ምዕራፍ ፳፯
ኢየሱስ ቤተክርስቲያኗን በስሙ እንዲጠሩ አዘዛቸው—ወንጌሉም አገልግሎቱንና የኃጢያት ክፍያውን የያዘ ነው—ሰዎች በመንፈስ ቅዱስም ይነፁ ዘንድ ንሰሃ እንዲገቡና እንዲጠመቁ ታዘዋል—ኢየሱስ እንደሚሆነውም ይሁኑ። ከ፴፬–፴፭ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በተጓዙበት እናም ስለተመለከቱአቸውና ስለሰሙአቸው ነገሮች በሰበኩበትና፣ በኢየሱስ ስም ባጠመቁበት ወቅት፣ እንዲህ ሆነ ደቀመዛሙርቱ በአንድ ላይ ተሰባስበው ነበር፣ እናም በብርቱ ፀሎታቸውና ፆማቸው አንድ ሆነው ነበር።
፪ እናም ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ ወደ አብ በስሙ በመፀለያቸው በድጋሚ ራሱን አሳያቸው፤ እናም ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆመ፣ እንዲህም አላቸው፥ ምን እንድሰጣችሁ ትፈልጋላችሁ?
፫ እናም እንዲህ አሉት፥ ጌታ ይህንን ቤተክርስቲያን የምንጠራበትን ስም እንድትነግረን እንፈልጋለን፤ ምክንያቱም ይህንን በተመለከተ በህዝቡ መካከል ጥል አለና።
፬ እናም ጌታም እንዲህ አላቸው፥ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ህዝቡ ስለዚህ ነገር ለምን ያጉረመርማል እንዲሁም ይጣላል?
፭ ስሜ የሆነውን፣ የክርስቶስን ስም በእራሳቸው ላይ መውሰድ እንዳለባቸው ቅዱሳን መጻሕፍትን አላነበቡምን? በዚህ ስም በመጨረሻው ዘመን ትጠሩበታላችሁና፤
፮ እናም ስሜን በራሱ ላይ የወሰደና፣ እስከመጨረሻው በዚህ የፀና በመጨረሻው ዘመን እርሱ ይድናል።
፯ ስለዚህ፣ ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ በስሜ አድርጉት፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያኗን በስሜ ጥሯት፤ እናም ወደ አብም በስሜ ፀልዩ እርሱም ለእኔም ሲል ቤተክርስቲያኗን ይባርካታል።
፰ እናም በስሜ ካልተጠራ የእኔ ቤተክርስቲያን እንዴት ሊሆን ይችላል? ቤተክርስቲያኗ በሙሴ ስም ከተጠራች የሙሴ ቤተክርስቲያን ትሆናለች፤ ወይም በሰው ስም ከተጠራች የሰው ቤተክርስቲያን ትሆናለች፤ ነገር ግን በወንጌሌ ላይ የተገነቡ ከሆኑ፣ በስሜ ከተጠራች የእኔ ቤተክርስቲያን ትሆናለች።
፱ እውነት እላችኋለሁ፣ በወንጌሌ ላይ ታንፃችኋል፤ ስለዚህ የምታደርጉትን ማንኛውንም ነገር በስሜ ትጠራላችሁ፤ ስለዚህ ለቤተክርስቲያኗ ወደ አብ በስሜ ከፀለያችሁ አብ ይሰማችኋል፤
፲ እናም ቤተክርስቲያኗ በወንጌሌ ላይ ከታነፀች አብም ስራውን ይገልፅባታል።
፲፩ ነገር ግን በወንጌሌ ላይ ካልታነፀች፣ እናም በሰዎች ስራ ላይ፣ ወይም በዲያብሎስ ስራ ላይ ከታነፀች፣ እውነት እላችኋለሁ ለጊዜው በስራቸው ደስታን ያገኛሉ፣ እናም ከጥቂት ጊዜም በኋላ ፍፃሜአቸው ይመጣልም፣ እናም ይፈረካከሳሉም፣ መመለስ በማይቻልበት እሳት ውስጥም ይወድቃሉ።
፲፪ ስራቸው ይከተላቸዋልና፣ በስራቸው ምክንያትም ተቆርጠው ወድቀዋልና፤ ስለዚህ የነገርኳችሁን ነገሮች አስታውሱ።
፲፫ እነሆ ወንጌሌን ሰጥቻችኋለሁ፣ እናም ለእናንተ የሰጠኋችሁ ወንጌልም ይህ ነው—ወደ ዓለም የመጣሁት የአባቴን ፈቃድ ለመፈፀም ነው፣ ምክንያቱም አባቴ ልኮኛልና።
፲፬ አባቴም በመስቀል እሰቀል ዘንድ ልኮኛል፤ እናም በመስቀል ላይ ከተሰቀልኩ በኋላ፣ ሰዎችን ሁሉ ወደ ራሴ አመጣ ዘንድ፣ እኔ በሰዎች እንደተሰቀልኩ በአብ አማካኝነት ሰዎች ይነሱ ዘንድ፣ መልካምም ይሁኑ መጥፎ በስራቸው እንዲፈረድባቸው በእኔ ፊት ለመቆም ይችሉ ዘንድ፣ ተሰቅያለሁ—
፲፭ እናም ለዚህም ምክንያት ተሰቀልኩኝ፤ ስለዚህ፣ በአብ ስልጣን መሰረት ሰዎች በሙሉ በስራቸው ይፈረድባቸው ዘንድ ወደ እኔ እንዲመጡ አደረግሁ።
፲፮ እናም እንዲህ ይሆናል ማንኛውም ንሰሃ የገባና በስሜ የተጠመቀ ይሞላል፤ እናም እስከመጨረሻው ከፀናም እነሆ ዓለምን የምፈርድበት ቀን ስትመጣ በአብ ፊት ከበደል የነፃ አደርገዋለሁ።
