2010–2019 (እ.አ.አ)
“አውቃችሁኝ ቢሆን ኖሮ”
ጥቅምት 2016 (እ.አ.አ)


15:42

“አውቃችሁኝ ቢሆን ኖሮ”

ስለ አዳኝ ብቻ ነው የምናውቀው፣ ወይስ በቀጣይነት እርሱን ወደ ማወቅ እየመጣን ነው? ጌታን ወደ ማወቅ እንዴት እንመጣለን?

አዳኝ በተራራ ላይ ያስተማረውን ትምህርት ሲያጠቃልል፣ የአብን ፈቃድ በመፈፀም ብቻ የወልድን የማዳን ፀጋ እንደሚገኝ” ያለውን ዘላለማዊ እውነት በጉልህ አሳየ።1

እንዲህም ብሎ አወጀ፤

“በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማይ የሚገባ አይደለም።

“በዚያን ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢትን አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።

“በዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ አመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።2

በድጋሚ የተከለሰውን ፅሁፍ ላይ ስናሰላስል የዚህ ትምህርት መረዳታችን ያድጋል። በኪንግ ጀምስ የመፅሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ “ከቶ አላውቃችሁም” በማለት የተገለፀው የአዳኝ ሀረግ፣ በዮሴፍ ስሚዝ ትርጉም ላይ “ከቶ አታውቁኝም” ወደ ሚለው መቀየሩ አስፈላጊ ነው።3

የአስርቱ ቆነጃጅት ምሳሌንም አስቡ። ሙሽራውን ለመቀበል የነበረውን ውካታ ከሰሙ በኋላ ለመብራታቸው ዘይት ለመግዛት ስለሄዱት አምስቱ ሰነፎች እና ያልተዘጋጁ ቆነጃጅት አስታውሱ።

“ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።

“በኋላም የቀሩት ቆነጃጅት መጡና ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።

“እርሱም ግን መልሶ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።”4

የዚህ ምሳሌያዊ ትምህርት ፍቺዎች በሌላ በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሳ ክለሳ ላይ ለእያንዳንዳችን በሰፊው ተብራርተውልናል። በኪንግ ጀምስ የመፅሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ “ከቶ አላውቃችሁም” የሚለው ሐረግ በዮሴፍ ስሚዝ ትርጉም ላይ “ከቶ አታውቁኝም” ወደ ሚለው በግልፅ ተቀምጧል።5

“ከቶ አታውቁኝም” እና “አታውቁኝም” የሚለው ሀረግ ለእንዳንዳችን የጠለቀ የመንፈሳዊ ግምገማ ምክንያት መሆን አለበት። ስለ አዳኝ ብቻ ነው የምናውቀው፣ ወይስ በቀጣይነት እርሱን ወደ ማወቅ እየመጣን ነው? ጌታን ወደ ማወቅ እንዴት እንመጣለን? እነኚህ የነፍስ ጥያቄዎች የመልእክቴ ትኩረት ናቸው። ይህንን በጣም ጠቃሚ ርእስ በጋራ ስናስብ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታን እጋብዛለሁ።

ወደ ማወቅ መምጣት

ኢየሱስ እንዲህ አለ፤

“እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ፤ በኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።

“እኔንስ ብታውቁን አባትን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር።”6

የእርሱን ተወዳጅ ልጅ ወደ ማወቅ ስንመጣ አብን ወደ ማወቅ እንመጣለን።

የሟችነት ህይወት አላማ ጥቅም ስለ አብ አንድያ ልጁ መማር ብቻ አይደለም ነገር ግን እሱን ለማወቅ መጣርንም ያካትታል። ጌታን ለማወቅ የሚረዱን አራት ጠቃሚ ደረጃዎች በእርሱ ላይ እምነትን መለማመድ፣ እርሱን መከተል፣ እርሱን ማገልገል፣ እና እርሱን ማመን ናቸው።

