ምዕራፍ ፮
ንሰሃ የገቡት ሰዎች ተጠመቁ እናም የቤተክርስቲያኗን ህብረት አገኙ—ንሰሃ የገቡ የቤተክርስቲያን አባላት ይቅርታን ተቀበሉ—ስብሰባዎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተከናውነዋል። ከ፬፻፩–፬፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም አሁን ጥምቀትን በተመለከተ እናገራለሁ። እነሆ ሽማግሌዎች፣ ካህናት፣ እናም መምህራን ተጠምቀዋል፤ እናም ለእዚህም ብቁ የሆኑ ትክክለኛ ፍሬ የሚያመጡ ካልሆኑ በስተቀር እነርሱ አይጠመቁም።
፪ በተሰበረ ልብ እናም በተዋረደ መንፈስ ካልመጡ እናም ለኃጢአታቸው በሙሉ በእውነት ንሰሃ እንደገቡ ለቤተክርስቲያኗ ካልመሰከሩ በስተቀር ወደ ጥምቀቱ ማንንም አልተቀበሉም።
፫ እናም የክርስቶስን ስም ካልለበሱ እናም እስከመጨረሻውም እርሱን ለማገልገል ካልወሰኑ በቀር ማንንም በጥምቀት አልተቀበሉም።
፬ እናም ከተጠመቁ እናም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በላያቸው ላይ ከሰራ እናም ካነፃቸው በኋላ፣ ከክርስቶስ ቤተክርስቲያን ህዝቦች ጋር ተቆጥረዋል፤ እናም እነርሱን በትክክለኛው መንገድ ለማቆየት፣ የእምነታቸው ደራሲ እና ፈፃሚ በሆነው በክርስቶስ በጎ ሥራ ላይ ብቻ በመደገፍ ፀሎታቸውን ያለማቋረጥ እንዲሚቀጥሉ ለመጠበቅ፣ የእግዚአብሔርን መልካም ቃል በመመገብ ይታወሱ ዘንድ ስማቸው ተወስደዋል።
፭ እናም ለመፆም እናም ለመፀለይ፣ እናም እያንዳንዳቸው ለነፍሳቸው ደህንነት እርስ በርሳቸው እንዲናገሩ ዘንድ ሁል ጊዜ በቤተክርስቲያን ይገኛሉ።
፮ እናም ጌታ ኢየሱስን ለማስታወስ ዳቦውን እና ወይኑን ለመካፈል፣ ሁልጊዜ በአንድነት ይሰበሰቡ ነበር።
፯ እናም በመካከላቸው ክፉ ነገር እንዳይኖርም በጥብቅ ይጠነቀቃሉ፤ በመካከላቸው ክፉ ነገር ሲያደርጉ የተገኙ፣ እናም በቤተክርስቲያኗ ሦስት ምስክሮች በሽማግሌዎች ፊት ከተወቀሱ፣ እናም ንሰሃም ካልገቡ፣ እናም ካልተናዘዙ ስማቸው ይሰረዛል፣ እናም ከክርስቶስ ሰዎች ጋርም አይቆጠሩም።
፰ ነገር ግን በእውነተኛ ፍላጎት ንሰሃ ሁል ጊዜም ከገቡ፣ እናም ይቅርታን ከፈለጉ ይቅር ይባላሉ።
፱ እናም ስብሰባዎችም በቤተክርስቲያኗ በመንፈስ ስራዎች እናም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይመራል፤ የመንፈስ ቅዱስ ኃይልም እንዲሰብኩ፣ ወይም እንዲያስጠነቅቁ፣ ወይም እንዲፀልዩ፣ ወይም ወደጌታ እንዲማፀኑ ወይም እንዲዘምሩ ይመራቸዋል፣ እንዲሁም ይፈጸማል።