፲፯ እናም እስከመጨረሻው ፀንቶ የማይቀጥል ግን በአብ ፍትህ የተነሳ፣ ተቆርጦ መጨረሻ ወደሌለው፣ ወደእሳቱ የሚጣል እርሱ ነው።
፲፰ እናም ለሰው ልጆች የሰጣት ይህች ቃል ናት። እናም በዚህ የተነሳ የተሰጠውን ቃላት ይፈፅማል፣ እናም አይዋሽም፣ ነገር ግን ቃሉን በሙሉ ይፈፅማል።
፲፱ እናም በመንግስተ ሰማይ ምንም እርኩስ ነገር ሊገባ አይቻለውም፤ ስለዚህ በእምነታቸው እናም ለኃጢአታቸው ሁሉ ንሰሃ በመግባታቸውና እስከመጨረሻው ባላቸው ታማኝነት በደሜ ልብሳቸውን ካጠቡት በስተቀር በእረፍቱ የሚገባ ማንም የለም።
፳ እንግዲህ ትዕዛዜ ይህች ናት፥ በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ ንሰሃ ግቡ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ትቀደሱ ዘንድ፤ በመጨረሻው ቀን በፊቴ ያለእንከን ትቆሙ ዘንድ ወደ እኔ ኑ፣ እናም በስሜ ተጠመቁ።
፳፩ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ የእኔ ወንጌል ነው፤ እናም በቤተክርስቲያኔም መስራት ያለባችሁንም ነገሮች ታውቃላችሁና፤ እኔ ስሰራው ያያችሁትን ስራ እናንተም ደግሞ ስሩ፤ ስሰራ ያያችሁትን ስራ እናንተም ያን ታደርጋላችሁ፤
፳፪ ስለዚህ፣ እነዚህን ነገሮች ከሰራችሁ የተባረካችሁ ናችሁ፣ በመጨረሻው ቀን ከፍ ትላላችሁና።
፳፫ ከተከለከሉት በስተቀር ስላያችኋቸው እናም ስለሰማችኋቸው ነገሮች ፃፉ።
፳፬ ወደ ፊት የሚሆን የእነዚህን ሰዎች ስራ ቀድሞ እንደነበረው አድርጋችሁ ፃፉት።
፳፭ እነሆም፣ ከተፃፉት እናም ከሚፃፉት መጽሐፍት ይህ ህዝብ ይፈረድበታል፣ ምክንያቱም በእነርሱ አማካኝነት ስራዎቻቸው ለሰዎች ይታወቃሉና።
፳፮ እናም እነሆ፣ ሁሉም ነገሮች በአብ ተጽፈዋል፤ ስለዚህ በተፃፉት መጽሐፍት መሠረትም ዓለም ይፈረድበታል።
፳፯ እናም ጻድቅ በሚሆነው ለእናንተ በሰጠኋችሁ ፍርድ መሰረት በዚህ ህዝብ እንደምትፈረዱባቸው ታውቃላችሁ። ስለዚህ፣ እናንተ ምን ዐይነት ሰዎች መሆን ይገባችኋል? እውነት እላችኋለሁ እንደ እኔ ሁኑ።
፳፰ እናም እንግዲህ ወደ አብ እሄዳለሁ። እናም እውነት እላችኋለሁ፣ አብን ማናቸውንም ነገሮች በስሜ ብትጠይቁት ለእናንተ ይሰጣችኋል።
፳፱ ስለዚህ፣ ለምኑ፣ እናም ይሰጣችኋል፤ አንኳኩ እናም ይከፈትላችኋል፤ የሚጠይቅ ያገኛልና፤ እናም ለሚያንኳኳም ይከፈትለታልና።
፴ እናም እንግዲህ፣ እነሆ፣ በእናንተና ደግሞ በዚህ ትውልድ ምክንያት ሙሉ እስከሚሆን ድረስ ደስታዬ ታላቅ ነው፤ አዎን፣ እናም በእናንተና በዚህ ትውልድ ምክንያት አብና ደግሞ ቅዱስ የሆኑ መላዕክቶች ሁሉ ተደስተዋል፤ ምክንያቱም ከእነርሱም ማንም አልጠፋምና።
፴፩ እነሆ፤ ምክንያቱም በዚህ ትውልድ በህይወት ስላሉት ስለእነርሱ እንደተናገርኩ እንድትረዱ እፈልጋለሁ፣ እናም ማናቸውም አይጠፉም፤ እናም በእነርሱ ሙሉ ደስታዬን አግኝቻለሁ።
፴፪ ነገር ግን እነሆ፣ ከዚህ ትውልድ አራተኛው ትውልድ ልክ በጥፋት ልጅም እንደሆነው በምርኮ ስለሚወሰዱ፣ እኔን አሳዝኖኛል፤ ምክንያቱም እነርሱ ለብርና ለወርቅ፣ እናም በብልም ለሚበላሸውና ሌቦች ሊሰብሩትና ሊሰርቁት ለሚችሉት ይሸጡኛል። እናም በዚያን ቀን ስራቸውንም በራሳቸው ላይ በመመለስ እጎበኛቸዋለሁ።
፴፫ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ይህንን ንግግሩን በጨረሰበት ወቅት ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፥ በጠበበው ደጅ ግቡ፤ እናም ወደ ህይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ስለሆነ፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸውና፤ ነገር ግን ወደ ሞት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነው፣ እናም ምሽቱ እስከሚመጣ ሰዎችም መስራት እስከማይችሉበት ድረስ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙ ናቸው።