ምዕራፍ ፲፩
የኔፋውያን የገንዘብ አያያዝ ተገለፀ—አሙሌቅ ከዚኤዝሮም ጋር ተጣላ—ክርስቶስ ሰዎችን ከነኃጢአታቸው አያድናቸውም—መንግስተ ሰማያትን የሚወርሱት ብቻ ይድናሉ—ሰዎች ሁሉ በህያውነት ይነሳሉ—ከትንሳኤ በኋላ ሞት የለም። በ፹፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ አሁን ማንኛውም ሰው የህጉ ዳኛ የሆነ፣ ወይም ዳኛ በመሆን የተሾሙት ለፍርድ በቀረቡት ላይ ለመፍረድ በሚሰሩበት ሰዓት መሰረት ደሞዝ ያገኙ ዘንድ የሞዛያ ህግ ነበር።
፪ አሁን አንድ ሰው በሌላው ባለእዳ ከሆነ፣ እናም ያለበትንም እዳ ካልከፈለ፣ ለዳኛው አቤቱታ ይቀርብበታል፤ እናም ዳኛው ስልጣኑን ተግባራዊ ያደርጋል፤ በፊቱ እንዲያቀርቡት ሹሞችን ይልካልም፣ እናም በህጉና በእርሱ ላይ በቀረቡት መረጃዎች መሰረት ይፈርድበታል፣ ሰውየው ያለበትን እዳ እንዲከፍል ይገደዳልም፣ አለበለዚያ ንብረቱ ይወሰድበታል፣ ካልሆነም ከህዝቡ መካከል ቀማኛና ሌባ በመባል ይጣላል።
፫ እናም ዳኛው በሰራበት መጠን ክፍያውን ይቀበላል—ለቀን አንድ ሰኒን ወርቅ፣ ወይም ከሰኒን ወርቅ እኩል የሆነ አንድ ሴነም ብር፤ ይህም በተሰጠው ህግ መሰረት ነው።
፬ አሁን እነዚህ የተለያዩት ቁራጭ ወርቆቻቸው እናም ብሮቻቸው በዋጋቸው መሰረት ስማቸው ናቸው። እናም ስሞቹም የተሰጡት በኔፋውያን ነው፣ በኢየሩሳሌም እንደነበሩት በአይሁድ አቆጣጠር አልተሰየሙም ነበርና፤ ወይም እንደ አይሁዶችም አለካክ አልለኩዋቸውም ነበር፤ ነገር ግን ስያሜያቸውንና መለኪያቸውን በመሳፍንት ንግስና ጊዜ በንጉስ ሞዛያ እስኪቋቋሙ ድረስ በህዝቡ አስተሳሰብ እና ጉዳዮች መሰረት በማንኛውም ትውልድ ይቀይሯቸው ነበር።
፭ አሁን አቆጣጠሩ ይህ ነው—አንድ ሰኒን ወርቅ፣ አንድ ሴን ወርቅ፣ አንድ ሹም ወርቅና አንድ ሊምና ወርቅ ነው።
፮ አንድ ሴነም ብር፣ አንድ አምኖር ብር፣ አንድ ኤዝረም ብር፣ እናም አንድ ኦንቲ ብር ነው።
፯ አንድ ሲነም ብር ከአንድ ሲነን ወርቅ ጋር እኩል ነበር፣ እናም ለአንድ መለኪያ ገብስና፣ ደግሞ ለሁሉም ዓይነት እህል ለአንድ መለኪያ ዋጋ ነበር።
፰ አሁን የአንድ ሴኦን ወርቅ መጠን ከሁለት ሲነን ወርቅ ዋጋ ጋር እኩል ነው።
፱ እናም አንድ ሹም ወርቅ ከሁለት ሲኦን ወርቅ ጋር ዋጋው እኩል ነበር።
፲ እናም አንድ ሊምና ወርቅ የሁሉም ዋጋ ድምር ነበር።
፲፩ እናም አንድ አምኖር ብር ትልቅነቱ ከሁለት ሴነም እኩል ነው።
፲፪ እናም አንድ ኤዝረም ብር ትልቅነቱ አራት ሲነም ያህል ነበር።
፲፫ እናም አንድ ኦንቲ ከሁሉም ድምር ጋር እኩል ነው።
፲፬ አሁን ይህ የአቆጣጠራቸው የትንሹ ቁጥር ዋጋ ነው—
፲፭ አንድ ሺብሎን የአንድ ሲነም ግማሽ ነው፤ ስለዚህ፣ አንድ ሺብሎን የግማሽ ገብስ መለኪያ ዋጋ ነው።
፲፮ እናም አንድ ሽብለም ግማሽ ሺብሎን ነው።
፲፯ እናም አንድ ልህ ግማሽ ሽብለም ነው።
፲፰ አሁን በአቆጣጠራቸው መሰረት ይህ ቁጥራቸው ነው።
፲፱ አሁን አንድ አንተአን ወርቅ ከሶስት ሽብሎን ጋር እኩል ነው።
፳ እንግዲህ ይህን ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ነበር፣ ምክንያቱም ደሞዛቸውን እንደስራቸው አግኝተዋልና፤ ስለዚህ፣ ገንዘብ በፊታቸው በመጡት አቤቱታ መሰረት ያገኙ ዘንድ ሕዝቡን ለርበሻዎችና ለሁሉም አይነት ሁከታዎች እና ክፋት አውከዋቸዋል፤ ስለዚህ ህዝቡን በአልማና በአሙሌቅ ላይ አነሳስተዋል።
፳፩ እናም ይህ ዚኤዝሮም አሙሌቅን እንዲህ በማለት መጠየቅ ጀመረ፥ እኔ የምጠይቀውን ጥቂት ጥያቄዎች ትመልስልኛለህን? አሁን ዚኤዝሮም መልካም የሆነውን ያጠፋ ዘንድ በዲያብሎስ ዕቅድ ባለሟል ነበር፤ ስለዚህ፣ ለአሙሌቅም አለው፥ በአንተ ላይ የማደርገውን ጥያቄዎች ትመልሳለህን?
