ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፳፰


ምዕራፍ ፳፰

ከአስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ዘጠኙ ሲሞቱ የክርስቶስን መንግስት ለመውረስ ፈለጉ እናም ቃል ተገብቶላቸዋል—ሦስቱ ኔፋውያን ክርስቶስ በድጋሚ ወደ ምድር እስከሚመጣ በምድር ላይ ለመቆየት ፈለጉና በሞት ላይም ስልጣን ተሰጣቸው—እነርሱም ተለውጠዋልና ሊነገሩ የማይገቡ ነገሮችን አዩ፣ እናም አሁን በሰዎች መካከል እያገለገሉ ናቸው። ከ፴፬–፴፭ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርት እንዲህ ሲል አንድ በአንድ ተናገራቸው፥ ወደ አባቴ ከሄድኩኝ በኋላ ከእኔ የምትፈልጉት ምንድነው?

እናም ከሦስቱ በስተቀር ሌሎች በሙሉ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፥ አንድ ሰው በህይወት የሚቆይበትን ያህል ጊዜ ከቆየን በኋላ፣ በአንተም የተጠራንበት አገልግሎታችን መጨረሻው ሲሆን፣ በፍጥነትም ወደአንተ መንግስትም እንመጣ ዘንድ እንፈልጋለን።

እናም እርሱም አላቸው፥ ከእኔ ይህን ነገር በመፈለጋችሁ እናንተ የተባረካችሁ ናችሁ፤ ስለዚህ፣ ሰባ ሁለት ዓመት ከሆናችሁ በኋላ ወደ መንግስቴም ትመጣላችሁ፤ እናም ከእኔ ጋር እረፍትንም ታገኛላችሁ።

እናም እነርሱን በተናገራቸው ጊዜም፣ ወደ ሦስቱ መለስ አለና እንዲህ አላቸው፥ ወደ አባቴ ስሄድ ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?

እናም የፈለጉትንም ለእርሱ ለመናገር ባለመድፈራቸው በልባቸው አዝነው ነበር።

እናም እርሱ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ያሰባችሁትን አውቃለሁ፣ እናም እኔም በአይሁዶች ከመሰቀሌ በፊት በአገልግሎቴ ወቅት ከእኔ ጋር የነበረውን የተወደደው ዮሐንስ የፈለገውን ነገር ፈልጋችኋል።

ስለዚህ፣ እናንተ ይበልጥ የተባረካችሁ ናችሁ፣ ሞትን በጭራሽ አትቀምሱምና፤ ነገር ግን በአብ ፈቃድ መሰረት ሁሉም ነገሮች ይፈጸሙ ዘንድ በክብር በሰማይ ኃይል እስከምመጣ ድረስ ለሰው ልጆች የሚያደርጋቸውን የአብን ስራዎች በሙሉ ለመመልከት ትኖራላችሁ።

እናም የሞት ስቃይ በጭራሽ አይደርስባችሁም፤ ነገር ግን በክብር በምመጣበት ወቅት ከሟችነት ሟች ወዳልሆነው በቅጽበት ትለወጣላችሁ፤ እናም በአባቴም መንግስት የተባረካችሁ ትሆናላችሁ።

እናም በድጋሚ፣ በስጋ በምትቆዩበት ወቅትም ህመምን፣ ለዓለምም ኃጢያት ካልሆነ በቀር ሀዘን አታውቁም፤ እናም ይህንን ሁሉ የማደርገው ከእኔ በፈለጋችሁት ነገሮች ምክንያት ነው፤ ምክንያቱም ዓለም እንዳለች በቆየችበት ወቅት ነፍሳትን ወደእኔ ለማምጣት ፈልጋችኋልና።

እናም በዚህ የተነሳ ደስታችሁ ሙሉ ይሆናል፤ በአባቴም መንግስት ትቀመጣላችሁ፤ አዎን አብም ሙሉ ደስታን እንደሰጠኝ ደስታችሁ ሙሉ ይሆናል፤ እናም እኔ እንደአባቴ እንደሆንኩ እናንተም እንደ እኔ ትሆናላችሁ፣ እናም አብና እኔም አንድ ነን፤

፲፩ እናም መንፈስ ቅዱስም ስለአብና ስለእኔ ይመሰክራል፤ አብም በእኔ የተነሳ መንፈስ ቅዱስን ለሰው ልጆች ይሰጣል።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም እነዚህን ቃላት በተናገረበት ወቅት፣ በምድር ላይ ከሚቆዩት ከሦስቱ በስተቀር፣ እያንዳንዳቸውን በጣቱ ነካ እናም ሔደ።

