጅግ የከፋ መሆን ጀመረ። እናም በሚጣሉበት ጊዜ፣ ህዝቡ በአንድነት ተሰብስቦ እንዲመጣ ያደረገችው ሴት አገልጋይ መጣችና፣ በህዝቡ መካከል ፀብ መሆኑን በተመለከተች ጊዜ እምባ እስኪወጣት እንኳን እጅግ አዝና ነበር።
፳፱ እናም እንዲህ ሆነ ሄደችና ከመሬት ንግስቲቱ ትነሳ ዘንድ በእጇ አነሳቻት፤ እናም እጇን እንደነካቻት ተነሳችና፣ በእግሮችዋ ቆመች፣ በሀይለኛ ድምፅ እንዲህም ስትል ጮኸች፤ አቤቱ ከመጥፎ ሲኦል ያዳንከኝ የተባረከው ኢየሱስ! አቤቱ የተባረክህ እግዚአብሔር ሆይ፣ በዚህ ህዝብ ላይ ምህረትን አድርግ!
፴ እናም እርሷ ይህንን በተናገረች ጊዜ፣ በደስታ ተሞልታ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑትን ነገሮች በመናገር አጨበጨበች፤ ይህንንም ባደረገች ጊዜ ንጉስ ላሞኒን በእጆችዋ ያዘችው፣ እናም እነሆ ተነሳና በእግሮቹ ቆመ።
፴፩ እናም ወዲያው በህዝቡ መካከል ያለውን ፀብ በተመለከተ ጊዜ ሄደ፣ እነርሱንም ወቀሰና በአሞን አንደበት ተነግሮ የሰማውን ማስተማር ጀመረ፤ እናም ቃሉን ከሰሙት ብዙዎች አመኑና፣ ወደ ጌታ ተለወጡ።
፴፪ ነገር ግን ከእነርሱ መካከል ቃሉን መስማት ያልፈለጉ ብዙዎች ነበሩ፤ ስለዚህ በመንገዳቸው ሄዱ።
፴፫ እናም እንዲህ ሆነ አሞን በተነሳ ጊዜ ደግሞ እነርሱን አገለገለ፣ ደግሞም የላሞኒ አገልጋዮች ሁሉም እንዲህ አደረጉ፤ እናም ሁሉም ልባቸው እንደተለወጠ፣ ክፉ ለማድረግም ከእንግዲህ ፍላጎት እንደሌላቸው ለህዝቡ አንድ ዓይነት ነገር አወጁ።
፴፬ እናም እነሆ ብዙዎች ለሰዎቹ መላዕክትን እንደተመለከቱ ከእነርሱም ጋር እንደተነጋገሩ ተናገሩ፣ እና እንደዚህም የእግዚአብሔርን ነገሮች፣ ፃድቅነቱንም ነገሩአቸው።
፴፭ እናም እንዲህ ሆነ ቃላቸውን ያመኑ ብዙዎች ነበሩ፤ እናም ብዙ ያመኑት ተጠመቁ፤ ፃድቅ ሰዎችም ሆኑና፣ በመካከላቸው ቤተክርስቲያኗን አቋቋሙ።
፴፮ እናም የጌታ ስራ በላማናውያን መካከል ተጀመረ፤ እንደዚህም ጌታ መንፈሱን በእነርሱ ላይ ማፍሰሱን ጀመረ፤ እናም ንስሃ በሚገቡ ሰዎችና በስሙ ለሚያምኑት ህዝብ ሁሉ ክንዱ መዘርጋቱን እንመለከታለን።