2010–2019 (እ.አ.አ)
ከአልማና ከአሙሌቅ ተማሩ
ጥቅምት 2016 (እ.አ.አ)


18:33

ከአልማና ከአሙሌቅ ተማሩ

ከደቀ መዝሙርነት መንገድ ለወጡ ሁሉ በልባቸው እንዲያዩ እና ከአልማና አሙሌቅ እንዲማሩ ተስፋዬ ነው።

ወጣቱ አልማ

ከቅዱሳን መጻህፍት ውስጥ፣ ከማይረሱት ገጸ ባህሪያን መካከል፣ ወጣቱ አልማ አንዱ ነው። የታላቅ ነቢይ ልጅ ቢሆንም፣ መንገዱን በመሳት “ሀጥያተና አመንዛሪ ሆኖ ነበር።” ለማናውቀው ምክንያት፣ አባቱን በትጋት ተቃወመ እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ተነሳሳ። እናም አንደበተ ብርቱ በመሆኑና አሳማኝ በመሆኑ፣ ታላቅ ድልን ተቀዳጀ።1

ሆኖም ግን፣ የጌታ መልአክ ሲገለጥለትና በመብረቅ ድምጽ ሲያናግረው የአልማ ህይወት ተቀየረ። ለሶስት ቀናትና ለሶስት ምሽቶችም፣ አልማ “በዘላለም ስቃይ ተጨነቀ፣ በተኮነነች ነፍስ ህመምም እንኳን ተሰቃየ።” ከዛም፣ ባልታዋቀ ሁኔታ፣ ግልጽ ያልሆነ ትውስታ በጨለመው አይምሮው ውስጥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “ለአለም ሃጢያት ቤዛ ለመሆን” እንደሚመጣ አባቱ ያስተማረው የዘላለም እውነት አስተጋባበት። አልማም ከዚህ በፊት እንደዚህ ያሉ ጽንሰ ሃሳቦችን ተቃውሞ ነበር፣ ሆኖም ግን አሁን “አይምሮው ይህንኑ በማሰብ ተይዞ፣” በትህትና፣ በቅንነትም እምነቱን በክርስቶስ የቤዛነት ሃይል ላይ አደረገ።2

አልማም ከዚህ ተሞክሮው ሲነቃ፣ የተቀየረ ሰው ነበር። ከዛም ጊዜ ጀምሮ፣ ከዚህ በፊት ያጠፋቸውን ጥፋቶች ለማስተካከል ህይወቱን አዋለ። እርሱም የንስሀ መግባት፣ የምህረት፣ እና በታማኝነት የመፅናት ምሳሌ ነው።

በመጨረሻ ላይ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን አናት በመሆን አባቱን እንዲተካ ተመረጠ።

የኔፋውያን አገር ዜጋ የሆነ ህዝብ ሁሉ፣ የአልማን ታሪክ ማወቅ አለበ። በሱ ጊዜ የነበሩ ትዊተሮች፣ እነስታግራሞች፣ እናም ፌስቡኮች በሱ ምስሎችና በሱ ታሪኮች ይሞሉ ነበር። ምናልባት በየጊዜው በሚወጣው በዛራሄምላ መጽሄት የፊት ገጽ ላይ በየሳምንቱ ቀርቦ ሊሆን እናም የጻህፊያን የመነጋግሪያ ርእስ ሊሆንም ይችላል። በአጭሩ፣ እሱ በጊዜው በጣም ታዋቂ ዝነኛ ሰው ነበር ማለት ይቻላል።

ነገር ግን፣ ህዝቡ እግዚአብሄርን መርሳት እንደጀመረ እና በኩራትና በጥል እራሳቸውን እንዳነሳሱ አልማ ሲመለከት፣ የመንግስት ሰራተኝነቱን አቁሞ፣“በቅዱሱ የእግዚአብሄር መንገድ ሊቀ-ካህን”3 በመሆን ለኔፋውያን ንስሃን ለመስበክ እራሱን ጻድቅ አድርጎ አቀረበ።

በመጀመሪያ፣ አልማ ወደ አሞኒሀሀ ከተማ እስከተጓዘ ድረስ፣ ታላቅ ስኬት አጋጥሞት ነበር። የከተማውም ህዝብ፣ አልማ የፖለቲካ መሪያቸው እንዳልሆነ ጣንቅቀው ስላወቁ፤ እሱ ላለው የክህነት ስልጣኑ፣ ቅንጣት የምታህል አክብሮት ነበራቸው። እሱንም አዋረዱት፣ ተሳለቁበት፣ አንዲሁም ከከተማ አርቀው ጣሉት።

