ምዕራፍ ፮
ያዕቆብ እንደገና የአይሁዶችን ታሪክ ተረከ፥ ስለባቢሎን ምርኮና መመለስ፤ ስለእስራኤሉ ቅዱስ አገልግሎትና ስቅለት፤ ከአህዛብ እርዳታን ስለማግኘታቸው፤ እና አይሁዶች በኋለኛው ቀን በመሲሁ ሲያምኑ ዳግሞ መመለሳቸውን። ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ የኔፊ ወንድም ያዕቆብ ለኔፊ ህዝብ የተናገራቸው ቃላት—
፪ እነሆ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ በእግዚአብሔር የተጠራሁትና በቅዱስ ስርዓቱን መሰረት ሹመትን ያገኘሁት፣ እናም እርሱን እንደ ንጉስ ወይም ተከላካይ በምታምኑትና፣ በእርሱ ለጥበቃችሁ ተስፋ በምታደርጉ በወንድሜ ኔፊ የተቀባሁት እኔ ያዕቆብ፣ እነሆ፣ እኔ እጅግ ብዙ ነገሮችን እንደተናገርኳችሁ ታውቃላችሁ።
፫ ሆኖም እኔ እንደገና እናገራችኋለሁ፤ ምክንያቱም ለነፍሳችሁ ደህንነት ፍላጎት አለኝና። አዎን፣ ለእናንተ ጭንቀቴ ታላቅ ነው፤ እናም እናንተ ሁልጊዜ ይህ እንደሚሆን ታውቃላችሁ። እኔ በሙሉ ትጋት መክሬአችኋለሁ፤ እናም የአባቴን ቃል አስተምሬአችኋሁ፤ እናም ከዓለም መፈጠር ጀምሮ ሁሉንም የተፃፉ ነገሮች በተመለከተ አነጋግሬአችኋለሁ።
፬ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ስላሉትና ስለሚመጡት ነገሮች እነግራችኋለሁ፤ ስለዚህ፣ የኢሳይያስን ቃል አነብላችኋለሁ። እናም እነርሱ ወንድሜ ለእናንተ እንድናገር የፈለጋቸው ቃላት ናቸው። እናም የምናገራችሁ ለእናንተ ጥቅም፣ እናንተ አምላካችሁን ታውቁትና ስሙንም ታወድሱ ዘንድ ነው።
፭ እናም አሁን እኔ የማነባቸው ቃላት ኢሳይያስ የእስራኤልን ቤት በተመለከተ የተናገራቸው ናቸው፤ ስለሆነም፣ ከእናንተም ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፣ ምክንያቱም እናንተ ከእስራኤል ቤት ናችሁና። እናም ከእስራኤል ቤት ስለሆናችሁ በኢሳይያስ የተነገሩ ለእናንተ የሚተገበሩ ብዙ ነገሮች አሉ።
፮ እናም አሁን፣ ቃላቱ እነዚህ ናቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል—እነሆ እጄን ወደ አህዛብ አነሳለሁ፣ አርማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በክንዳቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ይሸከሟቸዋል።
፯ ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፣ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ፊታቸውን ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፣ የእግራችሁንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እናም እኔ ጌታ መሆኔን ታውቂያለሽ፤ እኔን የጠበቁ አያፍሩምና።