በእርሱ ላይ እምነትን መለማመድ

በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት መለማመድ ማለት በእርሱ መልካም ስራ ላይ፣ ምህረት ላይ፣ እና ፀጋ ላይ መመርኮዝ ማለት ነው።7 መንፈሳዊ ስጦታዎቻችንን መጠቀም ስንጀምር እና ለቃላቶቹ በነፍሶቻችን ውስጥ ትንሽ ቦታ መስጠት እስክንችል ድረስ እንኳ፣ በትምህርቶቹ ላይ ሙከራን ስናደርግ፣ አዳኝን ማወቅ እንጀምራለን።8በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ሲያድግ፣ እናምነዋለን እናም በማዳን፣ በመፈወስ እና እኛን በማጠንከር ያለው ኃይል ላይ መተማመን ይኖራናል።

ትክክለኛ እምነት የተመሰረተው በጌታ እና በጌታ ላይ ብቻ ነው እናም ሁሌም ወደ ፃድቅ ድርጊት ነው የሚመራው። “በክርስቶስ ላይ ያለ እምነት በተገለፀው ሀይማኖት ላይ የመጀመሪያ መመሪያ፣ … የፅድቅ ሁሉ መሰረት እናም በሁሉም ብልህ ፍጥረት ውስጥ የድርጊት መርህ ነው።”9 ምክንያቱም ትክክለኛ እምነት ለመቀበል እና ለመለማመድ በትክክለኛው መርሆች ላይ በተገቢው መንገድ መተግበር ማእከላዊ መርህ እንደሆነ አዳኝ አወጀ። “እምነት ከስራ ተለይቶ የሞተ ነው”10 “ቃሉን የምናደርግ እንጂ ራሳችንን እያሳየን የምንሰማ ብቻ መሆን የለብንም”። 11

የእግዚአብሔርን ቃል መስማት እና በአዳኝ ላይ ያለን መንፈሳዊ የእምነት ስጦታን መቀበል በቅርብ የተዛመዱ ናቸው፣ ምክንያቱም “እምነት ከመስማት ነው፣ መስማትም በእግዚብሔር ቃል ነው።”12 በቅዱስ መፅሀፍ ውስጥ ያለውን እሱን ቃል ስናጠና እና ስንመገባቸው ከእሱ እና ከድምፁጋር ትውውቅ እየኖረን ይመጣል።13 በንፁህ ልባችሁ በስሙ ወደ አብ ፀልዩ፣14 እናም መንፈስ ቅዱስ ቋሚ ጓደናችሁ እንዲሆን እሹ።15የክርስቶስን ትምህርት መማር እና በህይወታችን ውስጥ ትምህርቱነረ መተግበር በእርሱ ላይ ያለን የእምነት ስጦታ ከመቀበላችን በፊት ማድረግ ያለብን ነገር ነው።16

በጌታ ላይ እምነትን መለማመድ እሱን ለመከተል አስፈላጊ ዝግጅት ነው።

እርሱን መከተል

“ኢየሱስም በገሊላ ባህር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማቾች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምኦንን ወንድሙንም አንድርያስን መረባቸውን ወደ ባህር ሲጥሉ አየ፥ አሳ አጥማጆች ነበሩና።

“እርሱም በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው።

“ወዲያዊኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት።”17

ጴጥሮስ እና አንድርያስ ኢየሱስ ክርስቶስን የመስማት እና የመከተል ጠንካራ ምሳሌዎች ናቸው።

“እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ እራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።”18 መስቀሉን መሸከም ማለት እራሳችንን ከሁሉም ሀጢያተኝነት እና ከሁሉም አለማዊ ምኞት መካድ እና ጌታን ትእዛዝ መጠበቅ ማለት ነው።19

አዳኝ ልክ እንደ እሱ እንድንሆን ገስፆናል።20 ስለሆነም፣ ጌታን መከተል ምሳሌዎቹን መከተልን ያካትታል። እንደ እሱ እንድንሆን የሚያደርገንን የእርሱ ቤዛነት ኃይል አማካኝነት ጌታን ስንሻው ያለማቋረጥ እሱን ወደ ማወቅ እንመጣለን ።