ልቡም ተሰብሮ፣ አልማ ከአሞኒሀሀ ከተማ ጀርባውን በመስጠት ሄደ።4

ነገር ግን መልአክ እንዲመለስ ተናገረው።

ይህን አስቡበት፥ ወደሚጠሉት እና ወደ ቤተክርስቲያኗ ንዴት ወዳለባቸው ሰዎች እንዲመለስ ተነገረው። አደገኛ፣ እና ምናልባትም ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ጥሪ ነበር። ሆኖም ግን አልማ ምንም አላቅማማም። “በፍጥነት ተመለሰ።”5

ወደ ከተማዋ ሲደስም አልማ ለብዙ ቀናት እየጾመ ነበር። በዚያም በፍጹም ለማያውቀው ስውን “ለታማኙ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚበላውን ትሰጠዋለህን?”6 ብሎ ጠየቀ።

አሙሌቅ

የሰውየው ስም አሙሌቅ ነበር።

አሙሌቅ ባለጸጋና የታወቀ የአሞኒያህ ነዋሪ ነበር። ለዘመናት አማኝ ከሆኑ ዘር የመጣ ቢሆንም፣ የሱ እምነት ግን መንምኖ ነበር። በኋላ ላይም እንዲህ በማለት ተናዘዘ፤ “ብዙ ጊዜ ተጠርቼ፣ ባለመስማቴ ልቤን አጠጥሬ ነበር። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ አወቅሁ። ሆኖም ግን እነዚህን ነገሮች [ለማመን] አልፈቀድኩም፤ ስለዚህም በእግዚአብሄር ላይ ለማመጽ ሄድኩ።”7

ነገር ግን እግዚአብሄር አሙሌቅን እያዘጋጀው ነበር፣ እናም እሱ አልማን ሲያገኘው፣ የእግዚአብሄርን አገልጋይ ወደቤቱ ጋበዘው፤ እናም አልማ በዛ ለብዙ ቀናት አሳለፈ።8 በዚህም ወቅት አሙሌቅ ለአልማ መልእክት ልቡን ከፈተ፣ ከዚያም ግሩም የሆነ መለወጥ በውስጡ መጣ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ አሙሌቅም ማመን ብቻ ሳይሆን፣ የእውነትም ባለ ድል ሆነ።

አልማ ተመልሶ በአሞኒሀሀ ህዝቦች መካከል ለማስተማር ሲሄድ፣ በአጠገቡ ሁለተኛ ምስክር አሙሌቅን ነበር፣ እርሱም ከህዝቡ አንዱ ነበር።

ቀጥሎም ያለው ክስተት ከቅዱሳን መጻህፍት ከሚገኙት ታሪኮች የላቀ በከፊል የሚያሳዝንና በከፊል ደግሞ የሚያሳዝን ነው። ስለዚህም ነገር አልማ ከምእራፍ 8–16 ድረስ ማንበብ ትችላላችሁ።

ዛሬ ሁለት ነገሮችን እንድታጤኑ እጠይቃችኋለሁ፤

መጀመሪያ፥ ከአልማ ምን መማር እችላለሁ?

ሁለተኛ፥ ከአሙሌቅስ ጋር በምን እመሳሰላለሁ?

ከአልማ ምን መማር እችላለሁ?

ላለፉት ጊዜያት፣ ለአሁን ወይም ለወደፊት የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን መሪ ይህን በመጠየቅ ልጀምር፣ ከአልማ ምን መማር ትችላላችሁ?

አልማ በተለየ መልኩ ተሰጦ ያለውና ችሎታ ያለው ሰው ነው። የሌላ ሰው እርዳታ አያስፈልገውም ብሎ ለማሰብ በጣም ይቀላል። ይህም ቢሆን፣ አልማ ወደ አሞኒያህ ከተማ በተመለሰበት ጊዜ ምን አደረገ?

አልማ አሙሌቅን አገኝው እናም እርሱን ለእርዳታ ጠየቀው።

እናም አልማም እርዳታን አገኘ።

ለምንም ምክንያት ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ እኛ መሪዎች እንደ አሙሌቅ ያሉትን ፈልገን እርዳታ ለመጠየቅ ችላ እንላለን። ምናልባት ስራችንን በራሳችን የተሻለ አድርገን የምንሰራ ይመስለናል፤ ወይም ሌሎችን ላለማስቸገር ብለን ችላ እንላለን፣ ወይም ሌሎች ለመሳተፍ አይፈልጉም ብለን እንገምታልን። ብዙውን ጊዜ ሰዎችን በመጋበዝ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ችሎታ እንዲጠቀሙና በታላቁ የማዳን ስራ እንዲሳተፉ ለማድረግ እናመነታለን።

አዳኝን አስቡት፣ ቤተክርስቲያኑን እራሱ ብቻውን አቋቋመ እንዴ?