፰ እናም አሁን እኔ ያዕቆብ እነዚህን ቃላት በተመለከተ በመጠኑ እናገራለሁ። እነሆም ጌታ እኛ ከመጣንበት በኢየሩሳሌም የነበሩት እንደተገደሉና በምርኮ እንደተወሰዱ አሳይቶኛል።
፱ ሆኖም፣ ጌታ እነርሱ እንደገና እንደሚመለሱ አሳይቶኛል። እናም ደግሞ ጌታ እግዚአብሔር፣ የእስራኤሉ ቅዱስ፣ በስጋ እራሱን እንደሚገልፅላቸው፤ እናም መልአኩ ለእኔ በተናገረው ቃል መሠረት፣ እራሱን ከገለፀ በኋላ ይገርፉታልም ይሰቅሉታልም።
፲ እናም በእስራኤሉ ቅዱስ ላይ ልባቸውን ካጠጠሩና አንገታቸውን ካደነደኑ በኋላ፣ እነሆ፣ የእስራኤል ቅዱስ ፍርድ በእነርሱ ላይ ይመጣል። እናም እነርሱ የሚቀጡበትና የሚሰቃዩበት ቀን ይመጣል።
፲፩ ስለሆነም፣ መላኩ እንዳለው፣ ወዲህና ወዲያ እንዲዘዋወሩ ከተደረጉ በኋላ፣ ብዙዎቹ በስጋ ይሰቃያሉ፣ በታማኝ ፀሎቶች የተነሳም እንዲጠፉ አይደረጉም፤ እነርሱ ይበተናሉ፣ ይገረፋሉ፣ እናም ይጠላሉ፤ ይሁን እንጂ፣ ጌታ ለእነርሱ መሀሪ ይሆናል፣ መድኃኒታቸውንም ሲያውቁት ወደ ርስት ምድራቸው በድጋሚ በአንድ ላይ ይሰበሰባሉ።
፲፪ እናም ነቢያት የፃፉላቸው አህዛብ የተባረኩ ናቸው፤ እነሆም፣ እነርሱ ንስሀ ከገቡና ከፅዮን ካልተዋጉ፣ እና እራሳቸውን ከታላቋና የርኩሰት ቤተክርስቲያን አንድ ካላደረጉ ይድናሉ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለልጆቹ የገባውን ቃል ኪዳን ይፈፅማልና፤ እናም ለዚህ ነው ነቢዩ እነዚህን ነገሮች የፃፈው።
፲፫ ስለዚህ፣ ከፅዮን ጋርና ከጌታ የቃል ኪዳን ህዝብ ጋር የሚዋጉ የእግሮቻቸውን ትቢያ ይልሳሉ፤ እናም የጌታ ህዝቦች አያፍሩም። የጌታ ህዝቦች እርሱን የሚጠብቁ ናቸውና፤ አሁንም የመሲሁን መምጣት ይጠብቃሉና።
፲፬ እናም እነሆ፣ በነቢዩ ቃላት መሠረት መሲሁ ለሁለተኛ ጊዜ እነርሱን ለማደስ እንደገና ይጀምራል፤ ስለዚህ፣ በእርሱ የሚያምኑበት ያ ቀን ሲመጣ፣ እራሱን በኃይልና በታላቅ ክብር ጠላታቸውን በመደምሰስ ይገልፃል፤ እናም በእርሱ የሚያምኑትን አንዳቸውንም አያጠፉም።
፲፭ እናም በእርሱ የማያምኑ በእሳትና፣ በአውሎ ነፋስ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና፣ በደም መፍሰስ፣ በቸነፈር፣ በረሀብና፣ በድርቅ ይጠፋሉ። እናም ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ መሆኑን ያውቃሉ።
፲፮ አደን ከሃያሉ ይወሰዳልን፣ ወይስ የህጋዊ ምርኮኞች ያመልጣሉን?
፲፯ ነገር ግን ጌታ እንዲህ ይላል፥ በኃያላን የተማረኩትም እንኳን ይወሰዳሉ፣ የጨካኞችም አደን ያመልጣል፤ ኃያሉ አምላክ የቃል ኪዳን ህዝቡን ያድናልና። ጌታም እንዲህ ይላል፥ ከእናንተ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ—
፲፰ እናም አስጨናቂዎችሽን ስጋቸውን አስበላቸዋለሁ፤ እናም እንደጣፋጭ ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ፤ እናም ስጋ ለባሹም ሁሉ እኔ ጌታ መድኃኒትሽና ቤዛሽ የያዕቆብ ኃያል እንደሆንኩ ያውቃሉ።