በምድራዊ አገልግሎቱ ላይ፣ ኢየሱስ መንገዱን አሳይቶናል፣ መንገዱን መርቶናል እንዲሁም ፍፁም ምሳሌን አስቀምጦልናል። “ትክክለኛው የእርሱ ፀባይ፣ የፍፁምናው፣ እና የባህሪያቱ ሀሳብ”21 በታማኝ የደቀ መዛሙርትነት መንገድ ላይ ስንከተለው ቀጣይነት ያለው አላማንና ግልፅ መመሪያ ይሰጠናል።

አዳኝን መከተል “የምንከተለው የህይወት መንገድ”22 በእግዚአብሔር ፍላጎት መሰረት እንደሆነ ማረጋገጫ እንቀበላለን። እንደዚህ አይነት እውቀት የማይታወቅ ሚስጥር አይደለም እናም በምድራዊ ፍላጎት ወይም በተራ ስጋዊ ሀሳቦች ላይ የሚያተኩር አይደለም። ይልቁኑንም፣ በቃል ኪዳን መጠበቅ መንገድ ላይ የፀና እና ቀጣይነት ያለው እድገት ለእርሱ የሚያስደስተው የህይወት መንገድ ነው።

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ያለው የሌሂ ህልም የሚያጋጥሙን መከራዎች፣ እናም አዳኝን በመከተል እና ወደ እሱ በመምጣት ውስጥ እኛን ለመርዳት የሚገኙት መንፈሳዊ መሳሪያዎችን ለይቶ ያሳያል። በጠባቡ አና በቀጭኑ መንገድ ላይ ወደፊት መጓዝ እርሱ እኛ እንድናደርግ የሚፈልገው ነገር ነው። የዛፍን ፍሬ መቅመስ እና በጥልቅ “ወደ ጌታ መለወጥ”23 እኛ እንድንቀበላቸው የሚሻቸው በረከቶች ናቸው። ለዚያም፣ “ኑና ተከተሉኝ” ብሎ ጋበዘን።24

እርሱን ለማገልገል እምነትን መለማመድ እና ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ሁለቱም ጠቃሚ ዝግጅቶች ናቸው።

እርሱን ማገልገል

“ያላገለገለውን አለቃ፣ እና እንግዳውን ከልቡ ስሜትና ሀሳብ የራቀውን፣ አንድ ሰው እንዴት ያውቃል?”25

ስናገለግለው እና በመንግስቱ ውስጥ ስንሰራ በተሻለ ሙላት ጌታን ወደ ማወቅ እንመጣለን። ይህንን ስናደርግ፣ በለጋስነት በመለኮታዊ እርዳታ፣ በመንፈሳዊ ስጦታ፣ እናም በትልቅ አቅም በደግነት ይባርከናል። በእርሱ የወይን ቦታ ላይ ስንሰራ በጭራሽ ብቻችንን አንተውም።

እንዲህም ብሎ አወጀ፥ “እነሆ ከፊታችሁ እሄዳለሁ፣ ቀኝ እጃችሁም እናም ግራ እጃችሁም እሆናለሁ እንዲሁም መንፈሴ በልቦቻችሁ ውስጥ ይሆናል፣ እናም እናንተን ለማንሳት የእኔ መላእክቶች በዙሪያችሁ ይሆናሉ።”26

እርሱ እኛ እንድንሄድ የሚፈልገው ቦታ ለመሄድ የተሻለ ስናደርግ፣ እኛ እንድንል የሚፈልገውን ለማለት ስንጥር፣ እንዲሁም እኛ እንድንሆን የሚፈልገውን ስንሆን አዳኝን ወደ ማወቅ እንመጣለን።27 በእርሱ ላይ ያለንን ሙሉ ጥገኝነት በትህትና ስናምን ከዚህ በፊት ከነበረው በተሸለ እንድናገለግል ብቃታችንን ያሰፋልናል። በስተመጨረሻም፣ የእኛ መሻት ከእርሱ መሻት ጋር ሙሉ በሙሉ መስመር ይይዛሉ እናም “ከ [እርሱ] ፈቃድ የሚቃረን ነገርን እስከማንጠይቅ” ድረስ የእርሱ አላማዎች የእኛ አላማዎች ይሆናሉ።28