፳፪ እናም አሙሌቅ እንዲህ አለው፥ በእኔ ውስጥ ባለው በጌታ መንፈስ መሰረት ከሆነ፣ አዎን፤ ከጌታ መንፈስ ተቃራኒ የሆነ ምንም አልናገርምና። እናም ዚኤዝሮም እንዲህ አለው፣ እነሆ ስድስቱ የብር ኦንቲዎች እነዚህ ናቸው፣ እናም የኃያሉን ፍጡር መኖር የምትክድ ከሆነ ይህንን በሙሉ እሰጥሃለሁ።
፳፫ አሁን አሙሌቅ እንዲህ አለ፥ አንተ የሲኦል ልጅ፣ ለምን ትፈትነኛለህ? ፃድቃን እንደዚህ ላለ ፈተና የማይበገሩ እንደሆነ አታውቅምን?
፳፬ እግዚአብሔር እንደሌለስ ታምናለህን? እኔ እንዲህ እልሃለሁ፣ አይሆንም፣ እግዚአብሔር እንዳለ ታውቃለህ፣ ነገር ግን ከእርሱ የበለጠ ገንዘብ ስለምትወድ ነው።
፳፭ እናም አሁን በእግዚአብሔር ፊት ዋሽተኸኛል። ከእኔም እነርሱን ለማስቀረት በልብህ ባሰብህ ጊዜ፣ ለእኔም፣ እነሆ ታላቅ ዋጋ ያላቸውን እነዚህን ስድስት ኦንቲዎች፣ እሰጥሀለሁ ብለኸኛል፤ እናም እኔን ታጠፋኝ ዘንድ ምክንያት እንዲሆንህ እውነተኛና ህያው የሆነውን እግዚአብሔርን እንድክድ ትፈልጋለህ። እናም አሁን እነሆ፣ ለዚህ ለታላቅ ጥፋት ዋጋህን ታገኛለህ።
፳፮ እናም ዚኤዝሮም እንዲህ አለው፥ እውነተኛና ህያው እግዚአብሔር አለ ትላለህን?
፳፯ እናም አሙሌቅ እንዲህ አለ፥ አዎን፣ እውነተኛና ህያው እግዚአብሔር አለ።
፳፰ አሁን ዚኤዝሮም እንዲህ አለ፥ ከአንድ አምላክ በላይ አለን?
፳፱ እናም እርሱ የለም ሲል መለሰለት።
፴ አሁን ዚኤዝሮም በድጋሚ እንዲህ አለ፥ እነዚህን ነገሮች እንዴት ታውቃለህ?
፴፩ እናም እንዲህ አለ፤ መልአኩ እነዚህን እንዳውቃቸው አደረገኝ።
፴፪ እናም ዚኤዝሮም በድጋሚ እንዲህ አለ፣ የሚመጣው ማን ነው? የእግዚአብሔር ልጅ ነውን?
፴፫ እናም እርሱ አዎን አለው።
፴፬ እናም ዚኤዝሮም በድጋሚ እንዲህ አለ፥ ህዝቡን በኃጢአታቸው ያድናቸዋልን? አሙሌቅም መለሰ፣ እናም አለው፥ ይህን አያደርግም እልሀለሁ፣ ምክንያቱም ቃሉንም ለመካድ አይቻለውምና።
፴፭ እንግዲህ ዚኤዝሮም ለህዝቡ እንዲህ አለ፥ እነዚህን ነገሮች ታስታውሱ ዘንድ ተመልከቱ፤ እግዚአብሔርንም ለማዘዝ ስልጣን ያለው ይመስል—አንድ ብቻ አምላክ አለ ብሏልና፤ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ ይመጣልም ብሏል፣ ነገር ግን ህዝቡን አያድንም ብሎ ተናግሯል።
፴፮ እንግዲህ አሙሌቅ በድጋሚ እንዲህ አለው፥ እነሆ አንተ ዋሽተሀል፣ ሰዎችንም በኃጢአታቸው አያድንም በማለቴ እግዚአብሔርን ለማዘዝ ስልጣን እንዳለኝ ተናገርኩ ብለሃል።
፴፯ እናም በድጋሚ እንዲህ እልሃለሁ ከነኃጢአታቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እኔም ቃሉን መካድ አይቻለኝምና፣ እናም ምንም እርኩስ ነገር መንግስተ ሰማያትን ሊወርስ አይችልም ብሏልና፤ ስለዚህ፣ መንግስተ ሰማያትን ካልወረስህ እንዴት ልትድን ትችላለህ? ስለዚህ ከነኃጢያትህ መዳን አትችልም።
፴፰ አሁን ዚኤዝሮም በድጋሚ እንዲህ አለው፥ የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ዘለአለማዊ አባት ነውን?