አይደለም።

የሱ መልእክት “እዛ ቁም፤ እራሴው አከናውነዋለሁ” የሚል አይደለም። ይልቁንስ “ኑ ተከተሉኝ” የሚል ነው።9 የሱን ተከታዮች መንፈሳቸውን አነሳሳ፣ ጋበዛቸው፣ አስተማራቸው፣ እንዲሁም “እኔ ስሰራ ያያችሁትን ስራ ስሩ” ብሎ እምነትን ጣለባቸው።10 በዚህም መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን ብቻ ሳይሆን አገልጋዮቹን ገነባቸው።

በማንኛውም ጥሪ ውስጥ እያገለገላችሁ ያላችሁ፣ የዲያቆኖች ጉባኤ ፕሬዘዳንት ብትሆኑ፣ የካስማ ፕሬዘዳንት ብትሆኑ ወይም የክልል ፕሬዘዳንት ብትሆኑ፣ ውጤታማ ለመሆን የራሳችሁ የሆነውን አሙሌቅን መፈለግ አለባችሁ።

ከአባላቶቻችሁ ውስጥ ራሱን ዝቅ ያደረገ ወይም ለአይን የማይታየውን ሰውዬ ሊሆን ይችላል። ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም አገልግሎት መስጠት የማይችለው የማይመስል ሰው ሊሆን ይችላል። የናንተ አሙሌቅ ወጣት ወይም ጎልማሳ፣ ወንዶች ወይም ሴቶች፣ ልምድ የሌለው፣ የደከመው፣ ወይም በቤተክርስቲያኗ ተሳታፊ ያልሆነ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በመጀመሪያ እይት ለማየት የማይቻለው ቢኖርም እኚህ ሰዎች “ጌታ ይፈልግጋችኋል! እኔ እፈልጋችኋለሁ!” የሚለውን ቃል ከናንተ ለመስማት የተራቡ ሰዎች ናቸው።

በጥልቀት ካየን ብዙ ሰዎች እግዚአብሄርን ለማገልገል ይፈልጋሉ። በእሱም መዳፍ መሳሪያ ለመሆን ይሻሉ። በማጭዳቸው በማጨድ እናም በሃይልም በመትጋት ይህችን ምድር ለአዳኛችን ምጽአት ለማዘጋጀት ይፈልጋሉ የሱን ቤተክርስቲያን ለመገንባት ይሻሉ። ነገር ግን ይህንን ለመጀመር ችላ ያሉ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ እስኪጠየቁ ድረስ ይጠብቃሉ።

በቅርንጫፎቻችሁና በአጥቢያዎቻችሁ እንዲሁም በሚሲዮናችሁና በካስማዎቻችሁ የጥሪ ድምጽን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንድታስቧቸው እጋብዛችኋለ። እግዚአብሄር እነርሱን በማዘጋጀትና ልባቸውን በማሳት ከነርሱ ጋር እየሰራ ነው። በልባችሁ በመመልከት አግኟቸው።

ድረሱላቸው። አስተምሯቸው። ለውጧቸው። ጠይቋቸው።

መልአኩ ለአሙሌቅ የተናገራቸውን ቃላቶች ----- የእግዚአብሄር በረከት በላያቸው እና በቤታቸው ላይ እንደሚሆን አካፍሏቸው።11 በሚያስገርም ሁኔታ ጀግና የሆነ የጌታ አገልጋይ፤ ባንደርስለት ግን ተሸፍኖ የሚቀር ሰው ልናገኝ እንችላለን።

ከአሙሌቅስ ጋር በምን እመሳሰላለሁ?

የተወሰነው አሙሌቅን መፈለግ ሲኖርብን፣ ለሌሎቻችን ደግሞ ጥያቄ መጠየቅ ያለብን “አሙሌቅን እንዴት ነው የምመስለው?” የሚለውን ነው።

ምናልባት ከቆይታ በኋላ በደቀመዛሙርትነታችሁ ቀንሳችሁ ሊሆን ይችላል። ምናልባት የምስክርነታችሁ እሳት ቀንሳ ሊሆን እችላል። ምናልባት እራሳችሁን ከክርስቶስ አካል አርቃችሁ ሊሆን ይችላል። ምናልባት በተሳሳተ ሃሳብ ተጉዛችኋል ወይም ተበሳጭታችኋል። እንደ ጥንት የኤፌሶን ቤተክርስቲያን፣ “የመጀመሪያ ፍቅራችሁ”12 የሆነውን— የላቀውን የዘላለማዊ እውነት፣ የክርስቶስ ወንጌልን ትታችሁ ይሆናል።