እርሱን ማገልገል ሙሉ ልባችንን፣ ኃይላችንን፣ አእምሮአችንን እና ጥንካሬያችንን ይጠይቃል።29 በማስከተልም፣ ሌሎችን ያለ ራስ ወዳድነት ማገልገል፣ እራስ ላይ ማተኮርን እና የተፈጥሮአዊ ሰውን የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎች ያሸንፋል። የምናገለግላቸውን ሰዎች ወደ መውደድ እንመጣለን። እና ሌሎችን ማገልገል እግዚያብሔርን ማገልገል ስለሆነ፣ በበለጠ ጥልቀት እርሱን እናም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ወደ መውደድ እንመጣለን። ይህም አይነት ፍቅር ንፁህ የክርስቶስ ፍቅር የሆነው የልግስና መንፈስ ነው።30

“በልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ሁሉ ላይ በሚፈሰው በዚህ ፍቅር ትሞሉ ዘንድ በሀይል ከልባችሁ ፀልዩ፤ የእግዚያብሔር ልጆች ትሆኑ ዘነድ፣ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ እንደርሱ እንድንሆን፣ እርሱ ልክ እንደሆነው እናየዋለንና፤ ይህም ተስፋ ይኖረናል፣ ልክ እርሱ ፍፁም እንደሆነ እኛም ፍፁማን እንሆናለን።”31

በፍቅሩ ስንሞላ እርሱን ወደ ማወቅ እንመጣለን።

እርሱን ማመን

እምነትን በእርሱ ላይ ተለማምዶ፣ እርሱን ተከትሎ፣ እርሱን አገልግሎ፣ ነገር ግን በእርሱ አለማመን የሚቻል አይደለም።

በቅዱስ መፅሐፍት ውስጥ ያሉትን እናም ከዚህ መድረክ ላይ የሚታወጅ አስተምሮት እና መርሆዎች እውነት እንደሆኑ አድርገው የሚቀበሉ የቤተክርስቲያን አባላትን አውቃለሁ። ሆኖም እነኛን የወንጌል እውነታዎች ለህይወታቸው እና ለሁኔታዎቻቸው እንደሚሆን ማመን ከሚከብዳቸው የቤተክርስቲያን አባላት ጋር ትውውቅ አለኝ። በአዳኝ ላይ እምነት ያላቸው ይመስላሉ ነገር ግን እርሱ ቃል የገባው በረከቶች ለእነርሱ እንደተቀመጡ ወይም በረከቶቹ በህይወታቸው ውስጥ መስራት እንደሚችሉ አያምኑም። እንዲሁም የጥሪ ሀላፊነታቸውን በትጋት የሚያሟሉ ነገር ግን የተመለሰው ወንጌል በህይወታቸው ውስጥ የሚሰራ እና ለዋጭ እውነት ያላመጣላቸው ወንድሞች እና እህቶች አገኛለሁ። ጌታን ወደ ማወቅ የምንመጣው በእርሱ ላይ በማመን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን እርሱን እና የገባቸውን ቃልም ስናምን ነው።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ አንድ አባት አዳኝ ልጁን እንዲፈውስለት ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤

“ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።

“ወዲያውኑ የብላቴናው አባት ጮኸ፣ አምናለሁ፣ አለማመኔን አርዳው።”32

በዚህ አባት ጥያቄ ላይ ብዙ ጊዜያት አሰላስያለሁ። ”አለማመኔን አርዳው።” የሰውየው የልመና አላማ በዋናነት ኢየሱስ እንደ አዳኛችን አድርጎ ለማመን እና በእርሱ የማዳን ኃይል ለማመን እንዲረዳው ስላለመሆኑ እራሴን እጠይቃለሁ። ክርስቶስን እንደ እግዚያብሔር ልጅ አድርጎ አምኖ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በእርግጥም የጌታ የማዳን ኃይል ላይ ለማመን እርዳታ የመፈለጉ ምክንያት በጣም ግለሰባዊ እና ግላዊ በሆነ መልኩ የራሱን ውድ ልጅ እንዲባርክ ሊሆን ይችላል። ጠቅለል ባለ ሁኔታ በክርስቶስ ሊያምን ይችላል ነገር ግን በልዩ ሁኔታ እና በግሉ ክርስቶስን አላመነውም።