፲፫ እናም እነሆ፣ ሰማያት ተከፈቱና፣ እነርሱ ወደሰማይ ተነጠቁና ለመነገር የማይችሉ ነገሮችን ተመለከቱ፣ እናም ሰሙ።

፲፬ እናም እንዳይናገሩም ተከልክለው ነበር፤ የተመለከቷቸውንና የሰሟቸውን ነገሮች ለመናገር እንዲችሉ ስልጣንም አልተሰጣቸውም፤

፲፭ እናም በስጋም ሆነ ከስጋ ውጪ መሆናቸውን ለማወቅ አልቻሉም፤ የእግዚአብሔር የሆኑትን ነገሮች ለመመልከት እንዲችሉ ለእነርሱ ከስጋዊ ሰውነት ሟች ወዳልሆነው ሰውነት የተለወጡ መሰላቸው።

፲፮ ነገር ግን እንዲህ ሆነ በድጋሚ በምድረ ገጽ ላይ ያገለግሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ በሰማይ በተሰጣቸው ትዕዛዝ ምክንያት ስለሰሙአቸው እናም ስለተመለከቱአቸው ነገሮች አላስተማሩም።

፲፯ እናም እንግዲህ፣ ከተለወጡበት ጊዜ ጀምሮ ሟችም ሆኑ የማይሞቱ እኔም አላውቅም፤

፲፰ ነገር ግን በተሰጡት ታሪክ መሰረት ይህን ያህል አውቃለሁ—እናም ህዝቡን ሁሉ በማስተማር፣ በሰበካቸው የሚያምኑ ብዙዎችን ከቤተክርስቲያኗ ጋር በማቀላቀል፣ በማጥመቅ በምድር ገጽ ተጉዘዋል፣ እናም የተጠመቁም ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል።

፲፱ እናም ከቤተክርስቲያኗ ባልሆኑት ወደ ወህኒ ተጥለዋል። እናም ሁለት ቦታም በመከፈላቸው እስር ቤቶቹም ሊይዟቸው አልቻሉም።

እናም ወደ ምድርም ውስጥ ተጣሉ፤ ነገር ግን ምድሪቱንም በእግዚአብሔር ቃል መቱ፤ በዚህም በኃይሉ ከመሬቱ ጥልቅ ድነው ነበር፤ እናም እነርሱን በበቂ ሁኔታ ሊይዝ የሚችል ጉድጓድ ለመቆፈር አልቻሉም።

፳፩ እናም ሦስት ጊዜም በእቶኑ ውስጥ ተወረወሩ፣ እናም ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም።

፳፪ እናም ሁለት ጊዜ በዱር አውሬ ዋሻ ተጣሉ፤ እናም እነሆ ልጅ ከሚጠባ የበግ ጠቦትጋር እንደሚጫወተው ከአውሬዎች ጋር ይጫወቱ ነበር፣ እናም ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ሰዎች መካከል ሔዱና፣ በምድረ ገጽ ላይም ለሁሉም ሰዎች የክርስቶስን ወንጌል አስተማሩ፤ እናም እነርሱ ወደ ጌታ ተለወጡና፣ ከክርስቶስ ቤተክርስቲያንም ጋር ተቀላቀሉ፣ እንደ ኢየሱስ ቃልም ያ ትውልድ በሙሉ እንደዚህ ተባርኮ ነበር።

፳፬ እናም እንግዲህ እኔ ሞርሞን፣ ለጊዜው እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ንግግሬን አቆማለሁ።

፳፭ እነሆ፣ ሞትን ቀምሰው የማያውቁትን ሰዎች ስማቸውን ልፅፍ ነበር፣ ነገር ግን ጌታ ከለከለኝ፤ ስለዚህ ከዓለም ተደብቀዋልና ስማቸውን አልጽፍም።