ምናልባት እንደ አሙሌቅ፣ በልባችሁ ውስጥ ጌታ “ብዙ ጊዜ ጠርቷችሁ፣” ሆኖም እናንተ ግን “[ያልሰማችሁ]” እንደሆናችሁ ታውቃላችሁ።

የሆነው ሆኖ ግን፣ ጌታ በአሙሌቅ ውስጥ እንዳየው በናንተም ውስጥ ጠቃሚ የሆነ ስራ ለመስራት እና ምስክርን ለመካፈል ችሎታ ያላችሁ የጀግና አገልጋይ ክህሎት ይመለከታል። እናንተ እንደምትሰጡት ሌላ ሰው ሊሰጠው የማይችለው አገልግሎት አለ። ጌታ ሌሎችን ለመባረክና ከፍ ለማድረግ የመለኮታዊ ክህሎቶች በተሞላው በቅዱስ ክህነቱ አምኗችኋል። በልባችሁ አድምጡ እናም የመንፈስ መነሳሻን ተከተሉ።

የአንድ አባል ጉዞ

“ጌታ በተጣራ ጊዜ፣ መስማት እችላለሁን?” ስላለው በአንድ ወንድም ጉዞ ውስጤ ተነካ። ይህንን ድንቅ ወንድም ዴቪድ ብዬ እጠራዋለሁ።

ዴቪድ ወደ ቤተ ክርስቲያን የተቀየረው ከሰላሳ አመታት በፊት ነበር። እሱም የሚሲዮን አገልግሎቱን አጠናቆ ወደ ህግ ትምህርት ቤት ተቀላቀለ። ወጣት የሆነውን ቤተሰቡን ለመደገፍ በመማር እና በመስራት ላይ ሳለ፣ ስለ ቤተክርስቲያኗ የተወሰኑ መረጃዎችን ሰምቶ ግራ ተጋባ። እነዚህን ብዙ አሉታዎች እየሰማ በሄደ ቁጥር፣ የውስጡ አለመርጋት እየጨመረ ሄደ። በመጨረሻም ላይ ስሙ ከቤተክርስቲያኗ መዝገብ እንዲሰረዝ ጠየቀ።

ከዚም ጊዜ ጀምሮ ልክ እንደ አልማ የማሳደጃ ቀናቶች፣ ዴቪድ ብዙውን ጊዜ ከቤተክርስቲያን ምእመናን ጋር በመከራከር፣ በድህረ ገጾች ውይይት ላይ በመሳተፍ እና እምነታቸውን ለመፈታተን ባለ አላማ አሳለፈ።

እሱም በዚህ ነገር ላይ በጣም ተክህኖበት ነበር።

አንዱን የተከራከረውን የቤተክርስቲያን አባል ጄከብ ብዬ እጠራዋለሁ። ጄከብ ለዴቪድ ቀና እና አክባሪ ነበር፣ ሆኖም ግን ስለ ቤተክርስቲያኗ ያለው አቋም የማይነቃነቅ ነበር።

ከአመታት በኋላ ዴቪድ እና ጄከብ የጋራ መግባባትና ጓደኝነትን ፈጠሩ። ዴቪድ ያላወቀው ነገር ቢኖር ግን፣ ጄከብ ስለ ዴቪድ መጸለይ ጀምሮ ነበር እንዲሁም ከአስር አመታት በላይ በእምነት አደረገ። የጓደኛውንም ስም በጌታ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲጸለይለት በማስቀመጥ የዴቪድ ልብ እንድትሳሳ ተስፋን አደረገ።

ከጊዜያት በኋላ፣ በዝግታ፣ ዴቪድ ተለወጠ። ስለነበረውም የመንፈሳዊ ተሞክሮ በፍቅር ማስታወስ ጀመረ፤ እናም የቤተክርስቲያን ምእመን ሲሆን ስለተሰማው ደስታም አስታወሰ።

እንደ አልማም ዴቪድ ከዚህ በፊት የተቀበለውን የወንጌልን እውነታነት ጨርሶ አልዘነጋውም። እንደ አሙሌቅም፣ ጌታ ወደ ዴቪድ ሲጠጋ ተሰማው። ዴቪድ አሁን በህግ ድርጅት ውስጥ አጋር ነው–ይህም ክብር የሚያስገኝ ስራ ነው። ቤተክርስቲያኗን በመንቀፍ ታዋቂነትን በማትረፉ ወደ ቤተክርስቲያኗ ዳግም ለመቀላቀል መጠየቅን ታላቅ ኩራት አደረበት።