በአብዛኛው ጊዜ እውነት እንደሆነ የምናውቀውን ነገር እንመሰክራለን፣ ነገር ግን በእርግጥም ለሁላችንም የተሻለ ጥያቄ የሚሆነው የምናውቀውን ነገር እናምናለን ወይስ አናምንም የሚለው ነው።

አዳኝን ለማመን፣ እሱን ወደ ማወቅ ለመምጣት፣ እናም በስተመጨረሻም የምናውቀውን ለማመን በትክክለኛው የክህነት ስልጣን የሚደረጉ ቅዱስ ስርዓቶች ጠቃሚ ናቸው።

“እናም የመልከፀዲቅ ስልጣን ወንጌልን ያስተዳድራል እናም የእግዚያብሔር መንግስትን ሚስጢራት ቁልፍ ይይዛል፣ የእግዚያብሔርን እውቀትን ቁልፍ ጨምሮ።

“ስለሆነም፣ ከዚያም በስርዓቶች ውስጥ፣ የቅድስና ኃይል ይገለፃል።”33

የእግዚያብሔር እውቀት ቁልፍ በሩን ከፍቶ እንዲሁም የቅድስናን ኃይል በህይወታችን ውስጥ ለእያንዳንዳችን እንድንቀበል የሚስችለን በመልከፀዲቅ ስልጣን አማካኝነት ሲተዳደር ጌታን እናምናለን እናም ጌታን ወደ ማወቅ እንመጣለን። ቅዱስ ስርዓቶችን በመቀበል እና በሙሉ እምነት ታማኝ ለመሆን እንዲሁም ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በፊታችን ምስሉን ስንቀበል አዳኝን እናምናለን እንዲሁም አዳኝን ወደ ማወቅ እንመጣለን።34 ለውጥ፣ ፈውስ፣ ጥንካሬን እናም የተሰዋውን የቤዛነቱ ኃይል በግላችን ተሞክሮን ስናገኝ ክርስቶስን እናምናለን እንዲሁም ክርስቶስን ወደ ማወቅ እንመጣለን። “የቃሉ ኃይል በውስጣችን ስር ሲይዝ፣”35 በአእምሮአችን ላይ እና በልባችን ላይ ሲፃፍ፣36 እርሱን በማወቅ “ሀጢታችንን ሁሉ ስንተው”37 ጌታን እናምናለን እንዲሁም እርሱን ወደ ማወቅ እንመጣለን።

እርሱን ማመን ማለት የእርሱ በጣም የበዙ በረከቶች እንደሚገኙ እና በግል ህይወታችን እና በቤተሰቦቻችን ላይ እንደሚሰሩ ማመን ነው። በሙሉ ነፍሳችን38 እርሱን ማመን የሚያመጣው በቃል ኪዳን መንገድ ላይ ወደፊት ስንጓዝ፣ ፍቃዳችንን ለእርሱ ፍቃድ አሳልፈን ስንሰጥ፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች እና ለእኛ ላለው የጊዜ መደብ እራሳችንን ስንሰጥ ነው። በእርሱ ማመን—የእርሱን ኃይልና ቃልኪዳኖችን—እይታን፣ ደስታንና ሰላምን ወደ ህይወታችን ይጋብዝልናል።

ቃል ኪዳን እና ምስክርነት

ወደፊት በሚመጣው ቀን፣ “የሁሉም ጉልበት ይንበረከካል እናም የሁሉም አንደበት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናዘዛል።”39 በዚያች የተባረከች ቀን፣ እያንዳንዳችንን በስማችን እንደሚያውቀን እናውቃለን። እናም ስለ ጌታ ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በእርሱ ላይ እምነትን ስንለማመድ፣ ስንከተለው፣ ስናገለግለው እናም ስናምነው እርሱን ወደ ማወቅ እንደምንመጣ እመሰክራለሁ እናም ቃል ገባለሁ። ይህንን የምመሰክረው ቅዱስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።”