ወደ ደስታ የሚያመራው ፍፁሙ መንገድ
ስለ ታላቁ ስጦታ እመሰክራለሁ ያም የሰማይ አባት ለእኛ ያለው እቅድ ነው። ወደ ሰላም እና ደስታ የሚወስድ ብቸኛው ፍፁም መንገድ ነው።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህ የጉባኤ ማእከል እንዲሁም በመላው አለም ያላችሁ፣ በዚህ ማለዳ ሀሳቦቼን ለእናንተ የማካፈል እድል ስላለኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።
ከሀምሳ አምስት አመት በፊት፣ በሐምሌ 1964 ውስጥ፣ የአለም ትርኢት በኒው ዮርክ በሚደረግበት ጊዜ እኔ ለስራ እዛ ነበርኩ። አንድ ቀን ጠዋት በትርኢቱ ላይ የነበረን የሞርሞን ጊዜያዊ ድንኳን ጎበኘሁ። የሰው የደስታ ፍለጋ የሚለው የቤተክርስቲያን ፊልም ልክ ከመታየቱ በፊት ነበር የደረስኩት የቤተክርስቲያኑ መለያ የሆነውን የደህንነት እቅድ ይዘግብ ነበር። 35 አመት ከሚሆነው ጎልማሳ ጎን ተቀመጥኩ። በትንሹ አወራን። የቤተክርስቲያናችን አባል አልነበረም። ከዛም መብራቶቹ ደበዘዙ፣ እናም ትይንቱ ጀመረ።
አቅራቢው አሳዛኝ እና አለም አቀፋዊ ጥያቄዎችን ሲያነሳ ድምፁን አዳመጥን፤ ከየት ነው የመጣሁት? እዚህ ለምንድነው ያለሁት? ይህን ህይወት ስተው የት ነው የምሄደው? ምላሹን ለመስማት ሁሉም ጆሮዎች ጓጉ፣ እና ሁሉም አይኖች በሚቀርቡት ምስሎች ላይ አተኮሩ። የቅድመ ምድራዊ ህይወታችን ማብራሪያ ተሰጠ፣ አብሮም በምድር ላይ አላማችንም ተገለፀ። አያት የሆነ የአንድ ሽማግሌን ከዚህ ህይወት መለየት እና ከእራሳቸው በፊት የመንፈስ አለም ከገቡት ጋር የነበራቸውን ክቡር ዳግም መገናኘትን ልብ በሚነካ አቅርቦት ተመለከትን።
በዚህ በሚያምረው የሰማይ አባታችን ለእኛ ስላለው እቅድ ምልከታ ማጠቃለያ ላይ፣ ሶዎቹ በፀጥታ እየወጡ ሄዱ፣ አብዛኞቹ ሰዎች በፊልሙ መልእክት እንደተነኩ ያስታውቅ ነበር። ከጎኔ የነበረው ጎብኚ አልተነሳም ነበር። የቀረበውን እንደወደደው ጠየኩት። አጥብቆ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ይሄ ነው እውነታው!”
ለእኛ ደስታ እና ደህንነት አባታችን ያለው እቅድ በአለም ዙሪያ በሚስኦናውያኖቻችን እየተነገረ ነው። ይህን መለኮታዊ መልእክት የሚሰሙ ሁሉም አይቀበሉትም እናም አይጠቀሙበትም። ሆኖም፣ በየቦታው ያሉ ወንዶች እና ሴቶች፣ በኒው ዮርክ የአለም ትርኢት ላይ እንደነበረው ወጣቱ ጓደኛዬ፣ እውነትነቱን ያስተውላሉ፣ እናም በደህንነት ወደ ቤት በሚመልሳቸው መንገድ ላይ ይተክላሉ ያስገባሉ። ህይወታቸው ለዘለአለም ይቀየራል።
ለእቅዱ ወሳኝ ክፍል የሆነው አዳኛችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ያለ እርሱ የመስዋእት ክፍያ፣ ሁሉም ነገር ጠፊ ነበር። በእርሱ እና በተልእኮው ማመን ብቻ ግን በቂ አይደለም። መስራት እና መማር፣ መሻት እና መፀለይ፣ ንሰሀ መግባት እና መሻሻል አለብን። የእግዚአብሔርን ህግጋት ማወቅ እና መኖር አለብን። የሚያድን ስርዓቶቹን መቀበል ያስፈልገናል። ይህንን በማድረግ ብቻ እውነተኛ ደስታን እናገኛለን።
እውነቱ ስላለን ተባርከናል። እውነቱን የማካፈል ሀላፊነት አለብን። አብ ለእኛ ያለውን ሁሉ እናገኝ ዘንድ እውነታውን እንኑር። እርሱ ለእኛ ጥቅም ያልሆነ ምንም ነገር አያደርግም። እንዲህ ብሎናል፣ “ይህ የእኔ ስራ እና ክብር ነው—የሰውን አለሟችነት እና ዘለአለማዊ ህይወት ማምጣት።”1
ከጥልቅ ነብሴ፣ እና በሙሉ ትህትና፣ ታላቅ ስጦታ ስለሆነው አባታችን ለእኛ ስላለው እቅድ እመሰክራለሁ። በእዚህ እናም በሚመጣው አለም ወደ ሰላም እና ደስታ የሚወስድ ብቸኛው ፍፁም መንገድ ነው።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ሳበቃም ፍቅሬን እና በረከቶቼን ለእናንተ እተውላችኋለሁ፣ እናም ይህን ያደረኩት በአዳኛችን እና ቤዛችን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።