ሆኖም ግን፣ እረኛው ወደራሱ ሲጎትተው ያለማቋረጥ ተሰማው።

“ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሄርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል” የሚለውን ቅዱስ ቃል ወደ ልቡ ወሰደው።13 እሱም እንዲህ በማለት ጸለየ “ውድ እግዚአብሄር፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን አባል ደግሜ መሆን እፈልጋለሁ፣ሆኖም ግን መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎችም አሉኝ።”

ከዚህም በፊት እንዲህ አድርጎ በማያውቀውም፣ የመንፈስ ቅዱስን ሹክሹክታ እና ጓደኞቹ የሚሰጡትን በመንፈስ የተመራ መልስን መስማትን ጀመረ። በመጨረሻ በድጋሜ የኢየሱስ ክርስቶስ እና መልሶ የተቋቋመው ወንጌል ምስክርነት እስኪሰማው ድረስ ጥርጣሬው አንድ በአንድ ወደ እምነት ተቀየረ።

በዚህ ጊዜ፣ ኩራቱን አሸንፎ ወደቤተከርስቲያኗ ዳግም ለመቀላቀል ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ እንደሚችል አወቀ።

በመጨረሻም፣ ዴቪድ ተጠመቀ እናም በረከቶቹም እስኪመለሱለት ድረስ ቀናቶችን መቁጠር ጀመረ።

የዴቪድ በረከቶች ያለፈው በጋ ላይ በሙሉ መመለሳቸውን ሳበስር በደስታ ነው። እሱም መልሶ በቤተክርስቲያኗ በሙሉ የሚሳተፍ ነው እንዲሁም በአጥቢያምው ውስጥ የወንጌል ትምህርቶች አስተማሪ ነው። ያጠፋውን ጥፋቶች ለመካስ እና የኢየሱስ ክርቶስ ቤተክርስቲያንና ወንጌል ምስክርነትን ለመሸከም፣ ስለ መቀየሩ ባጋጠመው እድሎች ሁሉ ይናገራል።

ማጠቃለያ

ውድ ወንድሞቼና ውድ ጓደኞቼ፣ በአውራጃዎቻችን እና በካስማዎቻችን ውስጥ እንደ አሙሌቅ ያሉ ሰዎችን እንሻቸው፣ እንፈልጋቸው፣ በመንፈስ እናነሳሳቸው እንዲሁም እንመካባቸው። ዛሬ በቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ እንደ አሙሌቅ ያሉ ሰዎች አሉ።

ምናልባት አንድን ሰው ታውቁ ይሆናል። ምናልባት እናንተም ከነዛ መካከል አንዱ ናችሁ።

ምናልባት ወደ መጀመሪያ ፍቅራችሁ እንድትመለሱ፣ ችሎታችሁን እንድታካፍሉ፣ በጻድቅም ክህነትን እንድትጠቀሙ፣ ከቅዱሳንም ጋር ጎን ለጎን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጠጋት እንድታገለግሉ እና የእግዚአብሄርን መንግስት እንድትገነቡ ጌታ በሹክሹክታ እየተናገራችሁ ይሆናል።

የተወደደው አዳኛችን የት እንዳላችሁ ያውቃል። ልባችሁን ያውቃል። እናንተን ለማዳን ይፈልጋል። ወደ እናንተ ይመጣል። ልባችሁን ለእርሱ ክፈቱ። ከደቀ መዝሙርነት መንገድ ለወጡ ሁሉ፣ በጥቂትም ቢሆንም፣ የእግዚአብሄርን መልካምነትና ጸጋን እንዲያሰላሰሉ፣ በልባቸው እንዲያዩ፣ ከአልማና አሙሌቅ እንዲማሩ፣ እናም ህይወት የሚቀይረውን ያዳኝን ቃላቶች እንዲያዳምጡ ተስፋዬ ነው። “ኑ፣ ተከተሉኝ።”

ለዚህ ጥሪ ትኩረት እንድተሰጡት እገፋፋችኋለሁ፣ በእርግጥም ይህንንም ስታደርጉ፣ የሰማይንም አዝመራ ትቀበላላችሁ። የጌታ በረከት በእናንተ እና በቤታችሁ ላይ ያርፋል።14

ስለዚህ የምመሰክረው እና እንደ ጌታ ሐዋርያ በረከቴን ለምሰጣችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።