፴፱ እናም አሙሌቅ እንዲህ አለው፥ አዎን፣ እርሱ የሰማይና የምድር፣ እናም በእነርሱም ያሉት ሁሉም ነገሮች እውነተኛ ዘለአለማዊ አባት ነው፤ እርሱ የመጀመሪያና የመጨረሻ፣ የፊተኛውና የኋለኛው ነው፤
፵ እናም ህዝቡን ለማዳንና ወደ ዓለም ይመጣል፤ በስሙ ለሚያምኑም መተላለፋቸውን በራሱ ላይ ይወስዳል፤ እነዚህም ዘለዓለማዊ ህይወት ያላቸው ናቸው፣ እናም ደህንነት ለሌላ ለማንም አይመጣም።
፵፩ ስለዚህ ለኃጢአተኞች የሞት እስር ከመፈታት በስተቀር ቤዛነት እንዳልተፈፀመ ሆነው ይቆያሉ፤ እነሆም፣ ሁሉም ከሞት የሚነሱበት፣ እናም ከእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙበትና፣ እንደስራቸውም የሚፈረድባቸው ቀን ይመጣል።
፵፪ እንግዲህ፣ ጊዜያዊ ሞት ተብሎ የሚጠራ ሞት አለ፤ እናም ሁሉም ከዚህ ከጊዜያዊው ሞት ይነሱ ዘንድ፣ የክርስቶስ ሞት የጊዜያዊ ሞትን እስር ይፈታል።
፵፫ መንፈስም ከስጋ ጋር ፍፁም በሆነ ሁኔታ በድጋሚ አንድ ይሆናል፣ እግርና እጅ እናም መገጣጠሚያዎች ተገቢ በሆነ ሁኔታ፣ እኛ አሁን ባለን አምሳል ይመለሳሉ፤ እናም ልክ አሁን እንደምናውቅ እያወቅንና፣ የጥፋታችን ሁሉ ትውስታ ግልፅ እየሆነልን በእግዚአብሔር ፊት እንቀርባለን።
፵፬ እንግዲህ፣ ይህ ዳግሞ መመለስ ለሁሉም፣ ለሽማግሌዎችና ለወጣቶች፣ ለታሰሩና ነፃ ለሆኑትም፣ ለሴትና ለወንድ፣ ለኃጢአተኞችና ለፃድቃን ይሆናል፤ እናም አንዲትም የራስ ፀጉራቸውም እንኳን አይጠፋም፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር፣ ልክ እንዳሁኑ፣ ወይም በሰውነት፣ በፍጹም መልክ ይመለሳል፣ እናም አንድ ዘለዓለማዊ አምላክ በሆኑት በወልድ በክርስቶስና በእግዚአብሔር አብ፣ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ የፍርድ ወንበር ፊት፣ መልካም ወይም ክፉዎች ቢሆኑ፣ እንደስራቸው ሊፈረድባቸው መልስ ለመስጠት ይመጣሉ።
፵፭ አሁን፣ እነሆ፣ ስለሚሞተው ሰውነታችን ሞት እናም ደግሞ ስለሚሞተው ሰውነታችን ትንሳኤ ተናግሬሀለሁ። ይህ የሚሞተው ሰውነት ወደማይሞተው ሰውነት ይነሳል፣ ይህም ማለት ከሞት፣ እንዲሁም ከመጀመሪያው ሞትም ወደ ህይወት፣ ከእንግዲህም ደግሞ እንዳይሞቱ ይነሳል እልሀለሁ፤ መንፈሳቸው ከሰውነታቸው ጋር አንድ ይሆናል፣ ከእንግዲህም አይለያይም፤ እንደዚህም አንድ የሆነው ሰውነትም መንፈሳዊና የማይሞት የማይበሰብስም ይሆናል።
፵፮ አሁን፣ አሙሌቅ እነዚህን ቃላት በጨረሰ ጊዜ ህዝቡ በድጋሚ መገረም ጀመረ፣ እናም ደግሞ ዚኤዝሮም መንቀጥቀጥ ጀመረ። እናም የአሙሌቅ ቃል አበቃ፣ ወይንም የፃፍኩት ሁሉ ይህ ነው።