፳፮ ነገር ግን እነሆ፣ እኔ አይቻቸዋለሁ፣ እናም እኔንም አስተምረውኛል።

፳፯ እናም እነሆ ከአህዛብ መካከል ይሆናሉ፣ አህዛብም አያውቋቸውም።

፳፰ ደግሞም ከአይሁዶች መካከል ይሆናሉ፣ እናም አይሁዶችም አያውቋቸውም።

፳፱ እናም እንዲህ ይሆናል፣ ፍላጎታቸው ይሟላ ዘንድና ደግሞም በውስጣቸው ባለው አሳማኝ በሆነው የእግዚአብሔር ኃይል ምክንያት፣ ጌታ በጥበቡ ብቁ መሆኑን በሚመስለው፣ ለተበተኑት የእስራኤል ነገዶች በሙሉና፣ ለሁሉም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ህዝብ ያገለግላሉ፣ እናም ደግሞ ከመካከላቸው ብዙ ነፍሳትን ወደ ኢየሱስ ያመጣሉ።

እናም እነርሱም እንደ እግዚእብሔር መላዕክቶች ናቸው፤ እናም በኢየሱስ ስም ወደ አብ ከጸለዩ መልካም በሚመስላቸው ለማንኛውም ሰው እራሳቸውን ለማሳየት ይችላሉ።

፴፩ ስለዚህ፤ ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት በእርግጥ መቆም ከሚገባቸው ከታላቁ እና ከሚመጣው ቀን በፊት፣ ታላቅ እንዲሁም ድንቅ ስራዎች በእነርሱ ይከናወናሉ፤

፴፪ አዎን ከፍርድ ቀን በፊት እንኳን በአህዛብ መካከል በእነርሱ አማካኝነት ታላቅ እና ድንቅ ስራ ይሰራል።

፴፫ እናም የክርስቶስን ድንቅ ስራዎች ታሪክ በሙሉ የሚናገሩት ቅዱሳን መጻሕፍት ካሉአችሁ፣ በክርስቶስ ቃላት መሰረት እነዚህ ነገሮች በእርግጥ እንደሚመጡ ታውቃላችሁ።

፴፬ እናም የኢየሱስንና ደግሞ እርሱ የመረጣቸውንና በመካከላቸው የላካቸውን ቃላት ለማያዳምጡ ወዮላቸው፤ የኢየሱስን ቃላትና የላካቸውን ቃላት የማይቀበሉ እርሱንም አይቀበሉም፤ እናም ስለዚህ እርሱም በመጨረሻው ቀን አይቀበላቸውም፤

፴፭ እናም እነርሱ ባይወለዱ ይሻላቸው ነበር። ደህንነት ለማምጣት በሰዎች እግር ስር የተረገጠውን እግዚአብሔር ቁጣ ፍርድ ለማስወገድ ይቻላል ብላችሁ ትገምታላችሁን?

፴፮ እናም እንግዲህ እነሆ፣ ጌታ ስለመረጣቸው፣ አዎን፣ በሰማያት ስለተወሰዱት ስለሦስቱ፣ እንደተናገርኩት ከሟችነት ወደማይሞተው መንፃታቸውን አላውቅም—

፴፯ ነገር ግን እነሆ፣ ከጻፍኩት በኋላ ጌታን ስለእነርሱ ጠይቄዋለሁ እና ለእኔም በሰውነታቸው ላይ ለውጥ መደረጉ አስፈላጊ መሆኑን አለበለዚያም ሞትን መቅመስ እንዳለባቸው ገልፆልኛል፤

፴፰ ስለዚህ፣ ሞትን እንዳይቀምሱ፣ በዓለም ኃጢያት ካልሆነ በቀር በህመም ሆነ በሀዘን እንዳይሰቃዩ በሰውነታቸው ላይ ለውጥ ተደርጓል።

፴፱ እንግዲህ ይህ ለውጥ በመጨረሻው ቀን ከሚከናወነው ለውጥ ጋር እኩል አይደለም፤ ነገር ግን ሰይጣን በእነርሱ ላይ ስልጣን እንዳይኖረው፣ እነርሱንም መፈተን እንዳይቻለው፣ ለውጥ በእነርሱ ላይ ተደርጓል፤ እናም በስጋቸው ተቀድሰዋልቅዱስም ነበሩ እናም የምድርም ኃይላትም እነርሱን ለመያዝ አይቻላቸውም።

እናም የክርስቶስ የፍርድ ቀንም እስከሚመጣ በዚህ ሁኔታ ይቆያሉ፤ እናም በዚያን ቀንም ታላቅ ለውጥን ይቀበሉና ከዚህ በኋላም ከአብ መንግስትም ላለመውጣት ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በሰማያት ለዘለዓለም ለመኖር ይቀበላሉ።