የመፅሐፈ ሞርሞን ኃይል
እያንዳንዳችን መፅሐፈ ሞርሞንን በየቀኑ በጸሎት እንድናጠና እና እንድናሰላስል እለምናችኋለሁ።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህ ታላቅ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የጉባኤ አዳራሽ ውስጥ እንደገና በምንገናኝበት በሙቀት ሰላምታ እሰጣችኋለሁ። ዛሬ ቀጥተኛ ንግግሬን ከመጀመሬ በፊት፣ በሚመጡት ወራና ዓመታት ውስጥ በሚከተሉት ቦታዎች የሚገነቡትን አራት አዳዲስ ቤተ-መቅደሶችን ማሰተዋወቅ እወዳለሁ፥ ብራዚሊያ፣ ብራዚል፤ ታልቁ የማኒላ፣ ፊሊፒንስ ክልል፤ ናይሮቢ፣ ኬንያ፤ ፖከቶሎ፣ አይደሆ፣ ዮ.ኤስ.ኤ፤ እና ሴረቶጋ ስፕሪንግ፣ ዩታ፣ ዩ.ኤስ.ኤ።
በዚህ ጠዋት ስለመፅሐፈ ሞርሞን ሀይል እና በዚህች ቤተክርስቲያን አባላት ይህን ስለማጥናት፣ ስለማሰላሰል፣ እና የዚህንም ትህምርት በህይወታችን ውስጥ ስለመጠቀም አስፈላጊነት እናገራለሁ። በመፅሐፈ ሞርሞን ጥብቅ እና እርግጠኛ ምስክርነት የመኖር አስፈላጊነት ሊጋነን አይችልም።
በታላቅ ችግር እና ክፋት ጊዜ ነው የምንኖረው። በአለም በብዛትከሚገኘው ከኃጢያት እና ከክፉ ምን ሊጠብቀን ይችላል? የአዳኛችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ፣ እና የእርሱ ወንጌል ጠንካራ ምስክርነት ደህንነትን እንድንገነዘብ ይረዳናል። መፅሐፈ ሞርሞንን በየቀኑ የማታነቡ ከሆናችሁ፣ ይህን እባካችሁ አድርጉ። በጸሎት እና እውነትን ለማወቅ ባለ ቅን ፍላጎት የምታነቡት ከሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ እውነቱን ይገልጽላችኋል። ይህም እውነት ከሆነ—እና ይህ እውነት እንደሆነ እመሰክራለሁ—ከዚያም ጆሴፍ ስሚዝ እግዚአብሔር አብን እና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየ ነብይ ነው።
መፅሐፈ ሞርሞን እውነት ስለሆነ፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በምድር ላይ የጌታ ቤተክርስቲያን ነው፣ እናም የእግዚአብሔር ቅዱስ ክህነት ለልጆቹ ጥቅም እና በረከት በዳግም ተመልሷል።
ስለእነዚህ ነገሮች ጥብቅ ምስክሮች ከሌላችሁ፣ ይህን ለማግኘት አስፈላጊ የሆነውን አድርጉ። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜዎች የራሳችሁ ምስክርነት ማግኘታችሁ አስፈላጊ ነው፣ የሌሎች ምስክርነቶች የተወሰነ እርዳታ ነው የሚሰጣችሁና። ይህም ቢሆን፣ ካገኛችሁት በኋላ፣ ምስክርነት በእግዚአብሔር ትእዛዛት ታዛዥነት እና በየቀኑ ጸሎት እና የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት በኩል ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በጌታ ስራ ውስጥ ውድ ጓደኞቼ፣ እያንዳንዳችን መፅሐፈ ሞርሞንን በየቀኑ በጸሎት እንድናጠና እና እንድናሰላስል እለምናችኋለሁ። ይህን ስናደርግ፣ የመንፈስ ድምፅን ለመስማት፣ ፈተናዎችን ለመቋቋም፣ መጠራጠርና ፍርሀትን ለማሸነፍ፣ እና በህይወታችን ውስጥ የሰማይ እርዳታን ለመቀበል በምንችልበት ቦታ ላይ እንገኛለን። በልቤ በሙሉ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።